Error
  • The RokSprocket Module needs the RokSprocket Component enabled.
Saturday, 25 February 2012 12:52

ስነ ሥርዓት፤ በዘረ - መልኛ

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

የተፈጥሮ ስነ ምግባር “ክርስቶስ” የሚያስተምረው ስነ ምግባር አይደለም፡፡ ግራ ጐንህን ሲያጮልህ ቀኙን አስተካክለህ መስጠት “ተሸናፊነት” ነው፡፡ ወይንም በዘረ-መል ቋንቋ  መጥፎ የጂን ባለቤትነት ነው፡፡ ተፈጥሮ፡- ጥሩ ሰው “Nice guy” ብሎ የሚጠራቸው፤ መቀበላቸውን እርግጠኛ ሲሆኑ ብቻ የሚሰጡትን ነው፡፡ መስጠት እና መቀበል ተመጣጣኝ ባልሆኑበት ስነ ምግባር ብሎ ነገር የለም፡፡ አብዝተው ሳይበዘብዙም፣ ሳይበዘበዙም የተፈጥሮ ተልዕኮን መወጣት መቻል፤ የጨዋታው ህግ አሸናፊ ያደርጋል፡፡

በፆታዎች መካከል የተደረገ ጦርነት

በተቃራኒ ፆታዎች መሀል ያለውን አሰቃቂ የተፈጥሮ ሰበቃ ለማሳየት ከእንስሳት ግዛት የምንመርጠው ምሳሌ የማርያምን ፈረስ ይሆናል፡፡

Ceremony of Innocence

የማርያም ፈረስ በእንግሊዝኛ Praying mantise ተብለው ይጠራሉ፡፡ ነፍሳቱ እጁን በፀሎት መልክ የሚያነካካበት ሁኔታ ሀይማኖታዊ ያስመስለዋል፡፡ ምስኪን መንፈሳዊ ቢመስልም፤ ከነብሳት ስጋ በሊታ በመሆኑ የተለየ ነው፡፡ ሴቷ የማርያም ፈረስ ወንዱን የምትፈልገው ወንዴ ዘሩን እንዲሰጣት ብቻ ነው፡፡ በተረፈ ወንዱ ለሴቷ የማርያም ፈረስ ምንም አይደለም፡፡ እንዲያውም ምግቧ ነው፡፡ የወሲብ ግንኙነት የሚያደርጉበት   ጊዜ ሲደርስ ወንዱ በቀስታ እና ጥንቃቄ ሴቷ ጀርባ ላይ ይወጣል፡፡

ቀስ ማለት አለበት፤ ካልሆነ፤ ገና ጀርባዋ ላይ ከመውጣቱ በፊት ወይንም ተራክቦ እየፈፀመ ባለበት ቅፅበት አሊያም ጨርሶ ወርዶ ሊሄድ ሲል … ትበላዋለች፡፡

የምትበላው ከጭንቅላቱ ጀምራ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ተራክቦ እየፈፀመ ባለበት ጊዜ ጭንቅላቱን ገምጣ ማላመጥ የተለመደ ባህሪዋ ነው፡፡ ነገር ግን፤ ወንዱም ጭንቅላቱ ቢበላበትም የወሲባዊ ተራክቦውን አያቋርጥም፡፡ እንዲያውም የተራክቦ ፍጥነቱን እና ቅልጥፍናውን ይጨምርለታል፡፡ ከመሞቱ በፊት ዘሩን በሴቷ ማሪያም ፈረስ ሰውነት ውስጥ ያኖራል፡፡ አገልግሎቱን ጨርሷል፡፡ እንቁላል ለምታስፈለፍለዋ እናትም የምግብነት አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ … ይህንን ንፅፅር በሰው ልጆች ላይ ያለውን የፆታ ጦርነት ሊገልፅልን ይችል ይሆን? ማርያምን የሚመሳስሉት ሴቶቻችን የተፈጥሮ ተልዕኮን በተመለከተ በሚከሰት የፆታ ጦርነት ላይ ግን እንደ ማርያም ፈረሱ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

በፆታዎች መሀከል ያለው ሰበቃ ምክንያቱ ምንድን ነው የሚለው ጥያቄ የእኔ የረጅም ዘመን ራስ ምታት ሆኖ ቆይቷል፡፡ የእናንተም እንደሚሆን ደግሞ አንዳችም ጥርጥር የለኝም፡፡

የሰው ልጆችን በተመለከተ ወንድ (እስፐርም ሴል) እና ሴት (እንቁላል) ያላቸውን አንድ ላይ አዋህደው (አዋጥተው) ፅንሱ ይፈጠራል፡፡ ፅንሱን እየመገበ የሚቆየው የሴቲቱ አካል ነው፤ የሴቲቱ ሰውነት፡፡ … ፅንስ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ሽሉ የሴቷን በንጥረ ነገር የተሞላ እንቁላል ለወራት ይመገባል፡፡

በዚህም ምክንያት ሴቲቱ ከወንዱ የበለጠ በልጁ ላይ የምታወጣው ግብአት ከዚህ የመጀመሪያ ነጥብ ይጀምራል፡፡ ለፅንሱ ተስማሚ የሆነ አባት በመምረጥም ላይ የበለጠ ጥንቁቅ የምትሆነው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

የሴቷ አካል እንቁላልን የሚሰራው በወር አንዴ ነው፡፡ ወንዱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የእስፐርም ህዋሶች በእየቀኑ ማምረት ይችላል፡፡ ይህንንም እስፐርም በተለያየ የሴት እንቁላል ላይ “ኢንቨስት” ሊያደርግ ይቻለዋል፡፡ … ትልቅ “ኢንቨስትመንት” አይደለም፡፡ ትልቅ ሀላፊነትም፡፡

የሴቷ እንቁላል በማይክሮስኮፕ የሚታይ ቀኒጥ ቢሆንም ከወንዱ እስፐርም ሴል በንፅፅር በአያሌ እጥፍ የገዘፈ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የወንዱን የመራቢያ ህዋስ ወደ አለበት ተጉዞ እንዲገናኘው ባለበት ሆኖ የሚጠባበቅ ነው፡፡ ሴት ወንድን ሄዳ በእለታዊ የአካል ህይወት ላይ እንደማትጀነጅነው ሁሉ፡፡

እንግዲህ እንደሚታየው ወንዱ በዝባዥ ሴቷ ተበዝባዥ ናት፡፡ ከመጀመሪያው የፅንስ ክስተት ጀምሮ ባሉት ቀጣይ ዘመናት የተወለደው ልጅ ቢሞት ከአባትየው ይበልጥ የምትጐዳው (ብዙ የምታጣው) እናት ነች፡፡ ወንዱ ፅንሱን በውስጡ አይሸከምም፣ የተረገዘውን አምጦ አይወልድም፣ ከተወለደ በኋላ ጡትም አያጠባም፡፡ ስለዚህ ሴቷ ሀላፊነትን የሚወስድ ወንድ ፈልጋ ከዚህ ወንድ ማርገዝ መፈለጓ፤ በተፈጥሮ የተሰጣት የተፈጥሮን ተልዕኮ መወጫ ታክቲክ ነው፡፡

መኪና ያለው፣ ቤት ያለው፣ ስራ ያለው፣ ትምህርት ያለው … ጉልበት ያለው፣ ስልጣን ያለው፣ ተፈላጊነት … ያለው ወንድ ላይ ሴቶች የሚንጠለጠሉበት ምክንያት ልጃቸውን ወልደው የሚያሳድጉበት አስተማማኝ ወንድ ፍለጋ ነው፡፡ በሚያድገው ልጅ ላይ መዋጮ የሚያደርግ የአባት ዘር ስለሚያዋጣቸው ይፈልጉታል፡፡ ፍቅር ብቻ ካለው አባት ቤት ያለው አባት በዘረ - መል እይታ ይበልጣል፡፡ … ምስኪን ከሆነው ያልሆነው ይሻላል፡፡

ወንዱም ሆነ ሴቷ ልጅ ለመውለድ ሲጣመሩ፤ ተመሳሳይ ዘረ-መል ይዘው አይደለም፡፡ የሁለቱም ዘር የሚጣመረው የተወለደው ልጅ ላይ ነው፡፡ ለሴቷም (በዘረ-መልኛ)  የወለደችው ልጅ ከሚሞትባት ባሏ ቢሞትባት እንደሚሻላት አያጠራጥርም፡፡ በልጇ ላይ ያዋለችው የራሷን መጠን በባሏ ላይ ካዋለችው ጋር በንፅፅር ውስጥ ገብቶ ሊመዘን አይችልም፡፡

ግን ልጇን ለማሳደግ የሚያግዛት አባት ልጁ በተረገዘበት ወቅት በድንገት ቢሞት ያረገዘችውን ሳታስወርድ ሌላ ባል ፈልጋ መውለድ ልትሞክር ትችላለች፡፡ እንደ ራሱ ልጅ አድርጐ እንዲያሳድገውም የእሱ አለመሆኑን ሳትነግረው፡፡

በተፈጥሮ የዘረ - መል ህግ በዚህ መልክ ሳያውቅ የራሱ ያልሆነ ዘርን የሚያሳድግ አባት የተሸነፈ ነው፡፡ በዘረ መል እይታ ያልወለዱትን ልጅ (ያልተዛመዱትን) በጉዲፈቻ ማሳደግ ትርጉም አይሰጥም፡፡ ተፈጥሮ ራሷ ይሄንን አትደግፍም፡፡ በሰው ልጆችም ላይ ባይሆን ለምሳሌ በአይጦች አለም ወንዱ አይጥ የሚያመነጨው ሆርሞን አለ፡፡ ሆርሞኑ በሴቷ ማህፀን ውስጥ ያለ ከእሱ ያልተረገዘ ፅንስን በፍጥነት እንዲያስወርዳት የሚያደርግ ነው፡፡ ከራሱ የተፀነሰ ከሆነ ግን በማህፀኗ ውስጥ ያለው ሽል ሳይነካ ማደጉን ይቀጥላል፡፡ ይህ ሁኔታ The Bruce effect ተብሎ የሚጠራው ነው፡፡ አይጣዊ ዲቃላን መቆጣጠሪያ ብልሐት ነው፡፡ ለአይጡ ብልሐቱን የሰጠው ተፈጥሮ ስለሆነ፤ ምናልባት ዲቃላን ተፈጥሮ አትደግፍም ማለት ይሆን?

በሰው ልጆች ዘንድ ለረጅም ጊዜ ሴቷ እና ወንዱ የሚያደርጉት መጠናናት በሴቷ አካባቢ ያሉ ሌላ ወንዶችን ለማስወገድ ነው፡፡ ከእሱ ወይንም ከሷ በስተቀር ሌላ ተፎካካሪ እንደሌለ ካረጋገጡ በኋላ ጋብቻ ይመሰርታሉ፡፡ ምናልባት ወንዶች በሴቶች ላይ ክብረ ንፅህና ማግኘት የሚፈልጉትም ከዚሁ ሳቢያ ሳይሆን አይቀርም፡፡

ሴቷ የዘር እንቁላሉዋን ለወንዱ ገበያ ከማቅረቧ በፊት ብዙ የመከላከያ እና የመፈተኛ ዘዴዎች አሏት፡፡ ሴቷ በመጀመሪያ ወንዱን ትመለከተዋለች - ወንዱ ሴቷን ከሚመለከታት በላይ፡፡ ወንዱ ወሲባዊ አካሎቿን የማየት አቅም ነው ያለው ሴቷ ግን ስነምግባርም ታያለች፡ በቀላሉ ለማዳ እና ታዛዥ ማድረግ የሚቻል ወንድ (ከሌላ እሴቶች በተጨማሪ) ልጇን ወልዳ ለማሳደግ ሊያግዛቸው ይችላል፤ ተመራጭ ነው፡፡

አንዱ መመዘኛ ሴቷ ራሷን እንደማትገኝ የሆነች አስመስላ መሸሽ ነው፡፡ ወንዱ መጠበቅ እና መታገስ የሚችል ከሆነ እሱ እያሳደዳት ሳለ እሷ ትቀልበዋለች፡፡ ጊዜያዊ ፍላጐት አንግበው የሚመጡትን (የሚያዋጡ) ለተፈጥሮ ግብ ከሚያዋጡት ጋር አወዳድሮ የማንፀሪያ አንዱ መንገድ ይህ ነው፡፡ ይህ በሰዎች ላይ ብቻ ያለ ተፈጥሮ አይደለም፡፡ በተለያዩ እንስሳት ላይ የሚታይ ነገር ነው፡፡

ወደ የተዋልደ ዘር ልውውጥ ከመሄዳቸው በፊት ወንዱ ለሴቷ ታዛዥነቱን ያሳያል፡፡ ቤት ልታሰራው ትችላለች፣ መኪና ልታስገዛው፣ በደንብ ሊመግባት እንደሚችል የተለያዩ ሆቴሎች እየጋበዘ እንዲያሳያት ልትጠይቅ ትችላለች፡፡

እሺ እስክትለው ብዙ የሚጠብቅ ወንድ ብዙ ክፍያ የከፈለም ነው፡፡ ብዙ የተለፋበትን (ፈሰስ የተደረገበትን) እንቁላል ጥሎ መሄድ ለወንዱም አይቻለውም፡፡ በመጨረሻ ለፍቃዱ ስትስማማ ወንዱም እሷን ከሚገባው በላይ ለምዷታል፡፡ ሊተዋትም አይችልም፡፡

በዚህ ረገድ ሴቶቹ በሁለት ይከፈላሉ፡፡ እሺ ለማለት ብዙ የሚያለፉት አይነቶች እና ወዲያው “እሺ” የሚሉት ናቸው፡፡

ቶሎ እሺ የሚሉት ቶሎ ዘሩን ዘርቶ መሄድ እንጂ ሀላፊነት ወስዶ ልጁን ለማሳደግ ለማይፈልገው አይነት ወንዴ ዘረ - መል የተጋለጡ ናቸው፡፡ እና በስተመጨረሻ ጨዋ የሚባሉት አጥንተው አስጠንተው በቀስታ ወደ አልጋ ቤት ወይንም ጋብቻ የሚገቡት ሴቶች የተሻለ ብልጫ አላቸው፡፡

ግን ብልጠትም ሆነ ብልጫ በጥንቃቄ ካልተያዘ … እሱም አስቸጋሪ ነው፡፡ ለረጅም ጊዜ ወንዶቻቸውን በማጥናት በመቆየት ወንዶቻቸውን የሚያጡ አሉ፡፡ ወይንም ዘግይተው በመውለዳቸው ምክንያት የሚወልዷቸውን ልጆች ቁጥር ማሳነሳቸው የማይቀር ነው፡፡ በተጨማሪ እናትነትን በብቃት መወጣት፣ ልጁን በቅልጥፍና ማሳደግ የሚችሉ እናቶች እድሜአቸው ዝቅተኛ በሆነ ወቅት ብቻ ነው፡፡ እድሜ ሲጨምሩ ለእናትነት የተሳለ ጠርዞቻቸው ይዶሎዱማል፡፡

በሀያ አመቷ የወለደች ሴት በአርባ አመቷ ከወለደችዋ የሀያ አመት ያህል ርቀት ወደፊት ትበልጣታለች፡፡ በተመቻቸ ሁኔታ ላይ የወለደችው ባለ አርባ አመቷ ብትሆንም፡፡ የልጅ ልጅ ያየችው ግን በሀያ አመቷ የወለደችዋ ትሆናለች፡፡ ዘረ መሏን ወደፊት በማሻገር አርባዋን ትበልጣታለች፡፡ በመራባት ትበልጣታለች፡፡ ያራባችው ዘር ግን የማይረባ ጂን የመሆኑ አዝማሚያ ግን በሀያ አመቷ ለወለደችው ፈጣኗ ኮረዳ ያመዘነ ነው፡፡

እነዚህ ፈጣን አይነት ሴቶች (በአሁኑ ወቅት በከተማችን እና በክልል ዩኒቨርስቲዎቻችን ያሉት) በቁጥር ሲበዙ የወንዱ ባህሪ የሴቶቹን ተከትሎ ይቀየራል፡፡ ሴቷ በቀላል የምትገኝ (ምንም ቅድመ ሁኔታ የማትፈልግ) ስትሆን ምንም ቅድመ ሁኔታ የማያሟላ፣  ከተኛ በኋላ ተነስቶ የሚጠፋ ወንድ … በሴቶቹ ልክ ይበዛል፡፡

እነዚሁ ሁለቱ የሚፈጥሯቸው ልጆች ከጊዜ በኋላ የአስተዳደግ ችግር መፍጠራቸው አይቀርም፡፡ አያቶች እየተቀበሉ የሚያሳድጓቸው ልጆች ሊበዙ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ጨዋ ወይንም አይናፋሯ ሴት ተፈላጊ እየሆነች መምጣት ትጀምራለች፡ ተኝቶ ዘሩን ዘርቶ መነሳት እንጂ ሀላፊነት መውሰድ እና ማሳደግ የማይችለው ወንድ አይናፋርዋን ሴት ለመለማመጥ እና ለማባባል ትዕግስት ስለማይኖረው ሊጠጋት አይችልም፡፡ ግን የተረጋጋ የዘር ውጤቱ ሲወለድ እና ሲያድግ ማየት ግዴታ ስለሚሆን ሴቷ ባህሪዋን ቶሎ “እሺ”  በማለት እና “ቀስ” በማለት መሀል ታስተካክለዋለች፡፡ ጨዋዎቹ ሴቶች 5/6 ይሆናሉ፤ ተመልሰው፡፡ አንድ ስድስተኛዎቹ (1/6) ደግሞ፤ ቶሎ “እሺ” ባይ ሆነው ይቀጥላሉ፡፡  በተፈጥሮ ቀመር ESS (Evolutionary Stable system) በዚህ አኳኋን ይገኛል፡፡ ሚዛናዊው ቦታም ይህ ነው ይለናል፤ የSelfish Gene መፅሐፍ ፀሀፊ፡፡

የትኛውም ፆታ ከዚህ ሚዛናዊ የተፈጥሮ “ሬሾ” ማፈንገጥ ከጀመረ፤ ተፈጥሮ ተቃራኒውን  ፆታ ባህሪ በመለወጥ የተዛባ የዘረ መል ዝግመተ ለውጥ ለማስከተል እርምጃ ትወስዳለች፡፡

ሴቶች፤ “ጥሩ” የወንድ አይነት ላይ ብዙውን ጊዜ ይስማማሉ፡፡ እነዚህ ወንዶች ለተተኪው ፍሬ ተስማሚ እና አስተማማኝ የሆነ ሁኔታ መፍጠር የሚችሉት መሆናቸው ነው፡፡ “አትይ መኪና እኔም እገዛለሁ እድሌ ሲቀና” የሚለው ተለማማጭ የወንድ ዜማ፤ ፍሬ ማሳደጊያ አስተማማኝ ሁኔታ መፍጠር ያልቻለው ነው፡፡ አስተማማኝ ሁኔታ መፍጠር ያልቻለውን … ተፈጥሮ ሊረዳው አይችልም፡፡ መጥፎ ዘረ-መል ብሎ ያሰናብተዋል፡፡ ምናልባት በዚህ ሁኔታ ላይ የተጠፈረ ሰው፤ ማጭበርበር ብቸኛ አማራጩ ሊሆን ይችላል፡፡ ሲሆንም በእየለቱ ይታያል፡፡ “ሀብት አለኝ፣ ንብረት አለኝ” ወይንም “ሀብት እና ንብረት ምን ያደርጋል? ጥለነው ለምንሞተው?” በሚለው የአጨዋወት እስትራቴጂ የሴቷን ስስ ጐኖች አሳስቶ መግባት እና ፍሬ ማፍራት …፡፡

የወንዱ መልክ ሁሉ አስቀያሚ ከሆነበት ቦታ ላይ፤ የተሻለ መልክ ያለው፤ ወይንም በንፅፅር ቆንጆ የሆነው ላይ ሴቶቹ እንደሚሻሙ አያጠራጥርም፡፡ ምክንያቱም በዘረ-መላዊ (ሸውራራ እይታ) ከቆንጆው ወንድ ሴቷ የምታፈራቸው ልጆች የተሻለ የመፈለግ አዝማሚያ ይኖራቸዋል፡፡ በቀላሉ ዘራቸው የሚራባ ይሆናል፡፡ …. በተለምዶው ጥቁር ተብሎ የሚጠራው ዘር (የተደፈጠጠ አፍንጫ፣ ቁርንድድ ፀጉር፣ ወፍራም ከንፈር …ወዘተ) በመልክ ራሱን አስቀያሚ አድርጐ የሚያይ ከሆነ፤ ትንሽ ነጣ ካለው የሰሜን  አፍሪካ ወይንም የምዕራባዊያን “ካውኬዝያውያን” መውለድ መፈለጉ … ነጭ ማምለኩ፤ ቁርንድድ ፀጉሩን “ፔሮክሳይድ” ቀብቶ (ብሎንድ) ቢጫ ማድረጉ … ወዘተ፤ መነሻው ግልፅ ይሆንልናል፡፡

በተጨማሪ፤ ጥቁር መልክ ከድህነት ኋላ ቀርነት ጋር አብሮ የታተመ ገፅታ በመሆኑ ተቃራኒውን ቀለም (ከሀብት፣ ስልጣኔ፣ እና ምቾት ጋር በአንድ መገለጫ የተቀረፀውን የነጭ ቀለም) መሆን፣ መቀላቀል፣ ማግባት፣ መውለድ …. መፈለጉ ከዘረ መል አመራረጥ ፅንሰ ሀሳብ ጋር የሚስማማ እንጂ የሚቃረን አይሆንም፡፡ “ነጩን ክርስቶስ” ማምለክ የተሻለ ዘረ መልን ማምለክ ነው፡፡ አምልኮቱ መቀጠሉም አያጠራጥርም፡፡

በዚህ ረገድ ከእንስሳቱ አለም የሚታወቅ የወፍ አይነት አለ፡፡ ኩኩ ተብሎ የሚጠራ ወፍ ነው (CUCKOO)፡፡ ወፉ በሌላ ወፎች ጐጆ ገብቶ እንቁላሉን ይጥላል፡፡ የራሱን ጐጆ የመስሪያ አቅምም ሆነ ተነሳሽነት የለውም፡፡ የራሱን እንቁላል ከጐጆው ባለቤት ወፎች እንቁላል ጋር ቀይጦ … ይሰወራል፡፡

የሚገርመው ግን ወላጁ “ኩኩ” ወልዶ ጥሎት የሄደው እንቁላል ባህሪ ነው፡፡ እንቁላሉ ከሌሎቹ እንቁላሎች ቀድሞ ይፈለፈላል፡፡ እንደተፈለፈለ የመጀመሪያ ተግባሩ፤ በጐጆው  ውስጥ ያሉ ሌሎች እንቁላሎችን እየገፋ ከጐጆው ማስወጣት ነው፡፡ ሌሎቹን እንቁላሎች ጥሎ ከፈጠፈጠ በኋላ፤ ብቻውን እንደ ብቸኛ ልጅ ባልወለዱት ወፎች የሚሰጠውን ፍቅር እና እንክብካቤ እያጣጣመ ያድጋል፡፡

ከጠቀስኩት የባሰ ሌላ ወፍም አለ “ሀኒጋይድስ” (honeyguides) ተብለው ይጠራሉ፡፡ ሀኒጋይዶችም እንቁላላቸውን በሌላ ወፎች ጐጆ ውስጥ ተደብቀው ገብተው ይጥላሉ፡፡ የተጣለው እንቁላል ሲፈለፈል ገና አይኑን እንኳን ሳይገልጥ ስል እና ቆልማማም በሆነ መንቁሩ በጐጆው ውስጥ ያሉ እንቁላሎችን እየጨፈጨፈ ይገድላቸዋል፡፡ …

የተፈጥሮ ስነ ምግባራዊነት የቱ ላይ ነው? ብላችሁ ልትጠይቁኝ ትችሉ ይሆናል፡፡ እነዚህ በአቋራጭ ለመራባትም ሆነ ለመኖር የሚሞክሩ ወፎች ቁጥራቸው እየጨመረ ሳይሆን እየተመናመኑ ይመጣል፡፡ ተፈጥሮ የሚመርጠው እና ራሱን እንዲተካ የሚፈቅደው ዘር እና ዘረ-መል በትክክለኛው መንገድ በብዛት ሳይሆን በጥራት ፍሬ አፍርቶ አይነቱም በቀጣይነት ማሻገር የቻለውን ነው፡፡

ለእንስሳት አለም የሚሰራ ህግ ለሰውም የሚሰራ ነው፡፡ ሰው ለራሱ የተለየ ቢመስለውም ለተፈጥሮ ግን ሁሉም ፍጡር አንድ ነገር ነው፡፡ የሪቻርድ ዳውኪንስ መፅሐፍ “The Selfish Gene” የሚያተኩርበት ዋና ነጥብም ይህ ነው፡፡

 

 

Read 3116 times Last modified on Saturday, 25 February 2012 13:00