Print this page
Saturday, 25 February 2012 12:52

የዕውቀትና የሠላም ዘመን አብሳሪው ማተማያ ቤት 90ኛ ዓመት

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(1 Vote)

ኢሕአዴግ በደርግ ዘመን ለተሰሩ መልካም ነገሮች ዕውቅና ለመስጠት አንዳች ፍላጐት ያለው አይመስልም፡፡ ደርግም ለንጉሱ ዘመን በጐ ተግባሮች በአድናቆት ምስክርነት ለመስጠት ንፉግ እንደሆነ የስልጣን ዘመኑ ተጠናቀቀ፡፡ መንግሥታቱ ወይም ባለስልጣናቱ ለመመሰጋገን ቢቸገሩም ሁሉም በየዘመናቸው የሰሩት ሰናይና እኩይ ተግባር ምን እንደሚመስል ታሪኩን መዝግበው ያኖሩ ተቋማት ግን አሉ፡፡ የካቲት 3 ቀን 2004 ዓ.ም የተመሠረተበትን 90 ዓመት ያከበረው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት አንዱ ማሳያ ነው፡፡

ማተሚያ ቤቱ የ90ኛ ዓመት ምሥረታ በዓሉን ሲያከብር ካሰናዳቸው ዝግጅቶች መካከል ለአንድ ሳምንት ለሕዝብ ክፍት የሆነው ኤግዚቢሽን አንዱ ነበር፡፡ ትርዒቱ ስለ ቁም ጽሕፈት ምንነት፣ ሕትመት በዓለም ላይ ምን ታሪክ እንዳለው፣ በአገራችን የሕትመት አጀማመር ምን እንደሚመስል፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ከንጉሱ እስከ ኢሕአዴግ ስላከናወናቸው ታላላቅ ተግባራት ምንነት፣ በዘመናቱ ውስጥ ማተሚያ ቤቱን በሥራ አስኪያጅነት ስለመሩ ሰዎች የሚገልጽ የጽሑፍና የፎቶ መረጃዎች ቀርበዋል፡፡ አቶ ደሳለኝ አየለ የ90ኛው ዓመት ኤግዚቢሽን አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው፡፡ ኤግዚቢሽኑን እንደሚከተለው ያስቃኙናል፡፡

ቁም ጽሕፈት አገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ ቦታዎች ሲሰራበት የነበረ ጥንታዊ ጥበብና ዕውቀት ነው፡፡ ሕትመት ከዛሬ 1412 ዓመት በፊት እንደ ጐርጐርያን አቆጣጠር በ594 ቻይናዎች በእንጨት ላይ በመሥራት እንደጀመሩት ይነገራል፡፡ በመቀጠል ጃፓኖች በታሪክ ተመዘገቡ፡፡ ቻይናዎች የእንጨት ብቻ ሳይሆን ሕትመትን በሸክላ ላይ በመሥራትም ቀዳሚ ናቸው፡፡

በ1440 እ.ኤ.አ ጀርመናዊው ዮሐንስ ጉተንበርግ፤ ፊደል የሚቀርጽ መሣሪያ በመፈልሰፉ የሕትመት ኢንዱስትሪው እንዲቀጣጠል አደረገ፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያ የሕትመት ታሪክ ከአፄ ምኒልክ ዘመን ነው የሚጀምረው፡፡ መርሀ ጥበብ ማተሚያ ቤት “አእምሮ” ጋዜጣ ይታተምበት ነበር፡፡ ማተሚያ ቤቱ እስከ ደርግ ዘመን ድረስ በገንዘብ ሚኒስቴር ስር ይገኝ ነበር፡፡ ደርግ በብርሃንና ሰላም ስር እንዲሆን አደረገው፡፡

ብርሃንና ሰላም የካቲት 3 ቀን 1914 ዓ.ም የማተሚያ አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ ከመመሥረቱ በፊት ለአራት ዓመታት ያህል ጥናትና ዝግጅት ተደርጐለታል፡፡ በ1910 ዓ.ም አለቃ ገ/መድህን ሐረር የሚባሉ ሊቅ የሚመሩት ኮሚቴ ተዋቀረ፡፡ ቅዱሳን መፃሕፍት፣ የመንግሥት ሰነዶችንና ስንክሳሮችን ለማሳተም ከተለያዩ ሊቃውንትና የቁም ፀሐፊዎች ጋር የሙከራው ኮሚቴ ጥናቱን ሲያጠናቅቅ “ፔዳል” የሚባል 70 50 እና 35 50 መጠን ማተም የሚችል የሕትመት ማሽን ተተክሎ ሥራው በ1914 ዓ.ም ተጀመረ፡፡ ማተሚያ ቤቱን በባለቤትነት ያቋቋሙት በወቅቱ አልጋ ወራሽ የነበሩት ራስ ተፈሪ መኮንን ሲሆኑ የማተሚያ ቤቱ አድራሻ አሁን 6 ኪሎ ዩኒቨርስቲ በሚገኝበት በአልጋ ወራሹ መኖሪያ “ጨው ቤት” በሚባል ክፍል ነበር፡፡ በዘመኑ ለሥራው 15 ሰዎች ተቀጥረዋል፡፡ የማተሚያ ቤቱ መጠሪያ ሥም “ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን” ሲባል በመጀመሪያው ሦስት ዓመት 18 መፃሕፍት አትሟል፡፡ ባቋቋሙት ማተሚያ ቤት የ”ቁጥር ትምህርት”፣ “የአማርኛ ሰዋሰው”፣ “መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር”፣ “ውዳሴ ማርያም” የተሰኙ መፃሕፍት መታተማቸውን ያዩት ራስ ተፈሪ መኮንን፤ ለማተሚያ ቤቱ ሠራተኞች ከለንደን ያመጡትን ካፖርት ሸልመዋል፡፡ ማተሚያ ቤቱ ብርሃንና ሰላም የሚለውን መጠሪያ ያገኘውም ከዚህ በኋላ ሲሆን የዕውቀት ዘመን፤ የሰላም ዘመን እየመጣ መሆኑን ለመግለጽ ነበር ብርሃንና ሰላም የተባለው፡፡ የሕትመት ሥራው እየሰፋ ስለመጣና የራስ ተፈሪ መኮንን መኖሪያ ግቢ የነበረው “ጨው ቤት” ስለጠበበ ማተሚያ ቤቱ አሁን የገንዘብ ማኒስቴር ሕንፃ ወዳለበት ቦታ እንዲመጣ ተደረገ፡፡ ይህም ቦታ ለሥራው ሳያመች ሲቀር የቀድሞ 2ኛ ፖሊስ ጣቢያ አጠገብ ወሎ ጋራዥን የሚጐራበተው የ”ሳንቃ ወላንሳ” ቤት በመከራየት ማተሚያ ቤቱ ወደ 4 ኪሎ መጣ፡፡ አሁን ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ያለበትን መሬት በ36 ሺህ ማርያትሬዛ ጳውሎስ ከሚባል ግብፃዊ እንደተገዛ ይነገራል፡፡ በሌላ በኩል ቦታው የቤተክህነት ስለነበር ለንጉሱ በነፃ ነው የሰጠችው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እውነቱ የቱ ነው ለሚለው ጥያቄ ለተመራማሪዎች ክፍት ተትቷል፡፡ የሆነ ሆኖ መሬቱ ከተገኘ በኋላ የ”ሳንቃ ወላንሳ”ን ቤት በመተው ማተሚያ ቤቱ አሁን በሚገኝበት ቦታ እንዲመጣ ተደርጐ ሥራውን ቀጠለ፡፡

በ1926 ዓ.ም ፋሽስቱ ጣሊያን አገራችንን ሲወርር የማተሚያውን ማሽን በመንቀል ጀርመን ኤምባሲ አጠገብ ወደሚገኘው የብላታ ኃይሌ ወ/ኪዳን ቤት እንዲሄድ ተደርጐ ለ5 ዓመት በሚስጥር የሕትመት ሥራ ሲሰራበት ቆየ፡፡ በዚህ ጊዜ ከሕትመቱ በተገኘው  50ሺህ ብር ትርፍ የኢትዮጵያ መንግሥትና አርበኞችን መርዳት ተችሏል፡፡

ጠላት ሲባረር ማተሚያ ቤቱ ተመልሶ ወደ 4 ኪሎ መጥቶ የቀድሞ ሥራውን ጀመረ፡፡ ንጉሱ በሱዳን እያሉ ማሳተም ጀምረውት የነበረው “ባንዲራችን” ጋዜጣ ከሚያዝያ 16 ቀን 1933 ዓ.ም ጀምሮ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት መታተም ጀመረ፡፡ ከነፃነት በኋላ ያለው ጊዜ አዲስ መሆኑን ለመግለጽ ታስቦም ከግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም ጀምሮ አዲስ ዘመን ጋዜጣ መታተም ጀመረ፡፡ ከዕለት ማግስት በሥራው፣ በሰው ኃይል፣ በአዳዲስ ማሽኖች እያደገ የመጣው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት በሥራው የሚያገኘውን ትርፍ ለቤተ ሳይዳ (አሁን የካቲት 12) ሆስፒታል ነበር የሚሰጠው፡፡ በ1948 ዓ.ም በብርሃንና ሰላም መጽሐፍ ቅዱስ መታተም በመቻሉ ታላቅ ደስታ ሆነ፡፡ የአገሪቱ ደስታ ያስደስታቸዋል ለተባሉ ለተለያዩ አገራት የፖለቲካና የሃይማኖት መሪዎች ዩኒቨርስቲዎች የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ተላከላቸው፡፡ 28ቱ ምስጋናና አድናቆታቸውን ደብዳቤ በመላክ አሳወቁ፡፡ ማተሚያ ቤቱን ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ታስቦ በ1956 ዓ.ም አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ በ4 ኪሎ ግቢ ሕንፃ ለማሰራት ጨረታ ወጣ፡፡ እስራኤላዊ መሐንዲስ አሸንፎ መጋቢት 2 ቀን 1956 ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ በማኖር የተጀመረው የሕንፃ ሥራ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሲጠናቀቅ 1 ሚሊዮን 700ሺህ ብር ወጭ ተደርጐለታል፡፡ ለሕትመት ሥራው የተለያዩ ማሽኖችን ለመግዛት ደግሞ 2 ሚሊዮን 700ሺህ ብር ወጣ፡፡ በአጠቃላይ በ4 ሚሊዮን 400ሺህ ብር ሙሉ ለሙሉ ሥራ የጀመረው የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሕንፃ በ1958 ዓ.ም ሲመረቅ ንጉሥ ኃይለሥላሴ የሚከተለውን ማስታወሻ ፃፉ “በ1914 ዓ.ም ይህ ብርሃንና ሰላም በትንሽ አቅም የተቋቋመው ዛሬ በትልቅ አድጐ ሲመረቅ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዕድገት የተመኘነው አንድ ክፍል ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምስጋና ለፈጣሪ ይሁን፡፡”

ከዚህ በኋላ ከጣሊያን፣ ከስዊዘርላንድና ከመሳሰሉት አገራት የተለያዩ ባለሙያዎች በማተሚያ ቤቱ የመቀጠር ፍላጐት እንዳላቸው ማመልከት ጀመሩ፡፡ ማመልከቻቸው ታይቶ ከተቀጠሩት አንዱ ጣሊያናዊው ጆሴፔ ይሳቅ፣ የሚስጥራዊ ሕትመት ክፍል ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል፡፡ በኋላ ላይ በግላቸው ማስተር ማተሚያ ቤትን አቋቋሙ፡፡ በንጉሱ ዘመን ለማተሚያ ቤቱ ዕድገት ከተሰሩ ሥራዎች መካከል በአክሲዮን እንዲደራጅ ሲደረግ ትርፉ ለቤተ ሳይዳ ሆስፒታል መሰጠቱ ተቋረጠ፡፡ የአክስዮን አባል ከሆኑት መሐል ንግድ ባንክ፣ ልዕልተ ፀሐይ ሆስፒታል፣ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በጐ አድራጐት ድርጅት፣ ትምህርት ሚኒስቴር ይገኙ ነበር፡፡ በደርግና በኢሕአዴግ ዘመን ማተሚያ ቤቱን ለማሳደግ በርካታ ነገሮች የተሰሩ ሲሆን በ90 ዓመት ውስጥ 20 ያህል ሰዎች በሥራ አስኪያጅነት መርተውታል፡፡ ከእነዚህ አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ሙሉወርቅ ገ/ሕይወት ብቸኛዋ ሴት በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን 18 ዓመታት በማገልገልም ሪኮርዱን ይዘዋል፡፡

 

 

Read 2538 times Last modified on Saturday, 25 February 2012 15:57