Error
  • The RokSprocket Module needs the RokSprocket Component enabled.
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 25 February 2012 13:01

“በሳይንስ አለም እዚህ አገር አልተሳካልንም”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

(የፊዚክስ ባለሙያው ዶ/ር ሙሉጌታ በቀለ፤

ከነቢይ መኰንን ጋር ያደረጉት ልዩ ቃለ-መጠይቅ)

ዶ/ር ሙሉጌታ በቀለ - ጠይም፣ አጭር፡፡ ቀስ ብለው የሚናገሩ ከፈለጉ ግን ቶሎ ቶሎ እየተራመዱ መሄድ የሚችሉ ሰው ናቸው፡፡ ዶ/ር ሙሉጌታ በቁመታቸው አንፃር ቀጭን አይባሉም፡፡ ጠንካራ ናቸው፡፡ በአዕምሮ ጉዳይ ካሰብናቸው ደግም የበለጠ ጠንካራ ናቸው፡፡ ትሁት ናቸው፡ የሚያውቃቸው ሰው ሁሉ በትዕግሥተኛነታቸው ያደንቃቸዋል፡፡ እሳቸው እራሳቸው፤ በገዛ አንደበታቸው፤ “አሥር አለቃ ከተማን፤ የከርቸሌውን የሥነ ስርዓት አስጠባቂ፣ አመላቸውን ችዬ፣ እግራቸውን (ቁርጭምጭሚታቸውን) አሽቼ አድኛቸዋለሁ፡፡ ያውም እሥረኛ በዱላ እያባረሩ ወደየጎሬው ሲያስገቡ’ኮ ነው እግራቸውን ወለም ያላቸው፡፡ ግን አሸኋቸው - በካቦው ተጋብዤ - ያውም እየተነጫነጩ፤ እየተቆጡኝ አሽቼ አዳንኳቸው! ከዚህ በላይ ትዕግሥት አለ? ታዲያ እኔ ታጋሽ ብሆን ይገርማል?” ብለዋኛል፡፡

እስቲ ስለ ሥራ ልምድዎ ያጫውቱኝ?

እኔ ከማስተማር ውጪ የሰራሁት ሥራ የለም፡፡ የመጀመሪያውን የማስተማር የሥራ ልምዴን ነገር ልንገርህ፡፡ ዱሮ በእኛ ጊዜ ዩኒቨርሲቲ ከ3ኛ ወደ 4ኛ ዓመት ስትዛወር ወደ አንድ ትምህርት ቤት ትላክና ታስተምራለህ፡፡ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ አገልግሎት (Ethiopian University Service) ይባላል፡፡ (አንድ ሰው፤ “በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ጊዜ የተጀመረ ነው - የዓለም ዩኒቨርሲቲ አገልግሎት (World University Service) ነበር የሚባለው፤ ብሎኛል፡፡) እኔ የተመደብኩት ደብረ ብርሃን ሃይለማርያም ማሞ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ነበር፡፡ ዶክተር ባሳዝነው ባይሳ የሚባል በኋላ የሳይንስ ዲን የሆነ ሰው ያኔ ምን እንዳለኝ ታውቃለህ “በውቃቢና በመተት የተተበተበ ህዝብ ነው፡፡ ያንን ሄዳችሁ መፍታት አለባችሁ!” ደብረ ብርሃን የ7ኛና 8ኛ ሳይንስ አስተማሪ ሆኜ ተመደብኩልህ፡፡ ሳስተምር ዋና ዋናዎቹን የሳይንስ አንጓዎች ማለትም Observation, Careful observation, Hypothesis ወዘተ. እያልኩ አስረዳቸዋለሁ፡፡ እግረ-መንገዴን ጠንቋይ፣ ቃልቻ ምናምን የሚባል ነገር ውሸት ነው እያልኩ በሙሉ ልብ እገልፅላቸዋለሁ፡፡ ተማሪዎቹ ታዲያ “ኧረ ጋሼ መጫኛ የሚያቆሙ፣ ባዶ ኮዳ አንከባለው ውሃ የሚሞሉ፣ ዕፀ መሰውር … የሚያሳዩ ሰዎች አሉ” ይሉኛል፡፡ እኔም “በእኔ ይሁንባችሁ፡፡ ውሸት ነው፡፡ አትመኑ፡፡ ብትፈልጉ ጠንቋይ የምትሉት ጋ ውሰዱኝ” እላለሁ፡፡ መቼም ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ከተማርክ ያዙኝ ልቀቁኝ፤ ዓለም በሳይንስ እጅ ናት ብለህ መፈላሰፍ ትፈልጋለህ! አንድ ቀን፤ 7ኛD ክፍል ይመስለኛል፡፡ አንድ ተማሪ አንድ ፈታኝ ነገር ይዞብኝ ብቅ ይላል፡፡

ምን?

ልነግርህ እኮ ነው! ያ ልጅ በኋላ ዩኒቨርሲቲ ገብቶም አይቼዋለሁ፡፡ “ጋሼ፤ መርፌ ላይ ሰባት ጊዜ ደግሜበት ጉንጬን በውስጥ በኩል ወግቼ በውጪው በኩል አወጣለሁ፡፡ አንዲትም ደም ጠብ ሳትል ነው ታዲያ!” አለኝ፡፡ እኔም፤ “አንተ እንደዚያ ለማድረግ ከቻልክ፤ እኔ ደግሞ መርፌው ላይ ሳልደግምበት፣ እንዲሁ፤ አንተ ያደረግኸውን ማድረግ አያቅተኝም” አልኩት፡፡ በድፍረት ነው የተናገርኩት፡፡ ድግምት የሚባል የለም ብዬ ብዙ ጎትጉቻለሁ፡፡ መዋረድ የለብኝም፡፡ ስለዚህ በሙሉ ልብ እኔም አደርጋለሁ ብዬ ተናገርኩ! ሆም ኢኮኖሚክስ የሚባል የባልትና ትምህርት ክፍል አለ፡፡ ከዚያ መርፌ አመጣን፡፡ ልጁ መርፌው ላይ ደገመበት፡፡ ከዛ በጉንጩ በውስጠኛው በኩል መርፌውን አስገብቶ ጉንጩን በስቶ በውጪው በኩል መርፌውን ብቅ አደረገውና “ያያሉ ቲቸር ምንም ደም ጠብ አላለም” አለ፡፡ ቀጥሎ መርፌውን ሙሉ በሙሉ ቆዳውን አሳልፎ አወጣው፡፡ ተማሪው ሁሉ ጉድ አለ! ሁላችንም ልጁ የሠራውን አይተናል፡፡ ቀጥሎ የኔ ጉዳይ ሊሆን ነው፡፡ አልተዘጋጀሁም፡፡ መርፌውን ተቀበልኩ፡፡ “ቲቸር ይቅርብዎ፡፡ በቃ ይቅር ግዴለም” አሉ የሚወዱኝ ተማሪዎቼ፡፡ እንዴት ያን ውርደት ልቀበል? ልሞክርና ይለይልኝ እንጂ ምን ዕድል አለኝ? ልበ-ሙሉነቴ ብቻ ነው እንጂ ልሥራው አልሥራው የማቀው ነገር የለም፡፡ መሸነፌን ለመቀበል አልፈለኩም፡፡ መርፌውን በአፌ ከትቼ ጉንጬን በውስጥ በኩል ወጋ ወጋ አደረኩት፡፡ ምንም አልተሰማኝ - አላመመኝም፡፡ ገፋሁት፡፡ ገባ ወደ ጉንጬ፡፡ የውጪኛው ቆዳዬ ጋ ሲደርስ ብቻ ትንሽ አመመኝ፡፡ እዚህ ደርሼማ አላቆምም ብዬ ገፍቼ ቆዳዬን በስቼ አወጣሁት፡፡ ግማሹ በውስጥ ግማሹ በውጪ ሆኖ ታየ፡፡ አላመንኩም እራሴ፡፡ በጣም ደስ አለኝ፡፡ ፈነደቅሁኝ፡፡ ወደማስተምርባቸው ክፍሎች ሁሉ ሄጄ አሳየሁኝ፡፡ ተመልሼ ለ7ኛ D ክፍል አሳየሁ፡፡ ትልቅ ለውጥ በራሴ ላይ ያመጣ ጉዳይ ነው፡፡ “እናንተም ሞክሩት” አልኩ ልጆቹን ሁሉ፡፡ አንዳንድ ተማሪዎች ላይ ብቻ የሚደማበትን ቦታ አየን፡፡ ፈተሸን፡፡ ጉንጭ መካከል ከሆነ አይደማም፡፡ ዝቅ ብሎ ከሆነ ግን የሚደማበት ሁኔታ አለ፡፡ በዚያን ዘመን ከግብፅ የመጣ አንድ ግብፃዊ ዶክተር ነበር፡፡ የሃይለማርያም ማሞ ሆስፒታል ሐኪም ነው፡፡ ጓደኛሞች ነን፡፡ በጋራ ከቲ.ቲ.አይና (ከመምህራን ማሰልጠኛ) ከሌሎች ሠራተኞች ጋር በምናደርገው ስበሰባ ላይ አገኘሁትና “መርፌ ጉንጬን በስቼ አወጣሁ! ምንም አልሆንኩም” አልኩት፡፡ “ምን?” አለኝ በቁጣ! “ውሸታም ነህ! ሁለተኛ ላይህ አልፈልግም” አለ፡፡ “ግዴለህም አሁን ላሳይህ እችላለሁ ኮ” ብለው፤ “አታሳየኝ ዞር በል ከፊቴ!” አለኝ፡፡ እስከዛሬ ለምን እንደዛ ድርቅ እንዳለ ይገርመኛል፡፡ የሳይንስ ምሁርም እንግዲህ ድርቅ ሲል ድርቅ ነው ማለት ነው፡፡ ለነገሩ ብዙ ጊዜ ከቆየሁ በኋላ የመርፌውን ነገር ሳወጣና ሳወርደው፤ አንድ ነገር ታየኝ፡- “እንዴ! እኛ ሆስፒታል ስንሄድ መዓት ጊዜ አይደለም እንዴ ታፋችን ላይ በመርፌ የምንጠቀጠቀው? መቼ ይደማል?” አልኩኝ፡፡ አየህ የማመንና ያለማመን ነገር ልዩነቱ በጣም ቀጭን ነው መንገዱ፡፡

ከዚያን ጊዜ በኋላ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑበት ነዋ ሌላው የሥራ ልምድዎ?

በትክክል፡፡

ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ የማስተማር አገልግሎት ተመልሰው 4ኛ ዓመት ገብተው ጨረሱ ማለት ነው?

የሚገርም ነገር ልንገርህ፡፡ እኔ ፊዚክስ በምማርበት ጊዜ ብቻዬን ነበርኩ፡፡

እንዴት ብቻዎትን?

በቃ፡፡ ከኔ በፊት አንድ አሥር የፊዚክስ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ከእኔ በኋላም እንደዛው አሥር ያህል ነበሩ፡፡ በእኔ ጊዜ ግን እስከ ኢዩስ የአስተማሪ አገልግሎት እስከምሄድ ድረስ ብቻዬን ነበርኩኝ፡፡ ያኔ በመጀመሪያ ሁለት ነበርን፡፡ አንድ ሰለሞን ከበደ የሚባል የናዝሬት ልጅ ነበር፡፡ እሱ ፊዚክሱን አቋርጦ ስታቲስቲክስ ገባ፡፡ በቃ ብቻዬን ቀረሁ፡፡ ታዲያ እንዳልኩህ ደብረ ብርሃን በማስተማር ላይ ሳለሁ (ለዛውም አንድ ዓመት) ዶክተር ቨርጊስ የሚባል ህንዳዊ ነበር የዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ ዲፓርትመንት ኃላፊ (ልጁ እንኳን አሁን ስለኢትዮጵያ ልምዱ መጽሀፍ ፅፏል) … ደወለልኝ፡፡ በደብረ ብርሃን ዳይሬክተር በኩል … ትፈለጋለህ ስልክ ከአዲስ አበባ ከዩኒቨርሲቲ ነው ብለው አገናኙኝ፡፡ ዶክተር ቨርጊስ ነው - “አራተኛ ዓመት ስትጨርስ ምን ለመሆን ትፈልጋለህ?” አለኝ፡፡ እኔም “ዩኒቨርሲቲ ቀርቼ ማስተማር ነው የምፈልገው” አልኩት፡፡ “እኛ ውጪ ልንልክህ እንፈልጋለን” አለ፡፡ “እሺ፤ ደስ ይለኛል” አልኩት፡፡

በምን ምክንያት ነው ሊልክዎ የፈለገው?

ያኔ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ የፉልብራይት ጎብኚ ፕሮፌሰሮች ነበሩ፡፡ ስኮላርሺፕ ለዩኒቨርሲቲው ይመጣል፡፡ ግን አራተኛ ዓመት ለጨረሰ ተማሪ ነው፡፡ ዕድሉ እንዳይበላሽ እኔ ባልጨርስም ሊልኩኝና እዛው አራተኛ ዓመት እንዳጠናቅቅ ያስባሉ፡፡ ከጎብኝዎቹ ፕሮፌሰሮች መካከል ቪ.ኢ.ፒልቸር የሚባል ሰው “አሜሪካን አገር እኔ ልቀበለው  እችላለሁ” ይላል፡፡ በቃ፡፡ ሂድና ተማር ተባልኩ፡፡

ወጪውንስ ማን ቻለልዎ?

ያኔ እንደዛሬ ገንዘባችን አልወደቀም፡፡  ዩኒቨርሲቲያችን 2000 የኢትዮጵያ ብር ሰጠኝ፡፡ በዛን ጊዜ ሲመነዘር 1000 ዶላር ነው፡፡ ለአሥር ወር ነው የተሰጠኝ፡፡ 100 ዶላር ለአንድ ወር ማለት ነው፡፡ መኝታና ምግብ የምማርበት ኮሌጅ ይችለኛል፡፡

ምን የሚባል ኮሌጅ ነው?

ዩኒየን ኮሌጅ፣ ስኬኔክታዲ፤ ኒውዮርክ ይባላል፡፡ ፍራተርኒቲ ሆስቴል ነው ያለው፡፡ ወንዶች ብቻ ነን የምናድርበት፡፡ ያን ዓመት ለመጨረሻ ጊዜ ነው የወንዶች ብቻ ሆኖ የቀጠለው፡፡ እኛ መባቻው ነበርን ማለት ይቻላል፡፡ ከዚያ ወዲያ ሴቶችም ገቡ፡፡ በፈረንጆች 1969/70 መሆኑ ነው፡፡

የማስተርስ ዲግሪዎትንም እዚያው ነው የሠሩት?

አይ፡፡ ማስተርሴን በ1973 ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሜሪላንድ፣ ኮሌጅ ፓርክ ነው ያገኘሁት፡፡

ዶክትሬትዎንስ?

እሱን በ1998 ከህንድ ነው ከባንጋሎር ኢንዲያን ኢንስቲቲዩት ኦፍ ሳይንስ ነው የወሰድኩት፡፡

ማስተርስዎን በ1973 አግኝተው ዶክትሬትዎን በ1998 ወሰዱ ማለት ከ25 ዓመት በኋለ ማለት’ኮ ነው፡፡ አልዘገየም?

እሱ እንግዲህ በማህል እሥር ቤት ገብቼ ስለነበር ከፊሉን በዛ ስለተመረቅሁ ነው፡፡

በደርግ ዘመን ማለት ነው?

አዎን፡፡

የት የት ታሠሩ? እሥርን እንዴት ያዩታል?

ጉደኛ ነገር ነው!! የአይጥ ጎሬ ነው የሚመስሉኝ፡፡ ከምድር በታች ያለን ይመስለኝ ነበር፡፡ ካንድ ጐሬ ሌላ ጐሬ ውስጥ ውስጡን የምንርመሰመስ ይመስለኛል፡፡ እሥር የጀመርኩት እንዳልኩህ ደብረ ብርሃን ሳስተምር በነበረ ጊዜ፤ ት/ቤት ተረብሾ በዛ ሰበብ ለአንድ ቀን ውሎ፣ ለዛውም አላሳደሩን፤ በኃይለ ሥላሴ ጊዜ ማለት ነው - ያኔ ነው የጀመረኝ፤ ነው የጀመርኩት?

ከዚያ በኋላ በደርግ ጊዜ በሰው ጥቆማ ከፍተኛ 12 ቀበሌ 19፣ ጣሊያን ኤምባሲ አካባቢ እንዲህ የእንጦጦን ሰንሰለት ይዞ በሚመጣው ተራራ በኩል፣ ያለ ቦታ ነው፡፡ የአብዮት ጥበቃው ሊቀመንበር ወደ ቢሮው ወስዶኝ እየፎከረ ገባ … ደነፋብኝ … ደነፋብኝ … ደነፋብኝ …. ያው ጉሮኖ ሊከተኝ ነው፡፡ ያይጥ ጎሬ፡፡

እሥር ቤቱ ምን ይመስላል?

በተለምዶ አሳሪዎቹ ሰፊ ግቢ ነው የሚመርጡት፡ ትልቅ ቪላ እና ሰርቪስ ክፍሎች፡፡ ዘመናዊ ቤት አይደለም ጭቃ ቤት ነው፡፡ አብዮት ጥበቃው ሊቀመንበር ቪላው ውስጥ ነው ያለው፡፡ ወጣት እሥረኛ ይበዛ ነበር እዛ፡፡ ከሥር ከሥር ወጣቱ እሥረኛ ይመረታል - እየታሠረ ይገባል፡፡

በምን ጉዳይ?

ያው በወቅቱ የፖለቲካ ጉዳይ ነዋ! እኛ ሁለት ሜትር በሶስት ሜትር የምትሆን ትንሽ ክፍል ውስጥ ነው የታሠርነው፡፡ አንድ አሸናፊ የሚባል ልጅ ትዝ ይለኛል፡፡ ከመርካቶ ነው የያዙት፡፡ በየቦታው ሲደበድቡት ቆይተው ነው እኛ ወዳለንበት ያመጡት፡፡ ሠፈሩ ግን ፈረንሣይ ለጋሲዮን ነው፡፡ ተረበኛ፣ የንግግር ችሎታ ያለው፤  ነገር አዋቂ የምትለው ዓይነት ነው፡፡ ያን ሁሉ ተደብድቦም፤ ሲያጫውተን ያመሻል፡፡ በኋላ ሁለት ቦታ ተከፍለን ሁለት የተለያየ ክፍል ገባን … የሚገርምህ በዚያም ደረጃ ከአብዮት ጠባቂዎቹ ጋር ግንኙነት ያላቸውና አብረው የሚያድሩ ሴቶች ነበሩ፡፡

ማደር ማደር?

አዎ እድር እድርድር ማለት! ከሴቶች እሥረኞች መካከል የአሸናፊ እህትም ነበረች፡፡ ይሄ እሥር የተካሄደበት እንግዲህ የመጀመሪያዋ የአይጥ ጉሮኖ ናት ለማለት ትችላለህ፡፡ ከዛ ወደ ራስ ሥዩም ግቢ ተወሰድን፣ እዛ ከየቀበሌው የተሰበሰበው ሁሉ ተጠራቅሟል፡፡ በጠዋት፣ በሌሊት ነው የወሰዱን፡፡ ቶርች ያደረጉን (የገረፉን) እዛ ነው!! (እነ ዘለቀ፣ ዘገየ ወዘተ .. እዛ ናቸው) ቀጥለው ደግሞ ወደ ከፍተኛው ዋና ጽ/ቤት ፈረንሣይ ኤምባሲ አጠገብ ወሰዱን፡፡ ከዛ በፊት ነው አሸናፊን የገደሉት! ካምፕፋየር አድርገው የገደሉበትም ሁኔታ አለ፡፡

እንዴት ካምፕፋየር?

አንድ ማታ እሳት አንድዱ አሉ … ጨፍሩ አሉ … ዘምሩ አሉ … እንዲህ ሞቅ ያለ ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ ከዛ ተኛን፡፡ ሌሊቱን ሰውን እየጠሩ ወስደው ገደሉ፡፡ ብዙም አርቀው አይደለም፡፡ ሬሣ በየቤቱ ደጃፍ ጣሉ፡፡ አስታወሳለሁ፤ ታሪኩ ጎንፋ የሚባለውን ልጅ ገድለው እናት አባቱ ቤት ደጃፍ ነው ጥለውት የሄዱት! እነ ብርሃኑ ዑመር (እሱ እንኳ መጀመሪያም ጠርጥሮ ሰግቶ ነበር) ሌሎችም ተገደሉ! አሰቃቂ ነበር! ስምንት ወር ከ20 ቀን ቆይተን፣ “ተመልሰናል ተመለሱ” በሉ ተብለን ዘምረን ጥቅምት 5 ቀን 1971 ዓ.ም ተፈታን፡፡ ጥር መጨረሻ መሰለኝ የታሰርኩት፡፡ ከዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ ሳለሁ  ነው የታሰርኩት!

የከፍተኛው እሥር ቤትስ ምን ይመስላል?

ግራውንድ ፕላስ ዋን ነው፡፡ ጋራጅ አለው፡፡ እሱ አልበቃ ብሎ የቆርቆሮ አዳራሽ ተሰርቶልን ነበር የምንኖረው፡፡ መግረፊያ ቦታ ሰርቪስ ቤት ውስጥ ነበረ፡፡ (ዕውነትም ሰርቪስ ቤት!)

ስትፈቱስ እንዴት ነበር?

ቀስ በቀስ ሁኔታው ላላና እየወጣችሁ ከተማ ዋሉ፣ ተመለሱና እደሩ ተባልን፡፡ የሚገርምህ ጠቋሚውም ተጠቋሚውም፣ ከነሱ ጋር ያበረውም ከነሱ የተጣላውም፤ ሁሉም ነበር ወጥቶ የሚመለሰው፡፡ ከዚያ ተፈታን፡፡ ማስተማር ጀመርኩ፡፡ ቆይቼ ደግሞ እንደገና ተያዝኩ፡፡

እንደገና?

አዎ እንደገና፡፡ ከባህር ዳር ነው የተያዝኩት፡፡ አስተዳዳሪው፤ ካሣዬ አራጋው ነው ያኔ ያለው፡፡ ደብረ ማርቆስ አምጥተው ደበደቡኝ! ከዛ ማዕከላዊ ምርመራ ድርጅት፣ ዋናው ቦታ አመጡኝ፡፡ የውጪውን ዓለም ረስተን የኖርንበት ሌላው ጎሬ! አምስት ዓመት እዚህ ጎሬ ቆይቼ ወደ ከርቸሌ ደግሞ ወሰዱን - ለሁለት ዓመት! ዞሮ ዞሮ ከጎሬ ጎሬ መርመስመስ ነው!

ያው ጎሬ ውስጥ ይሁን እንጂ ባችለር፣ ማስተርስ፣ ፒ.ኤች.ዲ እንደ ማግኘት ነው አደል?

በየደረጃው አዎ!

ልምዱ ምን ያስተማረዎ ይመስልዎታል?

አበራ የሚባል አንድ እሥረኛ ነበር ትዝ ይለኛል - ማዕከላዊ የረሀብ አድማ አድርጐ ነበር - አሁን አግብቶ ወልዷል፡፡ የተኩስን ድምፅ እንደሙዚቃ የለመደ ሰው ነበር፡፡ እሱ ያለኝ ትዝ ይለኛል፡፡ ከማዕከላዊ ቀድሞኝ ከርቸሌ ሄዷል፡፡ ኋላ እኔ ወደ ከርቸሌ ስሄድ ያገኘኛል፡፡

“… አንተኮ የትም ቦታ ለማደር ትችላለህ - ምንም አይቸግርህም! እንዳመጣጡ ለችግር መፍትሔ መፈለግ አያቅትህም፡፡ የመጣውን መቀበል የሚችል ጥንካሬ አለህ!” አለኝ፡፡ ዕውነቱን ነው፡፡ ለነገሩ እሱም በመከራ የተፈነ ሰው ነበር፡፡

በማዕከላዊም በከርቸሌም ቆይታዎ ወጌሻ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ ፊዚክስና ወጌሻነት - ፊዚዮ - ቴራፒ፤ ይገጣጠማል እንዴ?

ደረጀና ፀጋዬ ኃይሌ የሚባሉ ወዳጆቼ “ፊዚዮቴራፒ በእኛ  ነው የተለማመደው” ይሉኝ ነበር፡፡ በተለይ ፀጋዬ ኃይሌ ሳሸው ትንሽ ጠንከር ካደረኩ “ሌላ ቦታ ያልገደሉኝን አንተ ልትገድለኝ ነው?” ይለኝ ነበር፡፡ ከታሠርኩበት ክፍል (ማዕከላዊ ላይ - ቤት፣ ሁለት ቁጥር) ጀመርኩ፡፡ ቀስ ቀስ እያልኩ ሰው ለማሸት ሌሎቹን ክፍሎች ማዳረስ ጀመርኩ፡፡

አስበህበት ነው ወጌሻ የሆንከው?

ምንም አላውቀውም፡፡ ሥራ መፍታቴ ሳይሆን አይቀርም፡፡ መጽሀፍ ከማንበብ ጋር ሲጋራ ማቆም ተያይዞልኛል፡፡ ማጨሱን በማንበብ ለመተካት፡፡ ቢዚ መሆን፡፡ አስታውሳለሁ “ኤይቲንዝ ብሩሜር”ን፤ የማርክስን እያነበብኩ እየተረጎምኩ ነበር፡፡ ሲጋራ ከሌሎች እስረኞች  ጋር አቁመን ነበር፡፡ በኋላ አፈረስን፡፡ እኔ እንደገና አቆምኩ እሥረኛው ዘሪሁን  በንቲ (ቆይቶ ተገድሏል) እንዲህ አለኝ አንድ ቀን፡-

“ሲጋራ ታቆማለህ፡፡ እንደገና ትጀምራለህ … እንደገና ታቆማለህ ትጀምራለህ፡፡ ምን ትዋዥቃለህ? ገንዘብ የሚቸግርህ ከሆነ እኔ አለሁ” አለኝ ኮስተር ብሎ፡፡ ያ የመጨረሻ ትምህርቴ ሆነ፡፡ አቆምኩ አቆምኩ፡፡ ታዲያ ሲጋራውን ለመተካት የሆነ ሥራ መሥራት ነበረብኝ፡፡ ወጌሻነቱን ጀመርኩ፡፡ አንድ የሻቢያ ልጅ ከቤቱ የአኩፓንክቸር መጽሐፍ አመጣልኝ፡፡ እሱን እያነበብኩ ዋና ዋና ብልቶችን በጣቴ (እንደመርፌ) እየነካሁ ማሸቱን ተያያዝኩት በሽተኛ ተገኘ! ሞካሪ ተገኘ! ፈውስ ተገኘ!

በእርሶ ታሽተው፣ በጥይት የተመቱ፤ ሐብለሰረሰራቸው ተመቶ በክራንች የሚሄዱ ሰዎች ሳይቀሩ ሰዎች ሳይቀሩ ድነው ዛሬ ኳስ ይጫወታሉ ይባላል፡፡ እውነት ነው?

አዎ፡፡ ብዙ ሰዎችን ረድቻለሁ፡፡ የከርቸሌ የጥበቃ አሥር አለቃም በትዕግስት አሽቼ አድኛለሁ፡፡ ያውም እሥረኛ ሲያባርሩ ጉድጓድ ገብተው ወለም ብሏቸው፡፡

አንዳንድ ሰዎች በጐ ምግባር የፖለቲካዊነታችን ሰፊ ገጽታ ነው ይላሉ፡፡ በእሥር ቤት የሚያውቁትም ይሄን ይጋራሉ፡፡ እንዴት ያዩታል?

በጐ ለማድረግ የግድ ፖለቲከኛ መሆን አያስፈልግም፡፡ ምናልባትም በቅርብ ሊተሳሰሩ ይችሉ ይመስለኛል፡፡ አንተ ግን መልካም ማድረግ ውስጥህ ካለ በቃ መልካም ትሆናለህ፡፡ መልካምነት ከፖለቲካ ይሰፋል፡፡

ከእሥር ቤት ህይወት ያስተዋሉት ትልቅ ቁም ነገር ምንድን ነው?

ለሰው መድኃኒቱ ሰው መሆኑን! ዓለምን ዓለም ለማድረግ ያለነው እኛው መሆናችንን!  ሌላ ማንም ከውጪ መጥቶ አያድነንም፡፡ እኛው ብቻ ነን የችግራችን መፍትሔ!

ይሄንን ሁሉ የእሥር ቤት ዝርዝር የጠየኩዎትና ዳር ዳር ስል የቆየሁት አንድ ነገር ስለተጠራጠርኩ ነው፡፡

ምን ተጠራጠርክ?

የዘንድሮ የአንድሬ ሳካሮቭ የፊዚክስ ሽልማት አሸናፊ ተሸላሚ እርሶ ነዎት፡፡ የሽልማቱ ቦርድ በፃፈልዎ መግለጫ ላይ:-

“For tireless efforts in defense of human rights, freedom of expression, and education anywhere in the world, and for inspiring students, colleagues and others to do the same” ይላል፡፡ ይህ እንግዲህ በቁሙ ስንተረጉመው፤

“ለሰብዓዊ መብት፤ ሀሳብን ለመግለጽ እና ለትምህርት ነፃነት መከበር ደከመኝ፣ ታከተኝ ሳይሉ፤ ላደረጉት ጥረት እንዲሁም ተማሪዎች፣ የሥራ ባልደረቦችና ሌሎች የዘርፉ ተሳታፊዎች ለሙያው እንዲነሳሱ አርአያ በመሆናቸው ይህ ሠርተፊኬት ተሰጥቷቸዋል” እንደማለት ነው፡፡

ከዚህ አንፃር አሁን እርሶ ከሚያጠኑት የፊዚክስ ምርምር ጋር በቀጥታ ይያያዛል ይላሉ?

በጭራሽ!

ታዲያ ለምን የተሸለሙ ይመስልዎታል?

ምናልባት በሀገራችን እንደልብ ማስተማር በማይቻልበትና በከባድ ዘመን ውስጥ ፊዚክስ በማስተማር ሂደት ላይ ያጋጠሙኝን ችግሮችና ሥቃያት ታሳቢ አድርገውም ሊሆን ይችላል እላለሁ፡፡ በዛ አስከፊ ጊዜ ስለመሥራትህ ማለታቸው ይሆናል፡፡

እስቲ እርሶ የሚያጠኑትን የፊዚክስ ዘርፍ እንዲያው ለተራ ሰው በሚገባ መንገድ ይግለፁልኝ?

የእኔ ጥናት የHeat Engine የሙቀትን ኃይል የተወሰነውን ክፍል ለፍሬያማ ሥራ መጠቀም ነው፡፡ የመኪና ኤንጂን ነዳጅን አቃጥሎ በተወሰነው ኃይል መኪናን ማሽከርከሩን መሠረት ያደርጋል፡፡ ካርቦኃይድሬትን በሰውነታችን ውስጥ አቃጥሎ ጡንቻንና አዕምሮን ማንቀሳቀስም ያው ነው፡፡ ያካባቢን የሙቀት ልዩነት (Temperature Ingredient) የተወሰነውን ያህል ወደ ጠቃሚ ሥራ መለወጥ ነው፡፡ የፀሐይ ኃይል ለኤሌትሪክ ኃይል መጠቀም ለምሳሌ፡፡ ደረጃውን ከመኪናና ከባቡር ኃይል መጠን አሳንሶ፣ ወደሰውነት ሞለኪውሎች ደረጃ አውርዶ፣ በናኖ ቴክኖሎጂ ደረጃ፣ መጠቀም፡፡ ይቺው ናት ሥራዬ!

በSolar cell device - ፀሐይን ወደ ኤሌትሪክ፣ ወደሒት ፓምፕ መለወጥ እነዚህን ለመሥራት ትናንሽ መሣሪያዎችን መፍጠር፣ ወደ ማስ ፕሮዳክሽን (ወደ ሰፊ ምርት) ሳይኬድ ለቅድመ ጥናት መጠቀም! ይሄው ነው ጉዳዬ! ይሄን ጥናት ለማካሄድ ሰፊ እርዳታ የሚያደርግልኝ የስዊድን እርዳታ ነው፡፡ ጉባዔ ለመካፈል፣ ዕቃ ለመግዛት፣ ሰዎችን ለምርምር ለመጋበዝ፣ የረዳኝ ኢንተርናሽናል ፕሮግራም ኢን ፊዚካል ሳይንስስ (IPPS) ነው፡፡ እንጂ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚረዳው ከመቶ አምስት እጅም አይሆንም፡፡ ባሁኑ ጊዜ 6 የፒ.ኤች.ዲ ተማሪዎችን በማማከር ላይ ነኝ፡፡

የእኛን አገር የሳይንስ ሂደት እንዴት ያዩታል?

አዬ! በሳይንስ ዓለም እዚህ አገር fail አድርገናል - አልተሳካልንም፡፡ ይሄንን በደንብ ተረድቻለሁ፡፡ አርቲፊሻል ሆኖብኛል፡፡ እኔን የገባኝን ያህል ምን ያህሉን አስተላልፌያለሁ ብዬ ሳስብ ውድቀታችን ይታየኛል ይከነክነኛል! mode of investigation (መርምሮ መድረሻ) ሆኖ አይሰማኝም፡፡ ከ1965-2004 ዓ.ም የ40 ዓመት ጉዞ! ሳይንስ ለብ ለብ ሆኗል፡፡ ጨዋታ ነው፡፡ መመርመርና መቀየስ ያለብን ይመስለኛል - ከዜሮም ተነስተን ቢሆን! የእስከዛሬው የፉርሽ ጉዞ ነው! የከሸፈ ጉዞ ነው! አልረካሁም ነው የምልህ! ውጪ የሄዱ ሳይንቲስቶች እንጂ እዚህ ምንም አላፈራንም! There is no sense of depth (ለብ ለብ ነው) በራሴም ጭምር! መንግሥት የትምህርት ዓለሙን ለማሻሻል (በፊዚክስ ረገድ) እንደየኢትዮጵያ የፊዚክስ ባለሙያዎች ማህበር ዓይነቱ ጋር በቅርብ ደህና ዝምድናና ምክክር ፈጥሮ ካልተጓዘ፤ ተነጣጥሏልና ምንም እየተሰራ እንዳልሆነ ለማየት አይችልም!  ከዜሮ የምንነሳበትን መንገድ መፈለግ ያሻል፡፡ የሚመጣ ዕቃ መጠቀሚያ ነው እንጂ የራሳችንን ወጣቶች ይዘን የምንሄድበት ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡ ሥር እየያዘ አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ የፊዚክስ ባለሙያዎች ማህበር የወቅቱ ሊቀመንበር እርሶ ነዎት?

አዎን፡፡ ከዚህ ቀደም ለሁለት ተከታታይ ዓመት ተመርጬ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ከጊዜ በኋላ እንደገና ተመርጫለሁ፡፡ አምና ጂማ ዩኒቨርሲቲ ነበር ጉባዔያችን፡፡ ዘንድሮ ከኦክቶበር 7-8 ሐረማያ ነበር፡፡ መጪው 7ኛ ጉባዔ ደግሞ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ይካሄዳል፡፡

ጉባዔያችሁ ፍሬው ምንድን ነው ታዲያ?

ገና መንገድ ለመቀየስ ነው፡፡ ፊዚክስ ጠቀሜታ አለው ብለን መፎከር ነው እንጂ የሠራነው ነገር የለም፡፡ “ወሬ አታውራ፤ ዝም ብለህ ሥራ” ውስጥ አልገባንም፡፡ ዞሮ ዞሮ ችግሩም የእኛው መፍትሔውም በእኛው ነው!

የዓለም ሳይንስ ወዴት እያመራ ነው?

አንዱ ወገን የዩኒቨርስ አፈጣጠር ላይ መከራውን ያያል፡፡ ሌላው ወገን ዝግመተ - ለውጥ evolution, Biophysics of the living, ጂን የማስተላለፍ ጥንተ - ነገር (transcription) ላይ አተኩሯል፡፡ ሦስተኛው ወገን እያንዳንዱን ነገር አቶም በአቶም አንጥረን እንይ እያለ፤ ናኖ ሳይንስ ላይ አነጣጥሯል፡፡ ሦስቱ ሳይንስ ላይ ነው ያለነው!

ከፊዚስቶች እነማንን ያደንቃሉ?

ሁለት ሰዎች አሉ የማደንቃቸው፡፡ ሁለቱም የሙያ - መካሮቼ (አድቫይዘሮቼ) ናቸው!

አንደኛው ኩማር ይባላል፡፡ ዕውቀቱና ዕይታው የሚያስደንቀኝ ሰው ነው!

አንድ አባባሉን ልጠቅስ ዕወዳለሁ፡-

“የምወደውን ሥራ እየሠራሁ ይከፈለኛል! ከዚህ በላይ ምን ያስደስተኛል?” ሁለተኛው መካሬ፤ አላንታ - ክሪሽና ነው፡፡ ሥራው ላይ ተቸክሎ ነው የሚውለው፤ ውጤታማ ነው፡፡ የባለቤቴ እናት የሚጠቀሙባትን አንድ አባባል ባለቤቴ ትነግረኛለች፡፡ አባባሏ ለአላንታ ክሪሽና ትሠራለች፡፡ እንዲህ ትላለች፡-

“ሥራ የሚሠራው በቂጥ ነው” ካልተቀመጡና ካላተኮሩ ሥራ አይሰራም እንደማለት ነው!

የአንድሬ ሳካሮቭ ሽልማት አሸናፊ ሆነው ሽልማቱን ለመቀበል ወደ አሜሪካ ቦስተን እየሄዱ ነው፡፡ ባለቤትዎ አብረዎት ይሄዳሉ፡፡ ልጅዎ እምቢ ብላለች ተብሏል፡፡ እንዴት ነው ነገሩ?

የእኔ ተማሪዎች ናቸው ሀሳቡን ያመጡት - አሜሪካ ያሉ፡፡ ከሌሎች ጋር ተመካክረው ነው፡፡ እንዳሻው ኃይሉ ደውሎ ሲነግረኝ ባለቤቴን አማከርኳት፡፡

“ቆይ ልጃችንን ልንገራት” አለች፡፡ ልጃችን ረቂቅ 16 ዓመቷ ነው፡፡ 11ኛ ክፍል ናት፡፡ “እኔ ትምህርቴን ብማር ይሻለኛል፡፡ አልሄድም”፤ አለች፡፡ ብዙም ጉጉት አላሳየችም፡፡ ነፃነቷን አከበርንላት፡፡ ተቀበልናት፡፡

ዛሬ ወጣቱ ሁሉ አሜሪካ አሜሪካ በሚልበት ሰዓት እምቢ ማለቷ ይገርማል፡፡ ትምህርቱ ይበልጥብኛል ማለቷ ነው!

ምነው እንዲህ ያሉትን ወጣቶች ባበዛልን! በሉ መልካም ጉዞ! ሲመለሱ ስለሁኔታው ቃልዎትን እንደሚሰጡኝ በጉጉት እጠብቃለሁ፡

በሚገባ! አመሰግናለሁ!

 

 

 

Read 2539 times Last modified on Saturday, 25 February 2012 13:05