Saturday, 26 March 2016 15:32

ሥጋ ለባሹ ሞሰብና ተራማጁ ማንካ

Written by  በእውቀቱ ሥዩም)
Rate this item
(45 votes)

     ሳምንት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የታተመ “የከአሜን ባሻገር ጥቂት ውሸቶች“ የሚል ርእስ ያለው ጽሁፍ ደርሶኝ አነበብሁት፡፡ ዶኖ ኢበሮ የተባለ አስተያየት ሰጭ፤ ”የጎበና ቅኝት“ በሚለው ምእራፍ ሥር  ስለ ካፋ ግዛት በጻፍኩት ላይ ያለውን ቅሬታ ገልጧል፡፡ ሰውየው አንዳንድ ተገቢ ጥያቄዎችን አንሥቷል ፡፡ ለምሳሌ ፤”ከፋ“ ያልኩትን ካፋ ብየ እንዳርም ጥሩ ጥቆማ ሰጥቶኛል፡፡
በተቀረ፤አንዳንድ ጉልቤዎች የግለሰብን ሐሳብ ለማፈን የሚጠቀሙባትን ”ህዝብን መስደብ“ የምትል የተባነነባት ሀረግ ባይደጋግማት ጥሩ ነበር፡፡ በየሠፈሩ ራሱን የህዝብ የክብር ዘበኛ አድርጎ የሚሾም ሰው በዝቶ ተቸገርን!ለማንኛውም ለሰውየው ተገቢ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ እሰጣለሁ፤ እግረ መንገዴንም ለባልንጀሮቼ የማውቀውን አካፍላለሁ ብየ አቀድሁ፡ግን ሳውደለድል ያዲስ አድማስ ባቡር አመለጠኝ ፡፡ እነሆ የመጀመርያውን ክፍል በዌብሳይቱ ላይ እንዲለጠፍልኝ ሰድጀዋለሁ፡፡
ጉዳዩ ምንድነው?የኢትዮጵያ የንጉሥ ግዛት የተመሠረተው በዱላና በመላ ነው፡፡ ይህ አይካድም፡፡ ግን በዚህ መንገድ የገበሩ ትንንሽ ግዛቶች ራሳቸውን የቻሉ ዱለኞችና ጨቋኞች ነበሩ፡፡ ጭቆና ካንድ ብሄረሰብ ካንድ የገዥ መደብ ካንድ ዘመን የሚመነጭ አይደለም፡፡ የሁሉም  ዝንባሌ ነው፡፡ ቢመቸው ጎረቤቱን አፈር አስግጦ የማይገዛ ብሔረሰብም ሆነ ግለሰብ አልነበረም፡፡ ጎበናና ምኒልክ ለመጀመርያ ጊዜ  ጭቆናን በበቅሎ ጭነው ካንኮበር ወደ ደቡብ እንዳጓጓዙት ተደርጎ የሚነገረኝን አሜን ብየ  አልቀበለውም፡፡
ይቺን ለማስረዳት ግዛቶችን እየጠቀስኩ በምሳሌ ሳስረዳ ከቆየሁ በኋላ ካፋ ላይ ስደርስ ይቺን  ጣል አደረግኩ፡፡ “የካፋው ንጉሥ ምግቡን በእጁ ቆርሶ መብላትን እንደ ውርደት ስለሚቆጥረው አጉራሽ ሎሌ ነበረው፡፡ አጉራሹ ባርያ  ንጉሡን ከማጉረስ በቀር ሌላ የህይወት ተልእኮ ስላልነበረው ንጉሡን የሚያጎርስበት  እጁን በከረጢት ጠቅልሎ የመኖር ግዴታ ነበረበት፡፡ በንጉሡ አይን ይህ ሎሌ ሰው ሳይሆን ተንቀሳቃሽ ማንካ ነበር ማለት ይቻላል“
እዚህ ጋ የኔ ሥህተት፤ የጻፍኩት ጸሐይ የሞቀው እውነት ነው ብየ በማሰቤ ምክንያት ታሪካዊ ሰነድ  አለመጠቆሜ ነው፡፡ በሌላ በኩል ሁነቱን አጋንኘ ተርጉሜው ከሆነ በኩሸት እንጂ በውሸት ልከሰስ አይገባም፡፡
ተቺየ ይቺን ”ውሸቴን“ ውድቅ ለማድረግ የሚከተለውን የእስክንድር ቡላቶቪቺ ጥቅስ ተጠጋ፡፡(ቡላቶቪቺ ካፋን ለማስገበር በተደረገው ጦርነት ወቅት ከምኒልክ ጦር ጋር የነበረ ወዶ ዘማች ነው፡፡)
The dinner of the king was accompanied with great ceremonies. The only person allowed to go behind the curtains, where the tato made himself comfortable, was the one who had the responsibility to feed him and give him drink. The sovereign himself would not exert himself at all. The gentleman carver brought everything to him and placed it in his mouth. This post was considered very important in the court hierarchy. This dignitary had to be distinguished for the best moral qualities so as not to in any way harm the king. During the time when he was away from his main duties, his right arm was tied in a canvas sack, in order that this arm, which fed the king, not contract some illness or be bewitched.

አቶ ዶኖ ከላይ በተጠቀሰው ጥቅስ ላይ ተመሥርቶ ትንታኔውን እንዲህ ሲል አስከተለ፤
” የካፋው ንጉሥ መጋቢ፣ ባርያ ሳይሆን በታማኝነቱ የተመረጠ ሹም ነበር፡፡ ንጉሡ  ግብር በሚያበላበት ጊዜ ከታዳሚው ከሚለየው መጋረጃ፣ ከንጉሱ ጋር ገበታ የሚቀመጠው ይህ ሰዉ ብቻ ነበር (ቡላቶቪችም እንዳስቀመጠዉ)፡፡ የንጉሡ መጋቢ ንጉሱን የሚያጎርስበትን እጁን በጨርቅ  የሚሸፍነዉ በዕውቀቱ አጣሞ እንዳቀረበው፣ ሌላ የሕይወት ተልዕኮ ስላልነበረው አይደለም፡፡ ቡላቶቪች እንደጻፈዉ፡-
‘During the time when he was away from his main duties, his right arm was tied in a canvas sack, in order that  this arm, which fed the king, not contract some illness or be bewitched.’  ትርጉሙም፡- ‘ከዋና ግዳጆቹ የተለየ እንደሆነ ንጉሡን የሚያጎርስበትን ቀኝ እጁን ከበሽታና ከክፉ ድግምት (ጥንቆላ) ለመከላከል በጨርቅ ይሸፍን ነበር፡፡’ ይህ የቡላቶቪች ዘገባ በራሱ ግለሰቡ ሌሎች ስራዎች (duties) እንደነበሩት የሚያሳይና የበዕውቀቱን ውሸት የሚያስረዳ ነው፡፡“
ባጭሩ ተቺየን ሁለት ነጥቦች አስቆጥተውታል፡፡
1)የካፋን ንጉሥ  አጉራሽ ”ባርያ“ ብየ መጥራቴ፤
2) የንጉሡ አጉራሽ ሌላ የህይወት ተልእኮ አልነበረውም ብየ መጻፌ ፡፡
የባርያነቱን ጉዳይ ለመደምደሚያው  እናቆይና የህይወት ተልእኮውን ጉዳይ እናውራ፡፡ አጉራሹ ንጉሡን ከማጉረስ በላይ ምን የህይወት ተልእኮ ነበረው? ቡላቶቪቺ አልነገረንም ፤አቶ ዶኖም አልተናገረም፡፡ እኔ እንደገባኝ  ቡላቶቪቺ የሚለው፤የካፋው አጉራሽ  ማጉረስና ማጠጣት ተግባሮቹን በማይፈጽምበት ጊዜ እጁን በከረጢት ውስጥ ሸፍኖ ይይዝ ነበር፤ ይህን የሚያረገውም ንጉሥ መጋቢ እጁን ቡዳ እንዳይበላው ወይ በሽታ እንዳያጠቃው” ነው፡፡
ቡላቶቪቺ ያጉራሹ  ዋና ግዳጆች (main duties) ሲል ማጉረስና ማጠጣት ማለቱ  እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ሌላ ዋና ግዳጆች  እንደነበሩት አልተገለጸም፡፡ ሎሌው ተመላላሽ  አጉራሽ አልነበረም ፡፡  በዘበኝነትና በእረኝነት ሲያገለግል ውሎ  በትርፍ ጊዜው ንጉሡን ያጎርሳል ማለት አይደለም፡፡ አቶ ዶኖ main duties “የሚለውን ሐረግ  መጀመርያ ዋና ግዳጆች ብሎ በትክክል ተርጎሞታል፡፡ ግን ንጉሡን ከማጉረስና ከማጠጣት በላይ ምን ዋና ግዳጅ ነበረው? የሚለው ጥያቄ  ቢሰነዘርበት ምላሽ እንደማይኖረው  ገብቶታል፡፡ ስለዚህ  መውጫ ሲፈልግ “ይህ የቡላቶቪች ዘገባ በራሱ ግለሰቡ ሌሎች ሥራዎች እንደነበሩት የሚያሳይና የበውቀቱን ውሸት የሚያስረዳ ነው“ ብሎ አረፈ፡፡ በቡላቶቪቺ ጥቅስ  ውስጥ ”ሌሎች ሥራዎች “ የሚል ሐረግ የለም፡፡ የሌለ ነገር አለ ብሎ የሚጨምር ሰው ዋሾ ነው፡፡
ሩስያዊው  ወታደር የዘመን ጓድ የነበሩ   ያገራችን ጸሐፌ- ትእዛዝ ገብረሥላሴም  በግልጽ አስቀምጠውታል ፡፡ ስለ ካፋ  ንጉሡ  ወግ   ሲጽፉ፤“ አሣላፊው ለንጉሡ ካሣለፈ በኋላ እጁን በከረጢት ከቶ ይኖራል፡፡ በቀኝ እጁ አሳስቶት ሌላ ሥራ ሲሠራበት ሲበላበት የተገኘ እንደሆነ እጁን ይቆረጣል” ብለዋል፡፡(ታሪክ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ ፤ገጽ 272)
የሩስያው ወታደርና የኢትዮጵያው ዜና መዋእል ጸሀፊ  ተባብረው እንደ መሰከሩት ያጉራሹ ቀኝ እጁ የንጉሡ ብቸኛ ንብረት ነበር፡፡ አጉራሽየው በገዛ ቀኝ ክንዱ ላይ ስልጣን አልነበረውም፡፡ አይበላበትም፤ አይሠራበትም ፡፡  ይህንን ወዶ ገቡ ኮዛክ እንደ ክብር ቆጥሮት ከሆነ የራሱ ችግር ነው፡፡ እኔ እንደ ባርነት እቆጥረዋለሁ፡፡
ተቺየ ይቀጥልና በሚከተለው ሙግት መጣ፡፡
“የካፋ ንጉስ ምግቡን ከሰው እጅ መጉረሱ ለበዕውቀቱ እንዴት ከጭፍጨፋና ባርያ ፍንገላ እኩል ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ሆኖ እንደታየው ሊገባኝ አልቻለም። ኢትዮጵያዊ እንደመሆናችን አጉራሽ ማለት የፍቅርና አክብሮት መግለጫ ነዉ፡፡ እኔ እንደሚገባኝ ከአንድ ሰው እጅ መጉረስ ላጉራሹ ያለንን ፍቅር፣ እምነትና አክብሮት ያመለክታል፡፡ የካፋው ንጉሥም ቆርሶ መመገብን እንደ ዉርደት ስለሚቆጥር ተብሎ ሊወገዝ አይገባም፡፡“

ተቺየ የማይወዳደር ነገር ያወዳድራል፡፡ በርግጥ ዛሬ ጉርሻ የፍቅርና ያክብሮት ምልክት ነው፡፡ ዛሬ ማለዳ ላይ ሚስቴን ባጎረስኩበት እጄ ረፋድ ላይ  ከተገኘ የመኪና መሪ ካልተገኘ፤ ደግሞ ከዘራ እጨብጥበታለሁ ፡፡ ብፈልግ አፈር እዘግንበታለሁ፡፡ በሁለቱም እጆቼ  ላይ ሙሉ መብት አለኝ፡፡ የካፋው ንጉሥ አጉራሽ ግን እንዲህ ያለ መብት አልነበረውም፡፡ ቀኝ እጁ የራሱ እጅ  ሳይሆን በከረጢት ውስጥ የተቀመጠ የንጉሡ ሹካ  ነበር፡፡ ባርነት ማለት ደግሞ  የሌላው መሣርያ ወይም  ንብረት መሆን ማለት እንጂ ሌላ ምን ትርጉም አለው?
ለማንኛውም የካፋ  የባላባት ሥርአት ከመውደሙ በፊት በቦታው ተገኝቶ ጥናት የሠራው ጣልያኒያዊ  እንጦኒዮስ  ቼቼ የሚለውን እንስማ፤“”Quando l'Imperatore mangia, la tavola carica di vivande é sostenuta sulle spalle di uno schiavo, che deve starsene immobile per parecchie ore. Un altro schiavo di grado superiore al primo si tiene in piedi presso S. M. con un enorme corno di bufalo ripieno d'idromele, pronto a porgerglielo ad ogni suo cenno e a ritirarlo non appena ne ha bevuto qualche sorso”
(ንጉሡ  በሚመገብበት ጊዜ አንድ  ባርያ በምግብ የተሞላ ጠረጰዛ በትከሻው ይሸከማል፡፡ ለብዙ ሰአታት ሲሸከም ንቅናቄ ማሳየት የለበትም፡፡ ከጠረጰዛ ተሸካሚው በማእረግ የሚበልጥ ሌላ ባርያ በጎሽ ቀንድ የተሞላ ጠጅ ወደ ንጉሡ አፍ ያቀርባል፡፡ ምልክት ሲያሳየው አቅርቦ ትንሽ ካስጎነጨው  በኋላ ይመልሳል) “Da Zeila alle frontiere del Caffa ቅጽ 2 ፤ ገጽ 492
የጣልያኑ ዘጋቢ  ሁለቱንም፤ ”ባርያ“ ብሎ እንደጠራቸው ልብ እንበል፡፡ የንጉሡን ምግብ የተሞላ ጠረጰዛ የሚሸከመውን uno schiavo አንድ ባርያ ብሎ ሲጠራው፣ አጉራሽና አጠጭውን ደግሞ Un altro schiavo di grado superiore al primo ከመጀመርያው ባርያ በማእረግ የሚልቅ ሌላ ባርያ ብሎ ነው የገለጸው፡፡
ባጠቃላይ የካፋው ንጉስ ያመጋገብ ወግ ጭቆናን እንጂ ”ፍቅርና መከባበርን “የሚያሳይ እንዳልሆነ ከላይ የቀረበው ትረካ ምስክር ነው፡፡ ለብዙ ሰአታት ሳይንቀሳቀስ  የምግብ  ጠረጴዛ(ገበታ) በትከሻው እንዲሸከም የተፈረደበት  ሰውየና በንጉሡ መካከል የነበረው ግንኙነት “የፍቅርና ያክብሮት” ግንኙነት ተብሎ የሚተረጎም ከሆነ አንድ ያልገባኝ አገር በቀል  ፍልስፍና አለ ማለት ነው፡፡ በደንብ ካሰብነው እኒህ ሎሌዎች ከባርያም የከፋ እድል  ነበራቸው፡፡ አንዱ ስጋ ለባሽ  ሞሰብ ሲሆን፣ ሌላው እግር ያለው  ማንካ ነው፡፡


Read 15873 times Last modified on Saturday, 26 March 2016 15:55