Monday, 04 April 2016 08:01

የ‘ደስታ’ ነገር…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(10 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው… እነኚህ ፈረንጆቹ ጭራሽ “ደስተኛ አይደላችሁም...” ይሉናል! መቶ ምናምነኛ! ያውም ከምትታመሰው ሶማሊያ ብሰን አረፍን!
እኔ የምለው…ቆይ ይሄ ሁሉ ባቡር፣ ይሄ ሁሉ ቀለበት መንገድ፣ ይሄ ሁሉ ኮንዶሚኒየም፣ ይሄ ሁሉ ባለመስታወት ህንጻ፣ ይሄ ሁሉ ቢራ ምናምን እያለን እንዴት ነው ደስተኞች አይደላችሁም ብሎ ነገር!
ለጾም መግቢያ ሉካንዳ ቤቶችን እንደ ስታዲየም በር የምናጨናንቀው ደስ ቢለን አይደል!
ጉልበተኞች እንትናዬዎቻችንን ሲነጥቁን “እንትና ብትሄድ እንትና ትመጣለች፣” ብለን ዝም የምንለው ደስተኛ ብንሆን አይደል! …ቂ…ቂ…ቂ…
ይቺን ስሙኝማ…የሆኑ እንግሊዛዊ፣ ፈረንሳዊና ሩስያዊ ስለ ደስታ ትርጉም ያወራሉ፡፡ እንግሊዛዊው እንዲህ ይላል፡-
ለእኔ እውነተኛ ደስታ ማለት በቀዝቃዛ ቀን ማለዳ ተነስቶ፣ ፈረስ ላይ ወጥቶ፣ ውሾችን አስከትሎ ቀበሮ ማሳደድ ነው፡፡ ከዛም ቀበሮዋ እስክትገኝ ደረስ  አሳዶ ከገደሉ በኋላ ቤተ የዞ መመለስ፡፡ ከዛም እሷን እየጠበሱ መብላት ነው፣” ይላል፡፡
ፈረንሳዊው በበኩሉ እንዲህ ይላል፤ “ይሄ ደስታ አይደለም፡፡ ደስታ ማለት የምትወዳትን ሴት ማግኘት፣ አብረህ አሪፍ እራት መብላት፣ ግሩም የሆነ ሻምፓኝ መጠጣት፣ ከዛ አሪፍ የሆቴል ክፍል ተከራይቶ ሌሊቱን ሙሉ እነሆ በረከት መባባል፡፡ ደስታ ማለት ይሄኔ ነው፣” ይላል፡፡
የሩስያዊው ተራ ደረሰና እሱም እንዲህ አለ፡- “ሁለታችሁም ያላችሁት ደስታ አይባልም፡፡ ደስታ ማለት ቀኑን ሙሉ በፋብሪካ ስትለፉ ከዋላችሁ በኋላ ህጻኑን ኢቫንን ጉልበታችሁ ላይ አስቀምጣችሁ ፕራቭዳ ጋዜጣ እያነበባችሁ ነው፡፡ ከዛም ከመሸ በኋላ በራችሁ ይንኳኳል። ሦስት መለዮ ያደረጉ ሰዎች በራችሁ ላይ ቆመዋል፡፡
“ሴቴፓን ስቴፓኖቪች ማለት አንተ ነህ?” ይሏችኋል። እናንተም በእፎይታ ትተነፍሱና ‘እሱ የሚኖረው ላይኛው ፎቅ ነው፣’ ትላላችሁ፡፡ እውነተኛ ደስታ ማለት ይሄ ነው።”
እናላችሁ…ፈረንጆቹ ይበሉትም፣ አይበሉትም ስንት ራሳችንን ‘ቸስ’ የምናደርግበት ነገር አለን መሰላችሁ፡፡ የአንዳንዱ የደስታ ጫፍ ‘እንትን’ ነው። (እኔ የምለው…አንዳንዱ “የደስታ ጥግ ማለት ነው…” የሚለውን ለጊዜ ማሳለፊያ የምታደርጉ ልክ አይደላችሁም፡ በቃ…“የምሠራው ባጣ እንትን…” ምናምን ብሎ ምክንያት አሪፍ አይደለም፡፡)
እናማ…አንዳንዱ አለላችሁ….በጉራ ራሱን ‘የሚያስደስት፡፡’ የምር ግን በዚህ በሰለጠነ (በ‘ሰየጠነ’ የሚለውን ቃል እንደ ሁለተኛ አማራጭ ያዙልኝማ…) ዘመን ሦስተኛ የአፍሪካ ዋንጫ የወሰድን ጊዜ የነበረ አይነት ጉራ ቀሺም ነው፡፡ መአት ጊዜ እንዳወራነው ሄሊኮፕተር ዝቅ ብሎ ሲበር… “አጎቴ እንዳያየኝ…” ብሎ መደበቅ አይነት ጉራ ቀሺም ነው፡፡
በገንዘቡ ጉራ የሚነዛባችሁ አለላችሁ፡፡ (እኔ የምለው… ይሄ ሁለት ዲጂት ከሚባለው ነገር ድርሻችን የሚሰጠን መቼ ነው! አሀ…አንዳንድ ጊዜ እኮ በየቡና ቤቱ፣ በየሬስቱራንቱና በየካፌዎቹ በራፍ ስናልፍ…ሰዉ ‘ቸበር ቻቻ’ ሲል እያየን… “የሁለት ዲጂት ድርሻችንን ረሱን እንዴ!” እያልን ነዋ!)
እሱ ፈራንካ ስላለው እናንተ ልክ ለማሟያነት የተፈጠራችሁ አይነት ያስመስለዋል፡፡ የህጻናት ኃይማኖታዊ ትምህርት ቤት ነው፡፡ እናም… የሰው ልጅ እንዴት እንደተፈጠረ እያስተማሯቸው ነበር፡፡ ሔዋን እንዴት ከዓዳም ግራ ጎን አጥንት እንደተፈጠረችና ሚስቱም እንደሆነች ያስተምሯቸዋል፡፡ አንደኛው ትንሽዬ ልጅ ይሄ ነገር ከንክኖት ኖሯል፡፡ በተከታዩ ቀን ከአልጋው ሳይነሳ ይቆያል፡፡ እናቱም “ምን ሆንክ፣ ለምን አትነሳም?” ትለዋለች፡፡ ትንሹ ልጅ ሆዬ ምን ቢላት ጥሩ ነው…
“ግራ ጎኔን ያመኛል፣ ሚስት ላገኝ ነው መሰለኝ፡፡” አሪፍ አይደል!
አይታችሁልኛል…አሪፍ መኪና እየነዳ ራሱ ግማሹን በመስኮቱ አውጥቶ፣ ግራ ክንዱን በመስኮቱ አውጥቶ… አለ አይደል… “እንዴት ባደርግ ነው አንድ እግሬን በመስኮት ላወጣ የምችለው…” አይነት ጉራ በሽ ነው፡፡
እግረ መንገዴን… እናንተ አሪፍ መኪና የምትነዱ ሰዎች…እንዴት ነው ነገሩ፣ መንገድ ስንሻገር አንዳንዶቻችሁ ልክ እኮ በግቢያችሁ ‘አረንጓዴ መስክ’ ላይ የምንጎራደድ አይነት አትኮሳተሩብና!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በዛ ሰሞን አንድ ወዳጄ ከሆነ ሰው ጋር በሰውየው ‘ጋባዥነት’ አንድ ሁለት ይላሉ፡፡ በኋላም ‘ጋባዥ’ ሆዬ የሚከፍለው ገንዘብ ‘ፍለጋ’ አሥራ ምናምን ኪሶቹ ውስጥ ይገባላችኋል፡፡ ከዛ ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ይገርምሀል፣ የኤ.ቲ.ኤም ካርዶቼን በሙሉ ቤት ረስቼ መጣሁ፡፡” ሰውዬው እኮ አይደለም የኤ.ቲ.ኤም. ካርድ የሸማቾች ማህበር ካርድም የሌለው አይነት ነው። እና በዚህ ዘመን በደስታ ከረሜላ ‘ግዳይ ይጣልበት’ የነበረበት ዘመን አይነት ብልጠት አታምጡብና!
እናላችሁ…በጉራ ደስ የሚላቸው አሉላችሁ፡፡
እናላችሁ… ፈረንካው በምንም ይምጣ በምንም በጉራ ራሱን የሚያስደስት አለላችሁ፡፡
ደግሞላችሁ… በቦተሊከኝነቱ ‘የደስታ ጫፍ የነካ’ የሚመስለው ጉራ የሚነፋባችሁ አለ፡፡
(እኔ የምለው…እግረ መንገዴን… ቀደም ሲል በ“ማን መሰልኩህ!” አይነት ትከሻ ያሳዩን የነበሩ ሰዎች ምነው ቁጥራቸው ቀነሰሳ! ነገርዬው… “ልጄ፣ ሰው እርስ በእርስ በሚጠቋቆርበት ዘመን ማን ኢላማ ይገባል…” አይነት ነገር ነው እንዴ!
ስሙኝማ…ልጆች እኮ ቶሎ ነገር ይገባቸዋል። ይቺን ስሙልኝማ…የሆነ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። የምሳ ሰዓት ደርሶ ልጆቹ ምግብ እያነሱ ያልፋሉ። በአንድ ትልቅ ሳህን መአት አፕሎች አሉ። እናላችሁ…ሳህኑ ላይ “አንድ አፕል ብቻ አንሱ፣ ከዚያ በላይ ካነሳችሁ እግዚአብሔር እያያችሁ ነው፣”  የሚል ጽሁፍ አለ፡፡
ሁለት ጓደኛሞች ምግብ እያነሱ ሄዱና መአት ቸኮላት በትሪ በተከመረበት ስፍራ ደረሱ…እዛ ቦታ ላይ የሆነ ልጅ ምን የሚል ጽፎ ለጥፏል መሰላችሁ… “የፈለጋችሁትን ያህል አንሱ፣ እግዚአብሔር የሚጠብቅው አፕሎቹን ነው።”
አንድ እንጨምርማ…አንዲት እናት አምስትና ሦስት ዓመት ዕድሜ ላላቸው ልጆቿ ፓንኬከ እየሠራች ነበር። ልጆቹም መጀመሪያ ማን ይሰጠው በሚል ይጯጯሁ ጀመር፡፡ ይህ ጊዜ እናትዬው እግረ መንገዷን የሞራል ትምህርት ልታስተምራቸው ታስባለች፡፡
“ልጆችዬ፤ አንድ መልአክ እዚሀ መሀላችሁ ቢቀመጥ ኖሮ ምን ይላል መሰላችሁ ‘የመጀመሪያው ፓንኬክ ለወንድሜ ይሰጥ’ ይላል፣” ትላቸዋለች፡፡
ይሄ ጊዜ አምስት ዓመት የሆነው ልጅ ለታናሽ ወንድሙ ምን ቢለው ጥሩ ነው… “በቃ አንተ መልአክ ሁን፣” ብሎት አረፈ፡፡
ደግሞላችሁ…የሰው ክፉ ሲሰማ ደስ የሚለው አለላችሁ፡፡ የምር…አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡ “እከሌ እኮ ንግዱ ከስሮበት እንዴት ያሳዝናል መሰላችሁ!” ምናምን ብትሉ… “የታባቱ፣ እንኳንም ከሰረ!” ብሎ ከበር መልስ ሊጋብዝ የሚዳዳው ሞልቶላችኋል፡፡ ነጋዴው እኰ እሱን አንድ ቀን እንኳን እኮ ዝምቡን ‘እሽ’ ብሎት አያውቅም፡፡ የሰውየው ብቸኛ ‘ሀጢአት’ በንግዱ ስኬታማ መሆኑ ነው፡፡
የምር ግን… ነገርዬው ዘላለም ማለቃቀስ ምናምን ባይመስል… አሁን፣ አሁን በሰው ሰኬት ደስ ከሚለን ሰዎች ይልቅ የሚከፋን ሰዎች ለምንድነው የበዛን የሚመስለው! ባለሙያዎች የሆነ ምርምር ምናምን አድርጉና የሆነ ነገር በሉን እንጂ!
ብቻ… ፈረንጆቹ ምን አይተውብን እንደሆነ እንጃ… ደስታን በተመለከተ እዛ ታች ወርውረውናል። ስለዚህ… “ደስታን በማስፈን መልካም ገጽታን ለመገንባት ስትራቴጂ ቀርጸን በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ነው፡፡” ጨረስኩ፡፡
ማን ‘በዘመኑ ቋንቋ’ ተራቆ ማን ይቀራል!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5477 times