Monday, 04 April 2016 08:21

የአዲስ አበባ ስታድዬም ለዓለም አቀፍ ጨዋታ አይመጥንም

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

‹‹በቀለ ለረጅም ጊዜ የማውቀው ምርጥ ተጨዋች ነው››
ዋና አሰልጣኝ ክርስትያን ጉርኩፍ
የበረሃዎቹ ቀበሮዎች  ከዋልያዎቹ ጋር በአዲስ አበባ 3ለ3 አቻ ከተለያዩ በኋላ ማምሻውን በሸራተን አዲስ ሳገኛቸው፤ ወደአገራቸው ለመመለስ በጥድፊያ ላይ ሆነው ነበር፡፡  ከምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል ጀምሮ በሸራተን ሎቢ በማድፈጥ ስጠባበቃቸው ቆየው፡፡ ዋና አሰልጣኝ ጉርኩፍን ሳገኛቸው ቃል የገቡልኝን ቀጠሮ አስታውሰው ይህን ቃለምምልስ ሰጥተውኛል፡፡
ኢትዮጵያና አልጄርያ በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ  ማጣርያ በአልጀርስ እና በአዲስ አበባ ከተሞች ያደረጓቸውን የደርሶ መልስ ጨዋታዎች በአጠቃላይ እንዴት ነበሩ?
ሁለቱ ጨዋታዎች በማናቸውም መንገድ ፍፁም አይመሳሰሉም፡፡ በአልጀርስ የተጫወትንበት ተፈጥሯዊ ሜዳ ምቹ ሆኖ በመደልደሉ አንድ ለአንድ ቅብብል ለመጫወትና ብልጫ አግኝተን በሰገፊ ልዩነት ለማሸነፍ አልቸገረንም ነበር። በሜዳችን የተሻለ ውጤት ነበረን። እዚህ  አዲስ አበባ ላይ ግን ተፈጥሯዊው ሜዳው ዓለም አቀፍ ደረጃውን ያልጠበቀ እና ምቹ ያልነበረ ነው፡፡ ስለሆነም ጨዋታው አስቸጋሪ ሆኖብናል፡፡ በአጠቃላይ ጨዋታውን በአቻ ውጤት ማጠናቀቃችን ደስተኛ ሆነናል፡፡
አቻ ውጤቱ የአልጄርያን  የማለፍ እድል አላበላሸውም?
 በምድባችን ሁለት  ቀሪ የማጣርያ ጨዋታዎች አሉ። ማለፋችንን ለማረጋገጥ አንድ ጨዋታ ማሸነፍ ቢኖርብን ነው፡፡ በቀጣዩ ጨዋታ ካሸነፍን ወይንም አቻ ከወጣን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ልናልፍባቸው የምንችልባቸው ብዙ እድሎች ናቸው፡፡
 እዚህ አዲስ አበባ ላይ 3ለ3 አቻ በተለያተዩባቸው ጨዋታዎች ምርጥ እና ጠንካራ ብቃት ያሳዩ ተጨዋቾች እነማን ናቸው፡፡ በተለይ ከዋልያዎቹ ማለቴ ነው?
ከአልጄርያ  ተጨዋቾች በጥሩ ቴክኒክ ብቃታቸው የሚጠቀሱ ተጨዋቾች እነ ያሲን ብራሂሚ፤ ሪያድ ማህሬዝ እና ሶፍያን ፋጉሊ በሜዳው አለመመቸት እና አስቸጋሪነት ምርጥ ብቃታቸውን ለማሳየት  አልቻሉም፡፡ ኳስ እንኳን በአግባቡ መቀባበል አልቻሉም ነበር፡፡ ከዋልያዎቹ ግን በአጨዋወቱ የማረከኝ ተጨዋች ሽመልስ በቀለ ነው። ‹‹በቀለን›› ስከታተለው ረጅም ጊዜ ነው፡፡ በጣም ምርጥ ችሎታ ያለው ተጨዋች ነው ፡፡
በአልጄርያ ላይ  በሁለቱ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች 3 ጎል ያገባው ጌታነህ?
ልክ ነህ ጌታነህም ጠንካራ እና አደገኛ ተጨዋች ነበረ፡፡ ለእኔ ግን የጨዋታው ኮከብ ‹‹ በቀለ ›› ነበር፡፡
ስለ አዲስ አበባ ስታድዬም አጠቃላይ ድባብ ምን ማለት ይችላሉ?
 በስታድዬሙ የነበረው ተመልካች እና ድባቡ በጣም ምርጥ ነው፡፡ በዚያ ምንም ችግር የለብኝም፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ደረጃ የሚካሄዱ ትልልቅ ግጥሚያዎችን ደረጃውን በጠበቀ ስታድዬም ማስተናገድ ይኖርባታል፡፡ አዲስ አበባ ስታድዬም ጥሩ እና ለተመልካች የሚማርክ ግጥሚያ ለማድረግ በፍፁም የሚመች አይደለም። በእኔ አስተያየት ፊፋ እንደዚህ አይነት ሜዳዎችን ለዓለም አአቀፍ ደረጃ ያላቸው ጨዋታዎች መፍቀድ የለበትም፡፡ ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን የሚያስተናግዱ ስታድዬሞች በአግባቡ በተደለደሉ ተፈጥሯዊ ሲንቴቲክ ሜዳዎች የተሟሉ እንዲሆኑ በካፍ  ሆነ በፊፋ ግፊት መደረግ አለበት። እግር ኳስ አፍቃሪው የኢትዮጵያ ተመልካች በዋና ከተማ ደረጃውን የጠበቀ ስታድዬም ያስፈልገዋል፡፡  
በመጨረሻም ከኢትዮጵያ ጋር ካደረጓቸው የመልስ ጨዋታዎች በኋላ ከሃላፊነት እንደሚለቁ የአልጄርያ ሚዲያዎች በስፋት እያወሩ ነበር፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አስተያየት ይሰጡናል?
ታውቃለህ፤ የብሄራዊ ቡድን ሃላፊነት በየቀኑ በፍጥነት በሚቀያየሩ አጀንዳዎች የሚተራመስ ነው፡፡ እና በአጠቃላይ ማለት የምችለው እንካን ነጥብ አግኝተን ወጣን  ነው፡፡በብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝነት ዋናው ነገር አለመሸነፍ ነው፡፡ቀጣዩ ጊዜዬ ላይ የምሰጠው አስተያየት ነገም ሌላ ቀን ነው፡፡

Read 2199 times