Monday, 04 April 2016 08:20

‹‹በቀለ ለረጅም ጊዜ የማውቀው ምርጥ ተጨዋች ነው›› ዋና አሰልጣኝ ክርስትያን ጉርኩፍ የበረሃዎቹ ቀበሮዎች ከዋልያዎቹ ጋር በአዲስ አበባ 3ለ3 አቻ ከተለያዩ በኋላ ማምሻውን በሸራተን አዲስ ሳገኛቸው፤ ወደአገራቸው ለመመለስ በጥድፊያ ላይ ሆነው ነበር፡፡ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል ጀምሮ በሸራተን ሎቢ በማድፈጥ ስጠባበቃቸው ቆየው፡፡ ዋና አሰልጣኝ ጉርኩፍን ሳገኛቸው ቃል የገቡልኝን ቀጠሮ አስ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 ከአልጄርያ ጋር ደርሶ መልስ
    በ2017 የምእራብ አፍሪካዋ ጋቦን ወደየምታዘጋጀው 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ የ3ኛና 4ኛ ዙር የደርሶ መልስ ማጣርያ ጨዋታዎች ባለፈው ሰሞን በመላው አህጉሪቱ ተካሂደዋል፡፡ ባለፉት 10 ወራት 52 አገራትን በማሳተፍ የተካሄደው ማጣርያው በሚቀጥሉት 6 ወራት በሚከናወኑ የሁለት ዙር ማጣርያ ጨዋታዎች ይጠናቀቃል፡፡ የሰሜን አፍሪካዋ ሞሮኮ በ4 ጨዋታዎች ሙሉ 12 ነጥብ እና 7 የግብ ክፍያ በምድብ 7 በማስመዝገቧ ማለፏን ያረጋገጠች ብቸኛዋ አገር ነች፡፡ ከሌሎች ምድቦች አልጄርያ፤ ካሜሮን፤ ግብፅ፤ እና ሴኔጋል በ3ኛ እና 4ኛ ዙር የደርሶ መልስ ማጣርያ ጨዋታዎች ባስመዘገቡት ውጤት የምድቦቻቸውን መሪነት ቀጥለዋል፡፡  የማለፍ እድላቸውንም ከሶስት ወራት በኋላ በሚቀጥሉት የ5ኛ ዙር የማጣርያ ጨዋታዎች በማሸነፍ ሊያረጋግጡ ይችላሉ፡፡  ከትልልቅ የአህጉሪቱ ቡድኖች በምድብ 7 የምትገኘው ናይጄርያ መውደቋ ግን አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ በ2013 እኤአ ላይ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ የሆነችው ናይጀሪያ በ4 ዙር የማጣርያ ጨዋታዎች 5 ነጥብ ብቻ በመሰብሰቧ የማለፍ ዕድሏ አክትሟል፡፡
በምድብ 10 አልጄርያ ባለፈው ሰሞን በአልጀርስ እና በአዲስ አበባ ባደረገቻቸው ሁለት የደርሶ መልስ ጨዋታዎች 4 ነጥቦች በመሰብሰብ በ10 ነጥብ እና 12 የግብ ክፍያ  በመሪነቷ ቀጥላለች፡፡ ተጋጣሚዋ የነበረችው ኢትዮጵያ 5 ነጥብ እና በ5 የግብ ክፍያ ሁለተኛ ደረጃ ይዛ ትከተላለች። ከዚሁም ምድብ በደርሶ መልስ ጨዋታዎቻቸው በየሜዳቸው በማሸነፍ የመጀመርያቸውን ሙሉ ነጥብ ማግኘት የቻሉት ሲሸልስ በ4 ነጥብ እና በ3 የግብ እዳ  እንዲሁም ሌሶቶ በ3 ነጥብና በ4 የግብ እዳ 3ኛ እና 4ኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡ በማጣርያው የየምድቡ ሁለት  ቀሪ ጨዋታዎች በሚቀጥሉት 6 ወራት የሚደረጉ ናቸው፡፡ በምድብ 10 የምትገኘው ኢትዮጵያ በ5ኛ ዙር ማጣሪያ ከ3 ወራት በኋላ ከሜዳዋ ውጭ ከሌሶቶ ጋር እንዲሁም ከ6 ወራት በኋላ በሜዳዋ ሲሸልስን ታስተናግዳለች፡፡ የዋልያዎቹ ዋና አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ከአልጄርያ ጋር በመልስ ጨዋታ እዚህ አዲስ አበባ ላይ 3ለ3 ከተለያዩ በኋላ  በማለፍ እድሉ አለንበት ብለው ተናግረዋል፡፡ ተስፋ አለመቁረጣቸው ተገቢ ቢሆንም አስተያየታቸው የተሟላ መረጃን የተንተራሰ አልነበረም፡፡ በምርጥ ሁለተኛነት ለማለፍ መፎካከሩን ሁለት አገራት ናቸው ማለታቸው ስህተት ነው፡፡ ከስፖርት አድማስ አጫጭር ቃለምልልሶች ያደረጉት የዋልያዎቹ ወሳኝ ተጨዋቾች አጥቂው ጌታነህ ከበደ እና ዋና አምበሉ ሽመልስ በቀለ በበኩላቸው ጠንካራ የወዳጅነት ጨዋታ እና በቂ ትኩረት ያለው ዝግጅቶችን በማድረግ የማለፍ እድላችንን ልንወስን እንችላለን ብለዋል፡፡ በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያው ከተደለደሉት 14 ምድቦች በምርጥ ሁለተኛነት ለማለፍ በሚቻልባቸው 2 እድሎች ኢትዮጵያ በ11ኛ ደረጃ መጨረሻ ላይ ነው የምትገኘው፡፡ በምርጥ ሁለተኛነት የማለፍ እድል የደረጃ ሰንጠረዥ ከምድብ 3 ቤኒን በ8 ነጥብ መሪነቱን ስትይዝ፤ ከምድብ 1 ቱኒዚያ፤ ከምድብ 13 ሞውሪታኒያ፤ ከምድብ 4 ኡጋንዳ እንዲሁም ከምድብ 2 መካከለኛው አፍሪካ በ7 ነጥብ እስክ 5 ባለው ደረጃ ተቀምጠዋል፡፡  ከምድብ 6 ኬፕ ቨርዴ፤ ከምድብ 7 ኮንጎ እንዲሁም ከምድብ 5 ብሩንዲ በ6 ነጥብ ሲከተሉ፤ ከምድብ 12 ስዋዚላንድ እና ከምድብ 10 ኢትዮጵያ በ5 ነጥብ ተቀምጠዋል፡፡
ዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በአዲስ አበባ ስታድዬም ቡድናቸው በመልስ ጨዋታ 3 እኩል አቻ ከተለያየ በኋላ በሰጡት መግለጫ ከሃላፊነታቸው ስለመልቀቃቸው መወራቱን የማውቀው ነገር በለም የሚል አስተባብለዋል፡፡ በአልጀርስ ቡድናቸው 7ለ1 ከተሸነፈ በኋላ ዋና አሰልጣኙ የስራ መልቀቂያ ማስገባታቸው በሰፊው የተናፈሰ ቢሆንም፤ የሌለ ነገር አላወራም በማለትም አልፈውታል፡፡  ዋና አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የ7 ለ 1 ሽንፈቱ ጋ ከኳስ ውጭ ባጋጠሙ ችግሮች እንደተከሰተም ጠቅሰዋል፡፡ ለአስከፊው ውጤት ሙሉ በሙሉ ሃላፊነት እንደሚወስዱ በመናገር የኢትዮጵያን ህዝብ በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡  የቡድኑን የማለፍ እድል አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት በፉክክሩ አለንበት ብለው በሰጡት አስተያየት በጠቀሱት መረጃ ግን ተሳስተዋል፡፡ ከእኛ በላይ በነጥብ 6 ነጥብ ይዘው ያሉት ቡድኖች ሁለት ናቸው ብለው ነበር፡፡ እውነታው ግን ከ10 በላይ ቡድኖች ለምርጥ ሁለተኛነት የሚፎካከሩ መሆናቸው ነው፡፡ አሰልጣኙ ወቅታዊ መረጃ በማግኘት በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት ነበረባቸው፡፡
በምድብ 10 ኢትዮጵያና አልጄርያ በአልጀርስ እና በአዲስ አበባ የተገናኙባቸው የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ዙርያ የተፈጠሩ በርካታ ሁኔታዎች የሰሞኑ መነጋገርያዎች ነበሩ፡፡ ስፖርት አድማስ ይህን ምክንያት በማድረግም የሚከተሉትን ዘገባዎች አጠናቅሯል፡፡
ከአዲስ አበባው የመልስ ጨዋታ በፊትና በኋላ
ከመልሱ ጨዋታ በፊት ማክሰኞ ጠዋት በሸራተን አዲስ ከአልጄርያ ተጨዋቾች ጋር ቃለምልልስ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ነበር የደረግኩት፡፡ የአልጄርያ ብሄራዊ ቡድን ማንኛውም ልዑክ ከጨዋታ በፊት ምንም አይነት ከሚዲያ ጋር ግንኙነት መፍጠር  የለበትም በሚለው ህገ ደንብ የሚመራ በመሆኑ ቃለምልልሶቹ ብዙ የተሳኩ አልነበሩም።  ከጨዋታው በፊት በአመዛኙ ውይይት ማድረግ የቻልኩት ከቀድሞ ተጨዋቾች፤ ከተለያዩ የቡድኑ ልዑካንም አባላት ጋር ነበር፡፡ ከተጨዋቾች  ብዙዎቹን ብተዋወቅም በጥቂቱ  ያነጋገሩኝ ዋና አምባሉ ካርል ሜንጃኒ እና የ26 ዓመቱ ሪያድ ቡዴማውብ ናቸው፡፡
በቅድሚያ የተዋወኩት የቀድሞ ተጨዋች ነበር፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ጄነራል ማናጀር ወይም ዋና ስራ አስኪያጅ ሆኖ የሚያገለግለው እና ከደቡብ አፍሪካ ዓለም ዋንጫ አምበል የነበረው ያዚድ መንሱሪ ነው፡፡ ያዚድ እንደገለፀልኝ ማንኛውም የአልጄርያ ቡድን ተጨዋችና የአሰልጣኞች ስታፍ አባል ከጨዋታ በፊት ማናቸውም አይነት ቃለምልልስ ማድረግ አይፈቀድለትም፡፡ ይህ ሁኔታም በህግ ደንብ የፀደቀ ነው፡፡ በተጨዋችነት ዘመኑ በአማካይ መስመር ተጨዋችነት ያገለገለው ያዚድ መንሱሪ በፈረንሳይ ክለቦች በመጫወት ከፍተኛ ልምድ የነበረው ነው፡፡ የበረሃዎቹ ዋና አምበል የነበረውንና  በስፔኑ ክለብ ላሊጋ በሚወዳደረው ሌቫንቴ ክለብ የሚጫወተውን ካርል ሜንጃኒ  ከመልሱ ጨዋታ በፊት በሸራተን አዲስ ያስተዋወቀኝ ያዚድ ነበር። በመሃል ተከላካይ መስመር የሚጫወተው የበረሃዎቹ ቀበሮዎችዋና አምበል ካርል ሜጃኒ በፈረንሳይ  የታዳጊ እና ወጣት ቡድኖች ተጫውቶ ማለፉን ለስፖርት አድማስ ሲገለፅ፤ በአውሮፓ እግር ኳስ በተለይ በፈረንሳይ ሞናኮ፤ በቱርኩ ትራንዝስፖር፤ በእንግሊዙ ሊቨርፑል እና በበርካታ የፈረንሳይ ክለቦች በመጫወት ያሳለፈውን ልምድም በዝርዝር በመጠቃቀስ ነበር፡፡ በዚሁ አጭር ትውውቅም ተሰነባብተናል፡፡ ከመልሱ ጨዋታ በፊት ሌላው አጭር አስተያየት የሰጠኝ ተጨዋች በአጥቂ አማካይ መስመር ተሰልፎ የነበረው ሪያድ ቡዴማውብ ነበር እንደዋና አምበሉ ሁሉ በፈረንሳይ የታዳጊ እና ወጣት ቡድኖች ያሳለፈውን ልምድ በመግለፅ ከስፖርት አድማስ ትውውቅ ያደረገው ሪያድ ለፈረንሳዩ ክለብ ሞንትፕሌየር በ3.5 ሚሊዮን ዩሮ የዝውውር ሂሳብ እቐስከ 2019 ለመጫወት መስማማቱን አውግቷል፡፡ ከሁለቱ ተጨዋቾች በኋላ ከበረሃዎቹ ቀበሮዎች ፈረንሳዊ ዋና አሰልጣኝ ክርስትያን ጉርኩፍ ጋር ተዋውቀናል። ለቃለምልልስ ፈቃደኝነታቸውን ስጠይቅ ከጨዋታ በኋላ ማታ እንገናኝ ነበር ያሉኝ፡፡
ከአልጀሪያ የምንማረው
ኢትዮጵያና አልጀሪያ በአዲስ አበባ ስታድዬም ከመጫወታቸው በፊት ሰኞ አመሻሹ ላይ በርካታ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች የበረሃዎቹን ቀበሮዎች ልምምድ የመመልከት እድል አግኝተን ነበር፡፡ የበረሃዎቹ ቀበሮዎች የአዲስ አበባ ስታድዬም የልምምድ መርሃግብር ከፍተኛ ቁጭት የፈጠረብን አጋጣሚ ነበር፡፡ በተለይ ከዋና አሰልጣኝ ክርስቲያን ጉርኩፍ ጋር ከ14 በላይ የተለያየ ድርሻ ያላቸው ባለሙያዎች ልምምዱን ለማሰራት ሜዳ ገብተው ስንመለከት በጣም ተገርመናል፡፡ ምናለበት በኢትዮጵያ ዋና ብሄራዊ ቡድን የአሰልጣኝ ድጋፍ ሰጪ ሃይል ቢያንስ ሩቡ እንኳን ቢኖር  ብለን ተስፋ ሁሉ አድርገናል፡፡ በአልጄርያ ብሄራዊ ቡድን የአዲስ አበባ ስታድዬም ልምምድ ከዋና አሰልጣኙ ክርስትያን ጉርኩፍ ጋር ሁለት ረዳት አሰልጣኞች፤ ሁለት የግብ ጠባቂ አሰልጣኞች፤ ሁለት የአካል ብቃት አሰልጣኞች፤ ሁለት ዶክተሮች፤ 3 የታዳጊ እና የወጣት ቡድን አሰልጣኞች እንዲሁም የሴቶች ቡድን ማናጀር መገኘታቸውን መጥቀስይቻላል፡፡ እነዚህ የዋና አሰልጣኙ ድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎች 120 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመን ካለው የአልጄሪያ የቡድን ስብስብ ጋር ለልምምድ ሌላ ብሔራዊ ቡድን መስለው ተገኝተዋል፡፡ ያንኑ እለት ጠዋት ላይ ዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በአዲስ አበባ ስታድዬም ዋልያዎቹን ልምምድ ሲያሰሩ አብረዋቸውየነበሩት 1 ረዳት አሰልጣኝ፤ 1 የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ እና አንድ ዶክተር ነበሩ፡፡ በሁለቱ ቡድኖች በኩል ያልሆነ ልዩነት በመገንዘብ አያዳግትም፡፡
ዋልያዎች ከበረሃዎቹ ቀበሮዎች ጋር በአልጀርስ ባደረጉት የመጀመርያ ጨዋታቸው የገጠማቸው አስከፊው የ7ለ1 ሽንፈትም ከመልሱ ጨዋታ በፊት አነጋጋሪው አጀንዳ የነበረ ሲሆን ዋልያዎቹ በረጅም ጉዞ መጉላላታቸውና ሌሎች ከኳስ ውጭ የሆኑ ችግሮች መጎሳቆላቸው የሽንፈቱ ሰሰቦች መሆናቸውን በማያያዝ ከአልጄርያ ልዑካን እንቅስቃሴ የምንማርበትንም ሁኔታ ተመልክተናል፡፡
ከአልጄርያ ልዑካን አባላት እና የሚዲያ ባለሙያዎች በጉዳዩ ላይ ስናነጋግራቸው በሙሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን  አያያዝ አግባብ እንዳልሆነነና መሻሻል እንዳለበት ምክር ሰጥተዋል፡፡  ለመልሱ ጨዋታ የአልጄርያ ልዑካን አዲስ አበባ የገባው እስከ 100 የሚደርሱ አባላት በማቀፍ ነበር፡፡ የምግብ አብሳይ ባለሙያ፣ ኬክ ጋጋሪ፣ ከ10 በላይ ጋዜጠኞች ወዘተ ተረፈ።
ከሁሉ ያስገረመኝ ግን የአልጀሪያ አየር መንገድ ቻርተር አብራሪ ፓይለት ነው፡፡ ይህ ሰው በዓለም ዋንጫ ሁሉ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር አባል ሆኖ የተጓዘ  ነበር። ልምዱን ሲያጫውተኝም ለኢትዮጵያ ቡድን በዚህ መንገድ መሠራት ይኖርበታል የሚለው ሃሳብ ነው ነው የተፈጠረብኝ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለብሔራዊ ቡድን ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች መደበኛ የቻርተር በረራ ማዘጋጀት ይኖርበታል። ብሄራዊ ቡድኑ ውጤታማ ለማድረግ በአግባቡ መደገፍ እንደሚኖርበት ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች በሙሉ ይስማሙበታል፡፡ ለምሳሌ ብሄራዊ ቡድኑ ልምምድ የሚሰራበት በቂ ጊዜ እና ፕሮግራም ያስፈልገዋል፡፡ ከደርሶ መልሱ ጨዋታ በፊት ዋልያዎቹ 3 እና 4 ልምምድ ሲሰሩ፤ አልጄርያዎች ግን ቢያንስ 7 የልምምድ ፕሮግራሞች ነበሯቸው፡፡ በሌላ በኩል በወዳጅነት ጨዋታዎች ያሉ ሁኔታዎች ለውጥ ያስፈልጋቸዋል፡፡  ቢያንስ ጠንካራ የወዳጅነት ጨዋታዎች እንዲደረጉ ጥረት መደረግ ይኖርበታል፡፡
የበረሃዎቹ ቀበሮዎች ከ3 እኩል አቻ ውጤት በኋላ
ከጨዋታው በኋላ ከዋና አሰልጣኝ ክርስትያን ጉርኩፍ ጋር ስፖርት አድማስ ቃለምልልስ ለማድረግ ቢቻልም ከተጨዋቾች መካከል አንዳንዶቹን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ በተለያዩ ምክንያቶች የተሳካ አልነበረም፡፡ አዲስ አበባን ለቅቀው ለመውጣት እጅግ በመቻኮላቸው ተባባሪ  አልነበሩም፡፡ አንዳንዶቹ ከአረብኛ እና ፈረንሳይኛ በቀር አለመናገራቸው ቃለምልልስ ለማድረግ እንቅፋት የፈጠረ ነበር፡፡ ከጨዋታ በፊት ለትውውቅ ብዙም ያለመነቱት እና ትንሽ ያወራኋቸው እነ ያሲኒ ብራሂሚ እና ሶፍያን ፋጉሊ በውጤቱ በመበሳጨታቸው ምላሽ እንኳን አልነበራቸውም። ለማቀርብላቸው ጥያቄ ዝምታ ነበር መልሳቸው፡፡ ሻንጣቸውን እየጎተቱ ሸራተንን ለቅቀው ሲወጡ እስከ የሚሳፈሩበት አውቶብስ በመከታተል አስቸገርኳቸው ዝም ብለውኝ ገቡ፡፡  ኢስላም ሲሊማኒ ግን ከጨዋታ በኋላ አመሻሹ ላይ በሸራተን አዲስ ሳገኘው ያልጠበቅኩትን ቃለምልልስ ነበር የሰጠኝ፡፡ የ27 ዓመቱ ሲሊማኒ በፖርቱጋሉ ክለብ እስከ 2020 እኤአ ለመጫወት በ15 ሚሊዮን የዝውውር ገበያ የዋጋ ተመን የፈረመ እና ባለፉት ሁለት ዓመታት ከክለቡ ጋር ሁለት ዋንጫዎችን የተቀዳጀ ነው።  ለአልጄርያብሄራዊ ቡድን በ43 ጨዋታዎች በመሰለፍ 23 ግቦችን ያስመዘገበው ሲሊማኒ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በእንግሊዙ ክለብ ቶትንሃም እና በስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድ የሚፈለግም፡፡ በመጀመሪያውና መልሱ ጨዋታ በዋልያዎቹ ላይ 3 ግቦችን ቢያስቆጥርም ደስተኛ አልነበረም፡፡  ከጨዋታ በኋላ ለቃለምልልስ የሰጠውን ቀጠሮ አስታወሰና ቆም ብሎ በእንግሊዘኛ ‹‹አረብኛ ትችላለህ›› አለኝ
‹‹ ኖ››  አልኩት፤
‹‹ፈረንሳይኛ ትችላለህ››
አሁንም ኖ ነበር ምላሼ፤ ‹‹ፖርቹጊዝስ›› አለኝ  አሁንም በእንግሊዘኛ ነው፡፡ ‹‹ኖ›› አልኩት፤ ‹‹ሶ ኖ ኢንተርቪው›› ብሎኝ አመለጠ፡፡ የሚገርመው ከእኔ ጋር ያወራው በእንግሊዘኛ ሆኖ ቃለምልልሱን በእንግሊዘኛ መስጠት አለመፈለጉ ነው፡፡ በአዲስ አበባስታድዬም ምንም ተዓምር ማሳየት ያዳገተው የሌስተር ሲቲው ማህሬዝም እንዳኮረፈ ሹልክ ብሎ በሸራተን የምስጥር በር በመውጣት አውቶብሱን ተሳፍሯል፡፡
በመጨረሻ ግን ለግሪኩ ክለብ ፓነተኒያኮስ የሚጫወተው የ23  ዓመቱ አማካይ ማሂዲ አቤይድ በእንግሊዘኛ ቃለምልልስ ላድርግልህ ያልኩትን ጥያቄ በማክበር የሚከተለውን ቃለምልልልስ ሰጥቶኛል፡፡
ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር በደርሶ መልስ የተገናኘችሁባቸውን ጨዋታዎች እንዴት አገኘሃቸው?
ሁለቱም ትልልቅ ጨዋታዎች ነበሩ፡፡ በአዲስ አበባ ያደረግነው የመልስ ጨዋታ የአየር ሁኔታው  ከብዶናል በተለይ ደግሞ ሜዳው አስቸጋሪ ነበር፡፡
የሜዳው አስቸጋሪነት ምኑ ላይ ነው?
በተፈጥሮዊ ሳር ምቹ ሆኖ የተደለደለ አይደለም፡፡ ይህ ምቹ እናሲንቴቲክ ሜዳ ለለመድን ተጨዋች በጣም መጥፎ ጫና ነበር፡፡ ግን ሁኔታዎችን ተቋቁመን መጫወት ነበረብን።  ስለዚህም ከሁኔታው አስቸጋሪነት አንፃር ጥሩ ውጤት ይዘን ወጥተናል ለማለት እደፍራለሁ፡፡ አቻ ወጥተን 1 ነጥብ ማግኘታችን እንደ ጥሩ ስኬት ነው የምቆጥረው፡፡
ከዋልያዎቹ ተጨዋቾች እነማን  ጥሩ አቋም አሳይተዋል?
ከኢትዮጵያ እንግዲህ 18 ቁጥር (ሽመልስ በቀለ) እና 9 ቁጥሩ (ጌታነህ ከበደ) ሁለቱም  በጣም ምርጥ ነበሩ። በአጠቃላይ በደጋፊው ፊትና በሜዳው ቡድኑ ጥሩ ተንቀሳቅሷል፡፡ በአጠቃላይ ወደ ኢትዮጵያ የመጣነው አቻ ውጤት ይዞ ለመመለስ ነበር፡፡ ተሳክቶልናል፡፡

Read 1019 times