Saturday, 25 February 2012 13:21

የተቃዋሚ ፓርቲዎች ልደት ናፈቀኝ!

Written by  ኤሊያሰ
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮጵያ በሙስና “Top 10” ውስጥ አልተካተተችም!

“አዲስ ዘመን” ለባለሃብት ተሸጠ እንዴ …?

የዛሬ ወጋችንን የምጀምረው በኮፒራይት የጠቅላላ ዕውቀት ጥያቄ ነው፡፡ የዘፈን ወይም የፊልም ኮፒራይት ማለቴ ግን እንዳይመስላችሁ፡፡ የጥቅስ ወይም የአባባል ኮፒራይት ነው፡፡ በቀጥታ ወደ ጥያቄዬ፡፡ “መረጃ ሃይል ነው” የሚለው አባባል የእኛ ነው ወይስ ከፈረንጆች ቃል በቃል የተቀዳ (ከነ ኮማው!) እንደው ለጠቅላላ ዕውቀት ያህል አነሳሁት እንጂ የተለየ አጀንዳ እንኳን ኖሮኝ አይደለም፡፡ ሰሞኑን በሴቶች ላይ የሚደርሱ የፆታ ጥቃቶችን በተመለከተ በቀረበ የቲቪ ፕሮግራም ላይ አንዲት የካፌ ሃላፊ፣  ለመስተንግዶ ወደ ካፌው የሚመጡ “ቀበጥ ወንዶችን” በተመለከተ ስትናገር፤ “አንዳንድ ሌላ አጀንዳ ይዘው የሚመጡ ወንዶች አሉ” ብላለች (የካድሬ ቋንቋ ጉድ አፈላ አይደል!) ሃላፊዋ “ሌላ አጀንዳ” በማለት ያወሳሰበችው እኮ ወንዶቹ በቀላል ቋንቋ “ጠበሳ” የሚሉትን ነው፡፡ (እጩ ካድሬ ትሆን እንዴ?)

በሉ እንግዲህ ወደ ዛሬ ዋና አጀንዳዬ ልውሰዳችሁ፡፡ ባለፈው ረቡዕ ምሽት “ኢቴቪ ነፍሴ” የኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ የሰላምና የልማት ኢንስቲትዩት ከፍሬድሪክ ኤበርት ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን በሙስና አደጋ ላይ ያተኮረ ውይይት ሲዘግብ፤ ሙስና በአገር ሰላም፣ ደህንነትና ዲሞክራሲ እንዲሁም ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰውን የትየለሌ ጉዳትና ጥፋት ከጠቆመ በኋላ በዓለም ላይ በሙስና ከ1-10ኛ ደረጃ የተሰጣቸውን (በኮራፕሽን Top 10 እንደማለት) አገራት ዘረዘረና ኢትዮጵያ በስንተኛ ደረጃ ላይ እንዳለች ሳይነግረን  ወደ ሌላ ዜና ተሻግሮ ቁጭ አለላችሁ፡፡ እኔማ ምን አልኩ መሰላችሁ … ጋዜጠኛው ለምን “Top 10” ውስጥ አልገባንም ብሎ ተናዶ ይሆን እንዴ? ወንድምዬ “Top 10” በፊልምና በሙዚቃ እንጂ በሙስና እኮ ጥቅም የለው፤ ጉዳት ብቻ ነው፡፡ ለማንኛውም ግን ይሄን የመረጃ ንፉግነት ኢቴቪ እንዲያሻሽል እግረ መንገዴን ጠቆም አድርጌው ልለፍ፡፡ (ዘመኑ እኮ የኢንተርኔት ነው!)

የኢትዮጵያ ዓለምቀፍ የሰላምና የልማት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተርና አንጋፋው የህወሃት መስራች አቶ ስብሃት ነጋ፤ በአገራችን ስላለው የሙስና ሁኔታ ለኢቴቪ ሲናገሩ፤ ናይጄሪያና ኬንያን በመሳሰሉት አገራት ሙስና ከቁጥጥር ውጭ መሆኑን ጠቅሰው፤  በኢትዮጵያ ግን ሙስና ከቁጥጥር የወጣ አይመስለኝም ብለዋል፡፡ (ልብ አድርጉ!  አይመስለኝም ነው ያሉት በትህትና፡፡) ሙስና ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል የሚባለው መቼ እንደሆነ ሲያብራሩም፤ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሙስና ውስጥ ሲሳተፉ እንደሆነ ተናግረዋል - አቦይ ስብሃት፡፡ (አሁን ነው ጉዱ!) በአገራችን በከፍተኛ ባለስልጣናት ዘንድ Corruption አለ ተብሎ ይታማል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ሃሜቱ ወዲያውኑ ካልተጣራ ተሸፋፍኖ ሊቀር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ሙስና አደገኛ የመሆኑን ያህል ግን ጥንቃቄ አናደርግም ሲሉም ለሁላችንም በጅምላ ሂስ አድርገዋል (የሙስና ንስሃ ሊባልም ይችላል)

እኔ የምለው ግን በአዲሲቷ ኢትዮጵያችን “ከፍተኛ ባለስልጣናት” የሚባሉት እነማን ናቸው? መቼም አራት ኪሎ ቤተመንግስት የገቡት ብቻ እንዳልሆኑ እርግጠኛ ነኝ፡፡ እኔማ ከመሬት ጋር በተያያዘ በሙስና ተጠርጥረው ወህኒ የወረዱ አንዳንድ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከንቲባዎችና ምክትል ሃላፊዎች ሁላ “ከፍተኛ ባለስልጣን” እየመሰሉኝ … “ሙስና ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል” በማለት ሃሜት ስነዛ ከርሜላችኋለሁ (አሁንማ ሂሴን ውጬአለሁ!)

ቆይቼ ሳስበው ግን የጠ/ሚኒስትሩ የፓርላማ ንግግር እንዳሳሳተኝ ገባኝና ተረጋጋሁ፡፡ (እሳቸው አሳሳቱኝ አልወጣኝም ንግግራቸው ነው!) እና … አቦይ ስብሃት እንዳሉት ሙስና ከቁጥጥር ውጭ ካልሆነ ጠ/ሚኒስትሩ “ከሽብርተኛው ይልቅ ሙሰኛው ነው ጠላታችን” ብለው ለምን ተናገሩ? (ያውም በምሬት!) በነገራችሁ ላይ ይሄን ሙግት ያነሳሁት ሌላ ድብቅ አጀንዳ ኖሮኝ አይደለም - “ብዥታዬን” ለማጥራት ፈልጌ እንጂ፡፡

በዚህች አጋጣሚ ግን በአገራችን “ከፍተኛ ባለስልጣናት” የሚባሉት እነማን እንደሆኑ ዝርዝራቸው ይፋ እንዲደረግልን የሚመለከተውን አካል እጠይቃለሁ (የሚመለከተው ካለ) የሆኖ ሆኖ ግን ሙስና አሁን ከቁጥጥር ወጥቷል ባይባልም ማንቀላፋት የለብንም ብለዋል - አቦይ ስብሃት፡፡ ለምን ቢሉ…በአሁኑ አካሄድ ከቁጥጥር ሊወጣ ይችላልና (እስካሁን ካልወጣ ነዋ!)

እስቲ ደሞ ከሙስና ወደ ፌሽታና ፈንጠዝያ እንለፍ፡፡ ሰሞኑን እንዴት ነው የልደት “ፓሪ”ዎች አልበዙባችሁም? አንጋፋዋ ከተማና አንጋፋው ግንባር (ህወሃትን ማለቴ ነው) ልደታቸውን እያከበሩ መሆኑን ሳትሰሙ አትቀሩም ብዬ እገምታለሁ (ሃኪም ኢቴቪን ካልከለከላችሁ በቀር)

አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ የቆረቆሩዋት አዲስ አበባ የ125ኛ ዓመት የልደት በዓሏን ስታከብር፣ ኢህአዴግን ከፈጠሩት ግንባሮች ፊት አውራሪው ህወሃት ደግሞ የ37ኛ ዓመት ልደቱን በማክበር ላይ ነው፡፡ እኔ ደግሞ ልደት ሲባል እንደ ሰው ልደት አንድ ቀን ብቻ ተከብሮ የሚያበቃ መስሎኝ ተሸውጄላችሁ ነበር፡፡ ለካ የከተማና የፖለቲካ ድርጅት ልደት አንድ ዓመት ሙሉ ነው የሚከበረው፡፡ እናላችሁ…“የአፍሪካ መዲና” እያሉ የሚያሞካሹዋት አዲስ አበባችን ገና እስከሚቀጥለው ዓመት ህዳር ወር ድረስ ልደቷን እንደምታከብር ሰምቼ ሩሄን ስቼ ልወድቅ ምንም አልቀረኝ ነበር፡፡ ለምን መሰላችሁ? እንዴ…በዚህ የኑሮ ውድነት አንድ ዓመት ሙሉ “ፓሪ ለመጨፈር” ገንዘቡ ከየት ይመጣል? በዚህ የተነሳም መስተዳድሩ ለመዲናዋ የልደት አከባበር ብሎ ከባንክ ብዙ መቶ ሺዎች ብር ቢበደርስ? (እኛን በኮላተላራል ኢሶዞ) ደግነቱ ዘግይቶ የደረሰኝ መረጃ ትንሽ አረጋጋኝ፡፡ የአዲስ አበባ ልደት ዓመት ሙሉ የሚከበረው በፌሽታና ፈንጠዝያ ሳይሆን በልማት ሥራዎች መሆኑን መስተዳድሩ አስታውቋል (እፎይ!) መስተዳድሩ ለሚያወጣው ወጪ ምን አሳሰበህ የሚሉኝ አይጠፉም፡፡ ችግሩ ግን ምን መሰላችሁ? መዲናዋ ከየባንኩ ገንዘብ ተበድራ በኋላ ዕዳ አናቷ ላይ ሲያናጥጥባት ወደኛ እጅዋን መዘርጋቷ አይቀርም፡፡ እኛስ ዝም እንላታለን? በፍፁም! የቀረው ይቀራል እንጂ በሸገር ቀልድ የለም፡፡ ግን ደግሞ የኑሮ ውድነቱ አንጀታችንን ድርብ ያደርገዋል፡፡ ለዚህ ነበር የልደቷ ወጪ ያሳሰበኝ፡፡ ደግነቱ ግን ልደቱ የሚከበረው በልማታዊ መንገድ ነው ተባለና ተገላገልኩ፡፡

ባለፈው ሳምንት የመዲናዋ የልደት ፌሽታ ላይ ተጋብዞ የነበረው ወዳጄ “የራሳችን ገንዘብ ነው ብለን በደንብ ተጋበዝን” አለኝ፡፡ ደግ አደረጋችሁ አልኩት (አሹ አበጀሁ ነው ያለችው - ድምፃዊቷ!)

እኔ የምላችሁ ግን … የፓርቲ ልደት ለማክበር የግድ ጫካ ገብቶ መታገል ያስፈልጋል እንዴ? (ቢሆን ይመረጣል!) ገርሞኝ እኮ ነው …በአገራችን በምርጫ ቦርድ ተመዝግበው በፖለቲካ ፓርቲነት ሰርፊኬታቸውን የወሰዱ በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዳሉ መረጃዎች ቢጠቁሙም እስከ ዛሬ እንደ ህወሃት የልደት በዓላቸውን ሞቅ ደመቅ አድርገው ያከበሩ አልገጠሙኝም? ወይስ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ልደት የላቸውም? (ልደት የማክበር ባህል ማለቴ ነው!) አንዳንድ ውስጥ አዋቂ ምንጮች እንደሚሉት ግን ተቃዋሚዎች ሻማ ለኩሰው ልደታቸውን የማያከብሩት በዋናነት በአቅም ማነስ የተነሳ ነው፡፡ (በፋይናንስ እጥረት!)

ሌላው የፓርቲያቸውን ልደት እንዳያከብሩ የሚያግዳቸው ደግሞ የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ ነው ይላሉ የፖለቲካ ተንታኞች፡፡ (ጠ/ሚኒስትሩ ግን የጠበበ ምህዳር የለም ብለዋል እኮ)  ይሄውላችሁ…የፖለቲካ ምህዳር መጥበብ የሚባለውን በተመለከተ አስቤ አስቤ መፍትሔ ላገኝ አልቻልኩም (ጠ/ሚኒስትሩ አልጠበበም ያሉት እኮ ቢጨንቃቸው ነው) የፋይናንስ እጥረታቸውን በተመለከተ ግን ጊዜያዊ የመፍትሔ ሃሳብ አለኝ፡፡ ምን መሰላችሁ … አውራውን ፓርቲ ስፖንሰርሺፕ መጠየቅ! (እነሱ ክብራችን አይፈቅድልንም ካሉ ግዴለም እኔ እጠይቅላቸዋለሁ!) አንዳንድ “አክራሪ” ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን ዕድሜ ልካችንን የፓርቲያችንን ልደት ሳናከብር እንኖራታለን እንጂ የኢህአዴግን ደጅ አንጠናም … ብለው ሊያመሩ ይችላሉ (የራሳቸው ጉዳይ ነው!)  እነዚህ ፓርቲዎች ተጨነቁ ብሏቸው ነው እንጂ…ዛሬ ልደታቸውን ኢህአዴግ ስፖንሰር ቢያደርጋቸው ነገ እነሱም ተራቸው ደርሶ ሥልጣን ሲይዙ (ወይስ ተራ አይደርሳቸውም?) ውለታቸውን ስለሚመልሱ ጣጣ የለውም፡፡

የስፖንሰሩን መፍትሔ የጠቆምኩት አንድ “ፀረ - ኢህአዴግ” ጓደኛዬ “ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ” የሚለውን ተረት በማስቀደም “ስፖንሰሩ ቀርቶባቸው ሽብርተኛ እያለ ስማቸውን ማጉደፉን በተወ” ሲል ኢህአዴግን ወረፈውና አስደነገጠኝ፡፡ (“ሽብርተኞቹ ተሳስተናል ካሉ ነፃ ናቸው! አልተባለም እንዴ?)

እስቲ ሽልማት አልባ የልደት ጥያቄ ልጠይቃችሁ፡፡ የዘንድሮውን የህወሃትንና የአዲስ አበባን የልደት በዓል ልዩ የሚያደርገው ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? አንድ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ በዓሉን ልዩ የሚያደርገው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ተግባራዊ እየሆነ ባለበት ወቅት መከበሩ ነው ሲሉ ሰምቻለሁ (ትልቅ ኤክስ!)

… የዘንድሮውን የ125ኛ ዓመት የመዲናዋን የልደት በዓልም ሆነ የህወሃትን 37ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ልዩ የሚያደርገው … ከአዲሱ “የዜጐች ቻርተር” መውጣት ጋር መገጣጠሙ ነው (ትልቅ ራይት!) በነገራችሁ ላይ እንደተለመደው በኢህአዴግ የአፈፃፀም ችግር ካልተሰናከለ በቀር አዲሱ “የዜጐች ቻርተር” እንደዜጐች ልደት የሚቆጠር ነው የሚሉ የፖለቲካ ተንታኞች አልጠፉም (እንዴት ይጠፋሉ?) አያችሁ ኢህአዴግ 17 ዓመት ታግሎ ሥልጣን ላይ እንደወጣው ሁሉ እኛም 20 ዓመት ታግለን ነው (በዝምታ!) “የዜጐች ቻርተር” የመጣልን፡፡ በሌላ አነጋገር “ትዕግስት የወለደው ድል!   ሊባል ይችላል፡፡ (ብሶት የወለደው አልወጣኝም!) እናም … ከአሁን በኋላ እያንዳንዱ የመንግስት መ/ቤት ተገቢውን አገልግሎት ለግብር ከፋዩ (ለእኛ ማለት ነው) በቅልጥፍና የማይሰጥ ከሆነ ቅሬታችንን ለፓርላማ፣ ለእንባ ጠባቂና ለሚዲያዎች በማቅረብ መ/ቤቱን ማጋለጥ እንችላለን - ዕድሜ ለ”ዜጐች ቻርተር”!! (ስሙ ራሱ አይመችም?)

እኔ የምላችሁ… “አውራው” ጋዜጣችን “አዲስ ዘመን” አስገራሚ አዎንታዊ መሻሻሎችን እያሳየ መሆኑን ታዝባችሁልኛል? (ያዝልቅለት እንጂ!) እንደ ድሮው … መንግስት የነካውን ሁሉ እያንቆለጳጰሰ ማወደሱን ትቶ ትችት የሚያስፈልገውን የትችት ናዳ እያወረደበት ነው አሉ፡፡

እናላችሁ… የመንግስት ተቋማት ገና ካሁኑ ፍርሃት ፍርሃት ብሏቸዋል እየተባለ ነው፡፡

ለምን መሰላችሁ … አዲስ ዘመን “ጋዜጠኝነት በአዲስ መልክ ጀምረናል” (“ምግብ በአዲስ መልክ ጀምረናል” እንደሚሉት) የሚል ደብዳቤ ለየተቋማቱ አሰራጭቷል አሉ፡፡

አንድ “ማር አይጥምሽ” የምንላት ወዳጃችን ደስ ይላታል ብዬ የአዲስ ዘመንን በጐ ለውጥ ብነግራት የማይሆን ነገር ተናግራ አስከፋችኝ፡፡ ምን እንዳለችኝ ታውቃላችሁ?

“ለባለሃብት ተሸጠ እንዴ?” (ጋዜጣውን እኮ ነው!)

ቆይ “አዲስ ዘመን” ለምንድነው የሚሸጠው? (ቢራ ፋብሪካ መሰላት እንዴ?) በእርግጥ እንደ ቴሌ “የምትታለብ ላም” ወይም ገንዘብ ማተምያ ማሽን ላይሆን ይችላል፡፡

ሆኖም ሁነኛ አንደበቱ ነው - የመንግስት ወይም የኢህአዴግ፡፡

ስለዚህ እርምሽን አውጪ ብያታለሁ - ወዳጃችንን፡፡ “ነቄ” አልኩ እንጂ እሷም አላማዋ መንግስት “አዲስ ዘመንን” ዘግቶ (ሸጦ) ነፃውን ፕሬስ ደጅ እንዲጠና ነበር (ሱሚ ናት!!) በነገራችሁ ላይ እኔም እንደ አዲስ ዘመን “ፖለቲካ በፈገግታ”ን በአዲስ መልክ ለመጀመር አስቤአለሁና ስፖንሰር አፈላልጉልኝ (አደራ!!)

 

 

Read 3140 times Last modified on Saturday, 25 February 2012 13:24