Monday, 04 April 2016 09:15

አለማቀፍ ብራንድ ለመሆን የምትተጋው ዲዛይነር

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(6 votes)

    “ወደ 60ዎቹ እንመለስ” የሚል ትርኢት በኒውዮርክ ታቀርባለች
     አንድ ጊዜ የውጭ አገር ዜጎች በቡድን ወደ ሱቋ ገቡና፤ “ሳምራዊት ማናት?” በማለት ጠየቁ፡፡ “እኔ ነኝ” አለቻቸው። ዕቃ መረጡ፣ የተጠየቁትን ዋጋ ከከፈሉ በኋላ አላመኑም። በርካሽነቱ ተደንቀው፤ “ይኼው ነው የምንከፍለው?” ሲሉ ጠየቁ፡፡ “አዎ!” አለቻቸው፡፡ ከመሃከላቸው አንዷ፤ “በእኛ አገር ዲዛይነርነት ይከበራል፤ አከብርሻለሁ። እንደዚህ ዓይነት ምርጥ (ኳሊቲ) ዕቃዎች ደግሞ በጣም ውድ ናቸው፡፡ በጣም ነው ከልብ የምናደንቅሽ፤ በእኛ አገር ዲዛይነሮች በጣም ሀብታም ናቸው፡፡ አንቺ እንደዚያ እንዳልሆንሽ አውቃለሁ፡፡ በቦርሳዬ የቀረኝ 400 ዶላር አለኝ፡፡ እባክሽ ለአድናቆቴ መግለጫ እንዲሆነኝ ተቀበይኝ” በማለት ሰጧት፡፡ “ለምንድነው በእኛ አገር በቤልጂየም ሱቅ የማትከፍቺው?” ሲሉም ጠየቋት፡፡
በሌላ ጊዜ ደግሞ ሦስት የውጭ አገር ሰዎች ወደ ሱቋ ገቡ፡፡ አንድ ሴትና ሁለት ወንዶች የፈለጉትን መርጠው ከገዙና ዋጋውንም ከከፈሉ በኋላ ሴቷ፤ “እዚህ አገር ለሦስተኛ ጊዜ መምጣቴ ነው፡፡ ከሥራ በኋላ ባለኝ ጊዜ ከተማዋን እጎበኛለሁ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ዲዛይኑ ያማረና አጨራረሱ እንከን የማይወጣለት (ፐርፌክት ፊኒሽንግ) የሆነ ዕቃ አገኘሁ፡፡ ዋጋ ሊያስከፍልሽ ይችላል፡፡ ነገር ግን ወደፊት ትልቅ ቦታ ትደርሻለሽ፡፡ ኒውዮርክ ላይ አይሻለሁ፡፡ እነዚህንም ቦርሳዎች በትላልቅ መደብሮች ውስጥ አያለሁ፡፡ በርቺ!” በማለት አቅፋ አድናቆቷን ገለጸችላት፡፡
ጥራት ያለው ዕቃ ማየት ብርቅ በሆነበትና አገሪቷ በቻይቻ ርካሽ ዕቃዎች በተጥለቀለቀችበት ወቅት ባልተለመደ ድፍረት “ሳምራዊት መርስኤኅዘን” የሚል ስም (ታግ) የተለጠፈበት ምርጥ ዕቃ ማየት በጣም የሚገርምና እጅግ የሚያኮራ ነው፡፡
ወደ ሱቁ ሲጠጉ (ኧረ ከሩቅም ይታያል) “ሳምራ ላግዠሪ ወርልድ ክላስ ሌዘር” የሚል የብራንድ ስም ያያሉ። ሱቁ ውስጥ ሲገቡም ይኼው ስም ሁለት ቦታ አለ። ሱቁ የተሞላው የተለያዩ ዲዛይን ባላቸው ምርጥ የሴትና የወንድ ቦርሳዎች፣ የቆዳ ስካርፍና ምንጣፍ ነው፡፡ ወደ ሱቁ እንደገቡ አውሮፓ ወይም አሜሪካ ያሉ ሊመስልዎት ይችላል፡፡ በሚያዩት የቦርሳዎች ጥራት፣ ዲዛይን፣ አሰፋፍ፣ አጨራረስ፣ … ተገርመው “እውነት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ያለሁት?” ሊሉ ይችላሉ፡፡
ሳምራዊት መርስኤኅዘን፣ አዲስ አበባ አዲስ ገበያ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው የተወለደችው - በ1974 ዓ.ም፡፡ እስከ 12ኛ ክፍል የተማረችው እዚያው አካባቢ ባለና “ሴንት ሜሪ” እየተባለ በሚጠራ የሴቶች አዳሪ ት/ቤት ነው፡፡ ሳምራዊት በትምህርቷ ጎበዝ ብትሆንም እንዳትቀጥል የሚያደርጋት ነገር ተፈጠረ፡፡ 11ኛ ክፍል አጋማሽ ላይ “ሚግሬይን” የተባለ ኃይለኛ የራስ ምታት በሽታ ያዛት፡፡ እንደምንም ከበሽታው ጋር እየታገለች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስዳ ውጤት ቢመጣለትም ሐኪሞቿ በትምህርቷ መቀጠል እንደማትችል ስለነገሯት ለማቆም ተገደደች፡፡
ሳምራዊት ሕፃን እያለች (ከ10 ዓመት ጀምሮ) ለዲዛይን ልዩ ፍላጎት ነበራት፡፡ አሮጌ አንሶላዎች … ጨርቆች እየቀደደች ትሰፋ ነበር፡፡ ወላጆቿ ግን በዚህ ደስተኞች አልነበሩም፡፡ በትምህርቷ ላይ እንድታተኩር ስለሚፈልጉ ይገርፏት ነበር፡፡
የዩኒቨርሲቲው ትምህርት ሲቀር “ለምን የምወደውን ዲዛይን አልማርም?” ብላ ዲዛይን ት/ቤት ገባች፡፡ እዚያም ፓተርን ሜኪንግ፣ ስኬች (ንድፍ)፣ ፕሮቶታይፕ፣ … ተማረች፡፡ እንደ ዕድል ሆኖ በሙያው የተካኑ ሁለት የውጭ አገር ዜጎች አግኝታ “ፋሽን ፎርካስቲን” አስተማሯት። አንደኛው ዲዛይነር የቆዳ (ሌዘር) ኤክስፐርት ነው፡፡ እሱ ምን ዓይነት ዲዛይን ከምን ዓይነት ቆዳ ጋር ይሄዳል? የሚለውን አስተማራት፡፡
ዲዛይኑን ብትማርም የራሷን ሥራ ለመጀመር የሚያስችል የገንዘብ አቅም አልነበራትም፡፡ ገንዘብ ለማግኘት የተለያዩ አማራጮችን ብታስብም አልሆነም። በመጨረሻ ለመበደር ወሰነች፡፡ ገንዘብ የሚያበድሯትን ስትፈልግ ራቅ ካሉት ይልቅ በቅርቤ ባሉት ላይ ባተኩር ይሻላል በማለት ወንድሟን ጠየቀች፡፡ ታናሽ ወንድሟም ያለውን ሰጣት፡፡ ያ ብቻ በቂ አልነበረም፡፡ ጓደኞቿ ደግሞ ዕቁብ ሰበሰቡላት፡፡ ያንን ገንዘብ ይዛ የዛሬ 3 ዓመት ገደማ በ70 ሺህ ብር ቦሌ መድኃኒዓለም አካባቢ ሥራ ጀመረች፡፡
ሳምራዊት እውስጧ ያለ ነገር አለ፤ “ከሠራሁ ዓለም አቀፍ ብራንድ ያለው ነገር ነው የምሰራው” የሚል፡፡ ሥራ ከመጀመራ በፊት ገበያውንና ሥራው ያሉትን መልካም አጋጣሚዎች አጠናችና ያለውን ክፍተት አወቀች፡፡ በጣም ጥራት ያለው ቆዳ አለ፡፡ ሰው በቆዳው ቦርሳ ተሰርቶ ሲያይ፤ “አይ! ይህ የአገር ውስጥ ነው” እያለ ያናንቃል፡፡ ሳምራዊት ደግሞ “የአገር ውስጥና የውጪው በአጨራረስ መለየት የለበትም፤ አንድ ዓይነት መሆን አለበት፡፡ በዚህ ላይ ዓለም አቀፍ ብራንድ መሆን አለበት” የሚል አቋም አላት፡፡
መጀመሪያ ላይ ሁኔታዎች ሁሉ ችግር የበዛባቸውና ፈታኝ ነበሩ፡፡ ሱቅ ተከራይታ የኤክስፖርት ደረጃ ቆዳ ገዝታ፣ ዲዛይን አውጥታ፣ ወርክሾፕ ስለሌላት በሌላ ሰው ወርክሾፕ አሰርታ፣ ክሩ፣ ጨርቁ፣ ግብአቶቹ፣ ብረታ ብረቶቹ፣ … ሁሉም ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ስለሆኑ ወጪውን ሸፍኖ ያዋጣኝ ይሆን? ጥራቱንና ምርጥ ዕቃ መሆኑን አውቆ በሚያዋጣ ዋጋ የሚገዛ ይኖር ይሆን? የሚል ስጋትና ፍርሃት ገብቷት ነበር፡፡ ስለዚህ ለማለማመድ ትንሽ ትንሽ ታመርት ነበር፡፡
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለች ነው “እዚህ አገር ስመጣ ሦስተኛ ጊዜዬ ነው፡፡ ነገር ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የሚያምርና አጨራረሱ ያማረ (ፊኒሽንጉ ፐርፌክት የሆነ) ዕቃ ያገኘሁት፡፡ ዋጋ ሊያስከፍልሽ ይችላል፡፡ ወደፊት ትልቅ ቦታ ትደርሽያለሽ፡፡ ኒውዮርክ ላይ አይሻለሁ፡፡ እነዚህንም ቦርሳዎች በትላልቅ መደብሮች ውስጥ አያቸዋለሁ፡፡ በርቺ!” በማለት አቅፋ አድናቆቷን የገለጸችላትን ጋዜጠኛ ያገኘቻት (ጋዜጠኛ መሆኗንና በአዲስ አበባ የተካሄደ ትልቅ ጉባኤ ለመዘገብ መምጣታቸውን የነገረቻት በኋላ ነው)
በችግር ወቅት የሚደርስልህ ወዳጅ አትጣ ይባላል፡፡ ሳምራዊትም በችግሯ ወቅት የሚደርስላት ወዳጅ አላጣችም፡፡ ዳንኤል ተስፋዬ የሚባል ትንሽ ልጅና ታናሽ ወንድሟ ኤፍሬም መርስኤኀዘን በጣም እንደረዷት ትናገራለች፡፡ “እንደ ታናሽ ወንድም ሲከፋኝ ያፅናናኛል፣ተስፋ ስቆርጥ ያበረታታኛል፤ገንዘብ እንኳ ሳጣ ይሰጠኛል፤በጣም ነው የደገፈኝ” በማለት ያላትን አክብሮት ገልጻለች፡፡
ሥራ በጀመርኩበት ወቅት አንድ ትልቅ ስብሰባ በየዓመቱ በኢትዮጵያ ይካሄዳል፡፡ African Heads of State Peace and Security Meeting Tana Forum ለሚባለው ጉባኤ ቦርሳ እንዳቀርብ ተመረጥኩ፡፡ በጣም ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ትላልቅ ድርጅቶች እያሉ እኔ በመመረጤ ማመን አልቻልኩም፡፡ ከተባለው ጊዜ ቀድሜ አስረከብኩ፣ ጥራቱም በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ከዚያም በየዓመቱ ለመሪዎችና ለከፍተኛ እንግዶች የሚሰጥ ቦርሳ አቀርብ ጀመር፡፡ ከዚያም የኤክስፖርት ጥያቄዎች መምጣት ጀመሩ፤ ትላለች ሳምራዊት፡፡
በኤክስፖርቱ ጥያቄ ፈታኝ ችግር እንደገጠማት ትናገራለች፡፡ ሰዎቹ በኢትዮጵያ የተሰራ (ሜድ ኢን ኢትዮጵያ) አትበይ ይሏታል፡፡ እሷ ደግሞ ይህን ጥያቄ ለመቀበል አልፈለገችም፡፡ “እኔ ስሰራ ገንዘቡ ብቻ አይደለም ትርፌ፡፡ እኔ ብቻዬን አይደለም የምሰራው፤ አገር አለች፣ አብረውኝ የሚሩ ሰዎች አሉ፣ … ብዙ ነገር አለ፡፡ አገራችን የምትታወቀው በረሃብ፣ በድርቅ፣ በድህነት ነው። ነገር ግን እኛ ለዓለም የምንሰጠው ብዙ ነገሮች አሉን፡፡ “ጥሩ ቦርሳ ትሰሪያለሽ፡፡ ነገር ግን ሜድ ኢን ኢትዮጵያ አትበይ” ይሉኛል፡፡ ቆዳው ኢትዮጵያዊ ነው፤ የምንሰራው ኢትዮጵያውያን ነን፣ ይህ ቦርሳ ኢትዮጵያ ውስጥ ተረግዞ ኢትዮጵያ ውስጥ የተወለደ፤ እናቱም አባቱም ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ እኔ እናንተ እንደምትሉት ማድረግ አልችልም፡፡ ይህ ለእኔ አገር እንደመሸጥ ነው የምቆጥረው” ስለምትላቸው ከብዙ ሰዎች ጋር ሳትስማማ ቀርታለች፡፡ “ጥራቱንና ሁሉንም ነገሩን ወደውት ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ከጠሉ አይሆንም፡፡ አሁን ናሙና (ሳምፕል) ስጭን ሲሉኝ ‹ፕራውድሊ ሜድ ኢን ኢትዮጵያ› (በኩራት ኢትዮጵያ ውስጥ የተሰራ) ብለን ነው የምንሰጠው” ብላለች፡፡
ሳምራዊት፣ ስራዋ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም፣ ዓለም አቀፍ ብራንድ ሆኖ በፋሽን መድረኮች እንዲታወቅ ትፈልጋለች፡፡ እዚሁ በአገራችን ባለፈው ዓመት የአፍሪካ ምርጥ ዲዛይነሮች የተሳተፉበት Hub of Africa የተሰኘ የፋሽን ትርዒት በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዶ ነበር፡፡ ኔክዴፕ የሚባል ብራንድ ዲዛይነር ለእነ ኦባማ፣ ለእነ ሳሙኤል ጃክሰን… ጫማ የሚሰራ፣ ሼልደንና ሌሎችም በዓለም የታወቁ ዲዛይነሮች ነበሩ። ሳምራዊትም ስራዎቿ “ምርጥ ነው” ተብሎ ከእነዚህ ዲዛይነሮች ሥራ ጋር መቅረቡን ትናገራለች፡፡
አፍሪካን ፋሺን ዋክ የሚባል በኒውዮርክ አለ፡፡ በትርዒቱ ላይ ሳምራዊት ተሳትፋለች፡፡ በዚያ ትርዒት ላይ የኢጣሊያ “ቮቭ” መጽሔት አዘጋጅ ሳራ ማንዬ ነበረች፡፡ በኢጣሊያ ኤምባሲ በተደረገው የምርጥ ሰዎች የፋሽን ትርዒትም ሳምራዊትም ተመርጣ ሥራዎቿን አቅርባለች። ከአሁን በኋላ መሳተፍ የምትፈልገው በዓለም ትላልቅ በሆኑ በኒውዮርክ፣ በፓሪስ፣ በለንደን፣ በሚላን፣ በቶኪዮ የፋሺን ትርዒቶች ላይ ነው፡፡  
በአሁኑ ወቅት የውጭ አገር ፋሽኖች እየመጡ እኛ ላይ ይራገፋሉ፡፡ ለምሳሌ ራቁትነት (እርቃን መሄድ) ፋሽን እየሆነ ነው፡፡ ሳምራዊት ያንን አትቀበልም፡፡ ወደ ትክክለኛው አለባበስ መመለስ አለብን ትላለች፡፡ እኔ አንድ ኮሌክሽን ብሰራ ከ1950-1970 የነበረውን ስታይል እወዳለሁኝ፡፡ ያንን በዘመናዊ መልክ መስራት ይቻላል። እኛ ኢትዮጵያዊያን ጥሩ አለባበስ አለን፡፡ በዓለም መድረኮች መሳተፍ ስጀምር ስነ - ሥርዓት ያላቸውን ጨዋ አለባበሶች ከቦርሳዎቹ ጋር ይዤ ለመቅረብ እያሰብኩ ነው ብላለች፡፡
የሳምራዊት ደንበኞች አብዛኞቹ የውጭ አገር እንግዶች ቢሆኑም ኢትዮጵያዊያንም ይሄዳሉ፡፡ ኢትዮጵያዊያኑ ዋጋ አይደፍሩም፡፡ ይኼ እንዲህ ዓይነት ቦታ ዋጋው እንዲህ አይደለም እንዴ? ይላሉ፡፡ እኔ የምለው አንድ ነገር አለ፡፡ በህይወታችን ውስጥ ዕቃ ስንገዛና ስንሸጥ ጥራት ላለው ዕቃ ዋጋ መክፈል አለብን፡፡ ጥሬ እቃው ሲገዛ ውድ ነው። ቆዳ ሲባል ሁሉም ቆዳ ዋጋው አንድ ዓይነት አይደለም፡፡ ኤክስፖርት ደረጃ ያላቸው ቆዳዎች ውድ ነው የሚገዙት፡፡ የእኛ ቦርሳ ብራንድ ነው፤ ሃይ ኢንድ ፋሽን ነው፡፡ ለምሳሌ ከውጭ የመጣ ፕላስቲክ ቦርሳ የሆነ ሰው ስም ስላለው 5 እና 6 ሺህ ብር ይሸጣል፡፡ የእኛ ግን እውነተኛ፣ በጣም ጥራት ያላቸው ቆዳዎች ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ኤክስፖርት ደረጃ ስለሆኑ ከክር ጀምሮ ልዩነት አለን፡፡ ስለዚህ እኔ የምወዳደረው ከትላልቆቹ ብራንዶች ጋር ነው፤ ደግሞም ይቻላል!
በአንድ ወቅት አንድ ዲፕሎማት ወደ ሱቋ ገብተው፤ “ሳምራዊት አንቺ ነሽ?” በማለት ጠየቄ፡፡ “አዎ! እኔ ነኝ” አለቻቸው፡፡ “እኔ በየመን የኢንዶኔዥያ አምባሳደር ነኝ፤ አንድ ከእናንተ የተገዛ ቦርሳ አይተን በጣም ወደነዋል። አሁን ለባለቤቴና ለቤተሰቤ ለመግዛት ፈልጌ ነው የመጣሁት” አሉ፡፡ ቦርሳዎቹን ከመረጡ በኋላ “ዋጋው ስንት ነው?” አሏት፡፡ ነገራቻቸው፡፡ አላመኑም፡፡ “በብር ነው? በዶላር?” አሏት፡፡ በብር እንደሆነ ነገረቻቸው፤ “እንዴት ያዋጣችኋል? እኛ አሜሪካ ብንሄድ፣ እንዲህ ዓይነት ጥራት ያለውን አይደለም፤ ጥራቱ ከዚህ በጣም በብዙ  ያነሰ በከፍተኛ ዋጋ ነው የምንገዛው” ብለው የተጠየቁትን ዋጋ ከፍለው ሄዱ፡፡
የውጭ አገር ዜጐች “ጥራቱ እንዲህ ከሆነ ለምን በውጭ አገር ሱቅ አትከፍቺም?” እያሉ ይመክሯታል። ሳምራዊትም በውጭ አገራት ሱቅ ለመክፈት እያሰበች ነው፡፡ “ገበያውን የተቆጣጠሩ ቡድኖች አሉ፤እኛ ለእነሱ መጋቢ ሆነን መቅረት የለብንም፡፡ ራሳችን ገበያው ውስጥ መግባት አለብን፡፡ ምክንያቱም ከእኔ ከ50 ዶላር በታች አንድ ቦርሳ ገዝተው ምንም እሴት ሳይጨምሩበት ገበያውን ስለተቆጣጠሩት በ1000 ዶላር ይሸጡታል። ይኼ ልክ አይደለም፡፡ እኔ ሳምራዊት የሚለውን ኢትዮጵያዊ ብራንድ ይዤ ገበያው ውስጥ መግባት አለብኝ የሚል አቋም አለኝ፡፡” ብላለች፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ጥሩ ጥሩ ልብሶች፣ ጫማዎች፣ ቦርሳዎች፣ የሚያመርቱ ድርጅቶች አሉ፡፡ ምርቶቻችን ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው “አዲስ አበባ የፋሽን ሳምንት” እንዲፈጠር እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሁልጊዜ ፋሽን ተቀባይ ብቻ ሳንሆን ሰጪም መሆን አለብን፡፡ አጫጭር ልብሶች ወይንም እርቃን የሆኑ ፋሽኖች መቀበል የለብንም ብዬ አምናለሁ፡፡ እኔ ለውጥ ከሚፈጥሩ ሰዎች አንዷ መሆን እፈልጋለሁ፡፡
ሳምራዊ በኅብረተሰባችን ውስጥ ከባህላችን ውጭ ውስጥ ውስጡን እየተሰበከ ያለ ነገር አለ፤ መጥፎ አዝማሚያ ስለሆነ ማስቆም አለብን ትላለች። “እኔ ዲዛይነሯ፣ ዕንቁላል ቀቅላ፣ ቆሎ ቆልታና አዙራ የምትሸጠዋም ልጅ የምንሠራው ገንዘብ ለማግኘት ነው። ገንዘብ ማግኘት እስከ ምን ድረስ? የሚለው ጥያቄ ግን መመለስ አለበት፡፡ ሁላችንም የምንኖርለት ዓላማ አለን። ራሳችንን ሸጠን መሆን የለብንም፡፡ ለምሳሌ እኔ ትልልቅ ሥራዎች ያጋጥሙኝና ከሥራው ባሻገር ከእኔ የሚፈልጉት ነገር ሲኖር አቆመዋለሁ፡፡ ምክንያቱም እኔ መልካም ሴት በመባል ነው መታወቅ የምፈልገው፡፡ ታሪኬ ከእኔ በኋላ ለሚመጣው ትውልድ መልካም ሴት፣ ክብሯን የጠበቀች ሴት ተብዬ እንጂ ራሷንና ክብሯን ሸጣ ትልቅ መኪና ላይ የተቀመጠች ሴት መባል አልፈልግም፡፡” ስትል ታስረዳለች፡፡
“በአሁኑ ወቅት በአገራችን በሴቶች ላይ እየተሰበከ ያለው ውስጣችን እስከዚህም ቢሆን ውጪያችን ላይ ሠርተን ተኳኩለንና ተብለጭልጨን የሆነ ሰው እንዲገዛን ራሳችንን ዝግጁ የማድረግ ዝንባሌ ነው ያለው፡፡ መሆን የለበትም፡፡ ይህ በጣም ቆሻሻነት ነው። እኔ የማይገባኝን ነገር አድርጌ ትልቅ ቤት ቢኖረኝ ወይም ትልቅ መኪና ብይዝ የምደርስበት ቦታ ከሌለኝ ዋጋ የለውም፡፡ መኪና የምሄድበት ቦታ ማድረሻ እንጂ የመኖሬ ምክንያት አይደለም፡፡ ስለዚህ መጥፎ አርአያ ሆኜ መኖር አልፈልግም፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለሴቶቻችን የማስተላልፈው መልዕክት ራሳችንን እናክብረው። የሚሸጡ ዕቃዎች አሉ፤ እኛ ግን ዕቃዎች ስላልሆንን አንሸጥም፡፡”
በመጪው መስከረም በኒውዮርክ በሚካሄደው የፋሽን ትርዒት የምትሳተፈው ሳምራዊት፤ ትልቅ ቦታ እንደምደርስ አልጠራጠርም ትላለች፡፡ በኒውዮርኩ የፋሽን ትርዒት የምትሳተፈው በቦርሳ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ዲዛይኖች የተሠሩ ልብሶችም ይዛ ነው፡፡ እንግዲህ ከ1950-1970 ያለውን የአገራችንን አለባበስ ታደንቅ የለ፤ የፋሽን ትርዒቷ ስም፤ “ወደ 60ዎቹ እንመለስ” (ባክ ኢንቱ ሲክስቲስ) የሚል እንደሆነ ተናግራለች፡፡

Read 2685 times