Saturday, 09 April 2016 09:31

ለድርቅ ተጎጂዎች ከፍተኛ እርዳታ የሰጡ 6 አገራት!

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(4 votes)

• “የድርቅ ተጎጂዎችን ለመርዳት፣ 16 ቢ. ብር መድቤያለሁ” የኢትዮጵያ መንግስት
• “የኢትዮጵያ መንግስት፣ ለድርቅ ተጎጂዎች 8 ቢ. ብር አውጥቷል” ዩኤስኤይድ

   በድርቅ ለተጎዱ ኢትዮጵያውያን፣ እስካለፈው ሳምንት ድረስ፣ ከውጭ አገራት የተሰጠ እርዳታ ከ940 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ የገለፀው የአሜሪካ መንግስት፣ አብዛኛው እርዳታ ከስድስት አገራት የመጣ መሆኑን ያመለክታል።
በእርግጥ፣ የተለያዩ አገራት በቀጥታ ከሚለግሱት እርዳታ በተጨማሪ፣ በዩኤን እና በአውሮፓ ህብረት በኩል የሚልኩት እርዳታም አለ። ነገር ግን፣ የእያንዳንዱን አገር መዋጮ ማስላት ይቻላል። እናም፣ እንደ ወትሮው ከፍተኛ እርዳታ በመስጠት፣ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዘው የአሜሪካ መንግስት ሆኗል - 546 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ በማቅረብ። (በሌላ አነጋገር፣ ወደ ሃያ ቢሊዮን ብር ከሚጠጋው ጠቅላላ የድርቅ እርዳታ ውስጥ፣ 11.5 ቢሊዮን ብር ያህሉ ከአሜሪካ መንግስት የተለገሰ ነው)።
ለኢትዮጵያ በየአመቱ ብዙ እርዳታ በመስጠት የሚታወቀው የእንግሊዝ መንግስት፣ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
ለድርቅ ተጐጂዎች እስካለፈው ሳምንት ድረስ፣ 145 ሚሊዮን ዶላር (3 ቢሊዮን ብር) እርዳታ ሰጥቷል። በቅርቡም፤ ተጨማሪ እርዳታ ለመመደብ ቃል ገብቷል።
በሦስተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው የጀርመን መንግስት ነው። በአውሮፓ ህብረት በኩል የሚያበረክተው መዋጮና በተናጠል የመደበው እርዳታ፣ 75 ሚሊዮን ዶላር ይሆናል (ዘጠኝ መቶ ሚሊዮን ብር ገደማ)።
ስዊድን 33 ሚ. ዶላር፣ ጃፓን 28 ሚ. ዶላር እና ኔዘርላንድ 25 ሚ. ዶላር ሰጥተዋል።
ስዊዘርላንድ፣ አውስትራሊያና ካናዳም፣ በየፊናቸው ወደ ሃያ ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ እርዳታ ለግሰዋል።
በጥቅሉ ሲታይ፤ ዋናዎቹ እርዳታ ሰጪዎች አሜሪካና አውሮፓ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ አሜሪካ 58% ያህሉን ስትሸፍን፣ የአውሮፓ ህብረትና የአውሮፓ አገራት በተናጠል ከ35%በላይ አዋጥተዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ፣ የኢትዮጵያ መንግስት፣ የድርቅ ተጎጂዎችን ለመርዳት፣ በተለይም ከውጭ እህል ለመግዛት፣ በቂ እርዳታ ስላልተገኘ እስካሁን 16 ቢሊዮን ብር እንደመደበ ገልጿል። ዩኤስኤይድ እንደሚለው ግን፣ የድርቅ ተጎጂዎችን ለመርዳት፣ ከኢትዮጵያ መንግስት ካዝና የወጣው ገንዘብ 8 ቢሊዮን ብር ገደማ ነው (380 ሚ.ዶላር)።
ሁለቱ የኢትዮጵያ መንግስትና የዩኤስኤይድ መረጃዎች በጣም የሚራራቁ መሆናቸው ግልፅ ነው። ለዚህም ሁለት ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል።
አንደኛ ነገር፣ “ለእርዳታ ይሄን ያህል ገንዘብ እመድባለሁ ወይም መድቤያለሁ” ብሎ ቃል መግባት በቂ አይደለም፡፡ ቃል መግባት የመጀመሪያው ደረጃ ነው - (Pledge ይሉታል)። ቃል ከገባ በኋላ፤ ባይሳካለትና ያሰበውን ያህል እርዳታ ባይሰጥ፤ ግዴታ የለበትም። በተግባር “ይሄን ያህል የእርዳታ ገንዘብ ተሰጠ” የሚባለው ክፍያውን ሲፈፅም ነው። አልያም፣ ክፍያ ለመፈፀም ህጋዊ የውል ግዴታ ይፈራረማል፡፡ እርዳታ ለመስጠት ገንዘብ ወጪ እንዳደረገ ይቆጠራል - (Commitment ይሉታል)። እርዳታ ተሰጠ ተብሎ የሚመዘገበው እዚህ ደረጃ ላይ ከደረሰ ብቻ ነው፡፡
ምናልባት፣ የኢትዮጵያ መንግስት 16 ቢሊዮን ባጀት መድቦ ይሆናል። ነገር ግን፣ የተመደበው በጀት በሙሉ፣ ወጪ ሆኗል ማለት አይደለም። ስለዚህ፣ ገንዘቡ በሙሉ ለተረጂዎች ይውላል ተብሎ ሊመዘገብ አይችልም፡፡
በዚህም ምክንያት፣ በኢትዮጵያ መንግስት መረጃና በዩኤስኤይድ መረጃ መካከል ልዩነት ቢታይ አይገርምም።
ግን፣ ሌላ ምክንያትም አለ።    የድርቅ ተጎጂዎችን ለማገዝ፣ እነ አሜሪካና አውሮፓ ለጋሾች በቂ የእርዳታ ገንዘብ ቢሰጡ እንኳ፣ በዚሁ ገንዘብ ከተለያዩ አገራት እህል ገዝቶ ለማምጣት ረዥም ጊዜ ሊፈጅ ይችላል። ቶሎ አይደርስላቸውም። እህል ለመግባትና ለማጓጓዝ ከአራት ወር በላይ መጠበቅ የግድ ነው፡፡ እስከዚያው ግን፣ ለጋሾች እጃቸውን አጣጥፈው አይመጡም። አሁኑኑ፣ ከመንግስት እህል ተበድረው በመውሰድ፣ ለተረጂዎች ያከፋፍላሉ። ከጊዜ በኋላ፣ የተበደሩትን እህል ለመንግስት መልሰው ያስረክባሉ። ወይም ገንዘብ ይከፍሉታል።
ይሄ ሊሳካ የሚችለው ግን፣ መንግስት እህል ገዝቶና አከማችቶ ከጠበቀ ብቻ ነው። ለዚህም በጀት መመደብ ያስፈልጋል። ደግነቱ በአለም ገበያ የስንዴ ዋጋ ቀንሷል - በኩንታል ከ450 ብር በታች፡፡
ጥሩ መላ ነው። ነገር ግን፣ እህል ገዝቶ ለማከማቸት፣ በመንግስት የሚመደበው በጀት፣ ለእርዳታ እንደተመደበ ገንዘብ መቆጠር የለበትም። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ፣ ወጪውን የሚሸፍኑት ለጋሾች ናቸውና። መንግስት ግን፣ “ለእርዳታ የተመደበ ገንዘብ ነው” ሊል ይችላል። በዚህም ምክንያት፣ ከዩኤስኤይድ መረጃ ጋር፣ ልዩነት ይፈጠራል።

Read 3434 times