Saturday, 09 April 2016 10:01

“አይወዱህም!”

Written by  ፍፁም ንጉሴ
Rate this item
(12 votes)

 “ኡ!  ኡ! ኡ! …” ቅልጥ ያለ ጩኸት፡፡
“እግዚኦ … ጉድ ጉድ” የተደበላለቀ ጫጫታ፡፡
“ምንድነው? ማነው የሞተው?”
“ፍቅሩ ነዋ”
“የኛ ፍቅሩ?”
“አዎ”
“ፍቅሩ ተሰቅሎ ሞተ”
በመንደሯ ዳርቻ ያለው አስፈሪና አስቀያሚ የቆሻሻ መጣያ የገደል አፋፍ ቀውጢ ሆነ፡፡ ሰዎች በየዓይነቱ ተኮልኩለዋል፡፡ ሁሉም ያወራል፡፡ ከንፈሩን ይመጣል፡፡ ደረቅ አይኑን እየጠራረገ የበለጠ ያደርቀዋል፡፡ አንዱ ከሌላው እየተቀበለ፣ የደነገጠ ያዘነ መስሎ ለመታየት ይጥራል …
“አጋዤ ነበር … ታዛዤ”
“የማይከፋው የማይሰለቸው ‹እሺ› እንዳለ ሔደ”
“አይ ሙያ - አይ ግንበኛ!
“አናፂነቱስ!”
“ምን የማይችለው ነገር አለ ደግሞ ፍቅሩ!”
አሁንም አሁንም ወደ ግዙፉ ዋርካ ቅርንጫፎች ያያሉ፡፡ እንደተንጠለጠለ ነው፡፡ አይንቀሳቀስም፡፡ ደርቋል፡፡ ሁሉም ይጮሃል፡፡ ሁሉም ይለፈልፋል …
“ኧረ አባዲና … ጥሩ እንጂ አባዲና!”
“ፖሊስ … ፖሊስ ይጠራ!”
አንድ ጸጉረ ልውጥ ሰው ይታያል፡፡ ወጣት ቢመስልም ወጣትነቱን በእርግጠኝነት ማወቅ ያዳግታል፡፡ ጥላሸት መስሎ ያስፈራል፤ ድሪቶ ለብሶ ድሪቶ ተከናንቧል፡፡ ያነክሳል፡፡ ባዶ እግሩን ነው፤ እስካሁን ቃል አልተነፈሰም፤ ስለ ሟች አንዳች ነገር ለመስማት የፈለገ ይመስላል … ወደሚናገሩት ሁሉ እየተጠጋ ያዳምጣል፡፡ ማንም ግን ጉዳዬ አላለውም። ሃዘኑ ጥቁር ገፅታውን እያሸነፈው ሲጎላ ይታያል፡፡
ጥቂት የማይባሉት ታየን አልታየን እያሉ ወደ መንደሯ ፒስታ መንገድ ይሰወሩ ጀመር፡፡ የቀሩትም ጫጫታቸውን አርግበው በቡድን በቡድን ተከፋፍለው ወሬያቸውን ቀጠሉ፡፡
“ወይ ጉድ … ለመሆኑ እንዴት ገባ? በየት በኩል?”
“መቼም ማታ ወይም ሌሊት ነው የሚሆነው”
“ቦታው ለምዷል … ጠርቶት ነው”
ብዙ ሰዎች በዚህ የጉድጓድ ውሃ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ አዛውንቶች እንደሚሉት፤ድሮ ዋርካው አድባር ነበር፡፡ አሁን ያ ልማድ ሲቀርበት እየጠራ ይወስዳቸዋል ባይ ናቸው፡፡ በእርግጥ የፍቅሩ አሟሟት የተለየ ነው፡፡ ረግቶ በበሰበሰው፤ በየቀኑ ከሚውጠው ቆሻሻ፤ የድመት፣ የውሻና የዶሮ ሬሳዎች እያንሳፈፈ አፍንጫን የሚወጋ ግማት ሽቅብ በሚያተነው ውሃ ውስጥ ሰጥሞ አልሞተም፡፡ በግሙ ውሃ መሃከል ላይ እንብርት መስሎ ሽቅብ ተመዞ በገዘፈው ዋርካ ላይ ወጥቶ ነው የተንጠለጠለው፡፡ … በርግጥ ገደሉ ውስጥ ህይወት ያለው ሰው ገብቶበት አያውቅም፡፡ ድሮ ድንጋይ ማምረቻ እንደነበረ ይወራል፡፡ በቆሻሻው ተቃራኒ ስለታም አለታማ ተራራ ተገትሯል፡፡
“ለመሆኑ ማነው ያየው?”
“ያቺ ሰማያዊ ቱታው ናት እንዲታይ ያደረገችው”
“እሷኑ እንደለበሰ ሞተ!”
“ከነሷ ቅበሩኝ ብሎ ተናዞ እንዳይሆን ብቻ---”
እነሱ ለአሽሙር ቢናገሩትም ሰማያዊው ቱታው እንደ ባንዲራ የምትቆጠር ናት፡፡ በበዓል ቀን እንኳን ወልቃ አታውቅም፡፡ የፋብሪካዋን ስሪትና ፋሽን የረሳች፤ የመንደሩ መንገዶች የሰለቿት ጫማውም አብራው ናት፡፡
አባዲናም ፖሊስም ብቅ አላሉም፡፡ ይጠሩ አይጠሩ አልተረጋገጠም፡፡ ሁሉም ነገር እየረገበ ሄደ። ወዲያው  የፍቅሩ ሞት ትኩስ ዜናነት፣ የመሰቀሉም ዘግናኝነት የከረመ ያህል ተለመደ፡፡ ስለሞተበት ምክንያት ለማወቅ የሞከረ የለም፡፡ ያ ሰላይ መሳዩ ጥቁር ሰው ግን አይኖቹን ዋርካው ላይ ተክሎ ጆሮውን ጣል ከማድረግ አልቦዘነም፡፡  
ወደ መንደሯ ዘልቆ ‹ፍቅሬ ማ-ነው?› ብሎ የጠየቀ፣ ሰዎች ቀርተው ቤቶቹ አጥሮቹ፣ ድንጋይ እንጨቶቹ ሳይቀሩ ቁንጣን እስኪወጥረው ይነግሩታል፡፡ ፍቅሩ ማለት ሰዎችን ሁሉ በመውደድ እንደሚወዱትም በማመን ለነሱም በመገዛት የኖረ መሆኑን ይተርኩለታል፡፡ ስለ 16 ሰዓት ሰራተኛነቱ፤ ስለ መናጢ ድህነቱም ያክሉለታል፡፡ ሳቅና ፈገግታ ቁርሱ፤ ቁልምጫ ምሳው፤ አድናቆትና ምስጋና ራቱ መሆኑንም አይደብቁትም፡፡
ፍቅሩ ለምታፈቅረው ---- ለሚያፈቅራት ማርታ እንኳን ጊዜ አግኝቶ አያውቅም፡፡ ይህ አነፍናፊ ጥቁር ሰው እነዚህን ቀርቶ … ከሰውና ከስራ በቀር ምንም ሱስ እንደሌለበት ሊያውቅ ሁሉ ይችላል … የሌሎቹን ቤት ሲገነባና ሲያንፅ፣ሲቀባና ሲያሸበርቅ … ሃያ ዘጠኝ ዓመት የኖረባት ያባቱን ዛኒጋባ ከወደ ግንባሯ እየሰገደች … ከወደ ጎኗ ወደ መሬት እየገባች … ጣራዋ አሞራ ቢያርፍበት የሚነደል እስኪመስል አርጅቶ … እያየ እንዳላየ የሆነበትን ምክንያት ሳይቀር የሚያነፈንፍ ይመስላል ---- ጸጉረ ልውጡ፡፡
  “አቤት ምን አይነት የዋህ ነበር …”
“ጅል እንጂ! … የሰራበትን እንኳን የማይቀበል!”
“‘ፍቅርዬ የኔ ጌታ› ስለው እንደ ውሃ ፍስስ እያለ … አብሮኝ ወፍጮ ቤት ይሄድ ነበር …”
“ቪላውን ያሰራሁት እሱን ነበር … ግንበኛም አናፂም አድርጌ … አይቶት የማያውቀውን ራት ጋበዝኩትና በደስታ ሰክሮ ሄደ”
“ኧረ ጅል ነበር! … አምስት ክፍል ሰርቪስ ቤት ሰርቶ… ጉዱን ልየው ብዬ 100 ብር ስሰጠው እጅ ነስቶ ላሽ አለ”
“ኮርኒስ ሰርቶ፤ ቀብቶ … ማታ አብረን ድራፍት ጠጣን …በቃ ሂሳቡ ተጣጣ !”
ሁሉም ፍቅሩን አጃጃልኩ ያለውን በየተራ እንደ ገድል ያወራዋል፡፡
 ጥቁሩ ሰውዬ ሳቀ፡፡ የደስታ ግን አልነበረም፡፡ ማሽላ ሲያር ይስቃል የሚባለው ዓይነት ይመስላል። በግኗል በልቡ … “ወይኔ ፍቅሩ … ጉድህን ስማው እስኪ ---- አንድ አፍታ ነቃ ብለህ” እንደሚል ሁኔታው ይናገራል፡፡ … ደሞ ወደ ሌሎች ዞር ብሎ ያዳምጥ ጀመር፡፡
“እናቱ አልሰሙም ይሆን?”
“ብትሰማስ ወለደችው እንጂ … እሱ እኮ የሁላችንም ነበር ..”
“አባትና ወንድሙ እንኳን አይወዱትም”
“ደግ አደረጉ … እሱ እኮ ብኩን ነበር! ያንን የመሰለ ችሎታ ይዞ … ተርመጥምጦ ቀረ ኤዲያ!”
“ማርታስ?”
“ምን ታድርገው?! ያቺን የመሰለች ቆንጆ ከዚህ ዓይነቱ አመዳም ጋር መግጠሟ አንሶ ትዘለው ---?”
“የሀብታም ልጅ ሆና---- ስንት ወንድ እያለ! …”
ከሰል ፊቱ ከሰለ፡፡ መቋቋም አቃተው፡፡ አፋፉ ላይ ተንበረከከ፡፡ ማንም ልብ አላለውም … በእጆቹ ቆሻሻውን እያመሳቀለ … እየጨበጠ ወደ ዋርካው በተነ … ፍቅሩን ብቸኛ ያደረገው … ከአባትና ከወንድሙ ያጣላው፤ እናቱን ከመጦር ያናጠበውና ማርታን ከመሰለች ሴት ጋር በሰቀቀን ፍቅር ያሰረውን ችግር --- የተረዳለት ይመስላል፡፡ ጥቂት ቆይቶም ለራሱ ማነብነብ ጀመረ፤
 “አየኸው፤ ሳቃቸው ረትቶህ፣ ፍቅራቸው አውሮህ -----የሰራህበትን ባለመጠየቅህ፣ ‹ጅል› ብለው ሰየሙህ .. ፈገግታን ---ቁልምጫንና  ግብዣን አክብረህ ከደመወዝ በመቁጠርህ ---- ‹ከንቱ የማትረባ› ተባልክ … እናትህ የምትወድህ የዋህ ርግብ ነው ብላ ስላመነች እንጂ ባንተ ተስፋ ኖሯት አልነበረም፡፡ ታናሽ ወንድምህ ‹ለራስህ ሁን› ሲልህ “ሰዎች ውሸታቸውን ነው ፤አይወዱህም” ብሎ ሲመክርህ ጠላኸው፡፡ አባትህም “የማንም አሽከር ነህ” ብሎ አንቅሮ ተፋህ፡፡ ማርታን የመሰለች ልጅም በደልክ … ጉድህን ሰማኸው …አይደል!?”
ፍቅሩ ስድስተኛ ክፍልን ሁለቴ ሲወድቅ ትምህርቱን አቁሞ ከግንበኛ አባቱ ጋር መዋል ጀመረ። ብዙ ነገሮችን ከሰዎች መጋራት የጀመረው በለጋነቱ ነበር፡፡ እሱ በሙያው ከተካነ በኋላ አባቱ ከግንብ ላይ ወደቁና ክፉኛ ተጎዱ፡፡ እናም ከቤት ዋሉ፡፡ ዳግም ወደ ግንበኝነት ስራቸው አልተመለሱም፡፡ ሲሻላቸው በዘበኝነት ተቀጠሩ፡፡ ፍቅሩ ሁሌ ማታ ማታ ቤት ሲገባ አዋዋሉን ይጠይቁታል፡፡ ሲያንፅ ሲገነባ መዋሉን ይነግራቸዋል፡፡ “ደመወዝህስ?” ሲሉት “አግዘኝ” “እርዳኝ” ብለውኝ ስሰራ ዋልኩ ይላቸዋል፡፡ ሌላ ጊዜ ከኪሱ እዚህ ግባ የማይባል ገንዘብ ያገኛሉ፡፡ “ምንድነው ይሄ?” ብለው ሲጠይቁት ያሰሩት ሰዎች የሰጡት ክፍያ እንደሆነ ይነግራቸዋል፡፡ ለሥራው ቀድሞ መነጋገርና ክፍያውን መዋዋል አልሆንለት አለው፡፡
በመጨረሻ ከቤት እንዲወጣ ተፈረደበት፡፡ እናት አብረው ሊወጡ ተነሱ፤ ፍቅሩ በልመና መዓት እናቱን አረጋግቶ ብቻውን ወጣ፡፡ ማርታን ማግኘት ፈለገ። ከማንነቷ ዝቅ ብላ እንዳፈቀረችው ስለሚገባው ያዝንላታል፡፡ ፍቅሩን ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰሩትና ስራውን አድንቀው ከሚገባው በላይ የከፈሉት አባቷ  ናቸው፡፡ ያኔ ነበር የዋህነቱና ጥበበኛነቱ የማርታን ልብ የማረከው፡፡ ምሽት ቢሆንም ሄዶ አገኛት። ሁሉንም ነገራት፡፡ የሰራቸውን ስራዎች ሁሉ እንዲያሳያት ጠየቀችው፤ አሳያት፡፡ ለሰራው ሁሉ በአግባቡ ቢከፈለው እጅግ ሃብታም ይሆን እንደነበር በምሬት ነገረችው፡፡ ከሷ ጋር ሻይ ለመጠጣት ጊዜ እያጣ በፍቅር የቀጣትን ሁሉ እያነሳች ወቀሰችው። “ሰዎች አይወዱህም፤ አንተ ብትወዳቸውም እነሱ ይጠሉሃል፡፡ ወዝህን እየመጠጡ ነው፡፡ ቤት እየሰሩ ቤት አልባ አድርገውሃል፡፡ የላብህን ዋጋ እየነፈጉህ እንዴት ይወዱኛል ትላለህ … ፈገግታና ቁልምጫ ሆድ አይሞላም፡፡ ግብዣ አያዘልቅም፡፡” ለነገ ሳትል እንደ ጉድ ወረደችበት፡፡ ራሱን አመመው፡፡ “ግዴለም ሁሉም ይስተካከላል” ብሏት ሄደ … አሰበ ወሰነ … የወሰነውንም አደረገ …
ፖሊሶች ደረሱ፤ ፎቶግራፍ ተነሳ፡፡ ሆኖም እንዴት ከተሰቀለበት ሊያወርዱት እንደሚችሉ ግራ ተጋቡ፡፡ ያ ጥቁር ሰውዬ ሁኔታውን በሃዘን ይከታተላል፡፡ ሰዎች ሲያሸረግዱም አየ፡፡ ጥቂት ሰዎች በገመድ ወደ ውሃው ወርደው ዋርካው ላይ በመውጣት፣ አስከሬኑን በገመድ አስረው ወደ ታች እንዲያወርዱ ሃሳብ ቀረበ፡፡ ፈቃደኛ ግን ጠፋ … በዚህ መሃል ከመንደሯ ጩኸት ተሰማ … ሁሉንም የሚረብሽ ጩኸት… የፍቅሩ እናት እየበረሩ ደረሱ። “ልጄ ልጄ“ ይላሉ፤ራሳቸውን አያውቁም ነበር፡፡ ማርታ ከኋላ ትከተላቸዋለች … ወደ ገደሉ ሲሮጡ ሰዎች ያዟቸው፡፡ ማርታ ሳትታይ ወደ ገደሉ ስትሮጥ ጥቁሩ ሰው ተሹለክልኮ ያዛት …. እሱን አላየችውም …. ወደ ዋርካው ጮኸች …
ጥቁሩ ሰውዬ ከዚህ በላይ መቋቋም አልቻለም፡፡ የሁለቱ ሰዎች ለቅሶ … እውነተኛ ፍቅር--- አሸነፈው።
“ማርታ … እኔ ነኝ … እኔ ነኝ”
አልሰማችውም፤ ጥላሸቱን ጠራረገ፡፡ ድሪቶውን ጣለ፡፡ በድንጋጤ አፈጠጠችበት … “እናቴን ያዢልኝ …” እሱ ከፍ ወዳለ ቦታ ወጣና ጮክ ብሎ መናገር ጀመረ፤ “ፍቅሩ አልሞተም አለሁ … የተንጠለጠለው ‹ጅሉ› ያላችሁት እኔነቴን የወከለ ቱታዬን የለበሰው ፍቅሩ ነው…”
ሁሉም ደነገጡ … አላመኑም ግን እራሱ ነው፡፡ አውቀውታል፡፡  
“እንኳን ደስ ያላችሁ … ከናንተው አንዱ ሆኛለሁ … ከዘመኑ ታርቄአለሁ… ያንንን ቅበሩት መብታችሁ ነውና … እኔ አስመሳይ ፍቅራችሁን እመልስላችኋለሁ … እናንተ ደግሞ ላቤን ትመልሱልኛላችሁ ---- ህይወት ይቀጥላል”
ሁሉም አቀርቅሮ ቀረ፡፡

Read 4814 times