Saturday, 09 April 2016 10:30

የዶፒንግ ደወል በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ላይ…

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

      በሪዮ 2016 ኦሎምፒክ የኢትዮጵያ ተሳትፎን በተመለከተ አይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡
      ዓለም አቀፍ የፀረ ዶፒንግ ተቋማት  ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ጋር በቅርበት እየሰሩ ሲሆንየአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ እና የዋዳ ፕሬዝዳንቶች ለጉብኝት ይመጣሉ፡፡
      በሚቀጥሉት 5 ወራት ከ350 በላይ አትሌቶች በዶፒንግ ምርመራና ክትትል ውስጥ ያልፋሉ፡፡
 ሪንግናግሉኮስበስፖርቱየተከለከሉአበረታችቅመሞችቢሆኑም፤ አንዳንድየህክምናተቋማትናባለሙያዎቻቸው
      አትሌቶችን መውጋት ቀጥለዋል፡፡ ፌደሬሽኑም በተጨባጭ ማስረጃ እርምጃ ለመውሰድ ክትትል እያደረገ ነው፡፡
      ከ18ሺ ብር እስከ 35ሺ ብር ዋጋ ያላቸው የተከለከሉ አበረታች መድሃኒቶችና ቅመሞች ኢትዮጵያ ውስጥ     በህገወጥ መንገድ እየተሰራባቸው ነው፡፡
     የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፤ከፌደራል ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር፤ ከኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከብሔራዊ የፀረ ዶፒንግ ኮሚቴ ጋር በመተባበር አገር አቀፍ ዘመቻውን ተያይዘውታል፡፡ ዓለም አቀፉ የፀረ ዶንፒንግ ቁጥጥር ተቋም ‹‹ዋዳ›› እና አይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ኢትዮጵያ ከዋነኞቹ ተጠርጣሪዎቹ አምስቱ አገራት ሩሲያ፣ ኬንያ ፣ ሞሮኮ፣ ቤላሩስና ዩክሬን ተርታ መመደቧን ከወር በፊት ያስታወቀ ሲሆን በሚቀጥሉት 5 ወራት አገሪቱ በብሄራዊ ደረጃ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በስፋት እንድታከናውን እንዲሁም በፌደሬሽን የተመዘገቡ አትሌቶች የሽንት እና የደም ምርመራ  በማካሄድ አስፈላጊውን የናሙና ውጤት እንዲቀርብ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። የአትሌቶች ስፖርት ስልጠና፣ ጤና፣ አመጋገብ፣ አበረታች ቅመሞችና መድኃኒቶች ከህግና ሥነ ምግባር አንፃር በሚል ርዕስ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ሰሞኑን የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በማዘጋጀት በአገር አቀፍ ደረጃ እንቅስቃሴዎቹን ጀምሯል፡፡ ከ60 በላይ የስፖርት ጋዜጠኞች፣ ከኦሮሚያ፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉልና ከአዲስ አበባ ከ/አስ/ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና በሥራቸው ከሚገኙ ክለቦች የተወከሉ የአትሌቲክስ ስፖርት አመራሮችና አሰልጣኞች፣ ከኢሚግሬሽን፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከጤና ጥበቃና ከመሳሰሉት ዘርፎች የተውጣጡ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮቹ ተሳትፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ አለባቸው ንጉሤ በሰጡት መግለጫ ስፖርቱን ከተጋረጠበት አደጋ ለማዳን በዓለም አቀፉ የፀረዶፒንግ ተቋማት የተሰጠውን አሰራሮችን የማስተካከል ዕድል በጋራ እንጠቀምበት በማለት ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ፌደሬሽናቸው ከአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ በቅርበት፤ በመረጃ ልውውጥና ምክክር እየሠራ መሆኑን የገለፁት ፕሬዝዳንቱ፤ የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌደሬሽን በካሜሮን ያውንዴ ከተማ አድርጎት በነበረው ጉባኤ ላይ ከአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ፕሬዝዳንት ሴባስቲያን ኮው ጋር ባደረጉት ውይይታቸው በተለይ በዶፒንግ ዙርያ ትኩረት በመስጠት መነጋገራቸውን አንስተዋል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በዓለም የስፖርት መድረክ ከፍተኛ ክብርና አስተዋፅኦ እንዳለው የተናገሩት ሴባስቲያን፤  ዓለም አቀፉ ተቋም አገሪቱ ዶፒንግን ለመወጋት በምታደርገው ዘመቻ ቴክኒካዊ ድጋፎች በመስጠት እንደሚያዝ ቃል መግባታቸውን አመልክተዋል፡፡ አይ. ኤ. ኤ. ኤፍ ለአትሌቲክስ ፌደሬሽን በላከው መግለጫ  በሪዩ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ እንደምትሳተፍ ማረጋገጫ መስጠቱን ያስታወቁት አቶ አለባቸው ፤ የኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድኑ ሙሉ ዝግጅቱንና ስልጠናውን በትኩረት እንዲቀጥል ያገዘ ውሳኔ ነው ብለዋል፡፡ በስልጠና፣ በህክምና፣ በአመጋገብ የተነሳ በርካታ አትሌቶች የአበረታች መድሃኒት ተጠቃሚነት መጠርጠር ምክንያት እየሆነ መምጣቱን የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ተገንዝቧል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ አደጋዎቹን ለመከላከል አስፈላጊ ትምህርቶችን በመስጠትና ግንዛቤ በመፍጠር እየሠራን የስፖርቱን  ጤናማነት ማረጋገጥ እንቀጥላለን ብለዋል፡፡
አትሌቲክስ ፌደሬሽኑ በሚያዘጋጃቸው አገር አቀፍ ውድድሮች የአበረታች መድሃኒት ምርመራዎችና ክትትሎች በስፋት እንደሚደረጉ ያስታወቁት በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ከፍተኛ የስፖርት ህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር አያሌው ጥላሁን ናቸው፡፡ በሚቀጥሉት አምስት ወራት በሚካሄዱት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ የታዳጊዎች ሻምፒዮና እና ሌሎች ውድድሮች ላይ የሽንት እና እንደአስፈላጊነቱ የደም ምርመራዎችን እንደምናከናውን ይታወቅ ያሉት ዶክተር አያሌው፤ ክለቦች፤ ክልሎች፤ ማናጀሮች፤ አሰልጣኞችና አትሌቶች በተጠንቀቅ ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በአትሌቲክሱ ማህበረሰብ የአበረታች መድሃኒት ምርመራዎች በአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ቁጥጥር ኢላማ ውስጥ በገቡ 28 ኢንተርናሽናል አትሌቶች ላይ ብቻ እንዳተኮረ የሚሰሙ ወሬዎች አግባብ አለመሆናቸው የገለፁት ዶክተር አያሌው ምርመራዎችና ክትትሎች በማናቸውም በፌደሬሽኑ በተመዘገበ አትሌት ላይ እንደሚደረግም ያገነዝባሉ፡፡ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ከፍተኛ የስፖርት ህክምና ባለሙያ ዶ/ር አያሌው ጥላሁን በአበረታች መድሃኒቶች ምርምርና ክትትል  ዙርያ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 5 ወራት ልታከናውናቸው የሚገቡ  10 ተግባራት በዝርዝር መቀመጡን ሲያመለክቱም፤ አይ.ኤ.ኤ.ኤፍ እና ዋዳ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ሪፖርት እየተደረገላቸው ግምገማ እንደሚያካሂዱም አብራርተዋል፡፡
በሚያዚያ እና ግንቦት ወር መጨረሻዎች የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍና የዋዳ ፕሬዚዳንቶች ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ እንጠብቃለን የሚሉት ዶክተር አያሌው፤ ለአገራችን የሚሰጡትን ታላቅ ክብርና ቦታ በመጠቀም ስፖርቱን ከአደጋ ለማውጣት የምንተጋበት ጊዜ ነው ብለዋል፡፡ በፀረ አበረታች መድሃኒት ዙርያ ኢትዮጵያ የምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ስኬታማነት ለአገሪቱ የስፖርት እንቅስቃሴ አዲስ ምዕራፍ ሊከፍት እንደሚችልም ዶ/ር አያሌው ጥላሁን ይገልፃሉ፡፡ ከ20 ሚሊዮን ዩሮ በላይ በጀት በመያዝ የሚሰሩ የስፖርቱ ህክምና ተቋማት በዓለም ከ24 አይበልጡም የሚሉት ዶክተሩ፣ ውጤታማ ስራዎችን በማካሄድ ከዓለም አቀፎቹ ተቋማት ዕውቅና ካገኘንበት የምስራቅ አፍሪካ ላቦራቶሪ በአዲስ አበባ ለመስራት የሚያስችል ዕድል እንደሚፈጠር ጠቁመዋል፡፡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን  ስር የሚወዳደር ማናቸውም አትሌት የዶፒንግ ምርመራና ክትትል በቀጥታ ይመለከተዋል በማለት ዶክተር አያሌው ጥላሁን ያሳስባሉ፡፡ ፌደሬሽኑ በአይቲ ቴክኖሎጂ የዳበረ የግንኙነት መረብ በመገንባት ላይ መሆኑን ሲያስረዱም፤ ሁሉም አትሌት ሙሉ መረጃው እንደሚመዘገብ፤ ምርምራ እና ክትትትል በአስፈላጊው ጊዜ  እንደሚከናወንበትም ዶክተር አያሌው ሲያመለክቱ፤ በሚቀጥሉት 3 ወራት ማናቸውም አትሌት የእያንዳንዱ ቀን ውሎውን በቀጥታ  የሚሞላበት ፎርም ተዘጋጅቶ በድረገጽ እንደሚቀመጥ እና በዚህ መንገድም መረጃዎችን መሰብሰብ የሚያስችል አሰራር እንደሚዘረጋም አስታውቀዋል፡፡  
ከመጀመሪያው ምርጥ እስከ ታዳጊ ደረጃ ያለ ሁሉም አትሌት ለአበረታች መድሃኒት ምርመራና ክትትል በማናቸውም ጊዜ ዝግጁ መሆን እንዳለበት ያሳሰቡት ዶክተር አያሌው ጥላሁን፤ ምርመራው የሽንት እና እንደአስፈላጊነቱም የደም እንደሚሆን ጠቁመው፤ የምርመራ ናሙናዎች በኳታር ዶሃ በሚገኘው ዓለም አቀፍ ላብራቶሪ ተልከው የሚገኙት የምርመራ ውጤቶች በአዲስ አበባው የብሄራዊ ፀረ ዶፒንግ ተቋም ናዶ ጽ/ቤት ተገምግሞ እና የፍርድ ውሳኔ ተሰጥቶበት ሂደቱ እንደሚያበቃ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡  በሚቀጥሉት 5 ወራት ከ350 በላይ አትሌቶች በአበረታች መድሃኒት ምርመራዎች እና ክትትሎች ሂደት እንደሚያልፉ ታውቋል፡፡ የአንድ አትሌት የሽንት ምርመራ እስከ 100 ዶላር ተጨማሪ የደምና ሌሎች ምርመራዎች እስከ 350 ዶላር ወጭ እንዳላቸው ዶክተር አያሌው ሲናገሩ፤ በብሔራዊ ደረጃ በዘመቻ በሚከናወነው የምርመራ እና ክትትል በአፍሪካ ደረጃ ከሰለጠኑ 4 የዶፒንግ ኦፊሰሮች እንደሚያሳትፍ ገልፀው በተሟላ መንገድ ለመንቀሳቀስ ከመንግስት ከ5-6 ሚሊዮን ብር በጀት እንደተፈቀደላቸው አስታውቀዋል፡፡
ዶ/ር አያሌው ጥላሁን የችግሩን አሳሳቢነት ለማመልከት በጠቀሱት መረጃቸው ሪንግ እና ግሉኮስ የተባሉ አበረታች ቅመሞችን አንዳንድ የህክምና ተቋማትና ባለሙያዎቻቸው በህገወጥና ምስጥራዊ መንገዶች አትሌቶችን መውጋት እንደቀጠሉ ሲሆን እስከ 5ሺ ብር እየተከፈለባቸው የሚፈፀሙት እነዚህ የህክምና ህገወጥ ተግባራት ላይ ተጨባጭ ማስረጃ በመያዝ አስፈላጊውን ርምጃ ለመድውሰድ የፌደሬሽኑ ፅህፈት ቤት  ክትትል እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። በተለያዩ አዲስ አበባ የከተማዋ ክፍሎች እንዲሁም በገጠር ከተሞች የተስፋፋው ይሄው ሁኔታ መረጃዎች እየተሰባሰቡ መሆናቸውን የገለፀው ፌዴሬሽኑ ተጨባጭ ማስረጃዎች ሲገኙ ርምጃ ይወስዳል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ጥቂት የማይባሉ አትሌቶች አበረታች መድሃኒቶችን በእንክብል፤ በመርፌ ፤ በምግብ እና በግሉኮስ እየወሰዱ ናቸው፡፡ ከ18ሺ ብር ጀምሮ እስከ 35ሺ ብር ዋጋ ያላቸው አበረታች መድሃኒቶች በየጫካው፤ በየሆቴሉ እና በተለያዩ ምስጥራዊ መገናኛ ስፍራዎች እየተሸጡ መሆናቸውን  መድረኩ የተናገሩት ዶክተር አያሌው ጥላሁን ከሚረዘሯቸው መድሃኒቶች   ሜሌዶየም፤ አናቦሊክስ ፤ቴስቴስትሮን፤ ስታኖዞሎንኖርዳራናይሎን፤ ዴፒ ቴስቴስትሮን ጠቅሰዋል፡፡ በአትሌቲክሱ ያሉ አበረታች መድሃኒቶች ፆታን እስከመቀየር የሚቆጠር ሃጥያት እንደሚያሰሩ፤ ለአዕምሮ ችግር የሚያጋልጡ፤ ለተለያዩ የውስጥ ደዌዎች የሚዳርጉ እና የማይድኑ ነቀርሳዎችን የሚያመጡ ናቸው በማለትም  ዶክተር አያሌው ጥላሁን ያሳስባሉ፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር ፕሬዝዳንት የሆነው አትሌት ስለሺ ስህን በበኩሉ አትሌቶች ለአበረታች መድሃኒት ምርመራና ክትትል ቅድሚያ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ያሳስባል፡፡ ማንም አትሌት አልመረመርም ማለት እንደማይችል ያስገነዘበው አትሌት ስለሺ ስህን፤ አለመመርመር የዶፒንግ ጥፋተኛ ነኝ ብሎ እንደማመን እንደሚቆጠር እና በአጠቃላይ አለመተባበር በራሱ የሚያስቀጣ ጥፋት መሆኑን አትሌቶች መገንዘብ እንዳለባቸው መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡   በአበረታች መድሃኒት ምርመራ እና ክትትል ዙርያ ክልሎችና ክለቦች አትሌቶቻቸውን በመከታተል እና በማሳወቅ መስራት እንዳለባቸው ያሳስበው  አትሌት ስለሺ ስህን፤ የአትሌቶች ማህበሩ ግንዛቤን በሚያሳድጉ፤ የመከላከል እርምጃዎችን በሚያጠናክሩ፤ የአትሌቶችን ስምና ክብር በሚጠብቁ እንቅስቃሴዎች ለመስራት ጥረት ማድረጉን ይቀጥላልም ብሏል፡፡ የአትሌቶች ማህበር መንቀሳቀስ ከጀመረ ገና 1 ዓመቱ እንደሆነ ጠቅሶ፤ ብዙ ክፍተቶች የሚፈጠሩትም ከልምድ ማነስ ሊሆን ይችላል በማለት ያስረዳው አትሌት ስለሺ ስህን፤ በአበረታች መድሃኒቶችና ቅመሞች ዙሪያ እየተዘጋጁ ባሉት መድረኮች የአትሌቶች ማህበር ድርሻ ከግማሽ በላይ መሆኑን በመጠቆም  ስፖርቱን ከገባበት አደጋ ለማውጣት ለግንባር ቀደምነት ሲንቀሳቀስ የሚጠበቅባቸው አትሌቶች ናቸው ብሏል፡፡  በኬንያ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ሁሉም ለአመራር ደረጃ ያሉ ሰዎች ከሀላፊነት ተነስተዋል ያለው የአትሌቶች ማህበር ፕሬዚዳንቱ፣ በኢትዮጵያ አመራር ይህ ችግር አለመኖሩ እንደሚያበረታታ ገልፆ፤   ለታዋቂ አትሌቶች በየጊዜው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲኖራቸው እየጠየቅን  ነው ብሏል፡፡
በኢትዮጵያ የሚገኘው የብሄራዊ ፀረ ዶፒንግ ቁጥጥር ኮሚቴ ጽ/ቤት በአዲስ መልክ ተደራጅቶ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች መጀመሩን የገለፁት ደግሞ የፅህፈት ቤት ሃላፊውና  የህግ ባለሙያው አቶ መንግስቱ አበበ ናቸው። በህጋዊና ስነምግባራዊ ጉዳዮች አገር አቀፍ ግንዛቤዎችን በመፍጠር መንቀሳቀስ ጀምረናል ያሉት የህግ ባለሙያው፤ ኢትዮጵያ ህጐችና ደንቦችን በተመለከተ በዩኔስኮ የፀደቀ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሸን በ1999 ዓ.ም እንደተቀበለች በአገሪቱ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ በአንቀጽ 526 በ1997 ዓ.ም በአዋጅ መደንገጉን በመጥቀስ ስራዎችን በዚህ ህግ ለመስራት መደራጀታቸውን አመልክተዋል፡፡ በዶፒንግ ጥፋት የሚጠየቁ በወንጀል፣ በፍትሐብሔር፣ ህገወደንቦች እንደሚጠየቁ ያብራሩት አቶ መንግስቱ ባለድርሻ አካላት በመከላከል ርምጃ የሚንቀሳቀሱ ባለድርሻ አካላት  የህጉን ትንታኔ መገንዘብ አለባቸው ብለዋል፡፡ አቶ መንግስቱ አበበ እንዳስገነዘቡት የዶፒንግ ጥፋት በተጠቃሚው ላይ ከሚያስከትለው ቅጣት በተጨማሪ አበረታች ቅመሞቹንና መድሃኒቶቹን ያመረተ ወደ አጭር ውስጥ ያስገባ፣ የሸጠ፣ ያከፋፈለ፣ በባለሙያነት ያዘዘ እንዲሁም በህገወጥ መንገድ በድርጊቱ የተሳተፈ ሁሉ በአገሪቱ የወንጀለኛ፣ የፍትሐብሔርና አስተዳደራዊ ህግ መሠረተ ቅጣት እንደሚተላለፍበትም ገልፀዋል፡፡   
የዶፒንግ ቅሌትና ምርመራው ከራሽያና ኬንያ በኋላ  ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ የሚታወቅ ሲሆን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን 9 አትሌቶች በዶፒንግ ተጠርጥረው  በከፍተኛ ደረጃ ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑ  ከ2 ወራት በፊት ካሳወቀ በኋላ በአገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ የመካላከል ርምጃዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር መንቀሳቀሱን እንደቀጠለ ነው፡፡  የዶፒንግ ጥፋት ተጠርጣሪ አትሌቶች ማንነት ለማስታወቅ ዓለም አቀፍ ደንብ አይፈቅድልንም የሚለው አትሌቲክስ ፌደሬሽን በብሄራዊ ቡድን ደረጃ የተወዳደሩ አለመሆናቸውን የጠቆመ ሲሆን፤ የዓለም አቀፉ የፀረ ዶፒንግ ተቋም ‹‹ዋዳ›› እና የአለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር  ምርመራዎች ተጠናቅቀው ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ የአትሌቶቹ ማንነት በይፋ ይገለፃልም ብሏል፡፡
በዶፒንግ ተጠቃሚነት የተጠረጠሩት አትሌቶች ጥፋተኝነታቸው ከተረጋገጠ ከዓለም አቀፍ ውድድሮች ከ2 እስከ 4 ዓመታት የመታገድ ቅጣት የሚጠበቅባቸው ሲሆን አትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ይህን ቅጣት ከማፅናት ባሻገር በአገሪቱ ህገ ደንብ ተጨማሪ እገዳ እና የእስር ቅጣቶችን ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡
በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ‹‹አይ.ኤ.ኤ.ኤፍ› እና በዓለም አቀፉ የፀረ ዶፒንግ ኤጀንሲ ‹‹ዋዳ›› በዶፒንግ ጥፋት እግድ ከተጣለባቸው አገራት ከፍተኛውን የአትሌቶች ብዛት ያስመዘገበችው  57 ስፖርተኞች በቅጣት የታገዱባት ራሽያ ስትሆን 43 የቱርክ ፤ 38 የህንድ ፤ 14 የኬንያ፤ እያንዳንዳቸው 11 የሞሮኮ እና የአሜሪካ ስፖርተኞች  በቅጣት በመታገድ ተከታታይ ደረጃ ይወስዳሉ፡፡ የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች በሚኖሩባቸው አገራት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ  ጋር በተያያዘ ቀይ የደም ሴሎቻቸው መጠን ከፍ ያለ ስለሆነ  አበረታች መድሃኒቶቹን ቢጠቀሙም ባይጠቀሙም በውጤታቸው ላይ ለውጥ አያመጣም የሚል መላምት ነበር፡፡ በኬንያ በተካሄደ ጥናት ግን ይሄን መላምት የሚያፈርስ ውጤት ተገኝቷል፡፡ ይህም በኢትዮጰያ እና ኬንያ አትሌቶች ላይ በትኩረት ምርመራዎች እንዲካሄዱ ምክንያት ሆኗል፡፡ አበረታች መድኀኒቶች መጠቀም በሚከለክሉ ርምጃዎች ባለፉት ሶስት ዓመታት ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ተቋማት ከፍተኛ ትኩረት በማድረጋቸው በርካታ ስፖርተኞች በጥፋተኝነት ከውድድር እየታገዱ እና የሜዳልያ፤ የብር እና የሪኮርድ ውጤቶቻቸው እየተሰረዘባቸው ይገኛል፡፡

Read 3052 times