Saturday, 09 April 2016 10:35

ከፕሮስት ሕመም ማምለጥ ይቻላል?

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(3 votes)

 ከባለቤ ጋር መስማማት አቅቶናል። እኔ በእድሜዬ የ52 አመት ሰው ነኝ። ይሄ ፕሮስት የሚባል ሕመም ሽንት መሽናት ከልክሎኝ ስሰቃይ ከቆየሁ በሁዋላ ወደሐኪም ቤት ሄጄ አሁን ተሸሎኛል። ነገር ግን ባለቤ በሽንት ምጥ ስሰቃይ ፣ቶሎ ቶሎ ወደመታጠቢያ ቤት ስሄድ ፣ እና ሽንም መቅላቱን ከተመለከተች በሁዋላ አንተማ በሽታ ይዞሀል። ከዚህ በሁዋላ እኔ ልጆቼን ማሳደግ እንጂ ሌላ ፍላጎት የለኝም ብላ ይኼው በአንድ ቤት ተቀምጠን ነገር ግን ተለያይተን እንኖራለን።
እኔ ግን አንድ ጥያቄ አለኝ።
የወንዶች የወሲብ አካልና የሽንት መሽኛ አፈጣጠር ምን ይመስላል? ይሄ ያመመኝ በሽታስ ከወሲብ ፍላጎት ጋር ይገናኛልን? ስሜን ደብቁልኝ።
ባለፈው እትም ከዶ/ር ኢብራሂም መሐመድ ጋር ስለፕሮስት እጢና ካንሰር የጀመርነውን ማብራሪያ ቀጣይ ለዚህ እትም ማለታችን ይታወሳል። ዛሬም ጠያቂያችን ስለፕሮስት የላከሉንን ጥያቄ ግልጽ የሚያደርግ ተጨማሪ ሀሳብ አክለን ለአንባቢ አቅርበናል።  
የሽንት መሽኛ እና የወሲብ አካል አፈጣጠር፡-
ሽንት የሚፈጠረው ኩላሊት ውስጥ ነው። ኩላሊቶቻችን የሚገኙት ከሆዳችን ውስጥ ከወገባችን ትንሽ ከፍ ብሎ ከአከርካሪ አጥንት ጎን በግራና በቀኝ በኩል ነው። በእነዚህ ኩላሊቶች ውስጥ ሽንት ከተፈጠረ በሁዋላ ሽንቱ urethras በሚባሉ ቱቦዎች ወደ ፊኛ ይገባል። ከፊኛ ቀጥሎ ደግሞ urethra የሚባል ሌላ ቱቦ አለ። በዚህ ቱቦ በኩል ሽንት ከሰውነት ይወጣል። ሽንት ፊኛ ውስጥ ከተጠራቀመ በሁዋላ በመውጫው በኩል ላይ prostate የሚባል እጢ አለ። በተጨማሪም ከፕሮስት እጢ መሀል ሰንጥቆ የሚወጣ urethra የሚባል ሽንት የሚወጣበት ቱቦ አለ። ይህ በውጭ በኩል ያለው external ወይም ደግሞ penile urethra ይባላል። በውስጥ በኩል ደግሞ prostate urethra ይባላል ። እንግዲህ ይህ prostate የተባለው እጢ ሽንት ከፈኛ ሲወጣ አቅፎ የሚይዝ ነው።
የወሲብ አካል የሚባለው ከ prostate ጀምሮ urethra ጨምሮ ያለው የሽንት መሽኛው ክፍል ነው። የወሲብ አካል ተብለው የሚጠቃለሉት ከውጪ ያሉትን ፍሬዎች ጨምሮ ከውስጥ በኩል ደግሞ urethra እንዲሁም ወደ ውጭ በወንድ ብልት የሚያልፈው urethra external ወይም ደግሞ penile urethra የሚባለው ሁሉ ነው። የሽንት መሽኛ አካላት ከወሲብ አካል ጋር የሚገናኙት የሽንት መውጫው አካባቢ ብቻ ነው።
ማንኛውም ሰው ጤነኛ የሆነ የሽንት አሸናን አለው የሚባለው ሽንቱን ሲሸና ሕመም የማይሰ ማው ከሆነ እንዲሁም የሽንት መጠኑ በቂ ከሆነ ማለትም በአማካኝ በሀያ አራት24ሰአት ጊዜ ውስጥ ቢያንስ ከ800ስምንት መቶ ሲሲ ያላነሰ ሽንት መሽናት ሲችል ነው። በእርግጥ የሽንት መጠን ከስምንት መቶ ሲሲ በላይም ሊሆን ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ሽንቱ ሲሸና የማጣ ደፍ ሁኔታ ሲኖር የሽንት መቅላት ወይንም እንደደም መምሰል ሲከሰት እንዲሁም መጠኑ ተገቢውን ብዛት ማያክል ከሆነ ጤነኛ ያልሆነ የሽንት አሸናን አለ ያሰኛል።
   ዶ/ር ንዋይ ተክሌ አስቀድመው ከሰጡት መረጃ
ዶ/ር ኢብራሂም መሐመድ ዩሮሎጂስት ከሀያት ሆስፒታል የፕሮስት እጢን እብጠትን እና ካንሰር ለማስወገድ የሚሰጠው ሕክምና ምን ይመስላል? ከወሲብ ፍላጎት ጋር በተገናኘስ? ለመሆኑስ ከፕሮስት ማምለጥ ይቻላል? የሚሉትን ጥያቄዎች እንደሚከተለው አብራርተዋል።
ጥ/ የፕሮስት ሕክምናው ምን ይመስላል?
መ/ የፕሮስት ካንሰር ሕክምና የሚሰጠው በተለያየ መንገድ ነው። አንዱ በኦፕራሳዮን ሲሆን ኦፕራሲዮኑ በተለያዩ መንገዶች ማለትም ተከፍቶ ወይንም ሳይከፈት የሚሰራ ነው። ሌላው ደግሞ በጨረር የሚሰጥ ሕክምና ነው። ሌሎች ዘመናዊ የሆኑ ሕክምናዎችም እየመጡ ነው። ፕሮስቱ ኦፕራሲዮን በሚደረግበት ጊዜ በምን መንገድ ነው? እንዳለ ነው የሚወጣው?ወይንስ በከፊል ነው? ከቀዶ ሕክምናው በሁዋላስ ምን ይከተላል? የሚለውን ስንመለከት ብዙ ጊዜ ካንሰር ከሆነ እንዳለ የሚወጣ ነው የሚሆነው። እንዲያውም ከፕሮስቱም አልፎ በአካባቢው ባሉ አካላት ማለትም ሁለት የወንድ የዘር ፈሳሽ ከረጢቶችን ጨምሮ በአካባቢው ያሉ ነገሮች ተጨምረው እንዲ ወገዱ ይሆናል። በተጨማሪም ፕሮስት ሲወጣ በውስጡ ያልፋል የተባለው የሽንት ቱቦ ጭምርም የሚወጣበት ሁኔታ አለ። ስለዚህ ኦፕሬሽኑ በሽታውን ማውጣት ብቻ ሳይሆን ያንን አካባቢ መልሶ የመጠገን ስራ ነው የሚሰራው። ምክንያቱም ከሕክምናው በሁዋላ ታካሚው ሽንቱን በደንብ መሽናት እና መቆጣጠር እንዲችል ነው።
ጥ/ ፕሮስት ካንሰር በቀዶ ሕክምና ከተሰራ በሁዋላም ይሁን አስቀድሞ ከግብረስጋ ግንኘነት መቻል አለመቻል ጋር ይገናኛልን?
መ/ ፕሮስት ካንሰር እና ፕሮስት እብጠት የተለያዩ መሆናቸው መረሳት የለበትም። እብጠቱ ብዙም የከፋ ችግር የማያስከትል እና በቀላሉ ሊታከም እንደሚችል ከግንዛቤ ሊገባ ይገባል። የወሲብ ፍላጎትን የማወክ ባህርይም የለውም። ካንሰሩ ግን ከመታከሙ በፊትም ቢሆን የግብረስጋ ግንኙነትን የማወክ ባህርይ ይኖረዋል። በተረፈ ግን ከቀዶ ሕክምናው በሁዋላ የግብረስጋ ግንኙነት ማድረግ ያለመቻልን ሊያስከትል እንደሚችል መጠበቅ ይገባል። ይህ ደግሞ ሆን ተብሎ ሳይሆን በሽታው በሚፈጥረው ጉዳት የተነሳ ያንን ለማስተካከል ከምንም በላይ ደግሞ ካንሰሩ በተለያዩ አካባቢዎች ተሰራጭቶ ሕይወትን እንዳይጎዳ ሲባል በሚወሰደው እርምጃ በብልት አካባቢ ያሉ የተለያዩ አካላት ከበሽታው ጋር አብረው እንዲወገዱ ስለሚደረግ ነው። በእርግጥ ሁሉም የፕሮስት ካንሰር የሚያወጡ ሰዎች ተመሳሳይ ቀዶ ሕክምና ስለሚደረግላቸው ቀለል ያለና በዙ ሪያው ያሉ የተለያዩ አካላትን ሳይጨምር ሕመሙ ከውስን ቦታ የሚወገድላቸው ሰዎች ስለሚኖሩ እነርሱ ከሕክምናው በሁዋላ የወሲብ ችግር ይኖርባቸዋል ማለት አይቻልም። ስለዚህ ጉዳቱ እንደህመሙ ደረጃ ለያያል።
ጥ/ የበሽታው ባህርይ እንዴት ይገለጻል?
መ/ በአለም ላይ የፕሮስት ካንሰርን በሚመለከት የተለያዩ አንቱ የተባሉ ማእከላት እና በምርምር ስራ የተካኑ ባለሙያዎችን ጨምሮ ሁሉም የማይስማሙበት የሚለያዩባቸው ብዙ ነገሮች አሉ።የዚህ ምክንያቱም የፕሮስት ካንሰር በባህርይው ሲታይ አንዳንድ ጊዜ ካንሰሩ በአንድ በሽተኛ ላይ ምልክት ሰትቶ ሕመሙ መኖሩ እስኪታወቅ ድረስ ረዥም ጊዜ የሚወስድ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በጣም ፈጣን በሆነ መንገድ የሚታወቅበት ሁኔታ አለ። ይህንን በሚመለከትም በአሜሪካ አገር ጥናት ተደርጎ የተገኘ ውጤት አለ።  በእድሜያቸው ከ85/አመት ገደማ የማያንሱ በሌላ ሕመም ምክንያት የሞቱ  ወንዶች ላይ ምርምር ሲደረግ አብዛኛዎቹ ላይ የፕሮስት ካንሰር ሕመሙ  ተገኝቶባቸዋል። ነገር ግን ሰዎቹ የፕሮስት ካንሰር ሕመም እንዳለባቸው  ወይንም በዛ ምክንያት ህመም ደርሶባቸው አያውቁም። የሞቱትም በሌላ ሕመም  ነው።
ጥ/ ሕክምናው በአገር ውስጥ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
መ/ የፕሮስት ካንሰር ሕክምናም ሌላው አወዛጋቢ ጉዳይ ነው። አንድ ሰው ፕሮስት ካንሰር ሲይዘው በዚህ መንገድ ይታከም...የሚል በመመሪያ በፐሮቶኮል ደረጃ ከስም ምነት የተደረሰበት ሁኔታ የለም። ታካሚው እንዳለበት ሁኔታ እንደሚኖርበት የኑሮ ደረጃ የሚለያይ ነው።ሕክምናውን በሽተኛው የመጣበት የሕመም ደረጃም አንዱ ከአንዱ የሚለይበት ነው። ሕክምናውን በሚመለከት ለምሳሌ በእኛ ሀገር የጨረር ሕክምናው አለ ከሚባል የለም ቢባል ይሻላል። ምክንያቱም ሕክምናው የሚሰጠው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ ነው። በአገር ውስጥ በየትኛውም ሆስፒታል የጨረር ሕክምናው አይሰጥም።
 በታካሚዎቹ በኩል ደግሞ አብዛኞቹ ቆይተው ስለሚመጡ ወይንም በቀጥታ ሕመሙን ሊያውቅላቸው ከሚችል ባለሙያ ዘንድ ስለማይቀርቡ ማዳን የማይቻልበት ደረጃ ላይ ይደረሳል። ስለዚህም እድሜ መቀጠያ ወይንም ሕመም መቀነሻ ወደሆኑት ሕክምናዎች የግድ ይገባል። በሌላ በኩል ደግሞ quality of life የሚባል ነገር አለ። አንድ ሰው ሕመም ደርሶበት ሕክምና ሲደረግለት ሕክምናው በሽታውን ማስወገድ ብቻ ሳይሆን በሰውየው የወደፊት ሕይወት ላይ እንደ እድሜው ወይንም ኑሮው ችግር የሚያመጣበት ወይንም ደስታውን የሚነፍገው ከሆነ የሚታይበት ደረጃ አለ።ስለዚህ የበሽተኛውን ምርጫ መጠበቅና ከዛ ባለፈም ከቤተሰብ ጋር መመካከር ይገባል።
ጥ/ ከፕሮስት ሕመም ማምለጥ ይቻላል?
መ/ ከፕሮስት ሕመም ማምለጥ ይቻላል? የሚለውን መመለስ የሚቻለው የሚመጣበት ምክንያት ሲታወቅ ነው። ከሕመሙ ለማምለጥ ይህን ማድረግ አለብኝ ወይንም ይህን ማድረግ የለብኝም የሚባል ጎልቶ የሚታይ ነገር የለም። ሆኖም ግን ለፕሮስቱም ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የሆኑ ራስን በመጠበቅ ጉዳይ ሁሉም ሰው ኃላፊነት ሊሰማው የሚገባ ሲሆን እንደ ሲጋራ አልኮሆል የመሳሰሉትን መጠቀምን ማስወገድ ፣የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማድረግ ፣ውፍረትን መከላከል፣ በህክምና ጤንነትን በተወሰነ ጊዜ የመፈተሽ ልምድን ማካበት የመሳሰሉትን ማድረግ ይጠቅማል። በአጭሩ ከፕሮስት ሕመም ማምለጥ አይቻልም። ከመጣ ይመጣል። እንዳይመጣ ተጋላጭነትን መከላከል ግን ይገባል።

Read 6597 times