Saturday, 16 April 2016 11:10

እረኛውና ጠቦቷ

Written by  ድርሰት፡— አዚዝ ኔሲን ነፃ ትርጉም፡— ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(9 votes)

(ባለፈው ሳምንት ከወጣው ‘ራሴን አጠፋሁ’ ከሚለው የአጭር ልብ ወለድ መድብል የተወሰደ።)

    ከዕለታት አንድ ቀን በምሥራቅና ምዕራብ መስቀለኛ መንገድ፣ ለሰሜን ቀረብ ብሎ ከደቡብ ደግሞ ትንሽ ራቅ ብሎ አንድ እረኛ ይኖር ነበር፡፡ በርካታ በጎችና ጥቂት በግ ጠባቂ ውሾችም ነበሩት። ይህ እረኛ ሁላችንም ከምናውቃቸው እረኞች የተለየ ነው፡፡ በጣም ጨካኝና ድንጋይ ልብ ነበር፡፡ ለሌሎች አንዳችም ሀዘኔታ የለውም፡፡
መቼም ቢሆን ሌሎችን አያዳምጥም፡፡ ሌሎቹ እረኞች በሙሉ ዋሽንት ሲይዙ ይህኛው ሁልጊዜ የሚይዘው ዱላና ፊሽካ ነው፡፡ በጎቹን ወተት ያልባቸዋል፣ ፀጉራቸውን ይሸልትና አንጀታቸውን ይሸጣል፡፡ በጠጣቸውን ይሰበስባል፣ ቆዳቸውን ይገፋል፣ በሥጋቸው ይደሰታል፣ አጥንታቸውን ይጠቀምበታል፣ መቅኒያቸውን ያወጣል፣ በአጭሩ ምስኪኖቹ እንስሳት ሊያቀርቡ የሚችሉትን ሁሉ ይወስድባቸዋል፡፡
እረኛው በጎቹን በቀን ሦስቴ ጠዋት፣ ቀትርና ማታ ያልባቸዋል፡፡ ሆኖም ዘወትር ብዙ ወተት ባለመስጠታቸው ያጉረመርማል፡፡ በጣም ገብጋባ ከመሆኑ የተነሳ ተጨማሪ ለማግኘት ያለውን ጉጉት ምንም አያረካውም፡፡ በጎቹ ከጡታቸው ጫፍ ከወተት ይልቅ ደም መውጣት እስኪጀምር ያልባቸዋል፡፡ ከባዱ ህመም ዓይኖቻቸውን በዕንባ ሲሞላው ወይንም ደም ሲፈሳቸው በሰቆቃ ሲጮሁ ርህራሄ የሌለው እረኛ ጭንቅላታቸውንና አጥንት የሆኑ ጀርባዎቻቸውን በዱላ ይነርታቸዋል፡፡
“እናንተ ክፉ ፍጡራን!” ሲል ያመራል፡፡ “ከደረቁ ቆዳዎቻችሁ የመጨረሻዋ ጠብታ ወተት እስክትወጣ ድረስ አልተዋችሁም፡፡”
ከዱላውና ፊሽካው የማይለየው ክፉ ገብጋባ እረኛ፣ በጓ ከሀያ ኪሎ በላይ ክብደት ባይኖራትም ቢያንስ አርባ ሊትር ወተት ማለብ ይፈልጋል፡፡
የእረኛው ክፋት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደረሰ፡፡ የበጎቹ ቁጥርም በየቀኑ እየተመናመነ ሄደ። የሞቱት ዕድለኞቹ እሱ ከሚያደርስባቸው ስቃይ ዳኑ፡፡ በህይወት የቆዩት ዕድለ ቢሶቹ ግን ለሞቱት ዘመዶቻቸው ኃጢያቶች ከባድ ዋጋ መክፈል ነበረባቸው፣ ንፉጉ እረኛ በሞቱት በጎች ምክንያት ያጣትን እያንዳንዷን ሳንቲም በህይወት ካሉት በጎች ለማግኘት ከእሱ ጭካኔ አንዲት በግ ብቻ እንኳን ብትቀር ከሙሉ መንጋው የሚያገኘውን ወተትና ፀጉር ከዚቹ ከአንዷ ለማግኘት ይሞክራል። እረኛው የበጎቹ ቁጥር በመመናመኑ፣ የሚሰጡት ወተት በከፍተኛ ደረጃ በመቀነሱ፣ እበታቸውም በቀድሞው መጠን ባለመምጣቱ መበሳጨት ጀመረ። አንዳንዴ ልክ እንደ ለየለት ዕብድ ያደርገው ነበር፡፡ ዱላውን እያወዛወዘና ውሾቹን ወደፊት አስቀድሞ በጎቹን በኮረብታዎች ያሳድዳቸዋል፡፡
መንጋ ውስጥ አንዲት ትንሽ ቀጫጫ ጠቦት ነበረች፡፡ እረኛው ይህችን ትንሽ ጠቦትም ቢያንስ የሀያ ላሞች ወተት እንድትሰጥ ይጠብቅባት ነበር። ግን አንዲት ጠቦት እንዴት አድርጋ ነው ወተት የምትሰጠው! አንዲት ጠብታ እንኳን ማግኘት ያቅተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ያበግነዋል፡፡
አንድ ቀን በጣም ከመናደዱ የተነሳ ምስኪኗን ጠቦት ያለርህራሄ ይቀጠቅጣት ጀመር፡፡ ጠቦቷ ትንሽና አቅመቢስ ከመሆኗ የተነሳ ከጌታዋ ጭካኔ ማምለጥ አልቻለችም፡፡ ሆኖም አለንጋውን መቋቋም ሲያቅታት ክፉውን ጌታዋን ለመነችው። “የተወደድከው እረኛ! እኔ ትንሽዬ ጠቦት ነኝ። ትንንሽ እግሮቼ የተፈጠሩት ለመራመድ እንጂ ለመሮጥ አይደለም፡፡ እንደ በጎቹ ካንተ ሮጬ ማምለጥ አልችልም፡፡ እንዳታባርረኝና እንዳትደበድበኝ በቅንነት እጠይቃለሁ፡፡” እረኛው ግን የጠቦቷን ቃላት አልተረዳላትም፡፡
እረኛው፣ በጎቹ የሞቱት በከፍተኛ ጥላቻ መሆኑንን፣ ሊጎዱት እንዳቀዱና ክህደት እንደፈፀሙበት አመነ፡፡ “እነኚህ የተረገሙ ፍጡራን እኔ እከላከልላቸው የነበርኩትን ሰው ክህደት ፈፅመውብኛል፡፡”
እረኛው ጠቦቷን ይመለከትና ንዴቱ አናቱ ላይ ይወጣበታል፡፡ ምስኪኗ ጠቦት እረኛውንና ዱላውን ከመፍራቷ የተነሳ አብዛኛውን ጊዜ ሽሽት ላይ ነበረች፡፡ በተቻለ መጠን ከእረኛው ጋር ርቀቷን ትጠብቃለች፡፡ ራሷን ችምችም ባሉ ተዳፋቶች ውስጥ ለመደበቅ ቀጥ ያሉ ዓለታማ ኮረብታዎችን ትወጣለች፡፡ በዝግታና ደረጃ በደረጃ መሮጧ የሸሆናዎቿን ቅርፅ ለወጠው። ቅልጥሞቿ ባልተለመደ ሁኔታ ቀጫጭንና ረጅጅም ሆነው ከበፊቱ ፈጥና እንድትሮጥ አስቻላት፡፡
አሁን በትንሹም ከእረኛው ማመለጥ ቻለች፡፡ ሆኖም ብልጡ እረኛ በበለጠ ፍጥነት እንድትሮጥ አደረጋት፡፡ ስለታማዎቹ ዓለቶችና ቋጥኞች ሸሆናዋን ሰነጠቁት፣ ከጊዜ በኋላም ሹል ጥፍሮች ወዳሏቸው መዳፎች ተለወጡ፡፡ ሆኖም ክፉው እረኛ አልፎ፣ አልፎ እየያዛት ልቧ እስኪጠፋ ይደበድባታል። ጠቦቷም እሪታዋን ታቀልጠዋለች፣ በአሳዛኝ ሁኔታም ትለማመናለች፡፡
“የተከበርከው ጌታዬ! እኔ ጠቦት ነኝ፡፡ ይህንን ቀላል እውነታ ተረዳልኝ፡፡ ጠቦት ነኝ፣ ጠቦትም ከጠቦትነት ወደሌላ መቼም ሊለወጥ አይችልም፡፡”
እረኛው ግን የጠቦቷን ቃላት አልተረዳላትም፡፡
የእረኛውን ዱላ በመፍራት በተደጋጋሚ መሮጧ የጠቦቷን ሆድ አቀጠነው፡፡ ቁመቷ አደገ፡፡ ቀስ በቀስ ፀጉሯ እየረገፈ በትንሽ ግራጫ ቡኒ ፀጉር ተተካ። እረኛው ጠቦቷን መያዝ እያቃተው መጣ። በግ ጠባቂ ውሾቹም ሊያገለግሉት አልቻሉም፡፡ ሆኖም ጮሌው እረኛ ከስንት አንዴ ጠቦቷን እየያዘ ከበፊቱ በባሰ ይደበድባታል፡፡ ትንሽዬዋ ጠቦት የግዷን ትጮሀለች፡፡
“የተከበርከው ጌታዬ! እኔ ጠቦት ነኝ፣ ምንም ሳልሆን ጠቦት ብቻ!” ብላ ለመጮህ ትገደዳለች፡፡
እረኛው ግን የጠቦቷን ቃላት ሊረዳላት አልቻለም፡፡
ሳታስበው የመያዝ ፍርሀት ጠቦቷ አደጋን ከሩቅ ለማወቅ ጆሮዎቿን በተሻለ መጠቀም ጀመረች። ብዙም ሳይቆይ ጆሮዎቿን በሁሉም አቅጣጫ ማንቀሳቀስ ለመደች፡፡ ጆሮዎቿ በቅርፅ ሲለወጡ ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ አሁን በጣም ንቁ በመሆናቸው ከረጅም ርቀቶች የእግር ኮቴዎችን ድምፅ መለየት ቻለች፡፡ ይህ ማምለጫ ጊዜ ይሰጣታል፡፡ እንዲህም ሆኖ የእረኛው ርህራሄ የለሽነት ሰለባ መሆኗን ቀጠለች፡፡ ጠቦቶች በምሽት በደንብ ማየት እንደማይችሉ እረኛው ያውቃል። ስለዚህ ምስኪኗ ሰለባውን በምሽት ድንገት ያጠምዳት ጀመር፡፡ ከያዛትም ከፍተኛ ድብደባ ይፈፅምባታል፡፡ ጠቦቷም ከመጮህና ከማልቀስ ሌላ አማራጭ የላትም፡፡
“እባክህ የተወደድከው ጌታዬ! እኔ ጠቦት ነኝ፡፡ ከጠቦት ወደሌላ ልትቀይረኝ በመሞከር ጉልበትህን እያባከንክ ነው፡፡”
እረኛው ግን የጠቦቷን ቋንቋ አልተረዳላትም፡፡
የመደብደብ ፍርሃትና በምሽት የመያዟ አደጋ ጠቦቷን ማታ፣ ማታ ቁጭ ብላ እንድታድር አስገደዳት። ሌሊቱን ሙሉ እንቅልፍ በዓይኖቿ ሳይዞር ታድር ነበር፡፡ ይህም ዓይኖቿን አተለቃቸው። ብዙም ሳይቆይ እንደ ፍም ቀሉ፡፡ እንደሚንቦገቦጉ የክብሪት እንጨቶች የሚያበሩት ዓይኖቿ በጨለማም ሁሉን ነገር በግልፅ ማየት አስቻሏት፡፡
ለጠቦቷ እንቅስቃሴ ገና ያልተላቀቀው አንገብጋቢ መሰናክል ጭራዋ ነበር፡፡ ለማምለጥ በፍጥነት በምትሮጥበት ጊዜ እግሮቿ መሀል ይወሸቃል፡፡ ጭራ ባይኖራት ተመኘች! ይህ ምኞቷም ብዙም ሳይቆይ እውን ሆነ፡፡ በየጊዜው በፍጥነት መሮጧ የጭራዋን ስብ አቀለጠው፡፡ በጣም ልትሮጥ በፈለገች ጊዜም እንደ አለንጋ ቀጥ የሚል ቀጭን ረጅም ጭራ ሆነላት፡፡ ጠቦቷ አሁን ከምን ጊዜም በበለጠ ፍጥነት መሮጥ ቻለች፡፡ ግን ምንም ብታደርግም ሁልጊዜ ከሚያሳድዳትና ድንጋይ እየወረወረ ከሚመታት እረኛ ጨካኝ እጆች ማምለጥ አልቻለችም፡፡
ዘወትርም እረኛውን ምህረት ትለማመናለች፡፡
“የተከበርከው ጌታዬ! እኔ ጠቦት ነኝ። የተወለድኩት እንደ ጠቦት ነው፡፡ መሞት የምፈልገውም እንደ ትልቅ በግ ሆኜ ነው፡፡ አስገድደህ ምን ልታደርገኝ ነው የምትሞክረው? ለምን?”
በመጨረሻ ጠቦቷ ለጌታዋ ጭካኔ ምላሽ መስጠት ጀመረች፡፡ በጨለማ ጭር ያለ ቦታ …. በአዲስ መዳፎቿ እረኛው ላይ ቅጣት ለመሰንዘር አታመነታም፡፡ የተጫጫሩ እጆቿን እረኛውን ይበልጥ አጦዘው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ጥርሶቿን ሁሉ በጌታዋ ላይ ለመጠቀም ትሞክር ነበር፡፡ ሆኖም የጠቦቷ ሰፊ አገጭ ጥርሶቿን በሚገባ ለመጠቀም የምታደርገውን ሙከራ አስቸጋሪ አደረገው፡፡፣ ብዙም ሳይቆይ ሰፊ አገጯ መጥበብ ጀመረ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ጥርሶቿ እየተለቁ፣ ምላሷም እየረዘመ ሄደ። አሁንም መጮኋን ብትቀጥልም ድምጿ የጠቦት አይመስልም፡፡ ተደጋጋሚ ጩኸትና ልመና ድምጿን ሻካራና ጎርናና አደረጉት፡፡
አሁን እረኛው ውሾቹ ጠቦቷ ላይ ጥቃት እንዲሰነዝሩና እንዲያጠቋት ይገፋፋቸው ጀመር። ሆኖም ጠቦቷን እንደ በፊቱ በቀላሉ ሊቋቋሟት አልቻሉም፡፡ ጠቦቷ በመዳፎቿ ከበድ ባለ አንድ ምት አንዱን ውሻ ከመሬት ስትደባልቀው ሌላውን አንገቱን ትነክሰዋለች፡፡
ይህ ሁሉ እረኛውን ያሳብደዋል፡፡ እንደምንም ጠቦቷን በያዛት ጊዜ ዱላው ይበልጥ ርህራሄ የለሽ ሆነ፡፡
ጠቦቷ ማጉረምረም በመሰለ ድምፅ ለአለቃዋ ማስጠንቀቂያዎች መስጠት ጀመረች፡፡
“በቃህ እረኛ! አለበለዚያ ቀኑ ይፀፅትሃል፡፡”
እረኛው ግን የጠቦቷን ማስፈራሪያ አልተረዳላትም፡፡
በአንድ የክረምት ማለዳ ነበር፡፡ ሁሉም ነገር በወፍራም የበረዶ ግግር ተሸፍኗል፡፡ ማለዳ ተነሳ፡፡ በህይወት ከቆዩት ጥቂት በጎች የአሥር ላሞች ወተት ለማለብ በማቀድ ወደ በረቱ ለመሄድ እየተዘጋጀ ነበር፡፡ በእጁ እህል ውሀ የማያሰኝ ዱላ እንደያዘ ከቤቱ ወጣ! ምን ቢያይ ጥሩ ነው? በረዶው በቀያይ የደም ፍንጥቅጣቂዎች ተዥጎርጉሯል፡፡ የበጎቹ ጥምብ ተረፍርፏል፡፡ ሁሉም ተበጫጭቀዋል፡፡ በአንድ ወቅት በጣም ትልቅ ከነበረ መንጋ አንድም በህይወት የተረፈ በግ አይታይም፡፡
አንድ እጁን ከዓይኖቹ በላይ አድርጎ እረኛው ሩቅ አሻግሮ ሲመለከት ጠቦቷን አያት፡፡ በግዙፍ ሰውነቷ እግሮቿን ወደፊት ዘርግታ በረዶው ላይ ተጋድማለች፡፡ በደም የተበከለውን አገጯን በረጅሙ ምላሷ እየላሰች ለማጥራት እየሞከረች ነበር፡፡ ሁለቱ በግ ጠባቂ ውሾች ከጎንና ጎኗ ሞተው ተዘርረዋል፡፡
ጠቦቷ ብድግ አለች፡፡ እየጮኸችም በዝግታ ወደ እረኛው አቅጣጫ መንቀሳቀስ ጀመረች። እረኛውም በፍርሀት እየተርበተበተ ወደ ኋላ አፈገፈገና፣ “ጠቦት ሆይ፣ ውዷ ጠቦቴ፣ ቆንጆዋ ጠቦቴ!” ሲል ተንተባተበ፡፡
ጠቦቷ አጓራች፡፡ “ጠቦት አይደለሁም!”
እረኛው እንደገና ተንተባተበ፡፡ “ጠቦት ሆይ፣ ውዷ ጠቦቴ፣ ቆንጆዋ ጠቦቴ…”
ጠቦቷ እንደገና አጓራች፡፡ “በመልካሞቹ የቀድሞ ጊዜያት ጠቦት ነበርኩ፡፡ ለአንተ ምስጋና ይግባህና ዛሬ ተኩላ ሆኛለሁ፡፡”
“ግን እኮ የእኔ ጣፋጭ ጠቦት ነሽ፣ የማፈቅርሽ ጠቦቴ፣ ታዛዧ ጠቦቴ….”
“ውዱ እረኛ፡አሁን ጊዜው አልፏል፡፡”
እነዚህን ቃላት ከተናገረች በኋላ ሮጦ ለማምለጥ የቀቢፀ ተስፋ ሙከራ ያደረገው እረኛ ላይ ተከመረችበት፡፡ ወደ ተኩላነት ከተለወጠችው ጠቦት ማን ሊያድነው ይችላል? ሹል ጥርሶቿ አንገቱን በስተው ገቡ፡፡ ሞቃት ደሙም በበረዶው ተመጠጠ።
በነጩ በረዶ ላይ የተሸፈነውን ቀይ ፅሁፍ ማንበብ የሚችሉ ተላላፊ መንገደኞች የእረኛውንና የጠቦቷን ታሪክ ማወቅ ቻሉ፡፡ ለብዙ መቶ ዓመታትም ከትውልድ ትውልድ በሰዎች ሲተረክ ኖሯል፡፡

Read 3506 times