Print this page
Saturday, 16 April 2016 11:29

የቶታል ኢትዮጵያ የፈጠራ ውድድር አሸናፊዎች ተሸለሙ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የቶታል “ስታርት አፐር” የፈጠራ ውድድር አሸናፊዎች ከ350 ሺ ብር እስከ 150 ሺ ብር የተሸለሙ ሲሆን ውድድሩም ሆነ ሽልማቱ ለበለጠ ፈጠራ እንዳነቃቃቸው ተሸላሚዎቹ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል።
 በወድድሩ በኢንተርኔት የማስጠናት አገልግሎት (tutor) የሚሰጥ ተቋም የፈጠሩት ዶክተር ሄኖክ ወንድይራድ አንደኛ ሲወጡ፣ በጸሃይ ሃይል የሚሰራ የሞባይል ስልክ ቻርጀር የሰሩት አቶ ቢኒያም ተስፋዬ ሁለተኛ ወጥተዋል። በጸሃይ ሃይል የሚሰራ የትራፊክ መብራት፣ የሞባይል ቻርጀር፣ የቤት ውስጥ መብራት፣ የሶላር ጄኔሬተርና እስከ መቶ ሃያ እንቁላል የሚፈለፍል የሶላር ኢንኩቤተር የፈጠሩት አቶ ቃለ ዳዊት እስመአለም ደግሞ የሶስተኛነት ደረጃን አግኝተዋል፡፡ ከ1ኛ እስከ 3ኛ የወጡት አሸናፊዎች፡- የ350 ሺ፣ የ200ሺ እና የ150ሺ ብር የገንዘብ ሽልማት አግኝተዋል።
የቶታል “ስታርት አፐር” ፕሮጀክት ማናጀር አቶ ኢብራሂም ማማ፤አሸናፊዎቹ በቀጣይ ፈጠራቸውን እንዲያሳድጉ ተከታታይ ስልጠና ይሰጣቸዋል ብለዋል። ውድድሩ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ መካሄዱን በመግለጽም ወደፊት በየዓመቱ መሰል ውድድሮች በማካሄድ ቶታል ፈጠራን የማበረታታት እንቅስቃሴውን እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
አሸናፊዎቹ ከአገሪቱ የልማት አጀንዳ ጋር የተጣጣሙ ችግር ፈቺ የፈጠራ ውጤቶችን በማምጣት ላይ ናቸው ያሉት ማናጀሩ፤የተሸላሚዎቹ ፈጠራዎች በትምህርት ጥራት፣ በትራፊክ ዘርፍና በሃይል አቅርቦት ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ አቅምን የሚፈጥሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው፤የቶታል ኢትዮጵያን ተግባርና መሰል ፈጠራን የሚያበረታቱ ድርጅቶችን አድንቀው፤መንግስት በተቻለው አቅም ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ቃል ገብተዋል።
“አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦችን ያነገቡና የራሳቸውን ቢዝነስ ለማቋቋም የተነሳሱ ወጣቶች የአገሪቱ ኢኮኖሚ ተስፋዎች ናቸው” ብለዋል፤ ሚኒስትር ዴኤታው።
አንደኛ የወጣው የፈጠራ ሥራ በ34 የአፍሪካ አገራት በተካሄዱ የቶታል “ስታርት አፐር” ወድድሮች አንደኛ ከወጡ ሌሎች ፈጠራዎች ጋር እንደሚወዳደርም ተገልጿል።

Read 2913 times
Administrator

Latest from Administrator