Saturday, 16 April 2016 11:30

ቻይና ለኢትዮጵያውያን የነፃ የትምህርት እድል ልትሰጥ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 የኢትዮጵያ ቻይና የንግድ ምክር ቤት በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ለሚያመጡ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በየዓመቱ የነፃ ትምህርት እድል ለመስጠት ከዩኒቨርሲቲው ጋር ስምምነት ተፈራረመ፡፡
በኢትዮጵያ ለተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን የገለፀው ምክር ቤቱ፤ በቀጣይ በየዓመቱ ከመቶ በላይ የሆኑ የዩኒቨርሲቲው የላቀ ውጤት ባለቤት ተማሪዎች በውጭ ሃገራት የትምህርት እድል ያገኛሉ ተብሏል፡፡
በዚህ የትምህርት እድል የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ሁለተኛ ዲግሪና የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ታውቋል፡፡
የንግድ ምክር ቤቱ ለዩኒቨርሲቲው ይሄን ድጋፍ የሚያደርገው ዩኒቨርሲቲው በ2025 በአፍሪካ አንዱና ዋነኛው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን የወጠነውን ራዕይ ለማገዣ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ - ቻይና ንግድ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዦ ዮን ግሼንግ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ - ቻይና የንግድ ምክር ቤት ከ200 በላይ የተለያዩ የንግድ ተቋማትን ያካተተ ለትርፍ ያልተቋቋመ ምግባረ ሰናይ ተግባራት የሚያከናውን ተቋም ነው፡፡ በሌላ በኩል የፊርማ ስምምነቱ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በተከናወነበት ወቅት የቻይናው የቴሌኮም ኩባንያ ZTE እና ኢትዮ ቴሌኮም በጋራ ለዩኒቨርሲቲው የለገሡት የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ላብራቶሪ ተመርቋል፡፡
ላብራቶሪው ዩኒቨርሲቲው በተለይ በቴሌኮም ዘርፍ ለሚያደርጋቸው የምርምርና የማስተማር ተግባራት አጋዥ ይሆናል ተብሏል፡፡    

Read 2383 times