Saturday, 16 April 2016 11:32

ሶፍትዌር ወደ ውጭ ለመላክ የሚታትረው ኩባንያ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(8 votes)

      በአሁኑ ወቅት ግብይትን በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ፖስ (Point of sales software) ያለመጠቀም ሕገወጥና ወንጀል ነው፤ ያስቀጣል፣ ያሳስራል፡፡ ከ13 ዓመት በፊት ግን በዚህ መሳሪያ መጠቀም እንደ ወንጀል ይቆጠር ስለነበር ያስቀጣል። ያሳስራል፡፡ በወቅቱ ሽያጫቸውን በዚህ መሳሪያ የሚፈጽሙት ሁለት ብቸኛ ድርጅቶች ሸራተን አዲስና ሂልተን ሆቴል ነበሩ፡፡
በዚያን ወቅት የመሳሪያው ጥቅም ስለማይታወቅ ሶፍትዌሩን መሥራትም ሆነ መሸጥ ሕገ ወጥ ስለነበር፣ የኢትዮጵያ ጉምሩክና ገቢዎች ባለሥልጣን ሶፍትዌሩን የሚሠሩትንና የሚሸጡትን እያሳደደ ያስቀጣና ያሳስር ነበር፡፡ የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ መጠቀም አስገዳጅ እንዲሆን ሕግ በወጣበት በ2000 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጉምሩክና ገቢዎች ባለሥልጣን ከሽያጭ ታክስና ቀረጥ የሚሰበስበው ዓመታዊ ገቢ 4 ቢሊዮን ብር አይሆንም ነበር፡፡ መሳሪያውን መጠቀም በጀመረ 7 እና 8 ዓመት ውስጥ ዓመታዊ ገቢው በ4 እጥፍ አድጐ ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን የፖስ ሶፍትዌር አምራች የሆነው የሲኔት ሶፍትዌር ቴክኖሎጂስ መሥራች ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ በእምነት ደምሴ ተናግሯል፡፡
በቢሾፍቱ (ደብረዘይት) የተወለደው አቶ በእምነት ያደገውና የተማረው እዚያው ነወ፡፡ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስዶ ስላለፈ ምህንድስና (ኢንጂነሪንግ) ለመማር አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 5 ኪሎ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ክፍል ገባ፡፡ የወጣቱ ዝንባሌ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ነው፡፡ በአዕምሮው የሚያሰላስለውን ፈጠራ በተግባር ለመሞከር ትምህርቱን አቋረጠ፡፡ (በኋላ ግን አጠናቋል)
ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለ በወቅቱ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን የተባለ መ/ቤት ምርምርና ፈጠራን ለማበረታታት በአገር ውስጥ የሚደረጉ የምርምር ሐሳቦችን እየተቀበለ የገንዘብ ድጋፍ ያደርግ ነበር፡፡ በእምነት በብዙ የፈጠራ ውጤቶች ይታወቅ ነበር፡፡ ከፈጠራዎቹ አንዱ ኢንተሌጀንት ትራፊክ ኮንትሮልን ሲስተም ይባላል፡፡ ሲስተሙን የሠራው ከኮሚሽኑ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ነበር። ሲስተሙ የትራፊክ መጨናነቅ ያለው በየትኛው መስመር ነው? የትኛው መስመር ቢለቀቅ መጨናነቁ ይወገዳል? በማለት መኪኖችን የሚያስተናግድ ሲሆን 5 መስሮች ባሉት የአትላስ መንገድ ተሞክሮ ነበር፡፡
ዝንባሌው ቴክኖሎጂና አዳዲስ ነገሮችን መፍጠር በመሆኑ ከመንግሥት የሚሰጥ የገንዘብ ድጋፍ ከመጠበቅ በነፃነት በራስ መንቀሳቀስ ይሻላል በማለት፣ ከ13 ዓመት በፊት እ.ኤ.አ በ2003 ዓ.ም በ3000 ብር ካፒታል ሲኔት ሶፍትዌር ቴክኖሎጂስ የተባለውን ድርጅት መሠረተ፡፡ በአንድ ሰው የተመሠረተው ኩባንያ በአሁኑ ወቅት 270 ሠራተኞች ሲኖሩት ዓመታዊ ገቢውም 60 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ድርጅቱ እንደተቋቋመ በመጀመሪያ የሠራው ፖስ (Point of sales Software) ነበር፡፡ ያኔ የሶፍትዌሩ ጥቅም ስለማይታወቅ ለማስለመድ ብዙ ደክሟል፡፡ አንዳንዴ ከዋጋ በታች ያቀርባል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ እስቲ ሞክሩት በማለት በነፃ ይሰጣል፡፡ ችግሩ የተፈጠረው በኤሌክትሮኒክስ የሚሠራ ደረሰኝ በጉምሩክና ገቢዎች ኤጀንሲ እውቅናና ተቀባይነት ስላልነበረው ነበር፡፡ መንግሥት መሳሪያውን ቢጠቀም ማጭበርበር የሌለበት ከፍተኛ ገቢ መሰብሰብ እንደሚችል ከፋዩም ኅብረተሰብ በማንኛውም ጊዜ ሊያቀርበው የሚችልና የማይጠፋ አስተማማኝ ማስረጃ እንደሚኖረው ለማሳመን ያላሰለሰ እልህ አስጨራሽና ከፍተኛ ጥረት ተደርጐ የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ (ፖስ) መጠቀም ግዳጅ እንደሆነ የሚደነግግ ሕግ በ2000 ዓ.ም መውጣቱን አቶ በእምነት ገልጿል፡፡ ድርጅቱ ከመጀመሪያው ሶፍትዌር በኋላ ብዙ ሲስተሞችን ሠርቷል፡፡ በአብዛኛው ትኩረቱ ግን በኢንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላኒንግ (ERP) ላይ ነው፡፡ ኢ አር ፒ የንግድ ተቋማት የገንዘብ ምንጫቸውን፣ የሰው ሀብታቸውንና ንብረታቸውን የሚከታተሉበትና የሚቆጣጠሩበት ሶፍትዌር ሲስተም ነው፡፡ በዚህ ረገድ አራት ዓይነት ሶፍትዌር ያመርታሉ፡፡ ለሆቴሎች የሚሠሩት ሆስፒታሊቲ ሶፍትዌር ይባላል፡፡ ሁለተኛው መርቸንዳይዚንግ የተሰኘው ሲሆን ቸርቻሪ ነጋዴዎችና አከፋፋዮች የሚጠቀሙበት ሲስተም ነው፡፡ ለጤና ክብካቤ የመድኃኒት መደብሮች፣ መድኃኒት አከፋፋዮች ክሊኒኮችና ሆስፒታሎች የሚጠቀሙበት ሄልዝ ኬር ማኔጂንግ ሲስተም አለ፡፡ በቅርቡ የሚያስመርቁትና ለሁለት ዓመት ተኩል ሲሠሩ የቆዩት ደግሞ ፕሮዳክሽን ማኔጅመንት ሲስተም (የማኑፋክቸሪንግ ሪሶርስ ፕላኒንግ) ይባላል፡፡
ይህ አዲስ ሶፍትዌር ከአንድ ወር በኋላ በሚከበረው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሳምንት (አይቲዊክ) ላይና በሆቴሎች ሾው ወቅት ይቀርባል። ሲኔት ብቻውን ይመስረት እንጂ አሁን ሁለት ኩባንያዎች ጨምሮ ሦስት ሆኗል፡፡ ሲኔት፣ ሶፍትዌር ያመርታል ይገጥማል፡፡ ለኮምፒዩተር ሲስተሞች ድጋፍ ያደርጋል፡፡ አይ ፖስ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ (EPOS International Trading) የተባለው ድርጅት ደግሞ ለኢ አር ፒ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን (ሃርድዌር ዲቫይስ) ከውጭ አገር ያስገባል። አይቤክስ ኮሌጅ (IBEX College) የተባለው ሦስተኛው ድርጅት ኢ አር ፒ ተጠቃሚዎችንና አስተዳደሮችን በማሰልጠን ከሚጠቀሙት ሲስተም ጋር ያስተዋውቃል፡፡ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት 2,500 የሠለጠኑ ደንበኞችና 10ሺህ ተጠቃሚዎች አሉት፡፡
ኩባንያው በክልሎችም ቅርንጫፎች አቋቁሟል። በመቀሌ፣ ባህርዳር፣ ሀዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ አዳማ፣ ጐንደር፣ በቢሾፍቱና በደሴ፣ ስምንት ቅርንጫፎች አሉት፡፡ በዚህም የአገሪቷን 75 በመቶ የገበያ ድርሻ ይዟል፡፡
የኮከብ ደረጃ ከተሰጣቸው 180 ሆቴሎች 168ቱ ወይም 93 በመቶው፣ ጥሩ ደረጃ ካላቸው 52 ሱፐር ማርኬቶች 42ቱ ወይም 80 በመቶ፣ ጥሩ ደረጃ ካላቸው 305 ሬስቶራንቶች 420ዎቹ ወይም 72 በመቶ በሲኔት ምርቶች እንደሚጠቀሙና በአገሪቱ ውስጥ በ22 ከተሞች እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ታውቋል፡፡ ኩባንያው ወደፊት፣ ከውጭ አገር የሚገባውን የሶፍትዌር ወጪ ለመቀነስና ሶፍትዌሮችን ወደ ጐረቤት አገሮች በመላክና ሱቆች በመክፈት ለአገሪቷ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት አቅዷል፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ፣ በጅቡቲ፣ በሱዳን፣ በኬንያ፣ በደቡብ ሱዳንና በዩጋንዳ ሱቆች ለመክፈት የገበያ ጥናት እያደረገ ነው፡፡
ቦሌ ለሚ በሚገኘው አይሲቲ ፓርክ የዋና መ/ቤት ሕንፃ ለመሥራት ዲዛይኑን አጠናቆ የግንባታ ፈቃድ እየተጠባበቀ መሆኑን አቶ በእምነት ደምሴ አስረድቷል፡፡

Read 2954 times