Saturday, 23 April 2016 10:15

ተቃዋሚዎች በጋምቤላው ጥቃት መንግስትን ወቀሱ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ሰሞኑን በጋምቤላ ክልል 3 ወረዳዎች ከደቡብ ሱዳን ድንበር ጥሰው የገቡ ታጣቂዎች በፈፀሙት ጥቃት 208 ዜጎች ሲገደሉ፣ 108 ህፃናትና እናቶችም ታፍነው ተወስደዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ 20ሺ ዜጎች ሲፈናቀሉ፣ ከ2ሺ በላይ ከብቶችም ተዘርፈዋል፡፡ ጥቃቱን ተከትሎም መከላከያ ሰራዊት ደቡብ ሱዳን ድረስ ገብቶ 60 ያህሉን ጥቃት ፈጻሚዎች መግደሉ ተነግሯል፡፡ ይህን አሰቃቂ ጥቃት
በተመለከተ አስተያየት የሰጡ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፣ የድንበር አካባቢ የደህንነት ጉዳዮች አስጊ መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡ የሀገሪቱ የድንበር አጠባበቅ የዜጎችን ደህንነት ማረጋገጥ አለበት የሚሉት ተቃዋሚዎች፤ መንግስት የዜጎቹን ደህንነት በሚገባ እየጠበቀ አይደለም ሲሉም ይወቅሳሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ የተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን አነጋግሮ አስተያየታቸውን እንደሚከተለው አጠናቅሯል፡፡

“ድንበር መጠበቅ የመንግስት ኃላፊነት ነው”
(አቶ ነገሠ ተፋረደኝ -
የሰማያዊ ፓርቲ ም/ሊቀመንበር)
በጋምቤላ ለሞቱት ንፁሃን መንግስት ኃላፊነት መውሰድ አለበት፡፡ ድንበር መጠበቅ የመንግስት ኃላፊነት ነው፡፡ በደርግ ጊዜ ድንበሩ ይጠበቅ ነበር። ከድንበር ጥበቃ ጎን ለጎን ራሱን እንዲጠብቅ መንግስት ህብረተሰቡን ማደራጀት አለበት። ራሳቸውን የሚጠብቁበት የተመዘገበ ትጥቅም ሊኖራቸው ይገባል፡፡
መንግሥት ለሰራው ጥሩ ነገር እንደሚመሰገነው ሁሉ ለተከሰተው ጥፋትም ይወቀሳል፤ ለዚህም ጥፋት ኃላፊነት መውሰድ አለበት፡፡ መንግስት ታፍነው የተወሰዱ ዜጎችን ለማስመለስ የሚያደርገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ የአለማቀፍ ተቋማት፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ፣ የተለያዩ የእርዳታ ድርጅቶች በማስመለሱ ጥረት ተባባሪ መሆን አለባቸው፡፡
እኛ እንደ ማንኛውም ዜጋ ኃላፊነት ይሰማናል፤አንድም ኢትዮጵያዊ በከንቱ ህይወቱ ማለፍ የለበትም፤ ታፍኖም ሊወሰድ አይገባም፡፡

“በየትኛውም ድንበር አካባቢ የደህንነት ስሜት የለም”
(አቶ ገብሩ አስራት - የአረና ፓርቲ አመራር)
መንግስት እንደ ሌላው ዜጋ ሁሉ ሃዘኑን ብቻ እየገለፀ ነው ያለው፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው ልክ የእያንዳንዱን ዜጋ ደህንነት ማስጠበቅ ነው፡፡ የመንግስት አንዱና ዋናው ተግባር የዜጎቹን ደህንነት ማስጠበቅ ነው፡፡ ይሄ እየሆነ አይደለም፡፡ በኦሮሚያም በትግራይም፣ በአማራም፣ በጋምቤላም ሆነ በሌሎች ቦታዎች መንግስት ይሄን ኃላፊነቱን እንደዘነጋ እየታየ ነው፡፡ ዛሬ የተጨፈጨፉት ሰዎች፣ቀድሞ ታጣቂዎች ስለነበሩ ራሳቸውን በሚገባ ሲከላከሉ ነበር፡፡ መንግስት ነው ትጥቃቸውን ያስፈታው። መንግስት ይሄን ሲያደርግ በቂ ጥበቃ ሊያደርግላቸው ይገባ ነበር፡፡
 ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድንበሩ ሰፊ ስለሆነ ቦታ እየቀያየሩ ያጠቃሉ ያሉት መልስ አይሆንም፡፡ እነዚህ ሰዎች በ3 ወረዳዎች ላይ ነው ጥቃት የፈፀሙት፡፡ ድንበሩ ለምን አይጠበቅም? በሌላ ሀገር ወታደር ዋና ስራው ድንበር መጠበቅ ነው፡፡ እንደኔ በዚህ ጉዳይ መንግስት ዋንኛ ተጠያቂ ነው፡፡ ትኩረት ሊሰጥ የሚገባው ሰው ካለቀ በኋላ እርምጃ መውሰዱ ላይ አይደለም፡፡ ዋናው አደጋው እንዳይከሰት መከላከሉ ነው፡፡
እንደ እኔ መንግሥት የሚገባውን ያህል እየሰራ አይደለም፡፡ የዜጎች ደህንነት በሚገባ እየተጠበቀ አይደለም፡፡ በየትኛውም ድንበር አካባቢ የደህንነት ስሜት የለም፡፡ “አልተዘጋጀንም ነበር፤ ድንገተኛ ነው” የሚል ነገር ፈፅሞ መልስ መሆን አይችልም፡፡ የእነዚህ ዜጎች ጭፍጨፋ እንዲህ በቀላሉ መታለፍ ያለበት ጉዳይም አይመስለኝም፡፡

“የውጪ ግንኙነት ፖሊሲያችን ሊፈተሽ ይገባል”
(ዶ/ር ጫኔ ከበደ - የኢዴፓ ፕሬዚዳንት)
ኢዴፓ በአጠቃላይ በተፈጠረው አደጋ ሃዘኑ ጥልቅ ነው፡፡ መንግስት እየተከተለው ያለው የውጪ ግንኙነት ፖሊሲ እንደገና ትኩረት ተሰጥቶት ሊፈተሽ የሚገባ ነው፡፡ ክልሎች ከአጎራባች ሃገሮች ጋር የሚዋሰኑ በመሆኑ በተለይ ታዳጊ ክልሎች ራሳቸውን መከላከል የሚችሉበትን ስልት መቀየስ ያሻል፡፡ በክልሎቹ መንግስታት የሚመራ የሚሊሻና ታጣቂ ኃይል ያስፈልጋቸዋል፡፡ የጋምቤላን ጉዳይ ስንመለከት፣ መንግስት የታጠቁ ኃይሎችን ትጥቅ ማስፈታቱ ከፍተኛ ክፍተት ይፈጥራል፡፡ ሌሎች ክልሎችም ራሳቸውን የሚከላከሉበት መንገድ እንደገና መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ ከአሁን በፊትም በየድንበር አካባቢው ግጭቶችና የከብት ዝርፊያ አለ። ይሄኛው ግን ከዚያም አልፎ ክቡሩን የሰው ህይወት የነጠቀ መሆኑ እንደ ማንቂያ ደውል ሊታይ ይገባዋል፡፡ በሁሉም አካባቢዎች ችግሮቹ አሉ፡፡ በኤርትራ ተዋሳኞች፣ በኬንያ፣ በሱዳን ድንበሮች ያለው ሁኔታ ደህንነቱ በደንብ የተረጋገጠ አይመስለኝም፡፡ ከዚህ በፊት የኤርትራ ታጣቂዎች ሰዎችን አፍነው ወስደዋል፡፡ በኛ በኩል ድንበሩ በሚገባ እየተጠበቀ ነው ብለን አናምንም፡፡ ሰፊ ድንበር ጠባቂ ኃይል ሊደራጅ ይገባዋል፡፡
ይሄ አደጋ ዘግናኝና አሳፋሪ ነው፡፡ የሀገራችንን ገፅታም የሚያበላሽ ነው፡፡ የምንከተለው የውጭ ፖሊሲ በተለይ ከጎረቤት ሃገራት ጋር ያለው የዜጎችን ደህንነት የሚያስጠብቅ አይደለም፡፡ ድንበሮች ክፍት የሚሆኑት ለውጭ ሀገር ዜጋ እንጂ ለኢትዮጵያውያን አይደለም፡፡ ከጎረቤት ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ሰዎች እንዳሻቸው ሲሆኑ፣ በአንፃሩ ኢትዮጵያውያን መንቀሳቀስ አይችሉም፡፡ የሌሎች ሀገራት ዜጎች ከድንበር አልፈው በሰላም መሃል ሀገር ድረስ መኪኖቻቸውን ይዘው መጥተው እንዳሻቸው ይሆናሉ፡፡ በኬንያ በኩል ኬንያውያን እስከ ያቤሎ ድረስ መጥተው ጨፍረው የሚሄዱበት ሁኔታ አለ። በአሶሳ በኩልም ሱዳኖች በተመሳሳይ እንዳሻቸው ይወጣሉ ይገባሉ፡፡ የኛ ዜጎች ግን ከድንበር 30 ኪ. ሜትር እንኳ ርቀው ከሄዱ ይታሰራሉ፡፡ ይሄ ሁሉ የውጭ ፖሊሲያችን ውጤት ነው፡፡ እኔም የዚሁ ችግር ሰለባ የሆንኩበት አጋጣሚ አለ፡፡ ሞያሌ ላይ ወደ ኬንያ ድንበር ገብቼ እቃ ገዝቼ ስመለስ 12 ሰዓት ሆኗል ተብዬ ታስሬያለሁ፡፡ በአንፃሩ የነሱ ሰዎች ምሽቱን እንዳሻቸው ሆነው ከኢትዮጵያ ወደ ሃገራቸው ኬላ አቋርጠው ሲመለሱ በአይኔ አይቻለሁ፡፡ በአጠቃላይ በዚህ ረገድ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለን ግንኙነትና የዜጎቻችንን መብት የምናስጠብቅበት መንገድ የተሳሳተ እንደሆነ ነው ያስተዋልኩት፡፡
ከሰሞኑ በጋምቤላ ለደረሰው አደጋ ኃላፊነት ሊወስድ የሚገባ አካል መኖር አለበት፡፡ የሱዳን መንግስት ወይም የአማፂ ቡድን ወይም ሌላ ቡድን ካለ ኃላፊነት ሊወስድ ይገባል፡፡ እንደኔ ግን የደቡብ ሱዳን መንግስት ኃላፊነቱን ሊወስድ ይገባል፡፡ ሰራዊታችን ድንበር ጥሶ ህፃናቱን ለማስመለስ ወደ ደቡብ ሱዳን ቢገባ፣ ሉአላዊነትን በመዳፈር ሊከሱን ይችላሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የሀገሪቱ መንግስት ኃላፊነቱን ወስዶ ህፃናቱ እንዲመለሱ ማድረግ ያሻል፡፡ አልያም ወደ አለማቀፍ ህግ መሄድ ተገቢ ነው፡፡  

Read 3468 times