Saturday, 23 April 2016 10:22

‘ምስኪኗ ሀበሻ’ እና የምቀኞች ነገር…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(11 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪኗ ሀበሻ በተራዋ አቤቱታዋን ይዛ ወደ አንድዬ ሄዳለች፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ…
አንድዬ፡— ይሄን ድምጽ አውቀዋለሁ ልበል!
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ ምስኪኗ ሀበሻ ነኝ…
አንድዬ፡— ምስኪኗ ሀበሻ! አሁን አስታወስኩኝ፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ ረስቼሻለሁ እንዳትለኝ!
አንድዬ፡— ብረሳሽ ምን ይገርማል! ደግሞ ይቺ ማናት ብዬ ግራ ቢገባኝ ምን ይገርማል!
ምስኪኗ ሀበሻ፡— ይሄ ያህል አንድዬ!
አንድዬ፡— ምን አድርግ ትይኛለሽ፡፡ የዘንድሮ የእናተ ነገር እኮ በጣም ነው ግራ ያጋባኝ። መልካችሁ ተመሳሳይ፣ የምትለብሱት ተመሳሳይ፣ ጸጉራችሁ ተመሳሳይ፣ አወራራችሁ ተመሳሳይ! አንዳንዴ ምን እንደምል ልንገርሽ አይደል…እኔ ሔዋንን ለመፍጠር ከዓዳም ላይ ስምምነቱን ሳልጠይቅ ጎድን አጥንት ቀንሼ ስንት መከራ እንዳላየሁ አሁን ፋብሪካ ተቋቋመ እንዴ እላለሁ፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንተም እንዲህ ትላለህ! እዚህም አንዳንድ ወንዶች እንዲሁ እያሉን ሞራላችንን ለመስበር ሲሞክሩ አንድዬ አንተም በፋብሪካ ተሠራችሁ ትላለህ!
አንድዬ፡— አሥሬ ስትነዘንዙኝ የእናንተን አነጋገር ለመድኳ! የሆነው ሆነና ምስኪኑ ሀበሻ አያናግረኝም ብሎ ነው አንቺን የላከው!
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ እኔ ማንም አልላከኝም፡፡ ራሴን ችዬ ነው የመጣሁት፡፡
አንድዬ፡— ጎሽ በርትተሻላ፡፡ እንኳንም ራስሽን ቻልሽ… ምስኪን ሀበሻ እኮ ስንቴ ሲያደርቀኝ ነው የከረመው፡፡ መመካከሩን ተዋችሁት እንዴ!
ምስኪኗ ሀበሻ፡— ለእኔ አንድ ቀንም አንተ ዘንድ አቤቱታ ማቅረቡን ነግሮኝ አያውቅም፡፡ ምን ያማክረኝና…
አንድዬ፡— እሱ ላይ እንኳን ያው ናችሁ፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— እንዴት፣ አንድዬ?
አንድዬ፡— እናትሽ ሔዋን ዕፀ በለሱን ከመብላቷ በፊት ብታማክረው ኖሮ መች እንዲህ ምስቅልቅሉ ይወጣ ነበር፡፡ ወደ ጉዳይሽ እንግባና አንቺ ደገሞ ምን አድርግ ልትዪኝ ነው?
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ ምቀኛ፣ ምቀኛ አላስቀምጥ አለኝ፡፡
አንድዬ፡— ይሄ ምን አዲስ ነገር አለው፡፡ ሁላችሁም እየመጣችሁ ምቀኛ አላስቀምጥ አለኝ ትሉኛላችሁ፡፡ ሁላችሁም አቤቱታ አቅራቢ ከሆናችሁ ምቀኛው ማነው!
ምስኪኗ ሀበሻ፡— የእኔ ልዩ ነዋ አንድዬ፣ የእኔ ልዩ ነዋ! እኔን ሲያዩ እንዴት፣ እንዴት እንደሚያደርጋቸው ብታይ እኮ ታዝንልኝ ነበር፡፡ አንዳንዴ መፈጠሬን እጠላለሁ፡፡
አንድዬ፡— ለምን ፈጠርከኝ እያልሽኝ ነው?
ምስኪኗ ሀበሻ፡— እንደውም አንድዬ፡፡ ብቻ ምርር ሲለኝ፣ ሰዉም፣ እንሰሳውም አላስቆም አላስቀምጥ ሲለኝ ምን ላድርግ! ምነው እናቴ ሆድ ውሀ ሆኜ በቀረሁ እላለሁ፡፡
አንድዬ፡— እኮ አሁን ለምን ፈጠርከኝ ነው የምትዪው? እኔኑ ጥፋተኛ ልታደርጊኝ ነው!
ምስኪኗ ሀበሻ፡— ኧረ አንድዬ እንደ እሱ አታስብ! ብቻ ምን መሰለህ በቃ በገንኩ፡፡ በአንድ በኩል ምስኪኑ ሀበሻ ያበግነኛል፣ በዛ በኩል ኑሮው ያበግነኛል፣ በዚሀ በኩል ምቀኛው ያበግነኛል፡፡ ውይ!  ውይ! አንድዬ የእኛ ሰው ምቀኝነት እኮ ለወሬም አይመች፡፡
አንድዬ፡— እሺ፣ ምን አደረጉሽ?
ምስኪኗ ሀበሻ፡— ምን ያላደረጉኝ ነገር አለ አንድዬ፣ ምን ያላደረጉኝ ነገር አለ! አንድዬ፣ እንደው አርቲፊሻል ጉትቻ እንኳን አድርጌ ላልወጣ ነው!
አንድዬ፡— በጉትቻው ነው የሚመቀኙሽ?
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ ጉትቻ በለው፣ ጫማ በለው፣ ቦርሳ በለው፣ ብቻ ትንሽ ዓይን የሚገባ ነገር ላድርግ ቁጥር አንድ ወሬ ስለ እኔ ነው የሚሆነው፡፡
አንድዬ፡— እኮ ምን ይሉኛል ነው የምትዪው!
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ እንደው እኔ ፊት ስትቀርብ ትዋሽ እንደሆነ ልፈትናት ብለህ ነው እንጂ የሚሉኝን አንተ ሳታውቅ ቀርተህ ነው!
አንድዬ፡— ከእነሱ ጋር አማኸኝ ልትዩኝ ነው!
ምስኪኗ ሀበሻ፡— ኧረ አንድዬ እንደ እሱ አላልኩም፡ ምን ቆርጦኝ ነው እንዲህ የምለው!
አንድዬ፡— እኮ የሚሉሽን ንገሪኛ፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— ብቻ አንድዬ አንዲት ጫማ ልግዛ ከየት አምጥታው ነው፣ አናውቃትምና ነው፣ ባሏን አናውቀውምና ነው…ምን የማይሉኝ አለ፡፡ የእኔና የባሌ አልበቃ ብሏቸው ሌሎች ቤተሰቦቼና ዘመዶቼ አይቀሯቸውም። አንድዬ አሁን እኔ አምሬ ብታይ እነሱ ምናቸው ይነካል!
አንድዬ፡— እሱን እንግዲህ እነሱን መጠየቅ ነው፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ አሁን በዛ ሰሞን ጸጉሬ እየተነቀለ አስቸገረኝ፡፡ ብቻ ምን አለፋህ ትንሽ አደግ ሲል እርግፍ ነው፡ አደገ ሲል እርግፍ ነው፡፡ ሚዶ እንኳን ለምን ነክቶኝ ሲል አንድዬ ምን አደረግሁ መሰለህ...
አንድዬ፡— ምን አደረግሽ..
ምስኪኗ ሀበሻ፡— ከቤተሰቤም፣ ከዘመድም በመዋጮም በብድርም ገንዘብ ሰባሰብኩና ሂዩመን ሄይር ገዛሁ፡፡
አንድዬ፡— ሂዩማን ምን አልሽኝ?
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ኧረ ተው አታሳፍረኝ! አሁን ይሄንን ሳታውቅ ቀርተህ ነው!
አንድዬ፡— እኔ ምን አውቃለሁ፡፡ እኔ የማውቀው ሂዩመን ሄይር ራሳችሁ ላይ ከሰውነታችሁ ጋር አብሮ የተፈጠረውን ነው፡፡ ገዛሁ ስትይ እኮ ግራ ገብቶኝ ነው፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ ምን መሰለህ፣ እውነተኛው ሂዩመን ሄይር በተለያየ መልክ ይዘጋጅና ሱቅ ውስጥ ይሸጣል፡፡
አንድዬ፡— ጥሩ፣ ግን እውነተኛ የሰው ጸጉር ከሆነ ከየት አግኝተዉት ነው?
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ አታስዋሸኝ፣ እሱን አላውቅም፡ የሚያውቅም ያለ አይመስለኝም፡፡
አንድዬ፡— የኩላሊቱ ሲገርመኝ ሰዉ ጸጉሩን መሸጥ ጀመረ!
ምስኪኗ ሀበሻ፡— እኔ አንድዬ እሱንም አላውቅም፡፡
አንድዬ፡— ተዪው ተዪው አሁን ገባኝ፡፡ እኔ እኮ የምድር ቆይታቸውን ጨርሰው እኔ ዘንድ የሚመጣው ሁሉ ምነው ተመለጠ እያልኩ… (አንድዬ ሳቅ ያቋርጠዋል) እሺ ጸጉርሽ እየተነቀለ ሲያስቸግርሽ ሂዩመን ሄይር አደረግሽ፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አዎ፣ አንድዬ፡፡ ታዲያ የራሴ ጸጉር ለማበጠሪያ የማይበቃ ቢሆንብኝ ሂዩመን ሄይር አድርጌ አይተው ይኸው ነክሰው ይዘውኛል ነው የምልህ፡፡
አንድዬ፡— ግዴለም፣ ሌላ የሚነክሱት ሲያገኙ ይለቁሻል፡፡ እናንተ እንደዚሁ አይደላችሁ…
ምስኪኗ ሀበሻ፡— እንዴት አንድዬ?
አንድዬ፡— አንዱን ነከሳችሁ ትከርሙና ደግሞ ወደ ሌላው ትዞራላችሁ…
ምስኪኗ ሀበሻ፡— እሱ ብቻ መሰለህ አንድዬ፣ ምን አግኝታ ነው እንዲህ የወፈረችው እያሉ…
አንድዬ፡— እኔም እኮ ይህች ሴት ወፈረች እንዴ እያልኩ ነበር፡፡ …ከወደ ላይ ቀጠን ብለሽ ዳሌሽ አካባቢ ሰፋ ያልሽ ይመስላል። እንዲህ እንዳንቺ አይነቶቹን ሳይ ሥራ በዝቶብኝ ይሆን እንዴ ሂሳቡን አዛብቼ ያሰላሁት እላለሁ፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— ምን መሰለህ አንድዬ የአንተ አፈጣጠር ሳይሆን እኔ..እኔ…
አንድዬ፡— እኮ ንገሪኛ…
ምስኪኗ ሀበሻ፡— ቀጫጫ፣ ሰንበሌጥ፣ ስቲኪኒ ምናምን እያሉ ሲያስቸግሩኝ ይውጣላቸው አልኩና…አንድዬ፣ እንዴት ብዬ ልንገርህ ያሳፍራል…
አንድዬ፡— ምን ያሳፈራል፣ ባትነገሪኝም እኮ እደርስበታለሁ፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— ይኸውልህ አንድዬ ከጎንና ከጎኑ የሆነ ነገር የሚከተትበት የውስጥ ሱሪ አለ…አንድዬ እየሰማኸኝ ነው…
አንድዬ፡— እየሰማሁሽ ነው፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— እሱን ገዛሁልህና በቀደም አንድ ሰርግ ላይ ስሄድ ሰርግነቱ ቀረና ሁሉም ሰው እኔ ላይ አያፈጥ መሰለህ…
አንድዬ፡— ቆይ በደንብ አስረጂኝ… የውስጥ ሱሪ ውፍረት ይጨምራል ነው የምተዪኝ!
ምስኪኗ ሀበሻ፡— ሳይሆን በቃ ዳሌና ዳሌ አካባቢ ያሰፋና ወፍራም ያስመስላል፡፡
አንድዬ፡— አንቺ ቀጭን ነኝ ካልሽ ለምን ለሰውነትሽ የሚስማማ ልብስ አትለብሺም?
ምስኪኗ ሀበሻ፡— የሰዉስ ዓይን አንድዬ፣ የሰዉስ ዓይን!  ሽንኩርት እንኳን በቢላ እንደዛ አይላጥም፡ ዓይናቸው ቆዳና ስጋን አንድ ላይ ግሽልጥ ነው የሚያደርገው!
አንድዬ፡— አሁን ምን አድርግልኝ እያልሽ ነው…
ምስኪኗ ሀበሻ፡— ምቀኞችን አስታግስልኝ፣ ለቀቅ አድርጓት በልልኝ፡፡
አንድዬ፡— (ይስቃል) አሁንስ ሱቅ ዕጣን ግዛ ብለሽ የምትልኪኝ ነው የመሰለኝ፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንደዬ ኧረ በስመአብ በል! ይቅርታ… እኔው ራሴ ራሴ እላለሁ፡፡
አንድዬ፡— ከሰሙኝ እነግርልሻለሁ፡ ካልሰሙኝ ደግሞ ምን ይደረጋል፡፡ እናንተ እንደሆነ እኔን መስማት ካቆማችሁ ይኸው ስንትና ስንት ዘመን ሆነ!  በይ ለዛሬ ይበቃሻል፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እንደው ሰሞኑን እንደገና ባስቸግርህ ትፈቅድልኛለህ?
አንድዬ፡— ዛሬስ መቼ ያስፈቀድሽኝን!...በይ ፈቅጄልሻለሁ፡፡ ደህና ሁኚ፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ እንዴት እንደማመሰግንህ…
አንድዬ፡— ግዴለም ሌላ ጊዜ ይደርሳል፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 5510 times