Saturday, 23 April 2016 10:39

“ሄሎካሽ” የኅብረተሰቡን ሕይወት ለማቅለል እየሰራሁ ነው አለ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

     ሃሎካሽ የተሰኘ በወኪሎች አማካኝነት የሚሰጥ የባንክ አገልግሎት የንግድ ተቋማት የባንክ ወኪል ሆነው አገልግሎት የሚሰጡበት እና ገንዘብን በሞባይል የሚያንቀሳቅስ አገልግሎት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊ አገር ናት፣ በመላ አገሪቱ በተለይ በገጠር የባንክ ቅርንጫፍ ለመክፈት ከባድ ነው። አንድ ቅርንጫፍ ለመክፈት 4 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል፡፡ ይህን ወጪ ለመመለስ ደግሞ ሁለት ዓመት ይጠይቃል፡፡ ይህ ደግሞ የባንክ ቅርንጫፎች ተደራሽነት ላይ እንቅፋት ይሆናል፡፡
“የእኛ ዓላማ ኅብረተሰቡ ሞባይል ስልኩን በመጠቀም ሕይወቱን እንዲያሻሽል ወይም ሕይወቱን ቀላል እንዲያደርግ ነው” ይላሉ፤ የሃሎካሽ ኤጀንት ኔትዎርክ ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ጉልላት ሃሎካሽ ቀላል እና ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ነው። በሃሎካሽ ለመገልገል የሚያስፈልገው ሕጋዊ መታወቂያና ማንኛውም ዓይነት ሞባይል ስልክ ብቻ ነው፡፡
ሃሎካሽ ወኪል ጋር ሄደው የአገልግሎት ተጠቃሚ መሆን እንደሚፈልጉ ሲነግሩት መታወቂያዎን በማየት ፎርም ይሞላል፤ ስልክ ቁጥርዎን ይመዘግባል፡፡ ተመሳሳይ ያልሆኑ 4 ቁጥሮች በሞባይልዎ ይጽፋሉ፡፡ ያ ምስጢራዊ ቁጥር (ፒንኮድ) ገንዘብ ተቋሙ ጋ ይሄዳል፤ ተመዝገቡ ማለት ነው፡፡ ከተመዘገቡ በኋላ ገንዘብ ማስቀመጥ (ማጠራቀም) ነው፡፡ ለምሳሌ 2000 ብር አስቀመጡ ወይም ለወኪሉ ሰጡት እንበል፡፡ ወኪሉ ገንዘቡን ተቀብሎ ከራሱ ሂሳብ (አካውንት) ወደ እርስዎ ሂሳብ 2000 ብር ያስተላልፋል፡፡ ዜሮ ባላንስ የነበረው የእርስዎ ሂሳብ 2000 ይሆናል፡፡ ከሂሳብዎ ላይ 1500 ብር ለእናትዎ ላኩ እንበል፡፡ እናትዎ በአቅራቢያቸው ወዳለው ወኪል ጋ ሄደው ገንዘብ እንደተላከላቸው ሲጠይቁት፤ ከእሳቸው ሂሳብ ተቀንሶ ወኪሉ ሂሳብ ይጨመርና ገንዘቡን ይሰጣቸዋል፡፡
ሃሎካሽ በአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ፤ በኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክና በሶማሌ ማይክሮ ፋይናንስ የሚሰጥ አገልግሎት ሲሆን ቤልካሽ የተባለ ኩባንያ ደግሞ ለአገልግሎቱ የሚያስፈልገውን ቴክኖሎጂ ያቀርባል፡፡ በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ  ከሁለት ሺህ በላይ ወኪሎችና ከሁለት መቶ ሺህ በላይ ተጠቃሚዎች አሉት፡፡
አንድ ሰው የቤት ኪራይ፣ የመብራት፣ የውሃ፣ የስልክ… ክፍያዎችን የሚፈጽመው በትራንስፖርት ተጓጉዞና ጊዜውን አቃጥሎ ነው፡፡ በሃሎካሽ ሞባይሉን በመጠቀም እቤቱ ሆኖ እነዚህን ክፍያዎች በቀላሉ መፈጸም ይችላል ብለዋል አቶ አብርሃም፡፡
ሃሎካሽ 35 በመቶ የገንዘብ ማስተላለፍ የሚፈጽመው በአዲስ አበባ አካባቢ ሲሆን 65 በመቶ በክልሎች ነው፡፡ የሶማሌ ክልል ክልሎች ጋር ሲነፃፀር ኅብረተሰቡ አዲስ ነገርን ቶሎ የመቀበል ዝንባሌ ስላለው የገንዘብ መቀባበሉ ባህል ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህ ክልል በቀን 2.5 ሚሊዮን ብር ሲንቀሳቀስ፣ በአዲስ አበባ አካባቢ በቀን 1 ሚሊዮን ብር ያህል እንደሚንቀሳቀስ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
 የዚህ ቴክኖሎጂ አቅራቢ ድርጅቱ  የሆነው ቤልካሽ   ሃሎ ዶክተርና ፣ ሃሎ ሥራ እና  ሃሎ ገበያ የተባሉ  ሥራዎች እያከናወነ ሲሆን ወደፊት ለመጀመር ያቀዳቸው ደግሞ ሃሎ ቢል፣ ሰላም ባስን ቦታ መያዝ፣ ምግብ ማዘዝ… የመሳሰሉትን አገልግሎቶች ይጀምራል፡፡ ሃሎ ዲል የተባለም አገልግሎት ይሰጣል፡፡ አንድ ሰው ስማርት ፎን መግዛት ቢፈልግ ጥያቄውን ለሃሎካሽ ያቀርባል። ሃሎካሽም በስሩ ለተመዘገቡ ኩባንያዎች ይልካል። ኩባንያዎቹም ዓይነቱና ዋጋውን ለገዥው ይልኩለታል፡፡ ገዥውም ዋጋውን አማርጦ የተስማማውን ይገዛል ማለት ነው።
ወደፊት አሁን ያሉትን 2000 ወኪሎች ወደ 15 እና 20 ሺህ ማሳደግ፣ አሁን ያሉትን 200 ሺህ ደንበኞች ወደ 20 ሚሊዮን ማድረስ፣ ህዝቡን ሞባይል ስልክ በመጠቀም ህይወቱን ቀላል እንዲያደርግ ማስተማር፣ አሁን ያሉትን 250 ሰራተኞች ቁጥር ማሳደግ… የወደፊት ዕቅዳቸው መሆኑን አቶ አብርሃም ጉልላት ገልጸዋል፡፡

Read 1909 times