Saturday, 23 April 2016 10:47

ቅጣት ለሌላውም አስተማሪ ቢሆን...

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

  ልጅቷ አምስት አመትዋ ነው። ምንም አትናገርም። ተገዳ መደፈርዋን ቤተሰቦችዋም በቶሎ አላወቁላትም። እሱዋም አልተናገረችም። ላለመናገርዋ ምክንያቱ ደግሞ አስገድዶ የደፈራት ሰው ብትናገሪ እገድልሻለሁ ብሎ ስላስፈራራት ነው። ከሁለት ሳምንት በሁዋላ ልጅቱ ወደሆስፒታል ስትመጣ... በምትደፈርበት ወቅት ማህጸኑዋ በመተርተሩ ...ማህጸ ንዋና በአካባቢው ያለው አካልዋ በሙሉ በከፍተኛ ሁኔታ ቆስሎአል። ሆድዋ መግል ይዞ አል። የነበራት እጣ ፈንታ ገና የአምስት አመት ልጅ ብትሆንም ማህጸንዋን ኦፕራሲዮን አድርጎ ማስወጣት ብቻ ነበር። የሚያሳዝነው ነገር ...በከፍተኛ ሁኔታ የቆሰለው ማህጸን በኦፕራሲዮን ከወጣ በሁዋላ አለመትረፍዋ ነው። መድሀኒት እየወሰደች ባለችበት ሁኔታ ከአምስት ቀን በሁዋላ (Septic shock) በሚባል በሽታ ምክንያት ሕይወትዋን ማትረፍ አልተቻለም።
ዶ/ር ኑሩ መሐመድ ኡመር
ከላይ ያነበባችሁት ምስክርነት የዶ/ር ኑሩ መሐመድ ኡመር ነው። በስራቸው ያጋጠማቸውን አሳዛኝ ሁኔታ ሲገልጹ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እየተበራከተ ለመሄዱ አንዱ ምክንያት ህጉ በትክክል ተግባር ላይ አለመዋሉና ለሌላው አስተማሪ አለመሆኑ ነው ብለዋል።
ዶ/ር ኑሩ መሐመድ ኡመር በአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የጽንስና ማህጸን ህክምና የድህረ ምረቃ ተማሪ ናቸው።
ዶ/ር ኑሩ መሐመድ ኡመርን በአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ያነጋገርናቸው ባለፈው ሳምንት የጀመርነው ልዩ ፍላጎት ያላቸው ሕጻናት በአንድ ማእከል ሁሉንም አገልግሎት የማግኘታቸውን ልምድ ለሌሎችም ለማካፈል እንዲያመች በስፍራው ተገኝተን ሁኔታውን በመከታ ተላችን ነው። ይህ ማእከል ተገዶ በመደፈር ብቻም ሳይሆን በማንኛውም መልኩ ጉዳት ለደረሰባቸው ሕጻናት የህክምናው፣ የፖሊስ፣ የህግ አገልግሎት እና የስነልቡና የምክር አገል ግሎት የሚሰጥበት ማእከል ለምን እንደተመሰረተ የሚነግሩን የስነ ልቡና ባለሙያው አቶ መኮንን በለጠ ይባላሉ።
“ሕጻናቶቹ ችግር ተፈጥሮባቸው እና አገልግሎቱን ፈልገው ሲመጡ ከሚታይባቸው ባህርይ መካከል ሰው መሸሽና መጥላት ይገኝበታል። በማእከሉ ግን ፖሊስንም ሐኪሙንም እንዲሁም ማንኛውንም ባለሙያ እንዳይፈሩ በአሻንጉሊት እየተጫወቱ እና የተለያዩ ስእሎችን እያዩ ችግሩን በተቻለ መጠን እንዲረሱና እውነታውን በትክክል እንዲናገሩ ተደርጎ መረጃ የሚሰጡበት ነው። የህክምናውን ዘርፍ ስንመለከት ወደማእከሉ የሚመጡ ሕጻናት የሚታከሙት ከሙያ ባሻገር በተለይ በሚገባ የሰለጠኑ የህክምና ባለሙያዎች ስለሚያክሙዋቸው በትክክል ጤንነታቸው እንዲስተካከል እንዲሁም ወደሕግ የሚተላለፈው መረጃ ጥቃት አድራሹ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ ያስችላል። ከዚህም በተጨማሪ በተለያየ ሙያ ውስጥ የምንገኝ ባለሙያዎች ስለሕጻናቱ ያለን እውቀት የተለያየ ነበር። ነገር ግን የስነልቡናና ማህበራዊ ድጋፉ ምን መሆን አለበት የሚለው ሳይንስ ሁሉም ከሚያይበት ሙያ ወጣ ባለ መልኩ ችግራቸውን ለመረዳት ዝግጁ ስለሆነ እዚህ ቦታ ላይ በጣም ተጎድተው አይደለም ...በስስ ተጎድተው የሚሄዱ ሕጻናት ሁሉ ቁጥራቸው እየቀነሰ ነው። ከተለያዩ አካላት የሚሰጠን አስተያየትም እፎይታን ፈጠራችሁልን...ተገላገልን...ፍጹም የሆነ ስራ መሰራት ባይቻልም አንጻራዊ በሆነ መልኩ ግን ማእከሉ ጥሩ ስራ እየሰራ ነው የሚል ምስክርነት ተቸሮታል” ብለዋል አቶ መኮንን።
ዶ/ር ደሳለኝ ፈቃዱ በአደማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የቀዶ ህክምና የድህረ ምረቃ ተማሪ ሲሆኑ ወንዶች ተገዶ የመደፈር ወንጀል ሲፈጸምባቸው ሕክምና የሚሰጡ ባለሙያ ናቸው። ዶ/ር ደሳለኝ እንደሚሉት...
“የወንዶች ተገዶ መደፈር በየጊዜው ቁጥሩ እየጨመረና እየተባባሰ ነው። እንደጊዜውና አካባቢውም ሁኔታው ይለያያል። ለምሳሌ በአዳማ በተለይም ጫት እና ሺሻ የሚጠቀሙ እንዲሁም መጠጥ የሚጠጡ ወጣቶች ባሉበት አካባቢ ይህ ጥፋት በሰፊው የሚፈጸም ነው። በትምህርት ቤትም ከፍ ከፍ ያሉ ተማሪዎች በእድሜያቸው አነስ ያሉትን አስገድደው ይደፍራሉ። ወጣቶቹ እርስ በእርሳቸው ይህንን አድርጌአለሁ እየተባባሉ እርስ በእርስ በመማማርም ሙከራውን የሚያደርጉ አሉ። ወንዶች ልጆች ተገደው ሲደፈሩ አካላቸው ይደማል። በተለይም ግንኙነቱን የፈጸመው ሰው ከተደፋሪው እጅግ የላቀ ከሆነ ሰገራቸውን መቆጣጠር እስኪያቅታቸው ድረስ ጉዳት ይደርስባቸዋል። ኤችአይቪ ኤይድሰ፣ ሄፒታይተስ የመሳሰሉት በሽታዎች ከመተላለፋቸውም በላይ በኢንፌክሽን ምክንያት ብዙ የሚሰቃዩ ልጆች አሉ። ሕክምናው እስከ ቀዶ ሕክምና ድረስ ከፍ ሊልም ይችላል” ብለዋል።
ዶ/ር ኑሩ መሐመድ ኡመር ተገዶ መደፈር እድሜ አይወስነውም ብለዋል።
“ተገዶ መደፈር እድሜ አይወስነውም። ከ50 አመት በላይ የሆኑ ሴት ተገደው ተደፍረው ለህክምና መጥተዋል። ሕጻናቱ ደግሞ ከ5-7ወር ድረስ ያሉ ተገደው ተደፍ ረዋል። በእርግጥ ደፋሪዎቹ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ናቸው ሊባል ይችላል። ነገር ግን በአብዛኛው ጥቃቱ የሚፈጸመው በቅርብ ባሉ፣ በሚታወቁ፣ በሚታመኑ፣ ቤተሰብ በሆኑ ሰዎች ነው። ስለዚህ ቤተሰብ በተቻለ መጠን መጠንቀቅ ይገባዋል። የልጆችን አዋዋልና አቅጣጫ በተለይም ወላጆች ወደ ልጆቹ ቀረብ ብለው በነጻነት ውይይት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ልጆች በግልጽ የሆኑትን ነገር ለቤተሰባቸው እንዲናገሩ፣ ድብቅ እንዳይሆኑ እየነገሩ ማሳደግ ተገቢ ነው። በሌላም በኩል የህዝብ መገናኛ ብዙሀን ስለመደፈር አስከፊነት በግልጽ ህብረተሰቡን ማስተማር መቻል አለባቸው። ህብረተሰቡ ካልተማረ እና ልጆቹም እራሳቸውን መከላከል ካልቻሉ ጉዳቱ የከፋ ነው። በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ እራስን ለመከላከል በማይችሉበት እድሜ መደፈር እንደሚገጥም የታወቀ ነው። ነገር ግን ህብረተሰቡ በሚገባ ምን ማድረግ እንዳለበት አስቀድሞ ማወቁ ጠቃሚ ይሆናል። ሌላው ነገር... ያጠፋው ሰው በህግ ሲቀጣ ቅጣቱ ለሌሎችም አስተማሪ መሆን ይገባዋል። አንድ የማስታውሰው ነገር አለ... ‘አንድ ሰው አንዲትን ህጻን ልጅ አስገድዶ በመድፈሩ ለአስር አመት እስራት ተፈረደበት። ነገር ግን ገና በሶስት ወሩ መንገድ ላይ ሲያገኘኝ ...አስፈረዳችሁብኝ አይደል? እንገናኛለን...ግድየለም’ በማለት ነበር ዝቶብኝ የሄደው... ህብረተሰቡን በሁለት መንገድ ማስተማር ይቻላል። በአንድ በኩል በበጎ መልኩ እያባበሉ ትምሀርት እየሰጡ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ላጠፋው ጥፋት ተገቢውን ቅጣት እየሰጡ መሆን ይባዋል” ብለዋል ዶ/ር ኑሩ መሐመድ ኡመር ።
አቶ መኮንን በለጠ የስነልቡና ባለሙያ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህጻናት ሁሉንም አገልግሎት በአንድ ማእከል የሚያገኙበት ስፍራን አመሰራረት እንደሚከተለው አብራርተዋል ።
“በአዳማ ከተማ ውስጥ ተጥለው የተገኙ ህጻናት በብዛት ይገኙ ነበር። ተጥለው የተገኙትን ህጻናት ማህበረሰብ በማግኘት ለፖሊስ ሪፖርት ያደርጋል። ፖሊስ ደግሞ በቅድሚያ የጤንነት ሁኔታቸውን ለማረጋገጥ የሚመጣው ወደሆስፒታል ነው። ጤንነታቸው ከተረጋገጠ በሁዋላ ልጆቹ ለእንክብካቤ የሚወሰዱት እስር ቤት ወደአሉ ሴት እስረኞች ይሆናል። ፈቃደኛ የሆነ ድርጅትም ሆነ ግለሰብ እስኪገኝ ድረስ ሕጻናቱ የሚቆዩት በዚህ ሁኔታ ነበር። ቀድሞ የጎዳና ህጻናት ወደጆች ኢትዮጵያ ማህበር ይባል በነበረው መስሪያ ቤት ሁኔታው ሲጠና በመንገድ ላይ ተጥለው የሚገኙ ህጻናት የሚወለዱት ተገደው ከተደፈሩ ሴቶች መሆኑ ተረጋገጠ። የጥናቱ ውጤትም ይፋ ሲሆን የሚመለከታቸው የህብረተሰብ አባላት በሙሉ እድርና የሴት ባልትና፣ ማህበር የመሳሰሉት ሁሉ ተሰብስበው በጉዳዩ ላይ ሲመክሩ በስተመጨረሻም የአዳማ ከተማ ከንቲባ ቢሮ፣ የአዳማ ሆስፒታል ሀላፊዎች እንዲሁም የጎዳና ተዳዳሪ ወዳጆች ኢትዮጵያ ማህበር የአዳማ ቅርንጫፍ በጋራ በመመካከር ... የተጣሉ ሕጻናት ማቆያ... እንዲኖር ወሰኑ። ስለዚህም ተገደው የተደፈሩ ሕጻናት አገልግሎት የሚያገኙበት ይህ ማእከል ሲቋቋም የአዳማ ሆስፒታል ቦታውን በነጻ ሰጠ፣ የከተማው ከንቲባ ቢሮ የተወሰነ ገንዘብ ያዋጣ ሲሆን የጎዳና ተዳዳሪ ሕጻናት ማህበር ግንባታውን ጨርሶ ባለሙያዎችን ቀጥሮ ስራ እንዲጀመር ተደርጎአል።
አቶ መኮንን በለጠ የስነልቡና ባለሙያ አክለው እንዳብራሩት ልዩ ፍላጎት ያላቸው ሕጻናት የሚገለገሉበት ይህ ማእከል ከተመሰረተና ስራ ከጀመረ ወዲህ ባለሙያዎቹ የጋራ ምላሽ በጋራ አስተሳሰብና ግንዛቤ መፍጠር ስለጀመርን እኛ ባለሙያዎች እራሳችን የነበረንን እውቀት በተሻለ መንገድ ለማሳደግ ረድቶናል። ይህ አሰራራችን እኛን ባለሙያዎቹን ወደተሟላ ስብእናና ወደተሟላ አመለካከት እንድንገባ ያደረገን ነው። ስለዚህ ጠቀሜታው አገልግሎቱን ለሚወስዱ ብቻ ሳይሆን አገልግሎቱን ለምንሰጠው ሰዎች የተቀራረበ አስተሳሰብ፣ የተቀራረበ እንክብካቤ፣ የተቀራረበ ፍቅር ለተገልጋዮቹ ሰጥተን ተደስተው እንዲሄዱ የማድረግ ብቃታችን እየጨመረ እንዲሄድ ረድቶናል” ብለዋል።
ለወንድና ሴት ሕጻናቱ አገልግሎቱን በተበታተነ መልኩ የሚሰጡ ሁሉ አገልግሎቱን ወደ አንድ ማእከል ለማምጣት የሚያስችላቸውን የስራ ልምድ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆናቸውንና ለመጎብኘት ለሚፈልጉ ሁሉ በራቸው ክፍት መሆኑን አቶ መከኮንን በለጠ የስነልቡና ባለሙያ በስተመጨረሻው ገልጸዋል።

Read 1626 times