Saturday, 30 April 2016 11:21

የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ለሰጡት ቃለምልልስ የተሰጠ ምላሽ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

እንደሻው እምሻው
(የሰማያዊ የፅ/ቤትና አስተዳደር ኃላፊ)

   ባለፈው ሚያዝያ 8 ቀን 2008 ዓ.ም በወጣው የጋዜጣችሁ፣የነጻ አስተያየት አምድ ላይ “ሰማያዊ ፓርቲ አደጋ ላይ ነው; በሚል ርዕስ፣ ከፓርቲያችን ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ጋር ያደረጋችሁትን ቃለ ምልልስ አነበብኩት፡፡ ሊቀመንበሩ አንድም ጊዜ እንኳን እየመራሁት ነው የሚለውን ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ ሳይጠቅስ፣ የፓርቲውን ተቋማት ሁሉ እንደፈለገው ሲዘልፋቸው በመታዘቤ እኔም ይህን መልስ ለመጻፍ ተገደድኩ፡፡
ፓርቲያችን ሰማያዊ ጠቅላላ ጉባኤውን በነሀሴ 16 እና 17 2007 ዓ.ም ባደረገ ወቅት በብዙ ጉዳዮች ላይ የተወያየ ሲሆን ብሔራዊ ምክር ቤቱን፣ኦዲትንና ሊቀመንበሩን መርጦ ነበር የተጠናቀቀው፡፡ በፓርቲያችን መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 6፣ ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረትም፤ እኔም ሆንኩ አሁን የስራ አስፈጻሚ አባላት የሆኑት ለብሔራዊ ምክር ቤት አባልነት ተወዳድረናል፡፡ ጠቅላላ ጉባኤውም 37 ቋሚ፣ 13 ተለዋጭ የምክር ቤት አባላትንና አምስት የኦዲትና ምርመራ ኮምሽን አባላትን ከመረጠ በኋላ፣ የምክር ቤቱ አራተኛ ዓመት መስራች ስብሰባ ጳጉሜ 1 ቀን 2007 ዓ.ም ተካሂዶ፣ አቶ ይድነቃቸው ከበደን የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አድርጎ መረጠ፡፡ ከዛም በኋላ ከፓርቲው የጠቅላላ ጉባኤ ሰነድ ጋር ጳጉሜ 3 ቀን 2007 ዓ.ም አሁን የሰማያዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት (ያን ጊዜ የም/ቤት አባላት ነበሩ) ዝርዝራቸው ለምርጫ ቦርድ ገባ፡፡
እንግዲህ ተመልከቱ፤ሊቀመንበሩ ሁለት ገጽ ሽፋን በተሰጠው ቃለ ምልልስ፣ አንድም ጊዜ የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ ጠቅሶ ለማብራራት አልሞከረም፡፡ እንደገና የም/ቤቱ አራተኛ ዓመት አንደኛ መደበኛ ስብሰባ መስከረም 9 ቀን 2008 ዓ.ም ሲደረግ ይልቃል ለስራ አስፈጻሚነት ያጫቸውን እጩዎች በም/ቤቱ እንዲጸድቅለት ሲጠይቅ፣ ከቋሚ የም/ቤት አባላት ውስጥ ስምንቱን፣ ከተለዋጭ አባላት ውስጥ ደግሞ ሁለቱን አምጥቶ ስምንቱ እጩዎች የም/ቤት ድምጽ የመስጠት መብታቸው ሳይነሳ ድምጽ እየሰጡ ሰባቱ ካለፉ በኋላ ቀሪዎቹ ባለባቸው ችግር ምክንያት ም/ቤቱ ጣላቸው፡፡ ይህ እንግዲህ የሆነው በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ነው፡፡
ከዛ ተራው የፅ/ቤትና አስተዳደር ኃላፊ ሆነና ይልቃልና አዲሱ የም/ቤት ሰብሳቢ ተነጋግረው፣ በአንድ የስራ ቀን ሰብሳቢው ቢሮ መጥቶ፣“ከፅ/ቤት ኃላፊነትና ከም/ቤት አባልነት የቱን ትመርጣለህ; ብሎ ጠየቀኝ፡፡ እኔም “እዚሁ የፅ/ቤትና አስተዳደር ኃላፊ ሆኜ መቀጠል ነው የምፈልግው; በማለት ከመለስኩለት በኋላ የም/ቤት አባልነቴን ለቅቄያለሁ፡፡ እንግዲህ ይልቃል ይህን እያወቀ ነው ደንብ ሳይጠቅስ ዳር ዳሩን እየሄደ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብና አባላትን ለማደናገር የሚሞክረው፡፡ ሌላው የፓርቲያችን መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 37 የፅ/ቤትና አስተዳደር ኃላፊው ተጠሪነቱ ለም/ቤቱና ለሊቀመንበሩ ነው ይላል፡፡ ከዛ ደግሞ አንቀጽ 10/8 ደግሞ ከፓርቲው አባላት መካከል በምክር ቤት ሰብሳቢውና በሊቀመንበሩ በጋራ ተመርጦ የፅ/ቤትና አስተዳደር ኃላፊ ይሆናል ካለ በኋላ የምክር ቤት አባል ከሆነ ወንበሩን ለቆ በተለዋጭ አባል ይተካል ይላል፡፡ እንዲሁም አንቀጽ 10/13፤ የፅ/ቤት ኃላፊው በራሳቸው ፈቃድ ከለቀቁ ወይም የዲስፕሊን ጉድለት መፈጸማቸው አግባብ ባለው አካል ተረጋግጦ ከኃላፊነታቸው እንዲለቁ ሲደረግ፣ በቦታቸው በአንቀጽ 10/8 መሰረት ሌላ ሰው ይተካል ይላል፡፡
ሊቀመንበሩ ውሃ በማይቋጥር ቃለ ምልልሱ፤ አውቆ ሳይሆን የሚመራውን ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ ስለማያውቀው፣ ስለ እኔ ኃላፊነት ብዙ አውርቷል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የፅ/ቤት ኃላፊው ንብረትና ማህተም አላስረክብም ብሎ አሻፈረኝ ብሏል ይላል፤ማን ጠይቆኝ ለማንስ ላስረክብ ? እሱ እንዳደረገው ወይም እንደጻፈው ደብዳቤ፣ (“በሶስት ቀን ውስጥ ንብረት አስረክበህ ውጣ; ብሎ ነበር) ላድርግ? አላደርግም፡፡ ደንባችንም አይፈቅድም፡፡ ም/ቤቱም ሆነ ኦዲትና ምርመራ ኮምሽንም ከደንባችን አኳያ ይህን እንዳደርግ አልፈቀዱም፡፡
ይልቃል ስለ ጠቅላላ ጉባኤው፣ አራምባና ቆቦ የሚረግጥ መልስ ይሰጣል፡፡ ጉባኤው ከመድረሱ ሁለት ቀን በፊት ዮናታን ለይልቃል ድምጽ እንደሚሰጥ በፌስቡክ ገልጾ ነበር፡፡ የማይደርስ የለምና ጉባኤው ደርሶ ነሀሴ 17 ቀን 2007 ዓ.ም በተደረገው የሊቀመንበርነት ምርጫ ላይ ግን ሌሎቹ የተጠቆሙት አንወዳደርም ሲሉ፣ ዮናታን እንደ ይልቃል በግሉ እንደሚወዳደር በመግለጽ ለእጩነት ቀረበ፡፡ በሁለቱ መካከል በተደረገ የምርጫ ክርክርም፤ ዮናታን የውሸትም ቢሆን የጉባኤተኛውን ቀልብ ሳበ፡፡ በእያስጴድና በዮናስ ከድር አማካኝነት በጉባኤተኛው መካከል እየገቡ ዮናታንን እንዳትመርጡ እያሉ በመቀስቀሳቸው በውጤቱ ዮናታን 66 ድምጽ፣ ይልቃል ደግሞ 136 ድምጽ በማግኘት ምርጫውን ቢያሸንፍም በኋላ ላይ ሁለቱም ስለ ምርጫው የተሰማቸውን አስተያየት እንዲሰጡ በአስመራጭ ኮሚቴው እድል ይሰጣቸዋል፡፡ ዮናታን በሰጠው አስተያየት፤የዛሬ ሶስት ዓመት ሰላሳ ዓመት ስለሚሞላኝ ልምድ ይሆነኛል ሲል፣ ይልቃል ግን በገዛ እጄ አስጠግቼ ጉድ ሆኜ ነበር ብሏል፡፡ የጉባኤውን ፊልም በማየት ይሄን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ዮናታንም በአዲሱ የይልቃል ካቢኔ የም/ቤቱን ሙሉ ድምጽ በማግኘት የሕዝብ ግንኙነቱን ስልጣን በድጋሚ ቢረከብም አንድ ወር እንኳን ሳይሰራ ከኃላፊነቱ ለቀቀ፡፡ በኋላም ለእስር በቃ፡፡
በደንባችን አንቀጽ 13 የስራ አስፈጻሚው ስልጣንና ተግባር በሚለው ላይ፣ የስራ አስፈጻሚው ተጠሪነቱ ለሊቀመንበሩና ለስራ አስፈጻሚው መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ከአንድ እስከ 13 ያሉት ንዑስ አንቀጾች በሚያዙት መሰረትም፤ይልቃል ሊቀመንበር ስለሆነ ስራ አስፈጻሚውን ይከታተል ነበር ወይ ለሚለው መልሱን ለራሱ ትቼዋለሁ፡፡ አሁንም ሆነ በፊት የነበሩት ስራ አስፈጻሚዎች አንዳቸውም ቢሆኑ በተለይ አንቀጽ 13 ንዑስ አንቀጽ 10 በሚያዘው መሰረት፤መመሪያውን አዘጋጅቶ በስራ አስፈጻሚ ያጸደቀ የለም፡፡ ይልቃልም እንዲያዘጋጁ አይፈልግም፡፡ ይህን የሚያውቀው እሱ ብቻ ነው፡፡ ም/ቤቱም ይጨቀጭቃል፤ እሺ በማለት ይታለፋል፡፡ እኔም እንደ ኃላፊነቴ፤ በስንት ጭቅጭቅ የፅ/ቤት መመሪያ አዘጋጅቼ በስራ አስፈጻሚው ጸድቆ እየተሰራበት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የፋይናንስ መመሪያው ሲሆን በኃላፊው ተረቆ  በስራ አስፈጻሚው ተገምግሞ፣ በም/ቤቱ የጸደቀ ቢሆንም በመመሪያው መሰረት የገንዘብ አወጣጥ ስርዓቱ ባለመጠበቁ፣አሁን ለተፈጠረው የገንዘብ ሌብነት ምክንያት ሆኗል፡፡  
ይልቃል ከጉባኤ በፊት በሊቀመንበርነት ዘመኑ፣ በደንባችን አንቀጽ 26 መሰረት መስራት ከነበረበት ውስጥ ስንቱን ሰርቷል? በዛን ጊዜ በደንባችን ውስጥ የሌለ፣ በመመሪያ ያልተገለጸ በቃለ ጉባኤ ያልተያዘ ቢሆንም፣ የሙሉ ቀን ሰራተኛ ሆኖ የአምስት ሺህ ብር የወር ደሞዝ ተከፋይ ነበረ፡፡ ክፍያው አሁንም ድረስ ቀጥሏል፡፡ በእነዚህ ሶስት ዓመታት ውስጥ ቀኑን ሙሉ ቢሮ ሲውል ግን አንድ ነጠላ ወረቀት ፅሁፍ እንኳን ለፓርቲው አበርክቶ አያውቅም፡፡ አንቀጽ 26/6፤ በብሔራዊ ምክር ቤቱና በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ መሰረት የሚወጡ ደብዳቤዎችና ሰነዶች ላይ ይፈርማል ይላል፡፡
በእርግጥም እሱን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ከእዚያ ውጪ እድሜ ለቴክኖሎጂ፣በሞባይሉ ጌም ሲጫወትና ሌሎች ተግባራትን ሲያከናውን ነው ጊዜውን የጨረሰው፡፡ አሁን ደግሞ የማያመጣው ሰበብ የለ፣ ከመደብደብ ብዬ ቢሮዬን ወደ ካፌዎች አዛውሬያለሁ ይለናል፡፡
ሌላው ደግሞ በእሱ በኩል ካለው ጎራ፣ ብዙ ተተኪ አመራር ሊሆኑ የሚችሉ ወጣቶች አሉ ይለናል፡፡ ለመሆኑ ይልቃል ደጋፊ እንጂ አባል የሚሆኑ ወጣቶችን በዙሪያው ያስጠጋል? አጠገቡ ያሉት እስቲ በሚጽፉት የፌስቡክ ፅሑፍ ይመዘኑ፡፡ ከይልቃል አመራር ጋር ወደፊት የሚሉና ድርጅትን ሳይሆን ግለሰብ አምላኪ፣እድሜያቸውም ከሃያ አራትና ሃያ አምስት የማይበልጡ እኮ ናቸው፡፡ በመጨረሻ ለይልቃል ጥቂት ጥያቄዎች ላቀርብለት እወዳለሁ፡- “እስቲ በዙሪያህ ሆነው ያንተን ስልጣን ይናፍቁና ይጠብቁ ከነበሩ ወጣቶች ውስጥ ምን ያህሉ ከጠቅላላ ጉባኤ በኋላ እስር ቤት ገቡ? ምን ያህሉ አገር ጥለው ተሰደዱ? ምን ያህሉን በወያኔነት ፈረጅካቸው?; ይህንን ነው መመለስ ያለበት፡፡ ቅድም እንዳልኩት፤ የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ አንቀጾች በግድ ግለጽ አልለውም፡፡
 ለምን ቢባል ? እሱ ቀርቶ አሁን በስራ ላይ ያሉት የስራ አስፈጻሚ አባላት ቁጥር ሰባት መሆናቸውን እንኳን ዘንግቶ፣ስራ አስፈጻሚው በተሟላ መልኩ ስራውን እየሰራ እንደሆነ ነግሮናል፡፡ እናም አልፈርድበትም፡፡





Read 3605 times