Saturday, 30 April 2016 11:32

“ዘመኑ የጡዘት ነው”

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(9 votes)

በዘረኝነት ላይ ኢንተርኔት

  በጋምቤላ የተፈፀመው የጅምላ ግድያና የህፃናት እገታ፤ ዛሬ የተፈጠረ አዲስ አይነት ተግባር አይደለም፡፡ በጐሳ የተቧደኑ ሰዎች፤ በጭፍን እምነትና ክፉ የዘረኝነት ጥላቻን እየዘመሩ፤ በአጐራባች አካባቢዎች ላይ መዝመት፣ መግደልና መዝረፍ፤ አዲስ ፈጠራ አይደለም፡፡ በጋምቤላ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች፣ በመላ አፍሪካና በአለማችን ዙሪያ፤ ለምዕተ ዓመታት ብዙ እልቂት ሲያስከትል የቆየ ጥንታዊ ባህል ነው፡፡
በሌላ አነጋገር ድሮም የነበረ ነገር ነው፡፡ ዛሬ ግን፤ ነገሮችን የሚያጦዝ “ኢምፕሊፋየር” ተገጥሞለታል፡፡ እንዴት?
ህይወትን የማክበር ወይም የማናናቅ አማራጭ፣ እያንዳንዱን ሰው እንደየስራው የመመዘን ፍትሃዊነት፣ አልያም በተወላጅነት የመቧደን ዘረኝነት፣ ሰውን እንደየብቃቱ ማድነቅ አልያም በጅምላ ፍረጃ ተቧድኖ መፋጀት… እነዚህ አማራጮች ሁሉ ድሮም ነበሩ። ዛሬም አሉ፡፡
መምረጥ የሰው ተፈጥሮ ነው።
እንደየምርጫውም፣ ፍሬውን ይጨብጣል፤ መዘዙን ይሸከማል፡፡ ለሕይወትም ሆነ ለመሞት፣ ለስኬትም ሆነ ለጥፋት፣ የዘራውን ያጭዳል።
ይሄ ደግሞ የእውኑ ዓለም ዘላለማዊ ተፈጥሮ ነው።  ድሮም ዛሬም ነገም፣ ጥንትም አሁንም ወደፊትም... የነበረ፣ ያለ፣ የሚኖር።
ዛሬማ፤ እና ዛሬ ምን ተለወጠ? ለክፉም ለደጉም፣ ለስኬትም ለጥፋትም፣ የምርጫዎቻችን ፍሬ እና መዘዝ፣...እንደድሮ እየተንቀራፈፈ፣ በትንሽ በትንሹ፣ በቁጥቁጥ የሚመጡ አይደሉም። ፍጥነታቸው፣ መጠናቸው ስፋታቸው ለጉድ ሆኗል። የስኬት ፍሬው ይትረፈረፋል ወይ የጥፋት መዘዙ ያጥለቀልቃል።
 ሦስቱን አማራጮች ተመልከቱ፡፡
ለአእምሮና ለእውነት ዋጋ በመስጠት ፋንታ ጭፍንነት መያዝ፣
“የሌላ ጎሳ ተወላጅ እውነት ቢናገር እንኳ አትመነው፡፡ የጎሳህ ተወላጅ ከሆነ ግን ቢዋሸህ እንኳ በጭፍን ተከል።”
በጥረት ሃብት ማፍራትንና የንብረት ባለቤትነት መብትን ከማክበር ይልቅ፣ የዝርፊያና የመስዋዕትነት ጐዳናን መከተል፡፡
“ለሌላ ጎሳ ተወላጅ በጥረቱ ሃብት እያፈራ የስራ እድል ቢፈጥልህ እንኳ ንብረቱን ለመዝረፍና ለማቃጠል ዝመትበት፡፡ የራስህ ጎሳ ተወላጆች ግን ቢዘርፉህ እንኳ አሜን ብለህ ተቀበል።”
እያንዳንዱን ሰው እንደየብቃቱ የማድነቅ ቅድስናንና እንደየስራው የመዳኘት ፍትሃዊነትን ከመላበስ ይልቅ፤ በጅምላ ፍረጃ ጭፍን ጥላቻንና የመንጋ ማንነትን ማምለክ፡፡
“የሌላ ጎሳ ተወላጅ የቱንም ያህል ብቃት ተቀዳጅቶ ዘወትር መልካም ተግባር መፈፀም እንኳ፤  ጠላትህ ነው፡፡ ግደለው፡፡ የራስህ ጎሳ ተወላጆች ግን ቢገድሉህ እንኳ ውደዳቸው” ...እንዲህ አይነት የጭፍንነት አስተሳሰቦች፤ የጥፋት ተግባሮችና የጥላቻ ስሜቶች አዲስ አይደሉም፡፡ ጭፍን ሃሳቦች ይሰበካሉ፤ ዘመቻ ይካሄዳል፤ “ገዳዬ ገዳም” እየተባለ ጥላቻ ይጨፈራል ድሮም ዛሬም፡፡
ዛሬ ግን ሮኬት ተገጥሞላቸዋል፡፡
ድሮ ድሮ፣... በበርካታ ቦታዎች በተመሳሳይ ሰዓት ጥቃት ለመፈፀም የሚረዳ የሬድዮና የሞባይል ቴክኖሎጂ አልነበረም። በመልእክተኛ፣ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ወሬ ለማድረስ፣ ረዥም ጊዜና ጉልበት ይጠይቃል።
ድሮ፣ ክላሽንኮቭ እና ባዙቃ አልነበረም። በዱላና በድንጋይ... ከዚያ ካለፈ ደግሞ በጦርና በጎራዴ ነበር፣ የጥቃት ዘመቻ የሚካሄደው። ያለ ብዙ ድካም፣ በአንድ እሩምታ፣ ደርዘን ሰዎችን መግደል አይቻልም ነበር። በአንድ ድንጋይ፣ በጣም ከተሳካ፣ አንዱን ሰው መፈንከትና ማቁሰል ይቻል ነበር። አሁን ግን፣ በአንድ ቦምብ፣ ደርዘኖች ይሞታሉ።
ድሮ፣ ጭፍን ሃሳቦችን ከዳርዳር ለመስበክ፤ በዘር ተጠራርቶ ጥላቻን በስፋትና በፍጥነት ለመዘመር የሚያስችል፣ የኢንተርኔት አውታር አልነበረም። ከቤት ቤት እየዞሩ አልያም የመንደሩን ሰው እየሰበሰቡ፣ ሌት ተቀን፣ ጥላቻን መስበክ ደግሞ አድካሚ ስራ ነው። ዛሬ ግን፣ ከአልጋው ሳይነሳ፣ በኢንተርኔት አማካኝነት ጭፍን ሃሳቦችን መስበክና በተወላጅነት ማቧደን… የዘረኝነትና የጥላቻ መርዝን በፍጥነት ከዳር ዳር መዝራት ይቻላል።
እናም፣ የጭፍንነት፣ የዝርፊያና የዘረኝነት አስተሳሰቦች፤ ዛሬ ዛሬ “አምፕሊፋየር” ተገጥሞላቸዋል ማለት ይቻላል፡፡ መዘዛቸውም ከድሮው እግጅ በጣም የመረረ ሆኗል። የጋምቤላው የጅምላ ግድያ፣ ዝርፊያና እገታ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ምን ያህል ሃዘን፣ ቁጣና ቁጭት እንደፈጠረ መመልከት ትችላላችሁ።
አሳዛኙ ነገር፣ አሰቃቂውን ድርጊት ክፉኛ ብንቃወምም፤ ለአሰቃቂ ድርጊት መነሻ የሆኑ ጠማማ አስተሳሰቦችን በቸልታ እንመለከታለን።
መዘዛቸው የከፋ ሊሆን እንደሚችል፣ በደንብ ብንገነዘብ ኖሮ፣ በጎሳ የመቧደን፣ የመደራጀት፣ በቲፎዞነት የመጮህ ጭፍንነት በየአካባቢው እንደ አሸን ሲፈላ፣ እንደ ቀላል ስህተት ቆጥረን ለማለፍ አንደፍርም ነበር።
የተፃፈ መረጃና ሃሳብ፣ ከመፅሃፍ፣ ከጋዜጣ ወይም ከፌስቡክ ስናነብ፣ የመረጃውን እውነተኛነት አመሳክረን፣ የሃሳቡን ትክክለኛነት አገናዝበን ከመቀበል ወይም ከመተው፣ ከመደገፍ ወይም ከመተቸት ይልቅ፤ የፀሃፊውን ዘር ለመቁጠር የምንቸኩል ከሆነስ? መረጃው እውነተኛ ከሆነ፣ ከአንታርቲካ የመጣ ሰው ቢፅፈው ምን ችግር አለው? ሃሳቡ ትክክለኛ ከሆነ፣ በተለይም አዲስ ግንዛቤ የሚጨምርልን ከሆነ፣ ከማርስ አልያም ከጁፒተር የመጣ ፍጡር ቢፅፈው፣ ምን ችግር አለው? የመረጃዎችን እውነተኛነት በማመሳከርና የሃሳቦችን ትክክለኛነት በማገናዘብ አስተያየት ከመስጠት ይልቅ እንጂ፤ የፀሐፊውን የዘር ሀረግ በመቁጠር ቲፎዘር ተሳዳቢ የመሆን ሙከራዎች ሲበራከቱ እያየን ካልተቃወምን፤ የጋምቤላው አይነት እልቂትን በአገር ደረጃ መደገስ ይሆናል፡፡ እያንዳንዱን ሰው በድርጊቱና በባህርይው ከመመዘን ይልቅ በጅምላ የመፈረጅ ልምድ ሲስፋፋ እያየን ዝም ካልንም፤ የጥፋት ድግስ ተካፋይ እንሆናለን፡፡
ኢትዮጵያ ለሺ አመታት እንዲህ አይነት የጥፋት ድግሶችን አስተናግዳለች፡፡ አሳልፋለች፡፡ የዛሬ ልዩ የሚሆነው፤ “አምፕሊፋየር” የተገጠመለት የጦዘ ዘመን ላይ በመሆናችን ነው፡፡ የጦዘ ጥፋት ደግሞ፤ ለማገገም እድል አይሰጥም፡፡

 የተመራቂ ወጣቶች መበራከት

በ2001 ዓ.ም፤ እድሜያቸው ሃያ እና ከዚያ በላይ የሆኑ የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር 6.5 ሚሊዮን ገደማ ነበር። ከእነዚህ ውስጥ 760ሺ ያህሉ በዲፕሎም ወይም በዲግሪ የተመረቁ ናቸው።
ዛሬስ? የነዋሪው ቁጥር ጨምሯል ሃያ እና ከዚያ በላይ እድሜ ያላቸው የከተማ ነዋሪዎ ቁጥር 7.7 ሚሊዮን ሆኗል። ከእነዚህ ውስጥ 1.7 ሚሊዮኑ የዲፕሎማ ወይም የዲግሪ ተመራቂዎች ናቸው፡፡
ኮሌጅና ዩኒቨርስቲ ገብቶ የተማረ ወጣት፣ ስራ በመቀጠር አልያም ስራ በመፍጠር ኑሮውን በፍጥነት የማሻሻል እድል ይኖረዋል፡፡ ትምህርት፣ ለወጣት የስኬት “ሮኬት” ሊሆንለት ይችላል - (በአግባቡ ከተማረና የአገሪቱ ባህልና የኢኮኖሚ ስርዓት ለቢዝነስ የሚያመች ሆነ)።
በአግባቡ ካልተማረስ? የአገሪቱ ኋላቀር ባህልና የኢኮኖሚ ስርዓት፣ የቢዝነስ እንቅስቃሴን የሚያናንቅና የሚያደናቅፍ ከሆነ? ያኔ ችግር ይኖራል።
በብዙ የቀድሞ አባቶች ላይ እንደሚታየው፣ በዲፕሎማና በዲግሪ የተመረቁ ወጣቶች፣ የወትሮውን የድህነት ኑሮ በፀጋ የመቀበልና የመሸከም ትዕግስት ይኖራቸዋል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው። የቀድሞ ሰዎች፣ የኑሮ ችጋርና ድህነት ሲደራረብባቸው፣ “ባለመማሬ ነው” በማለት ሕይወታቸውን ለመግፋት ሞክረው ይሆናል። ተመርቆ የወጣው የዛሬ ወጣት ግን፣ እንደዚያ የማለት እድል የለውም። “ለተሻለ ኑሮ የሚመጥን ብቃት (ዲግሪ) ይዣለሁ። ኑሮዬ መሻሻል ይገባዋል” ብሎ የሚያስብ ወጣት ይበራከታል። እንዲህ እንዳሰበው፣ ኑሮው ካልተሻሻለስ? “እዚህ አገር ውስጥ አያልፍልኝም” ብሎ እየተማረረ፣ ለስደት ይነሳል። በ2005 ዓ.ም ወደ የመን የገቡ የኢትዮጵያ ስደተኞች 55ሺ ነበሩ። ከዚያ ወዲህ፣ ያቺ አገር በጦርነት ብትታመስም፣ ስደቱ አልቀነሰም። ዘንድሮ፣ በግማሽ አመት ውስጥ 55ሺ ኢትዮጵያዊያን በስደት፣ የመን ገብተዋል።
እንዲያም ሆኖ፤ በድህነት የተማረረ ወጣት በሙሉ፣ ይሰደዳል ማለት አይደለም። አብዛኛው ተመራቂ ወጣት፣ እዚሁ አገሩ ውስጥ ነው የሚፍጨረጨረው። እንዳሰበው ሳይሆንለት ሲቀር፣ የስራ እድል ሲያጣ ወይም የቢዝነስ ጅምሩ ሲደናቀፍ፣ እንደ ብዙዎቹ አባቶች “እድሌ ጠማማ” ብሎ የሚቆዝም ይኖራል። በርካታዎቹ ተመራቂዎች ደግሞ፤ “ተምሬያለሁ። ኑሮን የሚያሻሽል ዲግሪና ዲፕሎማ ይዣለሁ። ግን ሕይወቴ አልተሻሻለም። አንዳች አይነት በደል ደርሶብኛል” ብሎ ያጉረመርማል፤ ሲነሽጠውም እንደሐምሌ ነጎድጓድ ያስገመግማል።
ታዲያ፤ ከማጉረምረም (grambling) ወደ ማስገምገም (rumbling) ከዚያም ወደ መተራመስ የሚሸጋገረው፤ እንደ ድሮ እየተንቀራፈፈ አይደለም፡፡ ዘመኑ የጡዘት ነው፡፡ በበርካታ የአረብ አገራት እንዳየነው፣ ገሚሱ ተመራቂ ወጣት፣ በጭፍን ሲደናበር፣ የአመፅ እሳት ይለኩሳል። ገሚሱ፤ ለነውጥ እየተማገደ ይቃጠላል።
በአንድ በኩል፤ “ተምሮ መመረቅ”… ከዲፕሎማውና ከዲግሪው ጋር የሚመጣጠን የሙያ እውቀትንና ብቃትን የማያስጨብጥ የውሸት ትምህርት ከሆነ...
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የሙያ እውቀትንና ብቃት በከንቱ የሚባክን ከሆነ (ማለትም... የአገሪቱ ባህልና የኢኮኖሚ ስርዓት፣ የቢዝነስ ስራን የማያከብርና የሚያደናቅፍ ከሆነ...)  
ያኔ ተመራቂው ወጣት፤ ቴክኖሎጂን የሚፈጥርና የሚገነባ ሳይሆን፣ በቴክኖሎጂ የሚያፈርስና የሚያጠፋ ይሆናል። ሥራን የሚፈጥርና ሃብትን የሚያፈራ ሳይሆን፣ ለዝርፊያ የሚዘምትና ኢንቨስትመንትን የሚያቃጥል ይሆናል። ተመራቂ ተበራከተ ማለት፣ የጥፋት አማራጭን የሚያጦዝ ሰበብ ተበራከተ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን፤ በተቃራኒው፤ በስኬትየ የሚያመጥቅ “ሮኬት” ሊሆንልንም ይችላል - ተመራቂ ሲበዛ፡፡
መቼም ቢሆን፤ ድሮም ሆነ አሁን፤ አካባቢያችንን በማስተዋል እውቀትን መገንዘብ፣ የየራሳችን  ኑሮ ለማሻሻል መጣርና ስኬትን ማጣጣም እንችላለን፡፡ የምርጫ ጉዳይ ነው። በዚህ የስኬት አማራጭ ላይ፤ የትምህርት መስፋፋትና የትምህርት ጥራት ሲታከልበትስ? የስኬት አማራጫችን ይበልጥ፣ ይፋጠናል። ይመጥቃል። “አምፕሊፋይድ” ይሆናል።
በአጭሩ፣ ባለዲፕሎማ እና ባለየዲግሪ እየበዛ ሲመጣ፣ ለአገሪቱ “አምፕሊፋየር” እየገጠምንላት ወይም በአገሪቱ ላይ “አምፕሊፋየር” እየገጠምንባት እንደሆነ ማወቅ ይኖርብናል። ለስኬትም ለጥፋትም፣ ለክፉም ለደጉም፣... ትምህርት ተስፋፋ ማለት፣ የምጥቀት መንኮራኩር መጣልን ወይም የጡዘት መሳሪያ መጣብን እንደማለት ነው።
ቴክኖሎጂም እንደ ትምህርት    
በርካታ ሰው በሚተላለፍበት ጎዳና ላይ፣ እንደ እንስሳ እርስበርስ ለመራገጥ የሚሯሯጡ ውርጋጦች ያጋጥሙናል። ገበያ መሃል፣ ድንጋይ መወራወር፣ አዝናኝ ጨዋታ ሆኖ የሚታያቸው ጋጠወጦችም ሞልተዋል። የአሁኗ ድርጊት፣ ከቅፅበት በኋላ ከምታስከትለው መዘዝ ጋር ለማገናዘብ አይሞክሩም። አንዱን መንገደኛ ገፍትረው ይጥሉታል፤ ሌላኛውን ይፈነክቱታል። እንዲህ አይነት ሰዎች፣ ከቴክኖሎጂ ጋር ሲገናኙ አስቡት።
አደጋው ይጦዛል። በሰዓት 200 ኪሎሜትር የሚወነጨፉ መኪኖችን ይዘው፣ ከተማ ውስጥ መብረር ያምራቸዋል። ከነጭነቱ 300 ኩንታል የሚመዝን ትልቅ ገልባጭ መኪና ሲሆንስ? የአገራችንን የመኪና አደጋ እያያችሁ!
ለከት በሌለው ምላስ፣ ጎረቤትን የሚረብሹ ሰዎችም፣ ከድምፅ ማጉያ ቴክኖሎጂ ጋር ይገናኛሉ። በቃ፤ ሰፈር መንደሩን ይቀውጡታል። ዛሬ ዛሬማ፣ ከተማውን ሁሉ ለማዳረስ የሚንጠራሩ የድምፅ ማጉያዎች መጥተዋል። የሃይማኖት ተቋማትን መታዘብ ትችላላችሁ።    
ለቴክኖሎጂ የሚመጥን ስልጡን አስተሳሰብና ባህል ለመገንባት ከጣርን፤ ትምህርትና ቴክኖሎጂ የስኬት ማቀላጠፊያ አምፕሊፋየር ይሆኑልናል፡፡ ከኋላቀር አስተሳሰብና ባህል ጋር ተጣብቀን ለመቀጠል የምንፈልግ ከሆነ ደግሞ፤ የጥፋት ማጦዚያ ይሆኑብናል፡፡

Read 3997 times