Saturday, 07 May 2016 12:58

“በዓልን እንዴት ነው የምታከብሩት”…ብሎ ነገር

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(15 votes)

እንኳን ለዳግማይ ትንሳኤ አደረሳችሁ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በቀደም ለዶሮ ሦስት መቶ ሀምሳ ብር የተጠየቀ ወዳጃችን… “እኔ ቤት ዶሮ ብርቅዬ እንስሳ እየሆነች ነው…” ሲል ነበር፡፡
የምር ግን ምድረ ‘ስማርትፎን’ ጥቅሙ ይሄኔ ነው፡፡ ልክ ነዋ…ዶሮም ካለች፣ ‘ዕድል በራችንን አንኳኩታ’ በግም የተገዛ ከሆነ ካሁኑ ለታሪክና ለትዝታ በፎቶ ማስቀረት አሪፍ ነው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ልጆች፣ “አባዬ ከእማዬ ጋር ከተጋባችሁ ጀምሮ በግ ገዝታችሁ ታውቃላችሁ?” የሚል ጥያቄ ሲነሳ መልስ ይኖራላ፡፡ አልበም ይወጣል፡፡
“ይኸውላችሁ፣ ልጆች፣ ይሄኛው ፎቶ የዛሬ ስምንት ዓመት ለመጨረሻ ጊዜ ከገዛሁት በግ ጋር ከእናታችሁ ጋር የተነሳነው ነው…ይህኛው ደግሞ የዛሬ ዓመት ጎረቤቶቻችን ‘ኑና ከበጋችን ጋር የማስታወሻ ፎቶ አብራችሁን ተነሱ ሲሉን የተነሳነው ነው…ይህኛው ሦስተኛው ደግሞ በቀደም የገና ዋዜማ ዕለት በአዲሱ ገበያ በግ ተራ በኩል ስናልፍ የተነሳነው ነው…” እያሉ ማስረዳት ይቻላል፡፡
ስሙኝማ…ዕድሜ ለቲቪ የበዓል ልዩ ፕሮግራሞች ይሁንና…ቤታችን በግ ባይኖርም የበግ ጩኸት አይጠፋም፡፡
የምር ግን፣ እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የበዓል የቲቪ ልዩ ዝግጅቶች ነገር…አለ አይደል…፡፡ ግን፣ በቃ ለሁሉም ተመሳሳይ ‘ፎርማት’ ነው እንዴ የተሰጠው፡፡ “ከዚች ‘ፎርማት’ ዝንፍ ካላችሁ…” ምናምን የሚል ግዴታ ኮንትራታቸው ላይ ያስፈርሟቸዋል እንዴ! አሀ… ከሰዎች መለዋወጥ በስተቀር እኮ አብዛኞቹ ዝግጅቶች ብዙም ‘የተለየ’ የሚባል ነገር የላቸውማ!
ደግሞላችሁ…እንግዳው ማንም ይሁን ማንም፣ ዝግጅቱ ልዩም ሆነ መደበኛ ‘ያቺ’ የማትጠፋ ጥያቄ አለች፡፡
“እንግዳችን፣ ከበዓል ጋር የተያያዘ ወይም ሌላ ገጠመኝ ካለዎት!” የሚሏት ነገር አለች፡፡ እናማ… ለቃለ መጠይቅ ወይም ‘ለአንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪነት’ የሚሄድ ሰው ገጠመኞቹን አዘጋጅቶ መሄድ አለበት፡፡
ምን ይመስለኛል…ሰዎች ስለ ‘ገጠመኝ’ ወይም “በዓልን እንዴት ነው የምታከብሩት?” ተብለን የሲድኒ ሼልደንን የፈጠራ ችሎታ የሚያስንቅ ‘ፊክሺን’ ለመናገር እንገደዳለን፡፡ ልጄ… ማን ‘ሰው አፍ’ ይገባል!
ታዲያላችሁ…የበዓል ሰሞን ‘ቀውጢ’ እየሆነ…ጎረቤትን ሁሉ እንቅልፍ የሚነሳው ቤተሰብ እማወራ ስትጠየቅ… “የበዓል  ጊዜ ቤታችን ሳቅና ደስታ ነው፡፡
ሁሉም ተሰብስቦ መብላት መጠጣት ነው…” ትላለች፡፡ አብዛኞቹ ጎረቤቶች እዛ የቆዩት እኮ የሚከራይ የቀበሌ ቤት ስላጡ ነው!
‘ተኩስ’ የሚጀመረው እኮ ገና ለሆነ በዓል አሥራ አምስት ቀን ሲቀር ነው፡፡ አለ አይደል…የቀበሌ ሜጋፎን ተከራይተው የሚከራከሩ ይመስላል፡፡
“አንቺ ሴትዮ እኔ ገንዘብ እንደ ቅጠል ከዛፍ ላይ እየሸመጠጥኩ የማመጣ መሰለሽ!”
“እና እኔ ምን ልሁንልህ፣ ጠላው አሁን ካልተጠነሰሰ እንዴት ሊደርስ ነው! ለመጠጣቱ ጊዜ አንደኛ አይደለህ እንዴ!”
“ጠንስሽዋ! እኔ እንስራውን ላጥብልሽ ነው!”
“በየትኛው ጌሾና ብቅል ነው የምጠነስሰው?”
“ያለጌሾና ብቅል ጠንስሺዋ…ሴቱ ስንት ባልትና ይሠራል…”
እናላችሁ ጎረቤት በዓል መድረሱን የሚያውቀው በካላንደር ሳይሆን በእነሱ ጭቅጭቅ ነው፡ እናማ… “በዓልን እንዴት ነው የምታሳልፉት?” ሲባል ጨዋታ ነው መሳሳቅ ነው… ብሎ ነገር ደራሲዎች ሊቀኑበት የሚችሉበት የፈጠራ ችሎታ ነው፡፡
እዛው ጎረቤት ያለ የዘመኑ ወጣት ምን ይል መሰላችሁ… “‘በቅርብ ቀን’ ለሚመጣ በዓል እንደ ‘ትሬይለር’ ያገለግሉናል፡፡”  ቂ…ቂ..ቂ…
እናላችሁ…“በዓልን እንዴት ነው የምታከብሩት?” የሚሏት ፈተና፣ ከሰው እንደር ብለን ፊክሺን እንድናወራ ታደርገናለች፡፡
አጅሬ ለበዓል ዋዜማ ‘ጨርቅ ሆኖ’ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ሊመጣ ይችላል፡፡ እናትና ሦስት ልጆቹ ኩርምት ብለው ይጠብቃሉ፡፡ እናማ እንደገባ ከዚያ ሦስቱን ልጆች በደንብ ያያል፡፡
“አንቺ ልጆቻችን ስንት ናቸው?”
“ምን አይነት ጥያቄ ነው! ይኸው የምታያቸው ሦስቱ ናቸዋ!”
”ሦስት! አምስት እንደሆኑ እያየኋቸው ትዋሺኛለሽ! አሁን ሁለቱን ከየት እንዳመጣሻቸው ትናዘሻለሽ?”
ታዲያላችሁ… አጅሬው በቲቪ ካሜራ ፊት…“በዓልን እንዴት ነው የምታከብሩት?” ተብሎ ይጠየቃል፡፡
“በጣም ደስ በሚል ሁኔታ ነው የምናሳልፈው፡፡ ከዋዜማው ጀምሮ ከልጆቻችን ጋር ደስ የሚል ጊዜ እናሳልፋለን…” ምናምን ይላል፡፡ ምን ያድርግ…ዘንድሮ እቅጯን ተናግሮ ማን ‘የመሸበት ያድራል!’
ሀሳብ አለን… ሰዎች…“ቤተሰቡ በዓልን እንዴት ነው የሚያከብረው?” ተብለው ከተጠየቁ በኋላ ‘ለማጠናከሪያነት’ ጎረቤቶቻቸውም ይጠየቁልን።
“ጎረቤቶቻችሁ በዓልን እንዴት ነው የሚያከብሩት?”
“ኧረ እንደው ለእነሱ ሲል በዓል ባልመጣ ነው የሚያሰኘው!”
“ለምን?”
“ሰውየው የማታው አልበቃ ብሎት የበዓል ቀን ከጠዋት ጀምሮ ሲልፍ ይውልና ምሳ ላይ መጮህ ይጀምራል፡፡”
“ምንድነው የሚጮኸው!”
“አንቺ የገዛሽው ዶሮ ብልት ስምንት ብቻ የሆነው ለምንድነው ብሎ ይጮኸል፡፡”
“ስምንት ብቻ መሆኑን እሱ እንዴት አወቀ?”
“ምን አውቃለሁ የእኔ ልጅ! ወይ እንግዲህ በር ዘግተው ብልት እየተቆጣጠሩ በሰነድ ይረካካቡ እንደሁ…” ይሉና ጎረቤትዮዋ ሳቅ ያፍናቸዋል፡፡ “ከዛ በኋላ …ቁጭ ብለን የእነሱን ንትርክ ማዳመጥ ነው፡፡”
ስሙኝማ… “እንዴት ነው ስምንት ብልት ብቻ ያለው ዶሮ የገዛሽው?” ሲላት ምን ብላ የምትመልስ ይመስለኛል…
“አታውቅምና ነው! እዚህ ሰፈር ሁሉንም ነገር አይደል እንዴ የሚሸቅቡት፡፡ የዶሮዋን ብልት እንዴት አድርገው እንደቀነሱት እኔ ምን አውቃለሁ!” ቂ…ቂ…ቂ…
አጅሬውም… እንግዲህ የበዓል ሞቅታም አይደል… “ባለሙያ ሴት አሥራ አምስት ብልት ያላት ዶሮ ትገዛለች የእኔዋ ባለ ስምንት ገዛሽልኝ! የአንቺ ዶሮ ለቼልሲ ስትጫወት ጉዳት ደርሶባት ነው? የመጣችው ከየመን ጦር ሜዳ ነው? ወይስ ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች መንትፈዋት ነው!” ቂ…ቂ…ቂ…
ለነገሩ እኮ እማወራዎቹም ዋዛ አይደሉም፡፡ እሱዬው ከተማውን ሲዞር ውሎ ለራሱ አሪፍ ያለውን በግ ይዞ ይመጣል፡፡
“አበስኩ ገበርኵ!”
“ምን ሆንሽ?”
“ምኑን ነው ይዘህ የመጣህብኝ!”
“በግ ነዋ…እንግዲህ ሊጀምርሽ ነው!”
“በግ!…የእኔ ዶሮ ጸጉር አልለበሰችም እንጂ ከዚህ አትበልጥም! የሴቱ ባል ሙክት ይዞ ይገባል፤ የእኔው ጉድ ቡችላ እያስጎተትክ መጣህልኝ!” ቂ…ቂ…ቂ…
በጉን ‘ኢንዴንጀርድ ስፒሺየስ’ ከሚያደርግብን ዘመን ይጠብቀንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4029 times