Saturday, 07 May 2016 13:02

የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ - ከታቀደው ስንቱ ተሳካ?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

• በግንባታና ማስተላለፍ በኩል መዘግየት ይታያል - ታዛቢዎች
• “ህብረተሰቡ የቤት ዋጋ ጨመረ ብሎ አልሸሸም”

የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት፣ በመጀመሪያው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን
በአስር ዙር ከ140 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለነዋሪዎች ገንብቶ አስተላልፏል፡፡ አሁንም
ተገንብተው የተጠናቀቁና በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙ ቤቶች እንዳሉ ጠቁሟል፡፡ መኖሪያ ቤቶችን
ለነዋሪዎች በማስተላለፍ በኩል እስከ 2002 ዓ.ም ፍረስ የተፋጠነ ቢሆንም ከዚያ በኋላ ግን
መዘግየትና መጓተት እንዳለ የሚገልጹ ወገኖች አሉ። የተቋራጭ ድርጅቶች አቅም ማነስ፣የመሰረተ
ልማት አለመሟላት፣የግብአቶች አቅርቦት መዘግየት ወዘተ--- ለግንባታው መጓተት በምክንያትነት
ይጠቀሳሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ከፕሮጀክት ፅቤቱ የመንግስት ጉዳዮች
ኮሙኒኬሽን የስራ ሂደት መሪ አቶ ካሳ ወ/ሰንበት ጋር በግንባታ ሂደቱ፣ባጋጠሙ ፈተናዎች፣በዕቅድና
ግቦች ወዘተ ዙሪያ ቃለምልስስ አድርጋለች፡፡

እስከ 2002 ዓ.ም የጋራ መኖሪያ ቤቶች በፍጥነት ቢተላለፉም ከዚያ በኋላ ግን የማስተላለፍ ሂደቱ አዝጋሚ እንደሆነና የግንባታውም ሁኔታ እንደተጓተተ ይነገራል፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው?
 አሁን ያለነው የቤቶች ግንባታ ፅ/ቤት ውስጥ አይደለም፡፡ የማስተላለፉ ስራም የሌላ አካል ነው፡፡
ስለዚህ በጉዳዩ ላይ ምላሽ አልሰጥም፡፡ ግንባታውን በተመለከተ መጓተት አለ የተባለውም ትክክል አይደለም፡፡ በመጀመሪያው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መሰረት፣ በመጀመሪያዎቹ ሶስት ዓመታት (ይህን የምልሽ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እቅድ በሶስቱ ዓመታት ያልቅ ስለነበር) ውስጥ 95ሺህ ቤቶችን ለመገንባት አቅደን ነበር። በ2003 ዓ.ም 30ሺ፣ በ2004 ዓ.ም እንደዚሁ 30 ሺህ እና በ2005 ዓ.ም 35 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ነበር የታቀደው፡፡
እነዚህን 95 ሺህ ቤቶች በእቅዱ መሰረት ገንብተን አጠናቅቀናል፡፡ ከዚያ በኋላ የከተማ አስተዳደሩ እቅድ ከአገሪቱ እቅድ ጋር አምስት ዓመት ሆኖ መስተካከል ስለነበረበት በ2006 እና በ2007 ዓ.ም በእያንዳንዱ ዓመት 50 ሺህ ቤቶችን የመገንባት እቅድ ይዘን ነበር፡፡ እነዚህንም በእቅዳችን መሰረት ገንብተናል፡፡ በጠቅላላ ሲታይ ከእቅዳችን በላይ አሳክተናል ማለት ነው፡፡
ከእቅድ በላይ አሳክተናል ሲሉ ቤቶቹ፣ሁሉ ነገር አልቆላቸው አስረክባችኋል ማለት ነው?
ምናልባት እዚህ ላይ ሊነሳ የሚችለው---በዚህ ግንባታ ውስጥ መዘግየቶች ይታያሉ፡፡ ለነዚህም መዘግየቶች የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡
ምክንያቶቹን ሊጠቅሱልኝ ይችላሉ?
ከግንባታ መዘግየት ምክንያቶች አንደኛው፣ የግብአት አቅርቦት ችግር ነው፤ የነዚህ ግብአቶች በተለይ ከውጭ አገር በግዢ የሚመጡ ግብአቶች በሚፈለገው ወቅት አለመድረስ። የግዢ ሁደት መራዘምና በተፈለገው ጥራት አለመቅረብ ሌላው የመዘግየት ምክንያት ነው፡፡ ሁለተኛው የመሰረተ ልማት አቅርቦት ችግር ነው፡፡ እነዚህ የመሰረተ ልማት አቅርቦቶች እንደ ሌሎች አገሮች በግንባታ ቦታዎች ላይ መጀመሪያ ተሟልተው ግንባታ መጀመር ነበረበት፡፡ ነገር ግን እኛ ግንባታዎችን የምናካሂደው የመንገድ፣ የውሃና… የኤሌክትሪክ መስመሮች ባልተሟሉበት ሁኔታ ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ አገራችን ባለችበት ተጨባጭ ሁኔታ፣እነዚህን ነገሮች ሳናሟላ ነው ችግሩን ተቋቁመን እየገነባን ያለነው፡፡
ከግንባታው በፊት መሰረተ ልማቶችን ማስቀደም አይቻልም?
የመሰረተ ልማት ግንባታ ረጅም ጊዜ የሚወስድ ነው፡፡ የቤት ፈላጊው ሁኔታ ደግሞ ጊዜ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ስለዚህ ቤቶቹን እየገነባን ጎን ለጎን መሰረተ ልማቶቹን በተቻለ መጠን እያሟላን ነው። በተለይ የእነዚህ መሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት፣ እኛ ለቤት ግንባታው በምንፈልገው መጠን አገልግሎቱን ለማቅረብ አቅም የላቸውም ነበር። እርግጥ በአሁኑ ወቅት አቅማቸውን እያጎለበቱና ተናብበው እየሰሩ ነው፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ግን ይሄ ስላልነበረ ለመዘግየታችን ትልቅ ምክንያት ነበሩ።
በመሰረተ ልማቶች አለመሟላት የደረሰ ይሄ ነው የሚባል መዘግየት ሊጠቅሱልኝ ይችላሉ?
ለምሳሌ በኤሌክትሪክ አለመዘርጋት ከአንድ ዓመት በላይ ጣሪያቸው ቆርቆሮ ሳይመታ የቆዩ ሳይቶች ነበሩ፡፡ በርና መስኮታቸው ሳይገጠም ከአንድ ዓመት በላይ የዘገዩም ነበሩ፡፡ ሌላው ውሃ እስከ 20 እና 30 ኪ.ሜ በቦቴ እያመላለስን ነው ይህን ሰፊ ግንባታ እያከናወንን ያለነው፡፡ መንገድን ብንወስድ ሌላው የመዘግየታችን ምክንያት ነው። ምንም መንገድ በሌለበት በጥርጊያ መንገድ ነው የቤቶች ግንባታ እየተከናወነ ነው፡፡ በዚያ ላይ ዝናብ ጠብ ሲል፣ እነዚህ መንገዶች ስለሚጨቀዩ ፈጽሞ ሥራ አያሰሩም፡፡ በአንድ በኩል እነዚህን እንቅፋቶች እየተጋፈጥን፣ በሌላ በኩሉ የቤት ፈላጊውን ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት እየሰራን ነው፡፡
የተቋራጮች አቅም ማነስ ለግንባታው መዘግየት በምክንያትነት ሲጠቀስ ይሰማል…?
አዎ፤ እውነት ነው፡፡ በአገራችን በኮንስትራክሽኑ ኢንዱስትሪ አለማደግ ምክንያት ተቋራጮቹም ጀማሪ በመሆናቸው (በቂ እውቀት፣ መሳሪያና ገንዘብ ባለመደራጀታቸው) በአብዛኛው የእነሱን አቅም በመደገፍና ራሳቸውን ችለው እንዲቆሙ ለማድረግ ጥረት ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ይሄ ትልቅ ፈተና ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ የፕሮጀክቱ አንዱም ዓላማ ነው፡፡ ከውጭ አገር የሚመጡ እንግዶች ይህን ሲመለከቱ፣ ገንዘቡንና መሬቱን ከየት አመጣችሁት ብለው ይደነቃሉ፡፡ በእኛ አገር አሁን ለግንባታ የሚውለውን የመሬት መጠን ያህል በሌላው አገር የለም፡፡
 እኛ አገር ግን መሬት የመንግስትና የህዝብ በመሆኑ የተገኘ እድል ነው፡፡ ስራችንን እንደ ተአምር ነው የሚያዩት፡፡ ምክንያቱም እንደዚህ ዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል ለመጥቀም ተብሎና ታቅዶ የሚካሄድ የቤት ግንባታ በየትኛውም የአፍሪካ አገር የለም፡፡ በእርግጥ ቤት በስፋት በመስራት ልምድ ያላቸው እንደ ቻይና ያሉ አገሮች አሉ፤ ነገር ግን የሚሰሩት ለድሀ ብለው ሳይሆን ለንግድና ለሪል ስቴት ነው፡፡
 እኛ አገር ግን አንደኛ የምንጠቀመው ዝቅተኛ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ያለን የገንዘብ አቅምም ደካማ ነው፡፡
 የሰለጠነ የሰው ሀይል ችግርም አለ፡፡ ይህ ሁሉ ባለበት ነው ይህንን ሰፊ ግንባታ እያከናወንን ያለነው፡፡ በዚህ ላይ ከዲዛይን ጀምሮ እስከ ማጠናቀቂያው ድረስ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያዊያን ነው እየገነባን ያለነው፡፡ ይሄ ሊያስመሰግነን የሚገባ ስራ ይመስለኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት ያለው የተቋራጮቹ አቅምና ብዛት ምን ይመስላል?
ይህን ፕሮጀክት ስንጀምር በአንድ ጊዜ መቶ ተቋራጭ ማግኘት ፈተና ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ከ2500 በላይ ተቋራጮች በስራ ላይ አሉ። ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በጀማሪነት ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ እነሱን መደገፍ አለብን፡፡ ነገ የዚህ አገር የኮንስትራክሽን ባለቤቶች ናቸውና፡፡
አሁንስ ግንባታቸው የተጠናቀቀና ለእጣ የተዘጋጁ ቤቶች አሉ? ካሉ ምን ያህል ይሆናሉ? እጣቸው መቼስ ይወጣል? በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመንስ ምን ያህል ቤቶችን ለመገንባት ታቅዷል?
በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በየዓመቱ 50ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ታቅዷል። ይህን እቅድ ለማሳካት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው፡፡ ለምሳሌ መሬት ማዘጋጀት አንዱና ዋናው ሲሆን ቤቶቹ በየጊዜው በተለያየ ዲዛይን የሚገነቡ በመሆናቸው ዲዛይንም እየተዘጋጀ ነው።
 ግብአቶችና ተቋራጮችን የማዘጋጀቱም ስራ ሌላው የእቅዱ አካል ስለሆነ እየተዘጋጀንበት ነው፡፡ መሬቱ ከተገኘ በኋላ ደግሞ “Land development” እንሰራና ወደ ግንባታው እንሄዳለን ማለት ነው፡፡ ያለቁ ቤቶች መቼ ለነዋሪው ይተላለፋሉ ለተባለው ይሄን የሚያውቀው ቤት አስተላላፊው አካል ነው፡፡
እናንተ አጠናቅቃችሁ ለአስተላላፊው አካል የምታስረክቧቸው ቤቶች ለማለት ነው?
እኛ በቅርቡ ለማጠናቀቅና ለአስተላላፊው አካል ለማስረከብ ከፍተኛ ርብርብ እያደረግንባቸው ያሉ 39ሺ ቤቶች አሉ፡፡ ቤት አስተላላፊው አካል እጣ ያወጣባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በቅርቡ ሲባል መቼ ነው?
እኛ በዚህ ቀን በዚህ ወር እናጠናቅቃለን ለማለት እንቸገራለን፤ነገር ግን በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ከፍተኛ ስራ እየሰራን ነው፡፡ ሳይቶቹን በቦታው ተገኝቶ መመልከት ይቻላል፡፡ በምን ደረጃ ላይ እንዳሉና አሁን ያሉበትን የግንባታ መጠን ማለቴ ነው፡፡
እነዚህ 39ሺህ ቤቶች የት የት አካባቢ ያሉ ናቸው?
ቦሌ አረብሳ፣ ቂሊንጦ፣ ኩዮፈቼና ቦሌ አያት ሶስት፣ ቦሌ አያት አራትና ቦሌ አያት አምስት የተባሉ ሳይቶች ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት፤ በቅርቡ አጠናቀን ለአስተላላፊው አካል ለማስረከብ ቀን ከሌሊት እየሰራን ነው ያለነው።
 ቤት ፈላጊዎችንና በመቆጠብ ላይ የነበሩ ሰዎችን ለማነጋገር እንደሞከርኩት፣ ብዙዎቹ መቆጠብ እንዳቆሙ፣ ሌሎች ደግሞ ወራቸውን ጠብቀው እንደማይቆጥቡ ተረድቼአለሁ፡፡ ይሄ ከፋይናንስ አቅርቦት አንፃር ግንባታው ላይ ተፅዕኖ አይኖረውም?
በነገራችን ላይ ምን ያህል ሰው በአግባቡ እየቆጠበ ነው? ምን ያህሉ አቋርጧል? የሚለው መረጃ የሚገኘው ባንክ ነው፡፡ ባንክ ከሚያወጣው የስድስት ወር ሪፖርት እንደምንገነዘበው ደግሞ ህብረተሰቡ በከፍተኛ ደረጃ እየቆጠበ መሆኑን ነው፡፡ ህብረተሰቡ የመቆጠብ ችግር አለበት ብለን አናስብም፡፡
በሌላ በኩል የግንባታ ፕሮጀክቱ የፋይናንስ ችግር እንዳይገጥመው የከተማ አስተዳደሩ ለባንክ ቦንድ ሰጥቶ ብድሬን እከፍላለሁ ብሎ ቦንዱን አስይዞ፣ የቤቶቹን ግንባታ ይቀጥልና ግንባታው ሲጠናቀቅ፣ ለህብረተሰቡ እያስተላለፈና ህብረተሰቡ የቤቶቹን ዋጋ እየሸፈነ ነው ሂደቱ እየቀጠለ ያለው።
እስካሁን በግንባታ ሂደት ላይ የፋይናንስ አቅርቦት ችግር አላጋጠመንም፡፡ ነገር ግን ህብረተሰቡ በቆጠብኩት ልክ ቤት እየተገነባልኝ አይደለም በሚል የሚያነሳውን ጥያቄ መንግስት ይገነዘባል፡፡
መንግስት የቤቶችን ችግር አሁን ግንባታ ላይ ባሉት የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት፣ የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ---- አቅም ብቻ  ይፈታል የሚል እምነት የለውም። ስለዚህ ሌሎች አማራጮች መታየት አለባቸው ተብሎ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተነድፈው እነሱ ላይ እየተሰራ ነው ያለው፡፡
አማራጮች የተባሉት ምን እንደሆኑ ቢገልፁልኝ?
አንደኛው “ኮኦፕሬቲቭስ” የሚባሉ አሉ፡፡ ይሄ ማለት በማህበራት ቦታ ወስደው፣ የራሳቸውን ቤት ራሳቸው መገንባት እንዲችሉ ለማድረግ ነው፡፡ ሌላው ፐብሊክ ፕራይቬት ፓትርነር ሺፕ (PPP) የሚባል አለ፡፡ ይሄ ደግሞ መንግስትና የግል ባለሀብቶች በጋራ ሆነው በቤት ግንባታ ላይ የሚሳተፉበት ነው፡፡ ሌላው አማራጭ በቤት ግንባታ ስራ ትልልቅ ልምድ ያላቸው የውጭ ኩባንያዎች ገብተው በስፋት እንዲሳተፉ ማድረግ ነው፡፡ በነዚህ አማራጮች የቤትን ችግር ለመፍታት በመንግስት በኩል ጥናቶች ተጀምረዋል፡፡
እስካሁን በ20/80 ፕሮግራም ምን ያህል ቤቶች ተገንብተዋል? በ10/90ስ ግንባታው ምን ይመስላል?
 እስካሁን በ20/80 ፕሮግራም 276ሺ15 ቤቶች ተገንብተዋል፤ እየተገነቡም ነው፡፡ እንዲህ አይነት ግንባታ በየትኛውም የአፍሪካ አገር አይታይም። ከነዚህ ውስጥ ከ145 ሺህ በላይ ቤቶች ለነዋሪው ህዝብ ተላልፈዋል፡፡ ይሄ የምንኮራበትና ደረታችንን ነፍተን የምንናገረው፣ በተጨባጭ የሚታይ ሥራ ነው፡፡
አስር ዘጠናን በሚመለከት 123 ሺህ ሰዎች ተመዝግበዋል፡፡ እየተገነባ ያለውና የተገነባው ከ124ሺህ በላይ ነው፡፡ ከተመዘገበው በላይ አንድ ሺ ቤቶችን ጨምረናል ማለት ነው፡፡ እነዚህ ቤቶች ለልማ ተነሺዎች ይሰጣሉ፡፡
የቤት ግንባታው ዝቅተኛ ገቢ ላለው የማህበረሰብ ክፍል ነው ቢባልም በአሁኑ ሰዓት በኮንዶሚኒየም ቤቶች በብዛት የሚኖሩት ባለሃብቶች ናቸው፡፡ ይሄ እንዴት ነው የሚታየው?
እየኖረ ያለው ብቻ ሳይሆን ኮንዶሚኒየም ቤት ለማግኘት የሚመዘገበውና የሚሮጠው ባለሀብቱም ጭምር ነው፡፡
ተጨማሪ ----- የራሱ መኖሪያ ቤት እያለው…?
አዎ፤ቤት እያለው! በ2005 ዓ.ም ዳግም ምዝገባና አዲስ ምዝገባ ሲካሄድ ከፍተኛ ቁጥር  ያላቸው ባለሀብቶች ለምዝገባ መጥተዋል፡፡ መኪናቸውን ደርድረውት ሲታዩ፤ “እንዴ ለእነሱ ነው እንዴ የሚገነባው?” ያስብላል፡፡
ይሄ ግን ሁሉንም አያካትትም፤ ባለሀብት ሆነው ቤት የሌላቸውም አሉ፡፡ 40/60 መካከለኛና ከፍተኛ ገቢ ላላቸው እንዲሆን የተደረገውም ለዚህ ነው፡፡ የቤት ችግርን ለመቅረፍ እየተደረገ ያለው ጥረት ቀላል እንዳልሆነ በመገንዘብ፣የመንግስትንም ተግዳሮቶች መረዳት ተገቢ ይመስለኛል፡፡
ቤት ፈላጊዎች ቤታቸውን ሲረከቡ መጀመሪያ ከተዋዋሉበት ዋጋ በላይ ብዙ ጭማሪ እንደሚጠየቁ ይነገራል፡፡ ይሄ እውነት ነው?
የቤት ዋጋን በተመለከተ ከምዝገባው ዋጋ በላይ ይጨምራል ወይ? አዎ ይጨምራል፡፡ ግንባታ እስከተካሄደ ድረስ የግንባታ ዋጋ በተለያየ ምክንያት ይጨምራል፡፡ የጉልበት ዋጋ፣ የትራንስፖርት ዋጋ፣ በተለያየ ጊዜ የግብአቶች ዋጋ ሲጨምር የቤት ዋጋ ይጨምራል፡፡ ይሄ ግልፅ ነው፡፡ ብዙዎቹ እስካሁን የመጨመር እንጂ የመቀነስ ሁኔታ አይታይባቸውም። በብዛት የሚመረቱትም የግንባታ ግብአቶች እየጨመሩ ነው የሄዱት፡፡ መንግስት ከነዋሪው የሚጠይቀው ክፍያ የግንባታውን ነው። መሬትና መሰረተ ልማት በነፃ ነው፡፡
ህብረተሰቡ የሚከፍለው የሲሚንቶ፣ የድንጋይ፣ የቆርቆሮ፣ በአጠቃላይ ቤቱ ላይ የሚውለው ተሰልቶ ነው። እነዚህ ነገሮች ሲጨምሩ ዋጋው ይጨምራል። ህብረተሰቡ ይህንን ያውቃል፡፡ ስለዚህ ዋጋ ጨምሯል ብሎ ቤት ከመግዛት የቦዘነበት ጊዜ የለም። ምክንያቱም የሚገዛው ቤት ነው፤ ንብረት ነው፤ ለልጆቹ የሚያስተላልፈው ነው፡፡ አሁን በ10ኛው ዙር ለምሳሌ የቤት ዋጋ ጨምሯል ግን ህብረተሰቡ አልሸሸም፡፡ ሁሉም ቤቱን ተረክቧል፡፡
እስከ ዘጠነኛው ዙር ቤት ከወሰዱት ቁጥር ጋር ሲነፃፀር፣ በ10ኛው ዙር ምን ያህሉ ወስደዋል?
እስከ ዘጠነኛው ዙር እጣ ከወጣላቸው መካከል 65 በመቶ ያህሉ ብቻ ነበሩ ቤት ለመውሰድ የመጡት፤ 35 በመቶው በተለያየ ምክንያት አልመጡም ነበር፡፡ አገር ውስጥ ላይኖሩ ይችላሉ። በአቅም ማጣት ቀርተው አልያም በህይወት የሉ ይሆናል፡፡
 በ10ኛው ዙር ግን 94 በመቶው ቤቱን ተረክቧል፡፡ እንግዲህ በዚህኛው ዙር የቤቱ ዋጋው ጨምሯል፡፡ የግብአት ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ መሆኑን ማህበረሰቡ ተገንዝቧል ማለት ነው። መንግስት ሊያጭበረብራቸው እንደማይችል ያውቃሉ፡፡ ግልብጥ ብለው መጥተው ቤታቸውን ተረክበዋል፡፡



Read 3754 times