Saturday, 07 May 2016 13:02

የማንነት ጥያቄ ድንበር የለውም

Written by  ከመ.መ.አ
Rate this item
(13 votes)

የቡድን መሠረቱ ግለሰብ ነው። ቡድኖችና ማህበረሰቦች የሚኖሩት የግለሰቦችን ቀዳሚ ህልውና ተመርኩዘው እንደሆነ ይታወቃል። ከዚህም የተነሳ ይመስላል የሊብራሉ ዴሞክራሲ ትልቁን ትኩረት የሚሰጠው ለግለሰብ ሰብዓዊ መብቶች ከበሬታና አጠባበቅ እንደሆነ አብዝቶ ያቀነቅናል። ለቡድኖች መብት ጥበቃ ያን ያህል የሚነፍገው ትሩፋት ባይኖርም የግለሰቦች መብትና ነፃነት ካልተከበረ የቡድኖች መብት የላቀ ትርጉም አለው ብሎ አያምንም።
በስራ ላይ ያለው የአገራችን ህገ-መንግስት ግን ከዚህ የተለየ ነው። ስለ መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች ሲደነግግ፤ ከግለሰብ መብቶች ባልተናነሰ /ምን አልባትም በላቀ/ ሁኔታ ለቡድን መብቶች ትኩረት ይሰጣል። በህገ-መንግስቱ አንቀጽ /10/ ንዑስ አንቀጽ /1/ ስር እንደተደነገገው፤ የዜጐችና የህዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች እኩል እውቅና ተሰጥቷቸው የሚከበሩና የሚጠበቁ ጉዳዮች ናቸው።
እንደ ቡድን የሚገለፁ ሌሎች ማህበረሰቦች እንዳሉ ባይክድም ህገ-መንግስቱ “ህዝቦች” እያለ የሚጠራቸው በአንቀጽ /8/ እና በአንቀጽ /39/ ስር የተመለከቱትን ብሔሮችና ብሔረሰቦች እንደሆነ እዚህ ላይ በውል ማጤን ያስፈልጋል። በህገ-መንግስቱ መሰረት፣ አንድን ህዝብ ብሔር ወይም ብሔረሰብ የሚያሰኘው የጋራ መግባቢያ ቋንቋ፣ ኩታ ገጠም መስፈሪያ አካባቢ፣ የጋራ ባህላዊ ስሪት፣ የተዛመደ ህልውናን ዋቢ ያደረገ የማንነት እምነትና የስነ-ልቡና ዘይቤ፣ ወዘተ. . . ነው። እንግዲህ እነዚህን ነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታዎች አሟልቶ የተገኘ የትኛውም ምልዓተ-ህዝብ ራሱን እንደ አንድ ብሔር ወይም ብሔረሰብ ጠቅሶ በራስ መተዳደርን፣ ሲያሻውም ተገንጥሎ የራሱን ግዛት በመከለል ሉዓላዊ መንግስት የማቋቋምን መብቶች ያጠቃለለ ነፃነት እስከ ማወጅ እንደሚደርስ ህገ-መንግስቱ በግልጽ ይደነግጋል።
ሃያ አመት ባልዘለቀው የህገ-መንግስቱ አተገባበር እድሜ ታዲያ በአገራችን የየራሳቸውን ብሔራዊ እውቅና ለማስከበርና ከዚያም አልፎ አካባቢያቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር የጠየቁ ህዝቦች ነበሩ፣ ዛሬም በመጠየቅ ላይ የሚገኙ አሉ። አንዳንዶቹ ተሳክቶላቸው የየራሳቸውን ልዩ ዞን፣ ወረዳ ወይም ቀበሌ አስተዳደሮች እንዲያዋቅሩ በየታቀፉባቸው ክልሎች ድጋፍና በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ተፈቅዶላቸዋል። የስልጤ ብሔረሰብ ለዚህ የመጀመሪያው አብነት እንደነበር ሁላችንም እናስታውሳለን።
ሃገራችን ኢትዮጵያ በቋንቋ፣ በባህል፣ በሃይማኖትና በሌሎች ጠቃሚ እሴቶች የበለፀገች መሆኗ ይታወቃል። በርግጥ ይህ ፀጋ ለኛ ብቻ የተሰጠ አይደለም። ምንአልባትም ናይጀሪያና ህንድን የመሳሰሉት አገሮች ከኢትዮጵያ የበዛ ብሄር-ብሄረሰብና የቋንቋ ብዝሀነት ያላቸው አገሮች ናቸው። እንዲህ ያለው መስተጋብር በአግባቡ ከተያዘ በረከት እንጅ በራሱ እርግማን አይደለም።
በርግጥ እንደ ኢትዮጵያ ያለን ጥንታዊ አገር በቋንቋም ሆነ በእምነት ከፋፍሎና አስተዳደራዊ ግዛቶችን አጥርቶ መከለል ቀላል ስራ አይደለም። ሃገሪቱ ብዙ ማንነቶች ያሉባትና በርካታ ቋንቋዎች የሚነገሩባት ብትሆንም ዜጐቿ የሚኖሩት በከፍተኛ ስብጥርና ውርርስ መሆኑ መታወቅ አለበት። ዛሬ የኦሮሚያ ክልል ነው ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የአማርኛና የሌሎች ቋንቋዎች ተናጋሪዎች በስፋት አብረው እንደሚኖሩ አንድና ሁለት የለውም። በተመሳሳይ ሁኔታ በትግራይ ክልል የሚኖሩት ትግሬዎች ብቻ አይደሉም። የህዝቡ ባህልና ቋንቋ መወራረስ አንድን አካባቢ የአንድ ብሄር ወይም ብሄረሰብ ብቸኛ ሃብት ነው ለማለት የሚያስችል ሆኖ አናገኘውም። ከዚህ የተነሳ የእያንዳንዱ ብሄር ብሄረሰብ ወይም ህዝብ አንጡራ ባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ … ወዘተ በላቀ ሁኔታ እውቅና አግኝቶ እንዲከበር፣ እንዲያድግና እንዲበለጽግ ጥረት መደረግ ያለበት መሆኑ አስፈላጊ ቢሆንም ከዚህ ወይም ከዚያ በመለስ ያለው መሬት የዚህ ወይም የዚያኛው ብሄር ወይም ብሄረሰብ ብቻ ነው የሚለው ውሳኔ ግን ቢያንስ በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጡትን መለኪያዎች ተከትሎና በሚመለከተው ህዝብ ፈቃደኝነት ላይ ተመስርቶ ካልተከናወነ የዘፈቀደ እርምጃ ስለሚሆን ወደማያባራ የእርስ በርስ ብጥብጥ የመውሰድ አደጋ ይኖረዋል።
አሁን አሁን በየአካባቢው ለሚነሱት የማንነት እውቅና ጥያቄዎች በየአካባቢው መንግስታትም ሆነ በራሱ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አማካኝነት እየተሰጠ ያለው ምላሽ ጉራማይሌነት ይታይበታል። በአንዳንድ አካባቢዎች ከጊዜ እርዝማኔ የተነሳ ቋንቋቸው ለተዋጠ ወይም ለጠፋ ማህበረሰቦች ሳይቀር ከራሱ ከህገ መንግስቱ መንፈስ ባፈነገጠ እርምጃ የራስ በራስ አስተዳደር መብት እንዲጠበቅ ሲወሰንላቸው እናያለን። በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ “የአፍ መፍቻ ቋንቋችን እያለ በእርሱ እንዳንገለገል ታፍነናልና አሁን ከተጠቃለልንበት ክልል ወጥተን ከሚመስለን ቋንቋና ባህል ጋር እንደወትሮው መቀላቀል እንፈልጋለን” ብለው የተነሱ ህዝቦች ከጥያቄያቸው ጋር ግንኙነት የሌለው ታፔላ እየተለጠፈባቸው ሲንገላቱና ክፉኛ ሲዋከቡ እናስተውላለን። በኢትዮጵያ ህገ መንግስት መሠረት የማንነት እውቅና ጥያቄ በአንዱ ክልል ምርቃት፣ በሌላው ክልል ደግሞ እርግማን ሊሆን ከቶ አይችልም። ቀድሞ ነገር መርሁ ያዋጣናል ብለን ካመንበትና ከተቀበልነው ከጠርዝ እስከ ጠርዝ በእኩልነትና ያለ አድልኦ ልንሰራበት ይገባናል። ይልቁንም ጥያቄው ከህዝብ በተውጣጡ ወገኖች የቀረበ መሆኑ ከተረጋገጠ የክልሎች ድንበር ወይም ወሰን የሚገድበው አይደለም።
መሠረቱ ምንም ሆነ ምን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በህገ-መንግስት ደረጃ የተጠበቀ ዴሞክራሲያዊ መብት ነው። ዴሞክራሲ ደግሞ ሌሎች እንዲተገብሩት የምንመኘው ብቻ ሳይሆን እኛም ልንተገብረው የሚገባን  እሴት  ነው። መቸውንም ጊዜ ቢሆን በመብቱ የመጠቀም ዕድል ያላቸው ወገኖች ሁሉ ያላንዳች ገደብና አድልኦ እንዲሰሩበት መፈቀድ ይኖርበታል።
ኢትዮጵያ አሁን ያሏት ክልሎች በዋነኝነት የአፍ መፍቻ ቋንቋን መሠረት አድርገው የተቀረፁ ናቸው ቢባልም እውነታውን በመሬት ላይ ወርዶ ማረጋገጥ ቀላል አይሆንም። በርግጥ ጥቂት ክልሎችን ቁጥሩ በዛ ብሎ በተገኘው ነዋሪ ብሄር መጠሪያ ሰይመናቸው ሊሆን ይችላል። ሆኖም ይህንን ዓይነቱን አጠራር ተጠቅሞ እስከ መጨረሻው መዝለቅ አዳጋች ሆኖ በመገኘቱ ይመስላል ለምሳሌ፦ ወደ ደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አካባቢ ስንደርስ ክልሉን ከአንድ ነጠላ ብሄር ጋር አቆራኝቶ ለመሰየም ስለተቸገርን አካባቢው በመልክዓ ምድራዊ አቅጣጫ ብቻ እንዲጠራ አድርገናል። በተመሳሳይ ሁኔታ ጋምቤላ ውስጥ ከአንድ በላይ ብሄሮችና ብሄረሰቦች እንደሚኖሩ ብናውቅም ክልሉን በአንዱ ቡድን መጠሪያ ብቻ ለመሰየም አልደፈርንም። ቀድሞ ነገር እንዲህ ያለውን መስፈርት ተጠቅሞ ኢትዮጵያን በግዛት መከፋፈል በገቢር የማይቻል መሆኑን ይኸው ራሱ ያስረዳናል።
ያም ሆኖ በእያንዳንዱ ክልል ሰብሰብ ብለው በኩታ ገጠም አካባቢዎች የሚኖሩ ህዝቦች የሌሎችን መብት ሳይጋፉ ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበትን ዕድል መፍጠራችን ያን ያህል የተጋነነ ኪሳራ አልነበረውም፣ የለውምም። ቁም ነገሩ በአንድ ክልል ውስጥ ተሰባስበው የሚገኙት እነዚህ ህዝቦች “ማንነታችን ይታወቅ፣ የራሳችንን የአስተዳደር እርከን እናቋቁም፣ ወይም ተነጥለን ወደሚስማማን ክልል እንጠቃለል” የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ የምናስተናግድበት ዘይቤ ግልጽነትና ዴሞክራሲያዊነት ያለው መሆን አለመሆኑ ላይ ይመሰረታል። በመጀመሪያ ደረጃ ጥያቄውን የሚያቀርቡት ወገኖች የአፍ መፍቻ ቋንቋን ጨምሮ የራሳቸው ልዩ ማንነት /  Unique identity/ ያላቸው መሆን ይኖርባቸዋል። እዚህ ላይ ቡድኖች የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በድንበር ንክኪና በባህል ተወራራሽነት ምክንያት ሌሎች ተጨማሪ ቋንቋዎችን መናገር ከመቻል አለመቻላቸው ጋር የሚገናኝ አይደለም። ለምሳሌ፦ በ1983 ዓ.ም በኢህአዴግ አሸናፊነት በሃገሪቱ የተካሄደውን የመንግስታዊ ስርዓት ለውጥ ተከትሎ ከቀድሞው የበጌ ምድርና ሰሜን ጠቅላይ ግዛት ተቆርሶ ወደ ክልል አንድ /በኋላ ትግራይ ክልል ወደ ተባለው/ አካባቢ የተጠቃለለው የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ከአፍ መፍቻ የአማርኛ ቋንቋው ባልተናነሰ የትግርኛና በተወሰነ ደረጃ ደግሞ የአርበኛ ቋንቋ የሚናገር መሆኑ እውነት ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከዚህ አካባቢ በህዝብ ተወክለናል የሚሉ ወገኖች ይህንኑ ሁኔታ አጉልቶ በማውጣትና እንደ ኮሚቴ በመደራጀት “የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ማንነቱ ተጣርቶ እውቅና ይሰጠውና በኢፌዴሪ የክልሎች አደረጃጀት ውስጥ ወደ አማራ ክልል ይጠቃለል” የሚል ጥያቄ በማንሳት ላይ እንደሆኑ በተደጋጋሚ ይሰማል። ይሁን እንጅ ጥያቄያቸው እንደ ሌሎች ተመሳሳይ ቡድኖች በበጐ ከመታየትና ከመበረታታት ይልቅ “ቀድሞ ነገር የምትናገሩት የትግርኛ ቋንቋ በመሆኑ ወደ ትግራይ የተጠቃለላችሁት ታስቦበት ነው፤አርፋችሁ ተቀመጡ” መባላቸውን በቅሬታ ይገልፃሉ። ይባስ ብሎ ጥያቄያቸውን በህገ መንግስቱ መሠረት ደረጃውን ጠብቀው እስከ ፊዴሬሽን ምክር ቤት ድረስ ላሉ የመንግስት አካላት ለማቅረብ በተንቀሳቀሱበት ወቅት ታቅዶም ሆነ ሳይታቀድ ጉዟቸውን የተከተለ ከፍተኛ መሰናክልና ጊዜያዊ እገታን ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደደረሰባቸው ክፉኛ ሲያማርሩ ይደመጣሉ።
ግልጽ በሆነ ምክንያት የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃንን ባይጨምርም በተለያዩ ሚዲያዎች በተደጋጋሚ የሚሰማውንና የሚነበበውን ይህንን ስሞታ በዝርዝር ማጣራት ያስፈልግ ይሆናል። ይሁን እንጅ ከዚህ ጥያቄ በስተጀርባ በራሱ በክልሉ መንግስት አነሳሽነትና ፊታውራሪነት በተለይ “የማንነት እውቅና ጥያቄውን እንቃወማለን፣ ጥያቄ አቅራቢዎቹ እኛን አይወክሉንም፣ የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ትግሬ እንጅ አማራ አይደለም ወዘተ” እያሉ ወደ አደባባይ የወጡ የጐዳና ሰልፈኞችን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የትግርኛ ፕሮግራሞች ላይ ከተመለከትን ሩቅ ጊዜ አይደለም። በኔ አስተያየት እነዚህ ሰልፎች ጤናማ እንቅስቃሴዎች ነበሩ ለማለት አልደፍርም።
ከዚህ ይልቅ ይጠቅማል ብየ የማስበው “ማንነታችን ይታወቅ፣ የአፍ መፍቻ ቋንቋችን ይከበር” በማለት የሚጠይቁ ወገኖች ካሉ ሃላፊነት በተሞላበት መንገድ የመጀመሪያ ደረጃ ማጣራት እንዲካሄድ አድርጐ ቁጥራቸው ይነስም ይብዛ ጉዳዩን ነፃና ግልጽ ለሆነ ውሳኔ ህዝብ እንዲቀርብና የምልዓተ-ህዝቡ ትክክለኛ ፍላጐት በውል እንዲረጋገጥ መፍቀድ ብቻ ነው። ወልቃይት ባመዛኙ አማራ ይሁን ትግሬ ያላንዳች ተጽዕኖ መወሰን ያለበት የሚኖርበት የወልቃይት ነዋሪ ህዝብ እንጅ የትግራይ ክልል መንግስት ወይም እርሱ ባደባባይ አደራጅቶ የሚያስወጣቸው ሰልፈኞች ወይም ጥያቄ አቅራቢዎቹ ኮሚቴዎች እንጠቃለልበታለን የሚሉት የአማራ ክልል መንግስት ወይም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አይደሉም፣ ሊሆኑም አይችሉም።  ስለሆነም ሃገሪቱ የህዝቡን የልብ ትርታ በትዕግስት አዳምጦ ተገቢውን ምላሸ ለመስጠት የሚያስችል ህገ-መንግስታዊ ስርዓትና ተቋማዊ አደረጃጀት እያላት ጥያቄውን ከሩቁ እንደ ጦር መፍራትና የመብት ተቆርቋሪዎች ነን ብለው በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱትን ወገኖች ሃላፊነት በጐደለው መንገድ ማንገላታት በመንግስትና በዜጐቹ መካከል ሊኖር የሚገባውን የእርስ በርስ መተማመን አብዝቶ የሚሸረሽር መሆኑ ከወዲሁ ታውቆ ስሜት የሚያነሳሱ የደመ ነፍስ እርምጃዎችን ከመውሰድ ተቆጥበን፣ አመጽ ያልተቀላቀለበትን የትኛውንም ዓይነት የቡድን ጥያቄ ፊት ለፊት የመጋፈጥ ልምድ ብናዳብር ብንጠቀም እንጂ አንጎዳም እላለሁ፡፡  

Read 3922 times