Saturday, 07 May 2016 13:05

በ61ኛዋ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ዋንጫ የማድሪድ ክለቦች ይፋለማሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

    ከወር በኋላ በጣሊያኗ ከተማ ሚላን   በሚገኘው ጁሴፔ ሜዛ ስታድዬም ለ61ኛው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ የሚፋለሙት ሁለቱ የስፔን ክለቦች ሪያል ማድሪድ እና አትሌቲኮ ማድሪድ ይፋለማሉ፡፡  ጁሴፔ ሜዛ ስታድዬም የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ጨዋታ ሲያስተናግድ ለ4ኛ ጊዜ ነው፡፡ በ1965 እ.ኤ.አ የጣሊያኑ ኢንተር ሚላን፤ በ1970 የሆላንዱ ፋዬኖርድ  እንዲሁም በ2001 እ.ኤ.አ የጀርመኑ ባየር ሙኒክ ሻምፒዮን የሆኑባቸው 3 የዋንጫ ጨዋታዎችን ስታድዬሙ አስተናግዷል፡፡ 80ሺ ተመልካች የሚያስተናግደው ጁሴፔ ሜዛ የሁለቱ የሚላን ከተማ ክለቦች ኢንተር ሚላን እና ኤሲሚላን  ሜዳ ሲሆን ከ90 ዓመታት በላይ ሆኖታል።  በተያያዘ በ220 አገራት ከ200 ሚሊዮን በላይ የቲቪ ተመልካች በሚኖረው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ጨዋታ  አሜሪካዊቷ ሙዚቀኛ፤ የዜማና የግጥም ደራሲ አሊሻ ኪስ የሙዚቃ ድግስ እንደምታቀርብ ታውቋል፡፡ አሊሻ ኪስ በዓለም ዙሪያ ከ50 ሚሊዮን የአልበሞቿን ቅጂዎች ያሰራጨች እና 15 የግራሚ ሽልማቶችን የሰበሰበች ናት፡፡ በሻምፒዮንስ ሊጉ ከ61ኛው የዋንጫ ጨዋታ በፊት በተደረጉት 124 ጨዋታዎች 345 ጎሎች የተመዘገቡ ሲሆን የኮከብ ግብ አግቢነቱን የሪያል ማድሪዱ ክርስትያኖ ሮናልዶ በ16 ጎሎች እየመራ ነው፡፡
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ታሪክ የአንድ ከተማ ክለቦች በዋንጫ ጨዋታ ሲገናኙ ለ2ኛ ጊዜ ይሆናል። ከሁለት የውድድር ዘመናት በፊትም ሁለቱ የማድሪድ ከተማ ክለቦች ለዋንጫ ቀርበው ሪያል ማድሪድ 4ለ1 አሸንፎ ለ10ኛ ጊዜ ሻምፒዮን እንደሆነ አይዘነጋም። ዘንድሮ  ሪያል ማድሪድ  ለሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ  ጨዋታ ሲቀርብ  ለ14ኛ ጊዜ ሲሆን  አትሌቲኮ ማድሪድ ደግሞ 3ኛው ነው፡፡  አትሌቲኮ ማድሪድ አስቀድሞ ያደረጋቸው ሁለት የዋንጫ ጨዋታዎች በ1974 እኤአ ላይ ከባየር ሙኒክ ጋር  እንዲሁም በ2014 እኤአ ከሪያል ማድሪድ ጋር ተገናኝቶ የተሸነፈባቸው ነበሩ፡፡ በአንፃሩ ሪያል ማድሪድ በ2014 እኤአ ላይ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር ለፍፃሜ ቀርቦ 10ኛውን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ለመውሰድ በቅቷል፡፡ አትሌቲኮ ማድሪድ በሚላኑ የፍፃሜ ጨዋታ ሪያል ማድሪድን በማሸነፍ ዋንጫውን ከወሰደ  ለመጀመርያ ጊዜ ለሻምፒዮናነት የሚበቃ ሲሆን በውድድሩ ታሪክ 23ኛው የአውሮፓ ክለብ ሆኖ ይመዘገባል፡፡
በሌላ በኩል በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የ61 ዓመታት ታሪክ የአንድ አገር ሁለት ክለቦች በዋንጫ ጨዋታ ሲፋለሙ ዘንድሮ ለስድስተኛ ጊዜ ነው፡፡ በ2000 እኤአ ላይ የስፔኖቹ ክለቦች ሪያል ማድሪድ እና ቫሌንሽያ ተገናኝተዋል፡፡ በፈረንሳዩ ስታድዬም ስታድ ደፍራንስ በተደረገው የዋንጫ ጨዋታ ሪያል ማድሪድ 3ለ0 በሆነ ውጤት ቫሌንሽያን አሸንፎታል፡፡ በ2003 እኤአ ላይ ሁለቱ የጣሊያን ክለቦች ኤሲ ሚላን እና ጁቬንትስ ተገናኝተዋል። በማንችስተር ዩናይትድ ሜዳ ኦልድትራፎርድ በተደረገው የፍፃሜ ጨዋታ በመደበኛው የጨዋታ ክፍል ጊዜ 0ለ0 ተለያይተው በመለያ ምቶች ኤሲ ሚላን 3ለ2 በሆነ ውጤት ጁቬንትስን  በመርታት አሸንፏል፡፡ በ2008 እኤአ የተገናኙት ደግሞ ሁለቱ የእንግሊዝ ክለቦች ማን ዩናይትድ እና ቼልሲ ናቸው፡፡ ቼልሲ እና ማን ዩናይትድ የዋንጫ ጨዋታውን ያደረጉት በሞስኮው ሉዝንስኪ ስታድዬም ሲሆን በመደበኛው ጨዋታ ክፍለ ጊዜ አንድ እኩል አቻ ተለያይተው አሸናፊውን ለመለየት በተሰጡ የመለያ ምቶች ዩናይትድ 6ለ5 በማሸነፍ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡ በ2013 እኤአ የጀርመኖቹ ባየር ሙኒክ እና ቦርስያ ዶርትመንድ የተገናኙበት ነው፡፡ ባየር ሙኒክ በሳንትያጎ በርናባኦ የተደረገውን ጨዋታ የቅርብ ተቀናቃኙን ቦርስያ ዶርትመንድ 2ለ1 በማሸነፍ ዋንጫውን ወስዷል፡፡ በ2014 እኤአ ደግሞ  በፖርቱጋል ሊዝበን ከተማ በተካሄደው የማድሪድ ደርቢ ሪያል ማድሪድ 4ለ1 አትሌቲኮ ማድሪድን አሸንፎ ሻምፒዮን ሆኖበታል፡፡
ከ2 ዓመት በፊት ሁለቱ የማድሪዮ ክለቦች በፍፃሜ ጨዋታው ተገናኝተው ሪያል ማድሪድ ሲያሸንፍ የስፔን ዋና ከተማ ማድሪድ ለ11ኛ ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን በመውሰድ ከአውሮፓ ከተሞች አንደኛ ነበረች። ዘንድሮ ለ12ኛ ጊዜ ዋንጫው ወደ ማድሪድ በመግባቱ የውጤት ክብረወሰኑ በአንደኛነት የሚቀጥል ይሆናል።  በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ድሎች የከተሞች ስኬት ደረጃ ሚላን ከተማ በ10 የዋንጫ ድሎች ሁለተኛ ደረጃ ስትወስድ የስፔኗ ባርሴሎና፤ የጀርመኗ ሙኒክ እና የእንግሊዟ ሊቨርፑል ከተሞች እያንዳንዳቸው አምስት አምስት ጊዜ በመውሰድ እንዲሁም የሆላንዷ አያክስ አራት አራት ጊዜ በመውሰድ ተከታታይ ደረጃ አላቸው። በሌላ በኩል ባለፉት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የ60 ዓመታት ዋንጫዎች በሁለት ክለቦች 15 ዋንጫዎችን በመሰብሰብ የሚመራው የስፔኑ ፕሪሚዬራ ሊጋ ሲሆን ይህ የድል ብዛት ከወር በኋላ በሚካሄደው የማድሪድ ደርቢ ወደ 16 የሚያድግ ይሆናል፡፡   በ5 ክለቦች 13 ዋንጫዎችን በመሰብሰብ የእንግሊዙ ፕሪሚዬር ሊግ  በሁለተኛ የሚከተል ሲሆን የጣሊያኑ ሴሪኤ በ3 ክለቦች ባገኛቸው 12 ዋንጫዎች በሶስተኛ ደረጃ እንዲሁም የጀርመን ቦንደስ ሊጋ  በ3 ክለቦች 6 ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮን በመሆን  በአራተኛ ደረጃ ላይ ናቸው። በክለብ ደረጃ 10 የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን በመሰብሰብ የሚመራው የስፔኑ ሪያል ማድሪድ ሲሆን የጣሊያኑ ኤሲ ሚላን በ7 ዋንጫዎች በሁለተኛ ደረጃ ይከተላል፡፡ የእንግሊዙ ሊቨርፑል እና የስፔኑ ባርሴሎና እያንዳንዳቸው 5 ዋንጫዎችን በመሰብሰብ ሶስተኞች ናቸው፡፡ የጀርመኑ ባየር ሙኒክ በአራት  እንዲሁም የእንግሊዙ ማን ዩናይትድ በሶስት የዋንጫ ድሎቻቸው ተከታታይ ደረጃዎች አላቸው፡፡
የዋንጫ ስብስባቸው
ሪያል ማድሪድ በአገር ውስጥ ውድድሮች ከ60 በላይ፤ በአውሮፓ ደረጃ ከ12 በላይ ዋንጫዎችን ሲሰበስብ፤ አትሌቲኮ ማድሪድ በአገር ውስጥ ውድድሮች 24 በአውሮፓ ደረጃ ደግሞ 6 ዋንጫዎች አሉት፡፡
በስፔን ፕሪሚዬራ ሊጋ ሪያል ማድሪድ  32 አትሌቲኮ ማድሪድ 10
በኮፓ ዴላሬይ ሪያል ማድሪድ 19 አትሌቲኮ ማድሪድ 10
በስፓኒሽ ሱፕር ሪያል ማድሪድ ካፕ 9 አትሌቲኮ ማድሪድ 1
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሪያል ማድሪድ 10 አትሌቲኮ ማድሪድ 0
በአውሮፓ ማህበረሰብ ዋንጫ ሪያል ማድሪድ 2 አትሌቲኮ ማድሪድ ዩሮፓ ሊግ 2
በኢንተርኮንትኔንታል ካፕ ሪያል ማድሪድ 4 አትሌቲኮ ማድሪድ1
ስታድዬሞቻቸው
የሪያል ማድሪዱ ሳንቲያጎ በርናባኦ ከ85ሺ በላይ ተመልካች ያስተናግዳል፡፡ በ1947 እኤአ የተገነባ ሲሆን 288 ሚሊዮን ዩሮ ወጭ ሆኖበታል፡፡ የአትሌቲኮ ማድሪዱ ቪንሴንቴ ካልዴሮን ከ54ሺ በላይ ተመልካች ያስተናግዳል፡፡ በ1966 የተገነባ ሲሆን ወጭው እስከ 200 ሚሊዮን ዩሮ ነው፡፡አትሌቲኮ ማድሪድ ቪንሴንቴ ካልዴሮን ስታድዬምን በመልቀቅ በ2016 እኤአ ላይ 67500 ተመልካች ወደ የሚያስተናግደው አዲሱ ስታድዬሙ ኤስታድዮ ላ ፒዬንታ እንደሚዛወር ይጠበቃል፡፡
የተጨዋቾች ስብስብ እና የዋጋ ተመናቸው
ሪያል ማድሪድ በዘንድሮ አጠቃላይ የ22 ተጨዋቾች ስብስቡ በትራንስፈር ማርኬት 697.80 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመን ሲኖረው፤ የቡድኑ አማካይ እድሜ 26.9 ዓመት፤ የውጭ ፕሮፌሽናሎች ብዛት 13፤ የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች 17 ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የ22 ተጨዋቾች ስብስቡ በትራንስፈር ማርከት 363.50 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመን ያለው  አትሌቲኮ ማድሪድ የቡድኑ አማካይ እድሜ 26.4 ዓመት፤ የውጭ ፕሮፌሽናሎች ብዛት 14፤ የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች 13 ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
በመላው ዓለም ከፍተኛ እውቅና ካላቸው የእግር ኳስ ብራንዶች አንዱ ሪያል ማድሪድ ሲሆን ከ280 ሚሊዮን በላይ ክለቡን ይከታተላሉ፡፡ የተመሰረተው ከ114 ዓመት በፊት ነው፡፡ የተመዘገቡና መዋጮ የሚከፍሉ በርካታ ደጋፊዎች ካሏቸው የአውሮፓ ክለቦች አንዱ የሆነው አትሌቲኮ ማድሪድ በየውድድር ዘመኑ 65 ሺ ሙሉ ትኬት የሚገዙ አባላት አሉት፡፡ ክለቡ የተመሰረተው ከ113 ዓመታት በፊት ነው፡፡
ቅፅል ስሞቻቸው
አትሌቲኮ ማድሪድ ሶስት ቅፅል ስሞች አሉት፤ ሎስ ኢንድያንስ ማለት ህንዶቹ፤ ሎስ ኮልቾኔሮስ ማለት ብርድ ልብስ ሰፊዎቹ እንዲሁም ሎስ ሮጂብላንኮስ ደግሞ ቀይ እና ነጮቹ ማለት ነው፡፡ሪያል ማድሪድም ሶስት ቅፅል ስሞች አሉት፡፡ የመጀመርያው ሎስ ብላንኮስ ሲሆን ትርጉሙ ነጮቹ፤ ሎስ ሜሪንጊዌስ እና በቀድሞ የምስራቅ አውሮፓ ጦረኞች ስም ዘ ቫይኪንግስ ተብለውም ይጠራሉ፡፡
የሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊዎች
ከስፔን ሪያል ማድሪድ (10)፣ ባርሴሎና (5)
ከጣሊያን ኤሲሚላን (7)፣ ኢንተርሚላን (3)፣ ጁቬንትስ (2)
ከእንግሊዝ ሊቨርፑል (5)፣ ማን.ዩናይትድ (3)፣ ኖቲንጋም ፎረስት (2)
አስቶን ቪላ (1)፣ ቼልሲ (1)
ከጀርመን ባየር ሙኒክ (5)፣ ሀምበርግ (1)፣ ቦርስያ ዶርትወንድ (1)
ከሆላንድ አያክስ (4)፣ ፌዬኖርድ (1)፣ ፒ ኤስ ቪ (1)
ከፖርቱጋል ቤነፊካ (2)፣ ፖርቶ (2)
ከፈረንሳይ ኦሎምፒክ ማርሴይ፣  ከዩጎዝላቪያ ሬድ ስታር ቤልግሬድ፣ ከቡልጋርያ ስታዎ ቡካሬስት እንዲሁም ከአየርላንድ ሴልቲክ አንድ ጊዜ ሻምፒዮን ሆነዋል፡፡

Read 3121 times