Saturday, 07 May 2016 13:47

መንግስት በኮንቴነሮች ክምችት ለተጨማሪ ወጪ ተዳርጌአለሁ አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

ከ6ወር በላይ በወደብ የቆዩ ኮንቴነሮች ይወረሳሉ መባሉን ባለሀብቶች ተቃወሙ

    የኢትዮጵያ መንግስት ለጅቡቲ ወደብ ኪራይ በወር ከ300-400 ሚሊዮን ብር እየከፈለ እንደሚገኝ የተገለፀ ሲሆን የኮንቴነሮች ከወደቡ በፍጥነት ያለመጓጓዝ መንግስትን ለተጨማሪ ወጪና የአሰራር መስተጓጐል እየዳረገው መሆኑ ተጠቆመ፡፡
በሀገር ውስጥ የተቋቋሙትን ደረቅ ወደቦች በመጠቀም ቀደም ሲል ከወደብ እቃዎችን ለማንሳትና ለማጓጓዝ ይፈጅ የነበረው ጊዜ እያጠረ ቢሆንም ሀገር ውስጥ ባሉ ደረቅ ወደቦች ላይ የተከማቹ ኮንቴነሮች በተሠጣቸው የጊዜ ገደብ ባለመነሳታቸው የቦታ መጣበብ ከመፈጠሩም በላይ መንግስት ሊያገኝ የሚገባውን ጥቅም እያሣጣው እንደሆነ ተጠቁሟል።
በጅቡቲ ወደብ ለአነስተኛ ኮንቴነር በቀን ከ107 ብር በላይ ለኪራይ የሚከፈል ሲሆን ለትልቁ ኮንቴነር በቀን ከ236 ብር በላይ ኪራይ እንደሚከፈል የጠቀሱት የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አህመድ ቱሣ፤ ሀገሪቱ በአመት እስከ 5 ቢሊዮን ብር ለኮንቴነር ማስቀመጫ ቦታ ኪራይ እንደምትከፍል ተናግረዋል። መንግስት በቀን ለኮንቴነሮች ማስቀመጫ በሚል ለጅቡቲ ወደብ የሚያወጣውን ወጪ ለመቀነስ ከወደቡ በፍጥነት እቃዎችን ለማጓጓዝ ጥረት እያደረገ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አህመድ፤ 2600 ያህል ተሽከርካሪዎች ኮንትራት ወስደው እቃዎቹን ወደ ሀገር ውስጥ ደረቅ ወደቦች እያጓጓዙ መሆኑንና በቀን 400 ያህል ተሽከርካሪዎች እቃ ጭነው ወደ ሀገር ውስጥ እየገቡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ በዚህ መንገድ በወር እስከ 16ሺህ ኮንቴነር ወደ ሀገር ውስጥ እየተጓጓዘ መሆኑን ሃላፊው ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ አመት እስካሁን 12ሺህ ያህል የተለያዩ ተሽከርካሪዎችም ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን የጠቀሱት አቶ አህመድ፤ “ያገለገሉ” በሚል እየገቡ ያሉ ተሽከርካሪዎች በጉሙሩክ አቀራረጥ ላይ መጭበርበሮችን እየፈጠሩ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን፤ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው በደረቅ ወደቦች ተከማችተው በሚገኙ ኮንቴነሮችና ተሽከርካሪዎች ዙሪያ ከአስመጪዎች ጋር ባለፈው ረቡዕ ባደረገው ውይይት ላይ የባለስልጣኑ የጉምሩክ ዘርፍ ሃላፊዎች አንድ ከውጭ የገባ እቃ በደረቅ ወደቦች ሊቆይ የሚገባው እስከ ሁለት ወር ብቻ መሆኑን በመጠቆም ከ1ሺህ በላይ የሚሆኑ ኮንቴነሮችና ተሽከርካሪዎች ግን ከ3 ወር እስከ 4 አመት ገደማ ድረስ በየደረቅ ወደቦቹ ተከማችተው እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡
በሞጆና በገላን ደረቅ ወደቦች ከሁለት ወር በላይ የሆናቸው 1100 ያህል ኮንቴይነሮችና ቁጥራቸው በውል ያልተጠቀሰ ተሽከርካሪዎች ተከማችተው እንደሚገኙ የጠቀሱት የስራ ሃላፊዎቹ፤ ከእነዚህ ውስጥ እያንዳንዳቸው ከ3 እስከ 68 ያህል ኮንቴነሮች ያላቸው ባለሃብቶችና ድርጅቶች ይገኙባቸዋል ብለዋል፡፡
እቃ ከህግ አግባብ ውጪ በወደቦቹ አከማችተዋል የተባሉ 69 አስመጪ ድርጅቶችም ተለይተው መታወቃቸውን የባለስልጣኑ የስራ ሃላፊዎች ጠቁመዋል፡፡
ህጉ ከሚፈቅደው ጊዜ ገደብ በላይ በወደቦቹ ኮንቴነርና ተሽከርካሪ አከማችተዋል ከተባሉትና በውይይት መድረኩ ላይ ከተገኙ በርካታ ባለሀብቶች መካከል ከ20 በላይ የሚሆኑት በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አስተያየት እንዲሁም ያለባቸውን ችግር የገለፁ ሲሆን አብዛኞቹ እቃቸውን ለመውሰድ የገንዘብ እጥረት፣ የመረጃ ልውውጥና በባንክ አካባቢ የተፈጠሩ ችግሮች እንቅፋት እንደሆነባቸው አስረድተዋል፡፡
አንድ የኮንስትራክሽን እቃዎች አስመጪ ድርጅት ተወካይ፤ ከመንግስት የኮንስትራክሽን ስራ የሚኮናተሩ ባለሀብቶች መንግስት ገንዘብ በአስፈላጊው ጊዜ ስለማይለቅላቸው ከውጭ እንዲገባላቸው ያዘዙትን እቃ በተፈለገው ጊዜ እየተረከቧቸው ባለመሆኑ ኮንቴነራቸው በወደብ ላይ ለመዘግየቱ ምክንያት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ “መንግስት በነዚህና በመሳሰሉ ምክንያቶች በደረቅ ወደቦች ላይ የሚዘገይ ኮንቴነሮችን እወርሳለሁ ማለቱ ተገቢ አይደለም” ያሉት የድርጅቱ ተወካይ፤ ልማትን አበረታታለሁ የሚል መንግስት ንብረት ወርሶ ባለሀብቱን ከማዳከም ይልቅ እቃው በቆየ ቁጥር በቀን የሚከፈለውን የኪራይ መጠን ቢጨምርብን የተሻለ አማራጭ ነው ሲሉ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡ የድርጅታቸው 13 ኮንቴነር በደረቅ ወደብ ላይ እንደሚገኝ የጠቀሱት ሌላው ባለሀብት በበኩላቸው፤ ነጋዴዎች በደረቅ ወደብ ያሉ ኮንቴነሮችን አውጥተው ሸቀጦችን ለገበያ ካቀረቡ በኋላ የሚጠበቅባቸውን የጉምሩክ ክፍያ እንዲከፍሉ ቢደረግ ለችግሩ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ በተመሳሳይ ሌሎች ባለሀብቶችም በደረቅ ወደብ የተያዘው እቃቸው ተለቆላቸው፣ እቃውን ሸጠው የመንግስትን ድርሻ እንዲከፍሉ እንዲመቻችላቸውና የባንክ ብድር እስኪያገኙ የእፎይታ ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
ኩባንያቸው የተሽከርካሪ ጎማዎችን እንደሚያስመጣ የጠቀሱ ሌላው አስተያየት ሰጪ ባለሀብት፤ በሀገሪቱ ያለው የጎማ ገበያ ከፍተኛ ፉክክር ያለበት በመሆኑ ለተለያዩ ጎማ ፈላጊዎች የዱቤ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንና በርካቶች የሚፈለግባቸውን የዱቤ ክፍያ ስላልፈፀሙላቸው ከውጭ ያስመጡትን ምርት መረከብ እየተሳናቸው መሆኑን በመጠቆም መንግስት ያለባቸውን ጫና ተገንዝቦ፣ የእፎይታ ጊዜ እንዲሰጣቸው ተማፅነዋል። እኚሁ ባለሀብት ከውጪ ምንዛሬ ጋር የተያያዘ ችግርም በንግድ ስራቸው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥሮባቸው እንደነበር ጠቅሰው አሁን ላይ መጠነኛ መሻሻሎች መታየታቸውን ገልፀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የንግድ መቀዛቀዝ እንዳለ በአፅንኦት ያስረዱት ባለሃብቶቹ፤ የመረጃ ልውውጥ ድክመት እንዳሉ ጠቁመዋል፡- ከውጭ ያዘዙት እቃ እነሱ ሳያውቁ በባህርና ሎጀስቲክ መስሪያ ቤት በኩል ተጓጉዞ ሀገር ውስጥ ከገባ ቀናቶች ከተቆጠሩ በኋላ እቃችሁ መጥቷል እንደሚባሉ በመግለጽ፡፡
የባለሀብቱን አስተያየት ያዳመጡት በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የጉምሩክ ዘርፍ ም/ዳይሬክተር አቶ ሞገስ ባልቻ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ፤ “እቃውን አውጥተን እንጠቀምና የሚጠበቅብንን ክፍያ ለመንግስት እንፈፅም” በሚል ከባለሀብቶቹ የቀረበው ሀሳብ በጉምሩክ ህጉ የሚያስኬድ አለመሆኑን ጠቁመው፤ ተቋማቸው ያሳለፈውን የመጨረሻ ውሳኔ ለተሰብሳቢዎቹ ይፋ አድርገዋል፡፡
ከ6 ወር በላይ የቆዩ ኮንቴነሮች ከግንቦት 1 ጀምሮ እንዲወረሱ ውሳኔ ላይ መደረሱን ያስታወቁት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ ከ2 ወር እስከ 6 ወር የቆዩ እቃዎችን ባለሀብቶቹ በ1 ወር ጊዜ ውስጥ የሚፈለግባቸውን የጉምሩክ ስነ ስርአት አጠናቀው ማውጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ይህን ውሳኔ ተከትሎ ከተሰብሳቢዎቹ ከፍተኛ ተቃውሞ የቀረበ ሲሆን “ከግንቦት 1 ጀምሮ ንብረታችሁ ተወርሷል ለማለት እዚህ ድረስ መጥራት አልነበረባችሁም፤ በሚዲያ ልትገልፁ ትችሉ ነበር” ሲሉ አማርረዋል፡፡





Read 1296 times