Saturday, 07 May 2016 13:52

“ቻይልድ ፈንድ” በድርቁ እያከናወነ ያለው ድጋፍ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(13 votes)

     አንዲት ሴት ለመውለድ ወደ ጤና ጣቢያው ስትመጣ መጀመሪያ ቅድመ ወሊድ ክፍል ትቆያለች። ምጥ ሲጀምራት ወደ ማዋለጃ ክፍል ትወሰዳለች። ከወለደች በኋላ ደግሞ ተኝታ ወደምታገግምበት (ፖስትናታል) ክፍል ትወሰዳለች፡፡ እዚያ ቻይልድ ፈንድ ለሕፃናትና ለእናቶች ያስቀመጠው ፋፋ ዱቄት፣ ዘይት፣ ስኳር፣ ስላለ እንደባህላቸው እንዲጠቀሙ እንሰጣቸዋለን፡፡ በዚህ በጣም ደስተኞች ናቸው፡፡ 4 ቀን ሞልቷቸው “ውጡ” ስንላቸው፣ “አንወጣም፤ ትንሽ መቆየት እንፈልጋለን” የሚሉ እናቶች እንዳሉ የነገረን በፈንታሌ ወረዳ የቆየ ቀበሌ ጤና ጣቢያ ኃላፊ ግርማ ኃይሉ ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት ቻይልድ ፈንድ ኢትዮጵያ በኦሮሚያ ክልል ዝብ አጠርና በድርቅ በተጐዳው ፈንታሌ ወረዳ እያደረገ ያለውን ድጋፍ ለጋዜጠኞች አስጐብኝቷል፡፡ እኛም ለ3 ዓመት በአካባቢው የቆየው ድርቅ ላደረሰው ጉዳት መደጐሚያ የሚሆን ረሽን ለገልቻ ቀበሌ ነዋሪዎች ሲሰፈርለት ተመልክተናል፡፡ ለአንድ ቤተሰብ 25 ኪ.ግ አልሚ ምግብና ሁለት ኪሎ ተኩል ዘይት ሲሰጥ ነበር፡፡
ቻይልድ ፈንድ በድርቁ ለተጐዱ ከአምስት ዓመት በታች ላሉ 5.016 ሕፃናት፣ ለሚያጠቡ እናቶችና እርጉዝ ሴቶች ድጋፍ አድርጓል፣ ሕፃናት፣ ለሚያጠቡ እናቶችና እርጉዝ መስጠቱ ተገልጿል። ድርጅቱ፣ ከፈንታሌ የሕፃናትና ቤተሰብ በጐጐ አድራጐት ጋር በመተባበር በቆቦ ቀበሌ ጤና ጣቢያም ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ወ/ሮ ገሌ ጉምቢ የቆቦ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ “መንግሥት ጤና ጣቢያውን ቢሠራም በቁሳቁስ አልተሟላም ነበር፡፡ ይህ ድርደት ከመጣ ወዲህ ለሕፃናትና ለእናቶች ፎጣ ሳሙና፣ ልብሶች፣ ጫማ፣ ስለሚሰጥ በጣም ተደስተናል፡፡ በድርቁ ጉዳት የደረሰባቸው ብዙ ሕፃናት ወደ ጤና ጣቢያው እየመጡ ታክመው ተመልሰዋል፡፡ አምስት ሕፃናትም ተኝተው ታክመውና ድነው ሄደዋል፡፡ ትናንትም አንድ ጉዳት የደረሰበት ሕፃን መተኛቱን ሰምቻለሁ” በማለት ገልጸዋል፡፡
የጤና ጣቢያው ኃላፊ አቶ ግርማ፤ የተሟላ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንና ኅብረተሰቡም ጤና ጣቢያውን እንደወደደው ይናገራል፡፡ አንዲት እናት ከወለደች በኋላ 7 የልብስ ሳሙና፣ ላይፍ ቦይ፣ የሕፃን ጫማና ልብስ ዱቄት፣ ዘይት፣ ስኳር፣ ይሰጣታል። ባለፈው 2007 ዓ.ም በጤና ጣቢያው የወለዱ እናቶች ቁጥር 86 ነበር፡፡ ዘንድሮ በ8 ወር በጤና ጣቢያው የተገላገሉት እናቶች ቁጥር 198 ደርሷል፡፡
ቀደም ሲል የተሟላ አገልግሎት የማንሰጠው ከሕንፃው በስተቀር ምንም ነገር ስላልነበረን ነው። ወንበር እንኳ በተራ ነበር የምንጠቀመው፡፡ አሁን ቻይልድ ፈንድ ሁሉን ነገር አሟላልን፡፡ ወንበር፣ ጠረጴዛ፣ የማዋለጃና የመኝታ አልጋ፣ ፍራሽ፣ ብርድልብስ፣ አንሶላ አሟላልን የሕፃን ጫማና ልብስ፣ ሁለት ዓይነት ሳሙና፣ የፋፋ ዱቄት፣ አልሚ ምግቦች፣ ዘይት፣ ስኳር፣ ይሰጠናል፡፡ በፊት ውሃና መብራት አልነበረንም፡፡ ውሃ ከከተማ አንዱን ጀሪካን በ10 እየገዛን ነበር፡፡ ለመብራት የምንጠቀመው የእጅ ባትሪ ነበር፡፡ አሁን ውሃ በቦቴ ይቀርብልናል፡፡ ለመራት ደግሞ ማሾ ከእነዳጁ ተገዝቶልናል፡፡ በፊት የማዋለጃ አልጋችን አንድ ብቻ ስለነበር በወር በጤና ጣቢያው የሚወልዱ እናቶች ቁጥር 6 ብቻ ነበር። አሁን 4 የማዋለጃ አልጋዎች ስላሉን በአንድ ጊዜ ሦስት ወይም አራት ሴቶች እየተቀበልን በወር እስከ 3 እናቶች እናዋልዳለን፡፡
ሕክምናው የሚሰጠው ቻይልድ ፈንድ ባቀረበው መድኃኒት፣ ቁሳቁስ በነፃ ስለሆነ ለከብቶቻቸው ሳር ፍለጋ ቀዬአቸውን ጥለው የሄዱ አምቡላንስ እያስጠሩ፣ ከከተማ በባጃጅ እየመጡ እዚህ ይወልዳሉ…” በማለት አስረድቷል፡፡
በአካባቢው በርካታ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ይፈጸማሉ በተለይ አስገድዶ መድፈር፡፡ ስለዚህ ቻይልድ ፈንድ በሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል በመተሐራ ከተማ ስለ ጐጂ ባህላዊ ድርጊቶች ያስተምራል፡፡
ጥቃት የደረሰባቸው ሕፃናት ዳኛ ፊት ሳይቀርቡ በሌላ ክፍል ሆነው እየተጫወቱ የደረሰባቸውን ጥቃት የሚናገሩበት ፍርድ ቤት አቋቁሟል፡፡ ፍርድ ቤቱ ዘመናዊ ሲሆን በልጆቹ መጫወቻና በዳኞች ክፍል ካሜራ ተገጥሟል፡፡ በኮምፒዩተር ተደራጅቷል፣ ዲቪዴም አለው፤ በዳኞች ክፍል ካሜራ ተገጥሟል፣ በኮምፒዩተር ተደራጅቷል፣ ዲቪዲም አለው፤ የሕፃናቱ ክፍልም ሶፋና የተለያዩ መጫወቻዎች አሉት፡፡ ሕፃናቱን እያጫወቱ ቃላቸውን የሚቀበሉ ባለሙያዎችም አሠልጥኗል፡፡
መንግሥትም ድርጅቱ እያደረገ ላለው ድጋፍ እውቅና ሰጥቷል፡፡ የፈንታሌ ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሐጂ አህመድ፣ መንግሥት ድርቁ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን እየሠራ መሆኑን፣ አካባቢው ዝናም አጠር በመሆኑ በወረዳው ባሉ 18 ቀበሌዎች በአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን አማካይነት በወረዳው ለሚገኙ 59ሺ995 አባወራዎች በአንድ ሰው (በነፍስ ወከፍ) 15 ኪሎ ስንዴ ወይም በቆሎ፣ ማጣፈጫ እንደ ቦሎቄ ያለ፣ አንድ ኪሎ ዘይት እንደሚሰጥ ገልጸው ይህ ግን በቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
መንግሥት ብቻውን ድርቁን መቋቋም እንደሚከብደው የጠቀሱት አቶ ሐጂ፤ የአጋር ድርጅቶች ድጋፍ አስፈላጊና ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “ከእነሱ ጋር (ከፊንታሌ የሕፃናትና ቤተሰብ በጐ አድራጐትና ከቻይልድ ፈንድ) ጥሩ የተቀናጀ ሥራ እየሠራን ነው፡፡ ድርጅቶቹ፤ ጤና ጣቢያችንን ያግዛሉ፤ ለጤና ባለሙያዎች ሥልጠና ይሰጣሉ ለኤክስቴንሽን ሠራተኞች መንቀሳቀሻ ቢስክሌት፣ ለጤና ጣቢያው ሞተር ሳይክል፡፡ አቅርበዋል፡፡ በድርቅ ለተጐዱት በየወሩ 25 ኪ.ግ አልሚ ምግብና ሁለት ኪሎ ተኩል ዘይት ይሰጣሉ። እነሱ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉልን ስለሆነ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት” ብለዋል፡፡
የዓለም አቀፉ ቻይልድ ፈንድ ፕሬዚዳንትና ሥራ አስፈጻሚ ሚስ አንሌይማን ጐደርድ ከጉብኝቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ፣ መንግሥት ድርቁ ከቁጥጥር ውጭ ከአሜሪካህ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር እንዳይሆን ያደረገውን የተቀናጀ ጥረትና ድርቁን ለመከላከል ያስፈልጋል ተብሎ ከተገመተው 1.4 ቢሊዮን ዶላር መካከል ከግማሽ በላይ መሸፈኑን አድንቀው፣ ቻይልድ ፈንድ ለድርቁ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ከ74ሺህ ለሚበልጡ ሕፃናት ለእርጉዝ፣ ለሚያጠቡ ሴቶችና ለአረጋውያን የተመጣጠነ ምግብና ዘይት ማቅረባቸውን ገልፀዋል፡፡
ቻይልድ ፈንድ ለመጀመር ዋሽ ፕሮግራም በምንቀሳቀስባት አካባቢ ላሉ 75 ሺህ ሰዎች ውሃና የተመጣጠነ ምግብና ዘይት ማቅረብ ስላለብን፤ በሥራችን ስኬታማ ለመሆን እስካሁን ካደረግነው 2 ሚሊዮን ዶላር በተጨማሪ 5 ሚሊዮን ዶላር በአፋጣኝ ያስፈልገናል፤ በአገር ውስጥ ካሉ አጋር ድርጅቶችና ከመንግሥት ያገኘነው ድጋፍ የሚያበረታታ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በኤልኒኖ ተፅዕኖ ለተጐዱ 10 ሚሊዮን ሰዎች ድጋፍ ማድረጉ የሚያስደንቀው ነው፡፡ አገሬ እንኳ ይህ ዓይነት ችግር ቢያጋጥማት ይከብዳታል፡፡  

Read 1546 times