Saturday, 07 May 2016 13:53

እናት ስትደማ አይደለም ደም መጠየቅ ያለበት!

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

 የእናቶች ሞት ቅኝትና ተገቢው ምላሽ በሚለው አሰራር ዙሪያ፣ ሚያዝያ 12 እና 13 ቀን 2008 ዓ.ም በአዲስ አበባ አገር አቀፍ ሲምፖዚየም ተካሂዶ የነበረ ሲሆን ሲምፖዚየሙን ያካሄዱትም የኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስር ከአለም የጤና ድርጅት እንዲሁም ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ነበር። ሲምፖዚየሙ አላማው አድርጎት የነበረው የእናቶች ሞት ቅኝትና ተገቢ ምላሽ የሚለው አሰራር በአገር አቀፍ ደረጃ ከተጀመረ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ያለውን አገር አቀፍ አፈጻጸም መመልከት እና የጎደሉ ነገሮች እንዲሟሉ ውይይት ማካሄድ ነበር።
ባለፈው ሳምንት እትም በዚሁ ርእሰ ጉዳይ የተለያዩ ባለሙያዎችን ሀሳብ ለአንባቢዎች ያቀረብን ሲሆን በዚህም ዝግጅቱን ያስተባበሩት አቶ ስንታየሁ አበበ በሚኒስር መስሪያ ቤቱ በእናቶችና ሕጻናት ዳይሬክቶሬት የእናቶች ጤና ቡድን አስተባባሪ እንዲሁም ዶ/ር ሰናይት በየነ በኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስር የእናቶችና ሕጻናት ዳይሬክቶሬት የእናቶች ኬዝ ቲም ኦፊሰር እና ከጋምቤላና ሱማሌ ክልል የመጡ የጤና ቢሮ አባላት ከእንግዶቻችን መካከል ነበሩ። በሲምፖ ዚየሙ ላይ ተገኝተው ከነበሩ ድጋፍ ሰጪ አካላት መካከል የደም ባንክ አንዱ ነበር። ዶ/ር ስሜነህ አጥናፉ በብሔራዊ የደም ባንክ የላቦራቶሪና ሜዲካል አገልግሎት ዳይሬክተር ናቸው። በሲምፖዚየሙ ላይ እንደተገለጸው በተለያዩ ክልል መስተዳድሮች እናቶች በተለያየ ምክንያት ለሕልፈት ቢዳረጉም በተመሳሳይ ግን በሁሉም አካባቢዎች በመድማት ምክንያት የሚሞቱት እናቶች ቁጥር ከፍ ያለውን ድርሻ ይይዛል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የደም ባንክ ተደራሽነት ምን መልክ ይኖረዋል? ለሚለው ጥያቄ ዶ/ር አጥናፉ ከደም ባንኩ አሰራር ጀምሮ ያለውን ሁኔታ ያብራሩ ሲሆን ታነቡ ዘንድ ጋብዘናል።
ጥያቄ፡ የደም ባንክ አሰራር ምን ይመስላል?
መልስ፡ ...ብሔራዊው የደም ባንክ እንደኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ2004/ ዓ/ም ጀምሮ ከቀይ መስቀል ማህበር ስር ወጥቶ በኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስር ስር ከሆነ በሁዋላ የደም ባንክ አገልግሎት መስጫ ቁጥሩ ከ12/ ወደ 25/አድጎአል። አንዱ የብሔራዊው ደም ባንክ ሲሆን ክኒካል የሆኑ ስራዎችን የሚሰራ ነው። 24/ት የደም ባንኮች ከበጎ ፈቃደኞች ደም በመሰብሰብ አስፈላጊውን ስራ በላቦራቶሪ ውስጥ ይሰራሉ። ሆስፒታሎች ወይንም የጤና ተቋሞች አንድን ደም የማስተላለፍ ውክልና መስጠት እንዲችል ማሟላት ያለበት መመዘኛ ያለ ሲሆን በዚህም መሰረት ከደም ባንኮች ጋር የመግባቢያ ስምምነት ይኖራቸዋል። ይህ የስምምነት ሂደት ከተሟላ በሁዋላ ማንኛውም ሆስፒታል ወይንም የጤና ተቋም ደም ሲጠይቅ ከባንኩ ደም በነጻ ይሰጠዋል። ማንኛውም ሆስፒታል ወይንም የጤና ተቋም በነጻ ያገኘውን ደም ለታካሚው በነጻ መስጠት ይገባዋል።
ጥያቄ፡ ደም በምን መንገድ ይሰበሰባል?
መልስ፡ ደም የሚገኘው በሶስት መንገድ ነው።
ከበጎ ፈቃደኛ ለጋሾች፣
የታማሚ ቤተሰቦች ደም እንዲሰጡ ሲደረግ፣
እንዲሁም በክፍያ ተጠቃሚዎች የሚያመቻቹት የደም ልገሳ ነው።
 ከቤተሰብ በምትክ የሚሰጥ ደም እንዲሁም በክፍያ የሚሰጠው ሁለቱም አደገኛ ሁኔታ ያላቸው ሲሆን በበጎ ፈቃደኝነት የሚለገሰው ደም ግን ከተለያዩ በሽታዎች ነጻ ሆኖ ደሙን መጠቀም የሚቻልበት እድል እጅግ ሰፊ ሲሆን በግዢ ወይንም ከቤተሰብ የሚሰጠው ግን ምርመራዎች ከተደረጉ በሁዋላ በአብዛኛው በተለያዩ ምክንያቶች ጥቅም ላይ ሳይውል የሚጣል ነው። ስለዚህም የመጀመሪያው ንጹህ ደም የማግኛ መንገድ ንጹህ የሆነ ደም ለጋሽ ማግኘት ነው። ከበጎ ፋቃደኛ ለጋሾች ውጭ የሚሰበሰበው ደም ብዙ ችግር አለው።
ጥያቄ፡ በቤተሰብ እና በክፍያ የሚሰበሰበውን ደም ችግር ቢያብራሩልን?
መልስ፡ ደም በቤተሰብ ይሰጥ የሚለው ...ቤተሰብ የሌለውስ ማን ደም ይስጠው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ስለዚህ ደም ብሔራዊ ምርት፣ በዘር በሀይማኖት የማይለያዩበት፣ ሀብታም ደሃ፣ ሕጻን አዋቂ፣ ሳይል ዳር ድንበር የማያግደው የሰው ሕይወት ማዳኛ እንደመ ሆኑ ከበጎ ፈቃደኛ እየተሰበሰበ በነጻ መሰጠት አለበት። አንድ ሰው ደም ሲለግስ ለቤተሰቤ ብሎ ሳይሆን ደም ለሚያስፈልገው ለማንኛውም ሰው ብሎ መሆን አለበት።
 በክፍያ የሚሰበሰብ ደም...ይህ ማለት አንዳንድ ሰዎች ገንዘብ እየተቀበሉ ደም የመስጠት ተግባር ላይ ተሰማርተው እንደነበር አይዘነጋም። በእርግጥ በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ ይህ አይነቱ የደም አሰጣጥ ተወግዶአል። ነገር ግን እንደነዚህ አይነት ንግድ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ደም የመለገሻ ጊዜን ሳይጠብቁ ...ማለትም ከሶስት ወር በፊት እንዲሁም የተለያየ በሽታ እንዳለባቸውና ደማቸው ተወስዶ ከጥቅም ላይ እንደማይውል እያወቁ ለገንዘብ ሲሉ ስለሚሰጡ የደም ባንኩ ላይ የስራ ጫና ያስከትላል። በእርግጥ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ይህ አሰራር ቀርቶአል።
 በ2008/ ግማሽ አመት ግምገማ እንደታየው 97.3 በመቶ ደም የተሰበሰበው ከበጎ ፈቃደኞች በመሆኑ ስጋት የለም።
ጥያቄ፡ ከእናቶች መድማት ጋር በተያያዘ የደም ባንኩ ተደራሽነት ምን ይመስላል?
መልስ፡ እንደደም ባንክ የምንወስደው ኃላፊነት አለ። ይህም ጤንነቱ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ደም በበቂ መጠን ማዘጋጀት እና ለጤና ተቋማት ማቅረብ የሚል ነው። አሁን ባለኝ መረጃ በአገር አቀፍ ደረጃ መቶ በመቶ ባይሆንም ደም ባንኮች አስፈላጊውን ደም እያቀረቡ መሆኑን ነው። እኛ ይህንን ስናደርግ በጤና ተቋማቱ በኩል ደግሞ ሊደረግ የሚገባው ነገር አለ። አንዲት እናት ለመውለድ ወደ ጤና ተቋሙ ስትመጣ አይደለም የደም ጥያቄ መቅረብ ያለበት። መጀመሪያውኑ ተቋሙ ደሙን አዘጋጅቶ ተጠቃሚውን መጠበቅ ነው የሚገባው። ከዚህም በላይ አንዲት እናት በእርግዝና ክትትልዋ ወቅት የደም አገልግሎት ትሻለች ተብሎ ሲታመን ይህ አገልግሎት ወደሚሰጥበት ወይንም አቅሙ ወዳለበት ሆስፒታል ወይንም የጤና ተቋም መተላለፍ ይገባታል።
ጥያቄ፡ ደም ከበጎ ፈቃደኛ ለጋሾች ብቻ ተሰብስቦ የሚፈለገው መጠን ይገኛልን?
መልስ፡ በዚህ በሶስት አመት ውስጥ እንደታየው ከሆነ ውጤታማ ነው። ለምሳሌም አዲስ አበባ ያሉ ሆስፒታሎች ወይንም የጤና ተቋማት ከበጎ ፈቃደኞች በተለገሰ ደም መቶ በመቶ ፍላጎቱን አሟልቷል። አማራ 101ኀ ትግራይ 99 ኀ ፍላጎቱን አሟልተዋል። ሌሎች ክልሎችም ለምሳሌ እነሐራሪም ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በእርግጥ ራቅ ባሉ አካባ ቢዎች ችግር የለም ማለት አይቻልም። ለምሳሌም እንደሱማሌ እና ጋምቤላ በመሳ ሰሉት አካባቢዎች የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ቢኖሩም የሚፈለገውን ለማሟላት ገና ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል። ቢሆንም ግን በአለም ባለው መስፈርት መሰረት ከበጎ ፈቃደኞች የሚሰበሰበው ደም መጠን አንድ አገር 85ኀ እና ከዚያ በላይ ከሆነ መስፈርቱን እንዳሟላ ስለሚቆጠር የኢትዮጵያም ከዚያ በላይ ደርሶአል።
ጥያቄ፡ የደምባንኮች ከጤና ተቋማቱ በምን ያህል እርቀት መገኘት ይገባቸዋል?
መልስ፡ እንደአገር አቀፍ አንድ የደም ባንክ ከ150-200/ ኪሎ ሜትር ርቀት ላሉ ሆስፒታሎች መድረስ አለበት። በአሁኑ አደረጃጀት በተቻለ መጠን በዚህ ርቀት ላይ እንዲገኙ ተደርጎአል።
ጥያቄ፡ ሆስፒታሎች ወይንም የጤና ተቋማት የሚያቀርቡት የደም ጥያቄ በምን መልክ ይስተናገዳል?
መልስ፡ ከደም ባንኩ 150/ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለ የጤና ተቋም ወይንም ሆስፒታል የደም ጥያቄውን ማቅረብ ያለበት እናቲቱ ስትመጣ አይደለም። እንደሚፈለግ አስቀድሞ አውቆ እና ጠይቆ ደሙን በሆስፒታሉ ወይንም በጤና ተቋሙ ማስቀመጥ መቻል አለበት። በሆስፒታል ደም እንደሌለ እርግጠኛ ከሆነ ደግሞ ያች እናት እስክትደማ ሳይጠበቅ የተሻሉ አማራጮችን መውሰድ ይገባል። በደም ባንኩ በኩል ሆስፒታሎቹ እንዲያውቁት የሚፈለገው በስምምነታቸው መሰረት ሆስፒታሎች ማሟላት የሚገባቸው የሆስፒ ታሎች ትንሹ የደም ባንክ እንዳይራቆት ማድረግ ነው። ከዚያም ካለው አደጋ የተነሳ ለእናቶች ቅድሚያ በመስጠት የእናቶችን ሞት መቀነስ ይገባቸዋል። ሆስፒታሎቹ ተገቢውን አሟልተው የደም ባንኩን ሲጠይቁ ደም ማቅረብ ካልቻለ ኃላፊነቱ የደም ባንኩ ይሆናል ማለት ነው።
ማንኛዋም እናት፡-
ክብሯን የማያጉዋድልና አክብሮት የተሞላበት የጤና አገልግሎት የማግኘት፣
ከአድልዎ የፀዳ በእኩልነትና ፍትሐዊ የሆነ የጤና አገልግሎት ማግኘት፣
ጤንነቷ ተጠብቆ የመኖርና ተገቢ የጤና ክብካቤ በነጻነት የማግኘት፣
በነጻነት የጤና ክብካቤ የማግኘትና ያለመገደድ፣
ሰብአዊ ክብሯና የግል ውሳኔዋን የማስከበር መብት አላት።

Read 1808 times