Saturday, 14 May 2016 12:19

“ከፈለግን እናፈርሰዋለን…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(17 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው…የያዝነው ዘመን ምን የሚባለው ነው? ጆሯችን ከደግ ይልቅ ክፉ ወሬ በዛበታ! የምትከፍቱት የቴሌቪዥን ጣቢያ ሁሉ አንድ ‘ገር የሚመስል’ ዜና ከአምስት የ‘ስምንተኛው ሺህ’ አይነት ወሬ ጋር ያወራል፡፡ (‘ዛራና ቻንድራን ሳይጨምር!’ ቂ…ቂ…ቂ… እኔ የምለው…እነሱ ልጆች ገና ዕጣ ፈንታቸው ሳይለይ አወዛገቡንሳ!)
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…‘ራሱን የቀባ ንጉሥ’ እየበዛብን ነው፡፡ ልክ ነዋ…‘ላይስ’ እሺ ይሁን “ወደሽ ነው በቀበሌ ተገደሽ…” እንደሚሉት አይነት ንጉሥ ባይሆኑም እንደ ንጉሥ ሲያደርጋቸው ‘ዝም’ እንላለን፡፡ (የዘንድሮዎቹ መኪኖች ደግሞ ሲያማምሩ! ቂ…ቂ…ቂ…)
ታዲያላችሁ… ይሄ የ‘ንጉሥነት መንፈስ’ ታች ያለነው አካባቢ እየበዛ ሲሄድ አሪፍ አይደለም፡፡ አሀ…ማን ማንን ሊይዝ ነው! ባለቤት እንደሌለው ቤት ‘ሚጢጢው’ም፣ ‘ሱፐር ሚጠጢው’ም እየተነሳ…ኳስ አቀባይ አይነት ነገር ሲያደርገን የሆነ ነገር ተዛብቷል ማለት ነው፡፡ ለነገሩ ዘንድሮ…‘አንዳንድ የአዲስ አበባ’ ነዋሪዎች የሚሉት እንዳለ ሆኖ…ከተዛባው ያልተዛባውን መጥቀስ ባይቀል ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ‘ሆዴ ጭንቀቴ’ ምናምን እንዳንባባል እያደረገን ያለው ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…የአስተሳሰብ መዛባት፡፡
በቀደም ሬድዮ ላይ አንድ  ዜና ነበር፡፡ ኮንዶሚኒየም ግቢዎች ውስጥ ለጋራ መጠቀሚያ የሚዘጋጁ ስፍራዎች አሉ አይደል…እነሱን ምድረ ኮሚቴዎች በ“ምን ታመጣላችሁ” አይነት እያከራዩ ነው አሉ፡፡ ታዲያላችሁ የሆነ ኮንዶሚኒየም ግቢ ያለ የጋራ መጠቀሚያን እየሸነሸኑ ለምኑም ለምናምኑም ያከራያሉ፡፡ ነዋሪዎቹ “መጠቀሚያ አጣን…” ይላሉ፡ ‘ጉዳዩ የሚመለከታቸው’ ክፍሎች ኮሚቴዎቹ እንደዛ የማድረግ መብት የላቸውም ይላሉ፡፡
ታዲያላችሁ…የሆነ የኮሚቴው ሰው የነዋሪዎቹ የጋራ መጠቀሚያ ኮሚቴው ለሌላ አገልግሎት ማከራየት እንደማይችል በጥያቄ መልክ ሲቀርብለት ምን ቢሉ ጥሩ ነው…
“ከፈለግን እናፈርሰዋለን…” እናም፣ ህጉም ደንቡም ስልጣን ያልሰጠው አካል “ከፈለግን እናፈርሰዋለን…” የሚልባት አገር የእኛዋ ብቻ ሳትሆን አትቀርም፡፡
እናላችሁ…መከራ እየበላን ያለነው “ከፈለግን እናፈርሰዋለን…” አይነት አመለካከት ያላቸው ‘የበታች አካላት’ እየበዙ ስለሆነ ይመስለኛል፡፡
ራሳቸውን ቀብተው ያነገሡ የጥበቃ አባላት በየቦታው አሉላችሁ፡ ኮሚክ እኮ ነው…ጉዳያችሁ የፈለገ ከባድና አጣዳፊ ቢሆን፣ የፈለገ ቀጠሮ ቢኖራችሁ… የጥበቃ ሠራተኛው ‘የዓይናችሁ ቀለም’ ካላማረው…“መግባት አይቻልም” ሊላችሁ ይችላል። ‘የሚጠይቀው’ የለማ! ሀይ የሚል የሌለባት አገር እየመሰለች ነዋ! (አንዳንዴ..አለ አይደል…ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ብዙ ቦታ ውሳኔ ሰጪ የጠፋው፣ ብዙ ቦታ ለፊርማ የቀረቡ ፋይሎች አቧራ የሚቅሙት…በቃ ‘ፈራሚው’ ሁሉ ያደፈጠ ይመስለኛል፡፡) አሀ…
እግረ መንገዴን… የጥበቃ ነገር ግርም ይለኛል፡፡ ብዙ ቦታ ‘ተዳብሳችሁ’ ነው የምትገቡት፡፡ አንዳንድ ቦታ ደግሞ “ለፍተሻው ተባበሩን” የሚሠራው እንደ ሰዉ አይነት ነው፡፡ የእኔ ቢጤ ምስኪኑ ራቁቱን እንኳን ቢሆን ተበጥሮ ሲፈተሽ አንዳንዶቹ መለስተኛ ቡቲክ መስለው ‘ተሰግዶላቸው’ ይገባሉ፡፡  የውስጥ ሰርኩላር ምናምን ካለ ንገሩና! ‘ከልጅ ልጅ እየለዩ’ ዓመት የሚቆዩባት አገር የእኛዋ ብቻ ትመስለኛለች። ቂ…ቂ…ቂ…
የ‘ፈረንጅ’ ነገርማ ተዉት፡፡ ብዙ ቦታ “ፈረንጅ ምን በወጣው ነው የሚፈተሸው!” የተባለ ነው የሚመስለው፡፡ ሃሳብ አለን… የአንዳንድ አገር ዜጎች ያለቪዛ መግባት እንዲችሉ እንደሚደረገው አይነት ስምምነት... አለ አይደል… ዜጎቻቸው በአገሪቱ ህንጻዎች ሳይፈተሹ እንዲገቡ የሚል ስምምነት የተፈራረምናቸው አገሮች ካሉ ይነገረና! አሀ…ፈረንጅ ‘ፍሪጁን የከተተበት’ የሚመስል ቦርሳ ይዞ ሰተት ብሎ ሲገባ እየተሳቀቅን፣ በ‘ባላንስድ ዳየት እጦት’ የሳሳ ትከሻችን ጭርሱን ለፎቶ እንኳን ያህል ሊጠፋ ነዋ!
እናላችሁ…መከራ እየበላን ያለነው “ከፈለግን እናፈርሰዋለን…” አይነት አመለካከት ያላቸው ‘የበታች አካላት’ እየበዙ ስለሆነ ይመስለኛል፡፡
ራሳቸውን በንግሥትነት የቀቡ ጸሀፊዎች በየቦታው አሉላችሁ፡፡ (‘ሂዩመን ሄይር’ና አርቲፊሻል ዳሌ ዘንድሮ ጉድ አመጣብን እኮ! ዳሌ እወዳለሁ የምትለው ጓዴ…‘ፌኩ’ን ከእግዜር ሥራ የምትለየው እንዴት ነው! ማን ያውቃል…ዳሌ መውደድ ፋሺን የሚሆንበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል!)
እናላችሁ…ራሷን በንግሥትነት የቀባች ጸሀፊ አትጥመዳችሁ፡፡ እንደ እኛ አይነቱ ‘ኮመን’ ዓይነ ውሀው ልብ የማያነጥር ምስኪን…አለ አይደል…የጸሀፊዋን አጥር ለማለፍ ከልመና በተጨማሪ ሱባኤ ነገር ሳያስፈልገው አይቀርም፡፡ ቀጠሮ ይኑራችሁ አይኑራችሁ፣ ጉዳያችሁ አስቸኳይ ይሁን አይሁን… ዕድላችሁ ራሷን በ‘ንግሥትነት’ በቀባችው ጸሀፊ እጅ ውስጥ ነው፡፡ ከፈለገች ታስገባለች፣ ካልፈለገች አታስገባም፡፡
ፈረንጅ እንደሚለው… ‘ኤንድ ኦፍ ስቶሪ!’
እናላችሁ…መከራ እየበላን ያለነው “ከፈለግን እናፈርሰዋለን…” አይነት አመለካከት ያላቸው ‘የበታች አካላት’ እየበዙ ስለሆነ ይመስለኛል፡፡
እኔ የምለው እንግዲህ ጨዋታም አይደል…‘ላይ’ ያሉትም “ከፈለግን እናፈርሰዋለን…” አይነት ሲሉ…‘ታች’ ያለውም “ከፈለግን እናፈርሰዋለን…” እያለ መሀል ላይ እኮ ፉርኖ አደረጉን!
እናላችሁ…ነገሬ ብላችሁ ካስተዋላችሁ ከአንድ ቦታ ሌላ ቦታ እስክትደርሱ “ከፈለግን እናፈርሰዋለን…” አይነት መአት ነገር ይገጥማችኋል፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በዛ ሰሞን ‘ሲበቃ በቃ ነው’ አይነት ነገር ተጀምሮ አልነበረም! ለምን ይዋሻል…አንዳንዶቻችን የሆነ ሱናሚ ሊጀመር ነው ብለን ስናስብ…ነገሩ ሁሉ ‘ዘ ሴም ኦልድ ስቶሪ’ ሆነና ቀረ እንዴ! ስሙኝማ… የሆነ ጨዋታ ምናምን ላይ የቡድንና የቡድን አባቶች “ከትንሽ አሳና ከትልቅ አሳ” ስትባሉ…‘መምረጥ’ የእናንተ ፈንታ ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…መከራ እየበላን ያለነው “ከፈለግን እናፈርሰዋለን…” አይነት አመለካከት ያላቸው ‘የበታች አካላት’ እየበዙ ስለሆነ ይመስለኛል፡፡
የሆነ ከመዝገብ ቤት መውጣት ያለበት ዶሴ ምናምን አላችሁ፡፡ የበላይ አካል ፊርማ ግጥም ያለበት ደብዳቤ ይዛችሁ ወደ መዝገብ ቤት፡፡ የመዝገብ ቤቱ ሰውዬ ትንሽ ያንጎዳጎድና ምን ይላል መሰላችሁ… “መዝገቡን ላገኘው አልቻልኩም…” ይላችኋል፡፡ ሙሉው መዝገብ ቤት ያሉት ፋይሎች እኮ ሁለት መቶና ሁለት መቶ ሀምሳ እንኳን ላይሞሉ ይችላሉ፡፡ እና እንደው እንደ ባለጉዳይ “መብቴ ነው…”  “ታክስ ከፋይ ነኝ…” ቅብጥርስዮ ማለት ስትጀምሩ…“ጠፋ በቃ ጠፋ…ሲገኝ ይሰጥሀል…” ይላችኋል፡ እናማ…ራሱን በ‘ንጉሥነት የቀባው’ የመዝገብ ቤቱ ሠራተኛ ከፈለገ ያገኝላችኋል፣ ካልፈለገ አያገኝላችሁም፡፡
ፈረንጅ እንደሚለው… ‘ኤንድ ኦፍ ስቶሪ!’
እናላችሁ…መከራ እየበላን ያለነው “ከፈለግን እናፈርሰዋለን…” አይነት አመለካከት ያላቸው ‘የበታች አካላት’ እየበዙ ስለሆነ ይመስለኛል፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የመፍረስ ነገር ከተነሳ…አራት ፎቅ ህንጻ ገና ተገንብቶ ሳያልቅ “ከእነነፍሱ ዘጭ” የሚልበት ዘመን መጣ! እግረ መንገዴን…ተጀምረው ያላለቁ ህንጻዎች ሳይ ምን ይገርምህ ነበር አትሉኝም…የባንኮች እሽቅድድም! የምር እኮ የዛሬ ሁለት ዓመት ለማለቃቸው እንኳን የማያስተማምኑ  ህንጻዎች ምንም ባይኖራቸው የሆነ የባንክ ቅርንጫፍ ይኖራቸዋል፡፡ ወይ ባንኩ ተከፍቷል…ወይ ‘በቅርብ ጊዜ እዚህ የምናምን ባንክ ቅርንጫፍ ሥራ ይጀምራል” የሚል ባነር ይለጠፋል፡፡
እናማ…ራሳችንን በ‘ንጉሥነት የቀባን’ እየበዛን ነው፡፡ አንድ አገር ስንት ‘ንጉሥ’ መሸከም ትችላለች! ይሄ የራስ ተነሳሽነት ንግሥና ሲበዛ… “ከፈለግን እናፈርሰዋለን…” የሚለውም በዛው ልክ ሲጨምር…ተራዎቹ የት እንድረስ!
‘ባለፈው ስርአት’… (አይደል የሚባለው)  ምድረ ቀበሌ ሁሉ ዲሞትፈር ምናምን ታድሎ ያ ሁሉ ጉድ ከታየ በኋላ አንዱ ባለስልጣን … “አንድ ንጉሥ አውርደን ሁለት መቶ ሰማንያ ምናምን ስልጣን ላይ አወጣን…” አይነት ነገር ብለዋል ይባል ነበር፡፡
ያልተቀባ ንጉሥ ሲበዛ አሪፍ አይደለም… “ከፈለግን እናፈርሰዋለን…” ባይ ይበዛልና!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 6298 times