Saturday, 14 May 2016 12:33

ጅማ አባቡና እና ወደ ፕሪሚዬር ሊግ ግስጋሴው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

• በከፍተኛ ሊጉ የመጀመርያ ዙር በ39 ነጥብና 23 የግብ ክፍያ መሪ ሆኖ ጨርሷል
• ፕሪሚዬር ሊግ ከገቡ ተጨዋቾች በነፍስ ወከፍ 75ሺ ብር በከተማ መስተዳድር ይሸለማሉ
• የቀድሞ ታሪኩን በመመለስ ለፕሪሚዬር ሊግ ለመብቃት፤ በአህጉር ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ይሰራል
• በህዝባዊ መሰረት የተገነባ አደረጃጀት አለው፤ ከ3 ሚሊዮን በላይ ህዝብን ይወክላል
• ዓመታዊ በጀቱ ከ500ሺ ወደ 14 ሚሊዮን ብር አድጓል
• በኢትዮጵያ እግር ኳስ ለብሄራዊ ቡድንና በተለያዩ የእድሜ ደረጃዎች ለሚገኙ ቡድኖች ከ10 በላይ
ተጨዋቾችን ለማፍራት አቅዷል

    ባለፈው ሳምንት በጅማ ከተማ ነበርኩ፡፡ የጅማ አባቡና ስፖርት ክለብ እንቅስቃሴን ከተወሰኑ የስፖርት ጋዜጠኞች ጋር በመሆን ለመታዘብ በተፈጠረልን መልካም የጉብኝት አጋጣሚ ነበር፡፡ በአዲስ መልክ እንደገና ከተመሠረተ 3ኛ ዓመቱን የያዘው ጅማ አባቡና በ2008 የከፍተኛ ሊግ የመጀመርያውን ዙር በመሪነት ያጠናቀቀበት ወቅት ላይ ጉብኝቱን በማድረጋችን አጠቃላይ የክለቡን እንቅስቃሴዎች በስፋት ለመታዘብ ችለናል፡፡ በከፍተኛ ሊጉ የመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታው በጅማው ብሄራዊ ስታድዬም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በማስተናገድ 4 ለ 0 ሲያሸንፍ ተመልካቾች ነበርን፡፡ በስታድዬሙ ውስጥና ደጃፍ የነበረው አጠቃላይ የድጋፍ ድባብ በክለቡ ውጤታማነት በከተማው ህዝብ ላይ ከፍተኛ ተስፋ መፈጠሩን የሚያመለክት ነበር፡፡ ጅማ አባቡና በከፍተኛ ሊግ ውድድሩ ላይ በምድብ 2 ባደረጋቸው 15 ጨዋታዎች አንድም ሽንፈት ሳይገጥመው በ39 ነጥብ እና በ23 የግብ ክፍያ በአንደኛ ደረጃ ለመጨረስ በቅቷል፡፡  ይህም ሁኔታ በክለቡ አበይት ምዕራፍ መከፈቱን ወደ ፕሪሚዬር ሊግ ለማደግ የተጀመረውን ግስጋሴ በአጭር ጊዜ ለማሳካት ከጫፍ መድረሱን ያረጋገጥንበት ነበር፡፡ በሁለት ምድብ ተከፍሎ በ32 ክለቦች በሚካሄደው የከፍተኛ ሊግ ውድድር ወደ ፕሪሚዬር ሊጉ የሚያድጉት ክለቦች 4 መሆናቸውን ፌደሬሽኑ አስታውቋል፡፡
ባለፈው ሳምንት እሁድ አመሻሹ ላይ በጅማ ከተማ ሴፍ ሆቴል የተካሄደ ልዩ ስነስርዓትም ነበር፡፡  ክለቡ በከፍተኛ ሊጉ በአንደኝነት በመጨረሱ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የክለቡ አባላት ምስጋና ለማቅረብ እና የማበረታቻ ሽልማቶችን ለመስጠት የተካሄደው ስነስርዓቱ የጅማ አባቡና ኦፊሴላዊ ድረገፅን በይፋ ለመክፈት፤ የክለቡን የድጋፍ  መዝሙር ለማስመረቅ እና ከጅማ ሬድዮ ፋና ሳምንታዊ የ20 ደቂቃ የሬድዮ ፕሮግራም መጀመሩን አስመልክቶ ስምምነቱን ለመፈራረም የተዘጋጀም ነበር፡፡ በምሽቱ የክለቡ ፕሬዝዳንት፤ ዋና አስልጣኝ ፤ተጫዋቾች እና ሌሎች ድጋፍ ሰጭዎች በተመዘገበው ውጤት የነበራቸውን አስተዋፅኦ በማመስገን የማበረታቻ ልዩ ስጦታዎች እና የገንዘብ ሽልማቶች ተበርክተዋል፡፡  በተለይ ደግሞ የክለቡ አብይ ስፖንሰር ሆራይዘን ፕላንቴሽን ለክለቡ ዋና አሰልጣኝና ተጨዋቾች  120ሺ ብር የገንዘብ ሽልማት የተሰጠ ሲሆን፤ ዋና አሰልጣኙ ደረጀ በላይ 25ሺህ ብሩን ሲወስዱ ተጨዋቾች የቀረውን ተከፋፍለዋል። በጅማ ቡና ክለብ ውጤታማነት ወሳኝ ሚና ለነበራቸው አባላትም ልዩ ልዩ ስጦታዎች ከክለቡ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሰጥተዋል፡፡ በአጠቃላይ ሁሉም የክለቡ ባለ ድርሻ አካላት ወደ ፕሪሚዬር ሊግ መግባትን ተስፋ ያደረገ አንድነት ያንፀባረቁበት ልዩ ምሽት ነበር፡፡ የዞኑ መስተዳደር በክለቡ ውጤታማነት የቅርብ ክትትል እያደረገ ሲሆን ጅማ አባቡና ለፕሪሚዬር ሊግ ከበቃ እያንዳንዱ ተጨዋች 75ሺ ብር እንደሚሸለም በስነስርዓቱ ላይ በድጋሚ ቃል ገብቷል፡፡
የጅማ አባቡና የስፖርት ክለብ አጠቃላይ ሁኔታን በከተማው ተገኝተን ስንታዘብ በርግጥም ወደ ፕሪሚዬር ሊግ የሚያድግ ክለብ ያስታውቃል የሚል ግንዛቤ ነው የተፈጠብን፡፡ የጅማ አባቡና ስፖርት ክለብ በህዝባዊ መሰረቱ፣ በስኬታማ የቀድሞ ታሪኩ፣ በክለቡ ስራ አመራሮች የላቀ የስራ ትጋት፣ በከተማው ህዝብ ስፖርት አፍቃሪነት እንዲሁም በጅማ ዩኒቨርሲቲ በሚሰጠው ልዩ ድጋፍ እና በግንባታ ላይ በሚገኘው ስታድዬም አንኛር በክለቡ ዙርያ የሚስተዋሉት እንቅስቃሴዎች በኢትዮጵያ እግር ኳስ በተመሳሳይ ደረጃ ለሚወዳደሩ  ክለቦች ተምሳሌት የሚሆኑ ናቸው፡፡   ባለፈው ሳምንት በከተማው የነበርን የስፖርት ጋዜጠኞች የጅማ አባቡና የስፖርት ክለብ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ቅኝት እንድናደርግ የተፈጠረውም ዕድል በአርአያነት የሚጠቀስ ነው፡፡ በጅማ ብሄራዊ ስታድዬም ክለቡ በከፍተኛ ሊጉ ያደረገውን የመጀመርያ ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ተከታትለን ከክለቡ ዋና አሰልጣኝ እና ተጨዋቾች ጋር ከመወያየታችንም በላይ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ከክለቡ  ሁለት ስራ አስፈፃሚዎች ጋር ቃለምልልሶች አድርገናል፡፡ ሁለቱ የክለቡ ስራ አስፈፃሚ አባላት የጅማ አባቡና ስፖርት ክለብ ፕሬዝዳንት የሆኑትና የቀድሞ ክለቡ ታዋቂ ተጨዋች  አብዱልከሪም አባገሮ ወይንም በቅፅል ስማቸው የጅማው ፔሌ እንዲሁም በጅማ ዩኒቨርሲቲ የግብርና እና እንስሳት ህክምና ኮሌጅ ውስጥ የአስተዳደር ዳይሬክተር  ፤ የጅማ አባቡና ክለብ ስራ አስፈፃሚ አባል እና አቃቤ ነዋይ ወይዘሮ ኡሚ አብዱልቃድር  ናቸው፡፡የጅማ አባቡና ስፖርት ክለብ የቀድሞ ታሪኩን ለመመለስ ከዛም ባለፈ የዞኑ ምርጥ ቡድን በመሆን የሀገራችን እግር ኳስ አንድ ደረጃ ለማድረስ በማቀድ ስለሚሰራባቸው ሁኔታዎች ማብራርያ ሰጥተውናል፡፡
የ “ጅማው ፔሌን” ተዋወቋቸው
የጅማ አባቡና ስፖርት ክለብ ፕሬዚዳንት አብዱልከሪም አባገሮ ከ13 ዓመታቸው ጀምሮ እግር ኳስን በመጫወት ያደጉ ናቸው፡፡ በጅማ ከተማ ከ50 ዓመታት በፊት በነበሩት የእግር ኳስ ገናና እና ወርቃማ እንቅስቃሴዎች ያለፉ ምርጥ ስፖርተኛ ናቸው፡፡ በተለያዩ ክለቦች እና የዕድሜ ደረጀዎች እግር ኳስ ተጨዋች ሆነው ያሳለፉት አብዱልከሪም  አባገሮ  ‹‹የጅማው ፔሌ›› የሚለውን ቅፅል ስም ያተረፉት ያለምክንያት አልነበረም፡፡ በተጨዋችነት ዘመናቸው የነበራቸው ልምድ፤ ውጤታማነት በጣም የሚያስገርም ነው፡፡ ሁለት ቀዶ ጥገናዎችን በእግራቸው እና በጭንቅላታቸው ላይ በማድረግ ያሳለፉት የተጨዋችነት ዘመናቸው ከፍተኛ ተመክሮ ይገኝበታል፡፡ ዛሬ ክለቡን በፕሬዝዳንትነት በመምራት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ የሚገኙት አብዱልከሪም፤ የፔሌን የእግር ኳስ ህግጋት አጥንተው ራሳቸውን የገነቡ የቀድሞ ምርጥ ተጨዋች ሲሆኑ በተጨዋችነት ባለፉባቸው ክለቦቻቸውና ሌሎች ቡድኖች ከአሰልጣኞቻቸው ከሚያገኙት ድጋፍ እና ልምምድ ባሻገር በግል ጥረታቸው በትጋት ራሳቸውን በማሰልጠን አርዓየነት ያለው ተመክሮ ያሳለፉ ምርጥ ስፖርተኛ ነበሩ። አብዱልከሪም አባገሮ እንደፔሌ በሁለቱም እግሮቻቸው ይጫወታሉ፡፡ በመላው ሰውነታቸው ኳስን መቆጣጠር ይችላሉ፤ እንደ መድፍ የሚቆጠር የኳስ ምት ነበራቸው። በጭንቅላት ኳስ በመግጨት ምርጥ ነበሩ፡፡ የአብዶ ችሎታቸውም ልዩ ነበር፡፡ በ1973 ዓም በጅማ ከተማ ውስጥ በክለብ ደረጃ  እየተጫወቱ ለኢትዮጵያ ተስፋ ቡድን ተመርጠው  በወሎና በጎጃም ምርጥ ከነበሩት  ሙሉጌታ ከበደ፤ ሙሉጌታ ወልደየስ እና ገብረመድህን ሃይሌ ጋር ተጫውተዋል፡፡ በስራ ምክንያት ወሎ በነበሩበት ወቅትም ከ1974 እስከ 1978 ዓም ለወሎ ምርጥ ቡድን ከእነሙሉጌታ ከበደ ጋር በመጫወት አሳልፈዋል፡፡ በተለይ በ1975 ዓም ላይ የወሎ ምርጥ ከጎጃም ምርጥ ጋር ለኢትዮጵያ ትቅደም  አድርጐት በነበረው የፍፃሜ ጨዋታ ባለቀ ሰዓት እሳቸው እና ሙሉጌታ ከበደ ባገቧቸው ጎሎች ዋንጫ ማሸነፋቸውን አብዱልከሪም አባገሮ ያስታውሳሉ፡፡ አብዱልከሪም አባገሮ በእግር ኳስ ያላቸው ልምድ በተጨዋችነት ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በአሰልጣኝነት አስፈላጊውን ትምህርቶች ወስደው ከመስራታቸውም በላይ በዳኝነትም ስልጠና በማግኘት የእግር ኳስ እውቀታቸውን አዳብረዋል፡፡
ጅማና ስፖርት ከ50 ዓመታት በፊት
ጅማ የፍቅርና የሰላም ከተማ መሆኗን የሚናገሩት አብዱልከሪም አባገሮ በተለይ በ1960ዎቹ ከ7 በላይ የጎጆ ኢንዱስትሪዎች እንደነበሯት፤ ከኢትዮጵያ መዲናዎች ለመዝናኛነት ተመራጭ እንደነበረች፤ በሳምንት ከስድስት በላይ የአውሮፕላን በረራዎች የምታስተናግድ፤ መኪና እና ሌሎች ሸቀጦች የሚመረቱባት እና ለአገር አቀፍ ገበያ የሚቀርቡባት የንግድ መናኸሪያ እንደነበረችም ያስታውሳሉ፡፡ ከአባ ጅፋር ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያን በንግድ፤ በሃይማኖት ያስተዋወቀች ታሪካዊ ከተማ እንደነበረችም ይገልፃሉ፡፡ ከ50 ዓመታት በፊት የጅማ ከተማ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጠንካራ ስለነበር  ስፖርቱም በከፍተኛ ደረጃ የተስፋፋ እንደነበር ያወሱት አብዱልከሪም አባገሮ፤  በእግር ኳስ ብቻ ሳይሆን፤ በብስክሌት፤ በቅርጫት ኳስ እና በመረብ ኳስ ስፖርቶች በከተማዋ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንደነበር ሲያስታውሱ በተለይ በቅርጫት ኳስ 3 እንዲሁም በመረብ ኳስ 2 ተጨዋቾች ለብሄራዊ ቡድን ያስመረጠች ከተማ መሆኗን በማስረጃነት በመጥቀስ ነው፡፡  የጅማ አባቡና ስፖርት ክለብ በወቅቱ የእርሻ ተቋም በሚባለው በአሁኑ ጅማ ዩኒቨርስቲ ቅጥር ግቢ የተቋቋመው በ1948 ዓም እንደነበር የሚያስታውሱት አብዱልከሪም አባገሮ፤  ዮሴፍ ሙለታ ፤ አባካኖ፤ መልካሙ፤ ሃብታሙ እና ሌሎች እውቅ ተጨዋቾች የተሰባሰቡበት ጅማ አባቡና በክፍለሃገር ደረጃ በተከታታይ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃ፤ ልዩ ዝና እና የስኬት ታሪክ የነበረው ገናና ክለብ መሆኑን  ጨምረው ያስታውሳሉ። ገናና እና ወርቃማ ብለው በሰየሙት የተጨዋችነት ዘመናቸው በከተማው የነበረውን የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ሲያስረዱም በጅማ ከተማ 12  ክለቦች፤ 12 የቢ ቡድኖች፤ 13 የሲ ቡድኖች እንደነበሩ በማመልከት ነበር፡፡ ዛሬ የጅማ አባቡና ፕሬዝዳንት ለመሆን የበቁት አብዱልከሪም አባገሮ፤ በተጨዋችነት ዘመናቸው ወደ ዋናው ክለብ ከማደጋቸው በፊት በጊቤና በአየርመንገድ  የቢ እና ሲ ቡድኖች ተጫውተው ያሳለፉበትን ልምድ ሲያስረዱ በወቅቱ ስፖርቱ በህዝባዊ መሠረት የጠነከረ፣ በትምህርት ቤት እና በታዳጊ ውድድሮች የተስፋፋ መሆኑን በማስገንዘብ ነው፡፡ ጅማ አባ ቡና ስፖርት ክለብ በ1960ዎቹ በኢትዮጵያ ዝና ከነበራቸው ክለቦች አንዱ ነበር፡፡ ያኔ በከተማው ጠንካራ የክለቦች የውስጥ ውድድር  እንደነበር  ሲታወስ አባቡናን ጨምሮ ጅማ እና ፍሬው፤ሚያዚያ 27፤ ገነት ፤ ፖሊስ እና መድፈኛ፤የመሳሰሉት ጠንካራ ቡድኖች ነበሯቸው፡፡ በወቅቱ በተለይ ጅማ አባ ቡና  ከከተማው አልፎ የከፋ ምርጥ ቡድን በመሆን ሲታወቅ ከአዲስ አበባ ተወካዮች ቅ/ጊዮርጊስ ፣መቻልና ኦሜድላ፤ ከድሬደዋ ተወካዮች ሲሚንት ፣ኮተን እና ምድር ባቡር እንዲሁም ከኤርትራ ክለቦች በአገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ ሻምፒዮናዎች ጠንካራ ተፎካካሪ ነበር፡፡ ከ50 ዓመታት በፊት የነበረው ይህ የጅማ ከተማ ገናና እና ስኬታማ የስፖርት እንቅስቃሴ በከተማዋ የኢኮኖሚ ሁኔታ መቀዛቀዝ ሳቢያ ለበርካታ ዓመታት ተዳክሞ ቆይቷል፡፡ ይህን ሁኔታም አብዱልከሪም አባገሮ  ሲያስረዱ፤ የጅማ ከተማ የመዝናኛና የንግድ መናሐርያነት በደርግ ዘመን በመፍረሱ እንደሆነ ዋንኛው ተፅእኖ እንደነበር ጠቅሰው ስፖርት ከኢኮኖሚ ጋር ትስስር ያለው መስክ በመሆኑ ጅማ አባቡና እና ሌሎች ቡድኖች ተዳክመው በመፍረሳቸው የከተማው የስፖርት እድገት መሰናከሉን በቁጭት ገልፀዋል፡፡
የጅማ አባቡና ዳግም ምስረታ
“አባ ቡና ቀደም ሲል በጅማ ዩኒቨርሲቲ ያኔ እርሻ ተቋም በሚባልበት ወቅት ሲመሰረት በከተማው በጣም ባለዝና እንደነበር በከተማው ነዋሪዎችም የሚወደድ ውጤታማ ቡድን መሆኑን የሚጠቅሱት በክለቡ ስራ አስፈፃሚ የሆኑትና ለአቃቤ ነዋይነት የሚያገለግሉት ወ/ሮ ኡሚ አብዱልቃድር ናቸው፡፡ በወጣትነታቸው ታዋቂ የጠረጴዛ ቴኒስ ተጨዋች የነበሩት ወ/ሮ ኡሚ ሁሉም ስለአባ ቡና ሲያወራ በቁጭት ክለቡ በድጋሚ እንዲመሰረት የተደረገውን ውሳኔ ለማገዝ በፍላጎት ቡድኑን ለማገልገል መምጣታቸውን ገልፀው የጅማ አባቡና የቀድሞ ዝና ለመመለስ በህዝቡም ተወዳጅ ቡድን እንዲኖር ባለኝ ፍላጎት እየሰራሁ ነኝ ሲሉም ይናገራሉ፡፡ ባለፉት 5 ዓመታት የጅማ ከተማ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መነቃቃት ከጀመረ በኋላ የእግር ኳስ ህዳሴው መጀመሩን የሚገልፁት ሁለቱ የክለቡ ስራ አስፈፃሚዎች፤ የጅማ ከነማ እንዲሁም የጅማ አባቡና ክለቦች በአገር አቀፍ ውድድሮች በሚያደርጓቸው ተሳትፎዎች እየተጠናከሩ በመምጣታቸው መበረታታቸውን  ያመለክታሉ፡፡ በ2006 ዓ.ም በጅማ ዞን አስተዳደር አስተባባሪነት ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ተደርጎ የጅማ አባቡና ስፖርት ክለብ  በድጋሚ ተመስርቷል ፡፡ በምስረታው ላይ በነበረው የውድድር ዘመን  በምዕራብ ዞን የብሄራዊ ሊግ ተሳታፊ  ሆኖ አበረታች ውጤት ሊያስመዘግብ በቅቷል፡፡  በስብስቡ ወጣት እና ጠንካራ ተጫዋቾችን  አሰባስቦ የነበረው ክለቡ በወቅቱ ምርጥ እግር ኳስ በማሳየት የከተማውን የስፖርት ቤተሰብ ያነቃቃ ሲሆን፤  የምዕራብ ዞንን በሁለተኛነት አጠናቆ በ24 ክለቦች መካከል በድሬደዋ ከተማ  በተካሄደው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ ሻምፒዮና ላይ ተሳታፊ ሆኖ ነበር፡፡ በ2007 ዓም በድሬዳዋ በተካሄደው የብሄራዊ ሊግ ሻምፒዮና ላይም አራተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል ፡፡  
ከ3 ዓመት በፊት በተጠቀሱት ባለድርሻ አካላት ክለቡ ሲመሰርት 3 ሚሊዮን የከተማውን ህዝብ ለሚወክለው ክለቡ ስያሜ የቀረቡ አማራጮች ነበሩ፡፡ በተለይ አባ ቡና እና አባሻይ በሚሉት መጠሪያዎች ምክክር ተደርጓል፡፡ ጅማ የቡና መገኛ፤ ለረጅም ዓመታት ኢትዮጵያን ወክላ ለዓለም ቡና ኤክስፖርት በማድረጓ ቡና አለ፡፡ ከዚያም አባ የሚለው የማዕረግ ስያሜ ትርጉሙ አባት ወይም ባለቤት ማለት በመሆኑ፤ አባቡና የሚለው ስያሜ ተመራጭ እንደሆነ አብዱል ከሪም አባገሮ ገልፀዋል፡፡ የጅማ አባቡና ስፖርት ክለብ በሚለው ስያሜ መተዳደርያና መመስረቻ ደንቡ ፀድቆ ክለቡ ተቋቁሟል፡፡ ድሮ የክለቡ የመጀመርያ ዋና ማልያ እንደ አርጀንቲና ሰማያዊ እና ባለነጭ ሸንተረር እንደሆነ አያይዘው የገለፁት ፕሬዝዳንቱ፤ በምሰረታው ጊዜ ሰማያዊው እንዲሁም ለምለሟን ጅማ የሚመስል አረንጓዴ ቀለበት የማልያው መለያ እንዲሆኑ ተደርጐ መምረጣቸውን በዚያ መልክ መሰራት መጀመሩን ጠቅሰው ወደፊት በኦርጅናሉ የክለቡ የድሮ ማልያ ለመስራት እያሰብንበት ነው ብለዋል፡፡
ህዝባዊ አደረጃጀቱና የገቢ ምንጮቹ
የጅማ አባቡና ስፖርት ክለብ አደረጃጀትን አስመልክቶ ፕሬዝዳንቱ አብዱልከሪም አባገሮ ሲያብራሩ ህዝባዊ መሠረቱን በማጉላት ነው፡፡ ህብረተሰቡን በሚወክል ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚመራ፤ በስፖርቱ ህይወት ያለፉ እና የተጨዋችነት ልምድ ባላቸው፤ ከራሳቸው ኪስ ክለቡን ለመደገፍ ቆርጠው በተነሱ  ግለሰቦች ስራ አስፈፃሚው ተደራጅቶ እንደሚንቀሳቀስም ይገልፃሉ፡፡ በተጨማሪም የክለቡ ቴክኒክ ኮሚቴ የቀድሞ ተጨዋቾችን እንደሚያካትት፤ የደጋፊ ማህበሩ በህዝቡ ውስጥ ያሉ ግለሰቦችን በማሳተፍ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡ በክለቡ አደረጃጀት የአዳማ ከነማ፤ የሲዳማ ቡና እንዲሁም በአዲስ አበባ የሚገኙ አንጋፋ እና ስኬታማ ክለቦችን ተመክሮ መነሻ በማድረግ አስፈላጊ ልምድ መውሰዱንም ገልፀዋል። ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናትም በተለያዩ ክለቦች ጋር ሲጋጠሙ ያሉ ልምዶችንም መቅሰማቸውንም አውስተዋል፡፡ በአጠቃላይ በክለቡ ዳግም ምስረታ ስፖርት ወዳድ ህብረተሰብ፤ የከተማ መስተዳድሩ፤ የቡና ነጋዴዎች፤ የህዝቡ አስተዋጽኦ መሰረት መሆኑንም ያስገነዝባሉ፡፡  ክለቡን የሚያስተዳድረው የስራ አስፈፃሚዎች ስብስብ ስፖርቱን ከሚያውቁ እና ልምድ ካላቸው፤ ከነጋዴዎች፤ ከሲቪክ ማህበረሰብ፤ ከዩኒቨርስቲ፤ ከሚዲያ እና ከህዝቡ አስተዳዳሪዎች በተውጣጡ ግለሰቦች ሊደራጅ መብቃቱንም ያስረዳሉ፡፡
የጅማ አባቡና ስፖርት ክለብ ዘንድሮ በከፍተኛ ሊግ ሲወዳደር  እስከ 14 ሚሊየን ብር ዓመታዊ በጀት በመመደብ  ነበር፡፡ በአብይ ስፖንሰርነት ክለቡን የሚደግፈው ሊሙ ላይ የቡና እርሻ ያለው  ሆራይዘን ፕላንቴሽን ሲሆን   3 ሚሊየን ብር በየዓመቱ ለመደገፍ በመስማማት በግንባር ቀደምነት ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡ በተጨማሪ ክለቡ የህዝብ እንደመሆኑ አብዛኛው  የፋይናንስ ድጋፍ ከጅማ ከተማ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እየተሰበሰበም ይገኛል፡፡ በጅማ ከተማ የሚገኙ ሰራተኞች፤ ተማሪዎች እና ቡና አብቃይ ገበሬዎች በፕርሰንት መዋጮ  ያደርጋሉ። ስለሆነም በተጠቀሱት የክለቡ ባለድርሻ አካላት ያልተቆጠበ ድጋፍ ባለፉት ሁለት ዓመታት ጅማ አባቡና በብሄራዊ ሊግ እና በከፍተኛ ሊግ በነበረው ተሳትፎ  ምንም አይነት  የፋይናስ ችግር እንዳልገጠመው አቃቤ ነዋይ የሆኑት  ወይዘሮ ኡሚ አብዱልቃድር ያብራራሉ፡፡
የክለቡን የፋይናንስ አቅም ለማጠናከር የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያዎችን ለመስራት፤ ከክለቡ አባላት እና ባለቤቱ ከሆነው የጅማ ህዝብ የሚገኘውን መዋጮ በተቀናጀ መልክ ለማሰባሰብ በትኩረት እንቅስቃሴም በመደረግ ላይ መሆኑንም  ወ/ሮ ኡሚ ይገልፃሉ፡፡ የክለቡን አባላትን ለማብዛት እና ድጋፍ ሊሰጡ የሚችሉ ባለ ሀብቶችንም በማስተባበር በስፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ሲጠቅሱ በተለይ በጅማ ከተማ የሚገኙ  18ቱም ወረዳዎች የክለቡ ወሳኝ ባለድርሻ አካላት ሆነው እስከ 100 ሺህ ብር በመመደብ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ አብዱልከሪም አባጋሮ እና አቃቤ ነዋረ የሆኑት ወ/ሮ ኡሚ አብዱልቃድር የጅማ አባቡና ስፖርት ክለብ በከፍተኛ ሊጉ ሁለተኛ ዙር ተፎካካሪነቱን በማጠናከር ግስጋሴውን ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በማለፍ እንደሚያሳካ ሙሉ እምነት አላቸው፡፡ ጅማ አባቡና ፕሪሚዬር ሊጉን ከተቀላቀሉም ከፍተኛ በጀት እንደሚያስፈልገው ተረድተዋል፡፡ ስለሆነም በጅማ ዩኒቨርሲቲ በሚገኙ  ምሁራን በማርኬቲንግ ጥናቶች አሰርተው የክለቡን የበጀት አቅም ለማሳደግ እና አስተማማኝ ለማድረግ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡ ከቡና ላኪዎች እና ቡና አምራቾች እንዲሁም ከከተማው ህዝብ ጋር በመስራት ላይ እንደሆኑም ወይዘሮ ኡሚ አብዱልቃድር ይናገራሉ፡፡
ክለቡ ከ3 ዓመታት በፊት የከተማው የተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች ባደረጉት ድጋፍ  ተቋቁሞ መንቀሳስ የጀመረው በ570ሺ ብር ካፒታል ነበር፡፡ ዘንድሮ በጀቱ ወደ 14 ሚሊዮን ብር አድጓል፡፡ ወደ ፕሪሚዬር ሊግ ከገባ ደግሞ ይሄው በጀት በእጥፍ ማደጉ የማይቀር ነው፡፡  ለተጨዋቾች ለደሞዝ እስከ 380ሺ ብር፤ ለምግብ እስከ 150ሺ እንዲሁም በተለያዩ ክልሎች ለጨዋታዎች ጉዞ ሲያደርግ እስከ100ሺ ብር እንዲሁም ከተጨዋቾች ማበረታቻ ተደማምሮ  በየወሩ እስከ 700ሺ ብር ክለቡ ወጭ እንደሚያደርግ የገለፁት ፕሬዝዳንቱ አብዱልከሪም አባገሮ በበኩላቸው የገቢ ምንጩን ማስፋት እና የፋይናንስ አቅሙን ማጠናከር ወሳኝ እንደሆነ ያስገነዝባሉ፡፡ ወ/ሮ ኡሚ አብዱልቃድር እንደሚያብራሩት  በፋይናንስ ድጋፍ ረገድ በጅማዞን ያሉት 18 ወረዳዎች እና የተለያዩ የከተማው ማህበረሰብ ክፍሎች አስተዋፅኦ አላቸው፡፡ ባለፈው ዓመት በድሬዳዋ በተካሄደው የብሄራዊ ሊግ ውድድር ክለቡ በነበረው ተሳትፎ በከተማው የሚገኙት እነዚህ ወረዳዎች ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እስከ 900ሺ ብር ድጋፍ እንደሰጡ ገልፀዋል፡፡ በዞኑ ያሉ ከ900ሺ በላይ ተማሪዎች በፈቃዳቸው እያንዳንዳቸው 2 ብር እንደሚያዋጡ ሲገልፁም እሰካሁን  ድጋፋቸው 600ሺ ብር መድረሱን በመጠቆም ነው፡፡  በተለያዩ ተቋማት ያሉ ሰራተኞች በየወሩ በፕርሰንት መዋጮ እንደሚያደርጉ የተለያዩ ማህበራት እና ዩኒዮኖች ድጋፍ ለመስጠት ቃል መግባታቸውን በመዘርዘርም የክለቡ የፋይናንስ አቅም ለማጠናከር በሚደረገው እንቅስቃሴ ሙሉ እምነት እንዳላቸው አስገንዝበዋል፡፡
ለወደፊቱ ምን አቅደዋል…
የጅማ  አባቡና ስፖርት ክለብ ዘንድሮ  ወደ ፕሪሚዬር ሊግ መግባቱን ካረጋገጠ፤ ወደፊትም በጠነከረ ሁኔታ እንቅስቃሴውን ለመቀጠል የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ቀይሷል፡፡ በአፍሪካ ደረጃ ለመወዳደር፤ በታዳጊ እና ወጣት ፕሮጀክቶች ለመስራት ተጨዋቾች የማፍራት አቅሙን ለማሳደግ እና በአገር አቀፍ የእግር ኳስ እድገት አስተዋፅኦ ለማድረግ የወደፊት እቅዶቹ ናቸው፡፡ የክለቡን የገቢ ምንጮች ለማስፋት እና የፋይናንስ አቅም ጎን ለጎን ለማሳደግም ይሰራል፡፡ አብዱልከሪም አባጋሮ  በእነሱ ዘመን ትልቁ ሽልማታቸው የህዝቡ ደስታ እንደሆነ ሲናገሩ የጅማ አባቡና ክለብ በከተማዋ ህዝብ እየፈጠረ ያለው መነቃቃት ለወደፊቱ ስኬት ከፍተኛው ድጋፍ ነው ይላሉ፡፡ ገናና እና ወርቃማ እያልን የምንጠራው የኛ ዘመን  የእግር ኳስ ትውልድ ከትምህርት ቤት ፤ ከሰፈር እና ከመንደር ተጀምሮ የወጣ ነበር የሚሉት የጅማ አባቡና ክለብ ፕሬዝዳንት እግር ኳስን በልጅነት መጀመር አለበት ብለው መልዕክት ሲያስተላልፉ በየዞኑ፤ በየትምህርት ቤቱ፤ በየክልሉ በታዳጊዎች ደረጃ መሰራት ለአገር አቀፍ እግር ኳስ እድገት ወሳኝ ሚና እንደሚያበረክት መታወቅአለበት ሲሉ መክረዋል፡፡ ከላይ በተጠቀሱት አቅጣጫዎች ስኬት ለማስመዝገብ እየሰሩ መሆናቸውን አብዱልከሪም አባገሮ ሲያስረዱ ስለሆነም ከጅማ ዩኒቨርስቲ፤ ከትልልቅ ኩባንያዎች፤ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ተጨማሪ ድጋፎች እንደሚያስፈልግ ጥሪ በማቅረብ ነው፡፡
ወ/ሮ ኡሚ አብዱልቃድር  የክለቡ  ስራ አስፈጻሚዎች ዋንኛ አላማቸው የቀድሞውን የአባ ቡና ዝና መመለስ እንደሆነ ሲናገሩ፤ ክለቡ በድጋሚ ተደራጅቶ በመመስረት ወደ ውድድር ሲገባ  በ3 ዓመታት ውስጥ ፕሪሚየር ሊግ ለመግባት እንደሆነ ከአገር ውስጥ ውድድር ባሻገር  በአፍሪካ  ደረጃም ተወዳዳሪነትን ለማሳካት ማቀዱን በመግለፅ በአጭር ጊዜ ይህን ለማሳካት ያለበት ደረጃ የሚያበረታታ ነው ይላሉ፡፡ ጅማ አባቡና የስፖርት ክለብ መሰረቱ እና ባለቤቱ ህዝብ  መሆኑን የሚገልፁት ወ/ሮ ኡሚ  አብዱልቃድር  በበኩላቸው ከ3 ሚሊዮን በላይ የሚገመተው የጅማ ህዝብን በመወከል ለውጥ ማስመዝገቡ እንደሚቀጥል ተስፋ አድርገዋል፡፡
የጅማ ህዝብ ስፖርት ወዳድነት ባለፉት ሁለት ዓመታት የጅማ ከነማ እና የጅማ አባቡና ክለቦች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ መነቃቃቱን የሚገልፁት ደግሞ አብዱልከሪም አባገሮ ናቸው፤ ለዋና ብሔራዊ ቡድን የበቁት እነመሃመድ ናስር እንዲሁም በወጣት ቡድን የተመረጡ የከተማው ተጨዋቾች የክለቡን እምቅ አቅም  እንደሚያመለክቱ ያስረዳሉ፡፡ ጅማ አባ ቡና አራት ተጫዋቾችን ለኢትዮጵያ ወጣት ብሄራዊ ቡድን ማስመረጡ ትኩረት ያስገኘለት ሲሆን እነዚህ የክለቡ አሜ መሀመድ፤ ሱራፌል አወል፤ ዳዊት ተፈራ እና ሂደር ሙስጠፋ የተባሉት ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ለብሄራዊ በድን በተለያዩ ደረጃዎች ለሚገኙ ቡድኖች ከ10 በላይ ተጨዋቾችን የጅማ አባቡና ስፖርት ክለብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማስመርጥ እንደሚሰራ አብዱልከሪም አባገር በተጨማሪ ይገልፃሉ፡፡ የጅማ አባቡና የስፖርት ክለብ የተጨዋቾች ስብስብ የተሟላ ዲስፕሊን ያለው፤ የክለቡ አስተዳደር ለተጨዋቾች በሚሰጠው ትኩረት እና ሌሎች ማበረታቻዎች በአርዓያነት ሊጠቀስ የሚበቃ ነው፡፡
በቴክኒክ ኮሚቴ የሚሰሩት የቀድሞ ተጨዋቾች፤ ዋና አሰልጣኙና ዋና አምበሉ
በቴክኒክ ኮሚቴ ከተያዙት መካከል መልካሙ ደርሰ የተባሉ እና የጅማ አባቡና እና የከፋ ክፍለሃገር በሚወክል ቡድን ግብ ጠባቂ ሆነው ያገለገሉ የቀድሞ ተጨዋች እንዲሁም የጅማ መምህራን ማሰልጠኛ ምሩቅ የነበሩና በኋላም በከተማው በሚገኙየእግር ኳስ  ክለቦች እንዲሁም በጅማ አባቡና ተጨዋችነት ያሳለፉት ሃብታሙ ሐይለማርያም ይገኙበታል፡፡ ሁለቱ የቀድሞ የጅማ አባ ቡና ክለብ ተጨዋቾች፤ በተጨዋቾች ምልመላ፤ በየሳምንቱ የጨዋታዎች ግምገማ በስብሰባ በፅሁፍ በማቅረብ በቴክኒክ ኮሚቴው ውስጥ እየሰሩ ናቸው፡፡ ጅማ አባቡና ተመልሶ ህይወት መዝራቱ ከፍተኛ ደስታ ፈጥሮልናል የሚሉት የቀድሞ ተጨዋቾች መልካሙ ደረሰ እና ሃብታሙ ሃይለማርያም በአጭር ጊዜ ፕሪሚዬር ሊጉን በመቀላቀል እድገቱን እንደሚቀጥል ተስፋ ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡
የመጀመርያውን ዙር በጅማ ስታድዬም በደጋፊያችን ፊት ማሸነፋችን አስደስቶኛል ያሉት ዋና አሰልጣኝ ደረጀ በላይ ፤ በሁለተኛው ዙር ክለቡ የያዘውን ነጥብ አስጠብቆ ለመቀጠል ሙሉ የአንድነት መንፈስ እና ትጋት እንዳለው አምናለሁ ብሏል፡፡ የክለቡ ተጨዋቾች እያገኙ ባለው  ስኬት ወደሌሎች ክለቦች እንዳይሄዱ ለማቆየት ነፃነት በመስጠት እና በተለያዩ ማበረታቻዎች በማነቃቃት ፤ የቡድን መንፈስ በመጠቀም እና ምክሮችን በየጊዜው በመንገር እየሰራን ነው የሚሉት ዋና አሰልጣኙ፤ ለ20 እና  30 ዓመት ኳስ የተጠማውን የጅማ ህዝብ ወደ ፕሪሚዬር ሊግ በማለፍ እንደምንክሰው ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል፡፡  የከፍተኛ ሊግ ውድድሩ አድካሚ እና አሰልቺ ቢሆንም የመጀመርያ ዙሩን በመሪነት በማጠናቀቃችን ከፍተኛ ደስታ ፈጥሮልናል የሚለው የክለቡ ዋና አምበል ቢንያም ሃይሌ ወይም ዋሴ በአንድም ጨዋታ አለመሸነፋችን በቡድናችን ጠንካራ የአንድነት መንፈስ መኖሩን ያመለክታል ብሎ በሁለተኛው ዙር የያዝነውን መሪነት አሳልፈን ሳንሰጥ ወደ ፕሪሚዬር ሊጉ እናልፋለን ሲል ይናገራል፡፡ ጅማ ኳስ አፍቃሪ ህዝብ ያለበት እና ተሰጥኦ እና ብቃት ያላቸውን ልጆች የሚያፈራ ከተማ ነው በማለትም ዋና አምበሉ ሲናገር ደጋፊዎች በሜዳቸው ሲጫወቱ የሚያሳዩት ድጋፍ እንደሚማረኩ እና የናፈቀውን ድል ለማሳካት የቡድኑ አባላት እንደሚጥሩም ገልጿል፡፡

Read 3186 times