Saturday, 14 May 2016 12:33

በሩብ ክ/ዘመን ሥልጣን የታዘብናቸው ስኬቶችና ውድቀቶች!!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(24 votes)

የኢህአዴግ 25ኛ ዓመት በዓል ደርግን በማውገዝ አይከበርም
“ግንቦት 20 ውስጤ ነው!!” ለማለት ፈለግሁና ያዝ አደረገኝ

     እንኳን ለግንቦት 20፣ የሃያ አምስተኛ ዓመት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፡፡ በአሉ አይመለከተንም የምትሉ ውድ አንባቢያን (ኢህአዴግም ብትሆኑ!) በጨዋ ደንብ የድል መግለጫውን ዝለሉት፡፡ (ከእነአካቴው ጽሁፌን ከተዋችሁት ግን ቅራኔ ውስጥ እንገባለን!)  እናላችሁ----ኢህአዴግ ሥልጣን የያዘበት 25ኛ ዓመት ቢሆንም ሳትወዱ በግድ አክብሩ የሚላችሁ የለም፡፡ (ለነገሩ የሚል አይጠፋም ነበር!) ግን ዕድሜ ለህገመንግስቱ! ያሻንን የማክበርም ሆነ ያለማክበር መብት አጎናጽፎናል፡፡ (ይሄ በ20 ዓመት የሥልጣን ዘመን ከተገኙ ስኬቶች አንዱ ነው ብላችሁስ!)
ዋናው ቁምነገር ግን ምን መሰላችሁ? በዓሉን ያለማክበር መብታችሁ የሆነውን ያህል የሌሎችን በዓሉን የማክበር መብትም ከልባችሁ አምናችሁ መቀበል አለባችሁ፡፡ ዲሞክራሲ 101 ሆነባችሁ እንዴ? ግን እኮ እቺ ራሷ ጠፍታን ነው ለሩብ ክፍለ ዘመን ስንወዛገብ የከረምነው፡፡ (ይሄ ደግሞ ከውድቀታችን ይደመርልኝ!) እናላችሁ ---- ውስብስብ ፍልስፍና የለውም፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው መንግስት በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ-ዓለም (እስከ ዛሬ ባይገባንም!) የሚመራ ነው፤ወደድንም ጠላንም ልማታዊ መንግስት ነው፡፡ ርዕዮተ ዓለሙን መቃወም ይቻላል፤ ውዲቷን ጦቢያ መቀመቅ የሚከትብን ፖለቲካዊ አቅጣጫ ነው ብሎ ጥምብርኩሱን ማውጣት መብት ነው፡፡ ህገመንግስቱ ያስታጠቀን፡፡ (መሳሪያን ብቻ ሳይሆን መብትንም ይታጠቁታል!)  
እናላችሁ--- ስናከብር እንከበራለን፤ስናዋርድ እንዋረዳለን፡፡ በግንቦት 20 በዓል ብቻ ሳይሆን በሁሉም ህይወታችን፡፡ ወደድንም ጠላንም የኢህአዴጎችን ፖለቲካዊ አመለካከት ልናከብርላቸው ግድ ይለናል፡፡ በዓሉን ሲያከብሩ አብረን ባናከብርም መብታቸው መሆኑን አምነን መቀበል ከኛ ይጠበቅብናል፡፡ ለነገሩ ኢህአዴግ ነፍሴ፤ አምነን ተቀበልንም አልተቀበልንም ማክበሩን ይቀጥላል፡፡ መከባበሩ ግን ለዘላቂው ጉዟችን ይበጀናል፡፡ ወደ ሰለጠነ አስተሳሰብ የሚመራ ብቸኛው መንገድም ይሄው ይመስለኛል፡፡ መዲናዋን ከሞላት ይሄ ሁሉ የፎቅ ጋጋታ  ውስጥ አንድም “የመከባበር ፎቅ” አለመገንባታችን ያሳፍራልም፤ያሳዝናልም። ችግሩ ከአርኪቴክቱ ነው ወይስ ከኢንጂነሩ? የፎቅ በጀቱ በሙስና ተበልቶ ይሆን? የሆኖ ሆኖ ከ20 ዓመት ኪሳራችን መካከል ይመደብልን፡፡
ለመሆኑ ለአዲሱ ትውልድ የምናስረክባት አገር ምን ዓይነት ናት? ያው የሰራናትን ነዋ፡፡ እሷ ደግሞ ታሳፍራለች፡፡ በመናናቅ፣በጥላቻ፣በክፋት፣በምቀኝነት፣በስግብግብነት፣በኋላቀርነት፣ በዘረኝነት፣በድህነት፣በአጉል ልማድ፣በጭፍን አስተሳሰብ --- ወዘተ የተሞላች ድፍንፍን አገር ናት፡፡ ለልጆቻችን ብለን እንኳን ልንሸነፍ አልፈቀድንም፡፡ ሌላው ግዙፍ የ20 ዓመት ጉዞ ኪሳራችን ይሄ ነው፡፡
ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዳሉት፤ኢህአዴግ ከህብረተሰቡ እንደመውጣቱ ሁሉ እልኸኛ ነው - እንደ ማንኛውም አበሻ፡፡ ለነገሩ ተቃዋሚዎችም የባሰባቸው እልኸኞች ናቸው - እንደተቀረው አበሻ፡፡ ግን ቢያንስ ኢህአዴግ ለ25 ዓመታት መንግስት ሆኖ ቆይቷልና እንደ አገር ማሰብ መጀመር ነበረበት፡፡ በግንቦት 20 የሃያ አምስተኛ ዓመት በዓል ዋዜማ ላይ ኢህአዴግን እየወቀስኩ አይደለም፡፡ (ብወቅስም መብቴ ነው!) እኔ ግን አገሬን፣የወደፊት እጣ ፈንታዋን፣አዲሱ ትውልድ የሚረከባትን እምዬ ኢትዮጵያን መገምገሜ ነው፡፡  አንዱ የማደንቀው ገጣሚ፣ በጦቢያ ዙሪያ የማይቀለድ ቀልድ ቀልዷል፡፡  
አንዱ የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ ፡- ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
እኔም፡- እንዲህ ሆና ?
ምናልባት ጎበዝ ገጣሚ እንጂ ጎበዝ ኮማኪ ላይሆን ይችላል፡፡ እኔ ግን ምን እላለሁ መሰላችሁ? --- ኢትዮጵያማ ዝንተዓለም ትኑር!! ምንም ሆና ምንም ታፍራና ተከብራ ትኑር!! (ከእነኮተታችን፣ ከእነንትርካችን ችላናለች!) ወዳጆቼ፤ ለሁሉም ነገር ተጠያቂዎቹ እኛ እንጂ እናት አገር ጦቢያ አይደለችም፡፡ አሁንም እኮ ያቺ ቴዎድሮስ የሚያውቃት ጦቢያ ናት፡፡ ያቺ የጣይቱ ጦቢያ። ያቺ የዮሐንስ ጦቢያ፡፡ ያች የምኒልክ ጦቢያ፡፡ እኛ ነን ቆሌዋን የገፈፍናት፡፡ እኛ ነን ምስቅልቅሏን ያወጣናት፡፡
በአንድ ወቅት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ለአርሶ አደሩ በወባ መከላከል ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ የሚያከናውኑ የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ገበሬዎቹን ይሰበስቡና አንድ ስዕል ያሳዩዋቸዋል፡፡ ጎጆው ጽድት፣ጥንቅቅ ያለ---አባወራው ጸአዳ ልብስ የለበሰና እማወራዋ እንደ በረዶ የነጣ የአበሻ ቀሚስ የለበሰች ናት። ገበሬዎቹ ስዕሉን እንዳዬት አገሩመረሙ፤እንደ መሳቅም ዳዳቸው፡፡ የኮሙኒኬሽን ባለሙያው ግራ ገብቶት ችግር አለ ሲል ጠየቃቸው፡፡ አንዱ ገበሬ ሳቅ እያፈነው፤
“እኛን አይመስልም; አለ፡፡ (በውስጡ ለካስ አታውቁንም የሚል ሽርደዳ ባለው ቃና፡፡)
“እንዴት?; ጠየቀ ባለሙያው፡፡
“እንደ ከተሜ በጣም ጸዳ; ገበሬው መለሰ፡፡
“እና ይለወጥ፤እንደገና ይሰራ?; አስረግጦ ጠየቀ ባለሙያው፡፡
አንደኛው ገበሬ ከተቀመጠበት እመር ብሎ ተነሳና፤ “እሱ ምን ባደረገ? እኛ ነን መለወጥ ያለብን÷ የወረቀቱማ ሸጋ ነው” አለ፤ኮስተር ብሎ ከልቡ፡፡
ሁሉም በአንገት ንቀነቃና በጉምጉምታ ድጋፉን ገለጸ።
እናላችሁ ----የእምዬ ጦቢያም ነገር እንዲሁ ነው፡፡ እሷ ሳትሆን እኛ ነን መለወጥ ያለብን፤እሷን መምሰል፤ወደሷ መቅረብ ያለብን እኛ ነን፡፡
ወዳጀቼ፤ሳላስበው ከአጀንዳዬ ውጭ ብዙ ቀባጠርኩኝ መሰለኝ፡፡ ግን ደግሞ ሳይነሳ መታለፍ የሌለበት ዋና ጉዳያችን ነው - አንገብጋቢ አጀንዳችን!! የ25 ዓመታት ጉዞ ውድቀታችን!  ወደ ማክበር መከባበሩ ለአፍታ ልመልሳችሁ፡፡ ብትፈልጉ ለጊዜው ዲሞክራሲን መሳቢያ ውስጥ ክተቱት፡፡ በነገራችን ላይ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳሉ፣ ኢህአዴግ ነፍሴ ኢንፎርም ሳያደርጋቸው፣ ነጭ ካፒታሊዝምን ሲያፋፍም ድንገት ደረሱበትና አፋጠጡት፡- “ሶሻሊዝም የት ገባ?” ብለው፤(የሚመሩበት ርዕዮተ ዓለም ሶሻሊዝም ነበራ!) ኢህአዴግ ሆዬ፤ “ለጊዜው መሳቢያ ውስጥ ከተነዋል; ብሎ አበሸቃቸው፡፡ (የነጋሶ መንገድ በሚል መጽሃፋቸው እንደገለጹት) የእኔ ግን በግልጽ ነው፤በዚያ ላይ ዲሞክራሲ በመሳቢያ ውስጥ የሚቆየው አፍታ ለማትሞላ ጊዜ ነው፡፡ እና --- እስቲ እንቀጥል፡- በነገራችሁ  ላይ በሌላ የተፈጥሮ መመሪያም ቢሆን --- አንዳንዶች የዩኒቨርስ ህግ ይሉታል፡፡ ወይም ደግሞ ዘ ሎው ኦፍ አትራክሽን (የስበት ህግ እንደማለት፡፡) ተመሳሳይ ነው፡፡ እናላችሁ---- ብር ሰጥተን ወርቅ መቀበል አንችልም፡፡ እንክርዳድ ዘርተን ስንዴ ማጨድ አይሞከርም፡፡ ጥላቻን እያራገብን ፍቅርን ከጠበቅን ተሳስተናል፡፡ በስስትና በንፉገነት ተሞልተን፣ ደግነትንና ልግስናን መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡
 በሁሉም ነገር ተመሳሳይ ነው - ህጉ፡፡ ፖለቲካ ሲሆን የሚለወጥ ነገር የለም፡፡ በነገራችሁ ላይ ህጉን አመናችሁበትም አላመናችሁበትም መስራቱን ይቀጥላል።  በስበት (law of gravity) አናምንም ስላላችሁ ብቻ የስበት ህግ ስራውን እንደማያስተጓጉል ሁሉ፣ ዘ ሎው ኦፍ አትራክሽንም እንዲሁ ነው - የምትሹትን ነው የምትስቡት፡፡ ክብርና ፍቅር ለዩኒቨርስ ወይም ለሰው ልጆች ስትልኩ፣ ክብርና ፍቅር ይደርሳችኋል፡፡ የሌላውን መብት ስታከብሩ፣መብታችሁ ይከበርላችኋል፡፡ በጭፍን ስትፈርዱ በጭፍን ይፈረድባችኋል፡፡ (ሰባኪ መሰልኩ አይደል!) ግን እውነቱ ይሄው ነው፡፡ አሁን ዲሞክራሲያችንን ከመሳቢያው ውስጥ ማውጣት እንችላለን፡፡
ወደ ሌላ አጀንዳ ከማለፋችን በፊት የግንቦት 20ን የሃያ አምስተኛ ዓመት በዓል በተመለከተ ጥቂት እናውጋ፡፡ በነገራችን ላይ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስቴር አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ስለ በዓሉ አከባበር ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፤ኢህአዴግን ከደርግ ጋር በማነጻጸርም ሆነ ደርግን በመርገም የማክበር ዕቅድ እንደሌለ መናገራቸው ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ከ20 ዓመት የሥልጣን ዘመን ስኬቶች እንደ አንዱ ይቆጠርልን፡፡
ችግሩ ግን ምን መሰላችሁ? ሚኒስትሩ እንዲያ ቢሉም በየዓመቱ የግንቦት 20ን በዓል ደርግን በመኮነንና ኢህአዴግ የሚሻልበትን በማነጻጸር ዶክመንተሪም በሉት ደረቅ ፕሮፓጋንዳ ሲግተን የከረመው ኢቢሲ፤ስላልተዘጋጀበት ምን ሊያቀርብልን ነው? እኛ እንግዲህ የፈለገውን ቢያቀርብም አማራጭ ስላገኘን አያስጨንቀንም፡፡ በቃና ወይም በኢቢኤስ አሊያም በጆሲ ቲቪ እንሸውደዋለን፡፡ (ለ25 ዓመታት ፕሮፓጋንዳ፣ ካሣ ቢከፈለን ከሰሞኑ ሚሊዬነሮች ተርታ እንሰለፍ ነበር!)
በሩብ ክ/ዘመን ሥልጣኑ፣ኢህአዴግ በሚዲያ ነጻነት ረገድ አመርቂ ውጤት ባያመጣም፣ቢያንስ በሳተላይት ቲቪ ስላንበሸበሸን ከስኬት እንቆጥርለታለን፡፡ (ዛሬም ህዝባችን በደሉን የሚነግረው ለቪኦኤ መሆኑ ግን ያስቆጫል!) በ25 ዓመት ውስጥ አንድ የቪኦኤ ያህል የነጻነት ስሜት የሚፈጥርብን ሚዲያ እንዴት ላይኖረን ቻለ? ኢህአዴግስ በዚህ ምን ይሰማው ይሆን? “ግንቦት 20 ውስጤ ነው” ለማለት ፈልጌ አንዳች ነገር ያዝ አደረገኝ!! የሩብ ክ/ዘመን ስኬቶችና ውድቀቶች ይቀጥላሉ፡፡ እስከዚያው ግን “ኢትዮጵያ ውስጤ ናት!”       

Read 6701 times