Saturday, 14 May 2016 13:09

መሀላችን ያሉ አይጦችን ተጠንቀቁ

Written by  ድርሰት፡- አዚዝ ኔሲን ትርጉም - ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(13 votes)

(በቅርቡ ለንባብ ከበቃው “ራሴን አጠፋሁ እና ሌሎችም”
የአጭር ልብ ወለድ መድበል የተወሰደ)

ከዕለታት አንድ ቀን…ከአገሮች በአንዷ…
ይህ የፈጠራ አፈ ታሪክ አይደለም፡፡ ትክክለኛው ነገር የሆነበትን ስፍራና ጊዜ በመጥቀስ ክስተቱን መተረክ ነው፡፡ ጊዜው ከክርስቶስ ልደት በኋላ በሆነ ወቅት፣ ስፍራው ደግሞ በምድር በሆነ ቦታ፡፡
ጊዜና ስፍራውን ካወቅን ወደ ትረካው እንሂድ። ከፍ ብሎ በተጠቀሰው ጊዜና ስፍራ በጣም ግዙፍ ጐተራ ነበር፡፡ ጐተራው በምግብ፣ በልብሶች፣ በጽዳት ዕቃዎች ወዘተ የተሞላ ነው፡፡ ሁሉም ነገር በስርአት ተደርድሯል፡፡ ሩዝ፣ ባቄላና ምስር በአንድ በኩል፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ አጃ በሌላ በኩል፤ ሳሙና፣ ዘይትና ቅቤ በአንድ ወገን ተደርድረዋል፡፡ ጫማና ልብሶችም በሌላ ወገን ይገኛሉ፡፡
ይህን ጐተራ የሚያስተዳድረው አንድ ብቁ ሁሉን አውቃለሁ ባይ ሰው ነው፡፡ አንድ ቀን ይህ ብቁ፣ ሁሉን አወቅ ሰው ጐተራው በአይጦች ስለተወረረበት የሚያደርገው ይጠፋዋል፡፡ ምግቡ ቀን በቀን እየቀነሰ ሄደ፣ ሳሙናና ዓይብ በየቀኑ እየተቆነጠረ ተበልቶ ያገኛል፡፡ በእርግጥ ብቁው ሥራ አስኪያጅ እጆቹን አጣምሮ አልተቀመጠም። ከአይጦቹ ጋር በቁርጠኝነት ተፋለመ፡፡ ምንም ቢያደርግ ግን ፍልሚያውን ሊያሸንፍ አልቻለም። ቀኖች በሄዱ ቁጥር እየተቆነጠሩ የሳሱት ሳሙናና ዓይብ ጭርሱን ይሰወሩ ጀመር፡፡ ልብሶቹ ቡቱቶ ሆኑ፡፡ አይጦቹ የዱቄት ጆንያዎቹ ላይ ይፈነጩ ገቡ፡፡
በጐተራው አይጦቹ የማይደርሱበት ስፍራ አልነበረም፡፡ እህሉንና ቅቤውን እንዳሻቸው እየተመገቡ እየደለቡ፣ እየወፈሩ ሄዱ፡፡ አካላቸው እየገዘፈ ሲሄድ ለመቆጣጠር ይበልጡኑ አስቸጋሪ ሆኑ፡፡ በብዛትም ይዋለዱም ገቡ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ጐተራው በአይጦች ሠራዊት ቁጥጥር ስር ሆነ። እነሱን መቆጣጠሩ አልተቻለም፡፡ የሚበላውን ሁሉ በመብላትና ልብሶችን በመበጣጠስ ብቻ አልተገደቡም፣ በተጨማሪም ጫማዎችን፣ የቆዳ ቁሳቁሶችን መብላትና እንጨት ሳይቀር መቦርቦር ጀመሩ፡፡
በመጨረሻም የድመቶችን ያህል ፋፉ፣ ብዙም ሳይቆይ ውሾች አከሉ፡፡ አሁን ጐተራ ውስጥ የሚያሰናክላቸው አንዳችም ነገር አልነበረም። እንደፈለጉ መፈንጨትና ድብብቆሽ መጫወት ይችላሉ፡፡ ከሁሉ የከፋው ደግሞ የጐተራው በፀሐይ ብርሃን የተጥለቀለቀው ወገንም ቢሆን ብዙም ሳይቆይ በቁጥጥራቸው ስር ሆነ፡፡
ብቁው ሥራ አስኪያጅ፤ ከአይጦቹ ጋር የሚያደርገውን ፍልሚያ ቀጠለ፡፡ በጐተራው በሙሉ እጅግ ውጤታማ የአይጥ መርዝ አስቀመጠ፣ ሆኖም ለውጥ አላመጣለትም፡፡ የሰው ልጅ ደስ የሚሉ መርዞችን እንደሚላመደው ሁሉ ጎተራው ውስጥ ያሉ አይጦችም ብቁው ሥራ አስኪያጅ ያስቀመጠውን መርዝ ተለማመዱት። እንደውም በየቀኑ ፍጆታቸውን እየጨመሩ ሄዱ፡፡ የቀን አቅርቦታቸው ካልተጨመረላቸው ጐተራውን ያተራምሱታል፡፡
ሥራ አስኪያጁ ምርጥ አዳኝ ድመቶች አመጣና ጐተራው ውስጥ ለቀቃቸው፡፡ ሆኖም በሚያሳዝን መልኩ በተከታዩ ቀን ጥቂት የድመቶቹ ፀጉር ትራፊና ጥቂት አጥንቶች እዚህም እዛም ተበታትነው ተገኙ፡፡ እንደ ገዳዩ መርዝ ሁሉ ድመቶቹ ከአይጦች ጋር በተደረገው ጦርነት ተሸነፉ፡፡
ቀጥሎም ሥራ አስኪያጁ ጐተራ ውስጥ ወጥመዶች ማስቀመጥ ጀመረ፡፡ አንዳንድ አይጦች ወጥመዶች ውስጥ ይገባሉ፡፡ ግን ማታውን አምስቱ ቢያዙ፣ በበለጠ ፍጥነት ስለሚራቡ በማግስቱ ሃያ ይጨምራሉ፡፡
በመጨረሻ ከተከታታይ ውይይት በኋላ ሥራ አስኪያጁ አንድ ዘዴ አገኘ፡፡ ሦስት ትላልቅ የሽቦ ቤቶችን አሠራ፡፡  ከእነህይወታቸው በወጥመድ የሚያዙት አይጦች በእነኚህ ሽቦ ቤቶች ውስጥ ይወረወሩ ጀመር፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እያንዳንዱ የሽቦ ቤት በአይጦች ተሞላ፡፡ ሽቦ ቤት ውስጥ ለተሰባሰቡት አይጦች ምግብ አይሰጣቸውም፡፡ ሽቦ ቤት ውስጥ ለጥቂት ቀናት ረሀብ ካሰቃያቸው በኋላ አይጦቹ ከመካከላቸው ደካማ የሆኑት ላይ ጥቃት በመሰንዘር፣ በልተዋቸው ረሀባቸውን ማስታገስ ጀመሩ፡፡ በዚህ መንገድ ቀኖች እየገፉ ሲሄዱ ሦስቱ የሽቦ ቤቶች ውስጥ ያሉት አይጦች ቁጥር መቀነስ ጀመረ። ደካሞቹና ትንንሾቹ ለምግብነት ተበጣጥሰው ተበልተው፣ ጠንካሮቹ ብቻ በህይወት ተረፉ፡፡
ቀደም ሲል በአይጦች ተሞልተው የነበሩት የሽቦ ቤቶች ወደ ጦር ሜዳነት ተለወጡ። በመጨረሻ እያንዳንዱ የሽቦ ቤት ውስጥ ሦስት፤ አራት አይጦች ብቻ ተረፉ፡፡ ተራፊዎቹ አብረዋቸው ሽቦ ቤት ውስጥ ያሉት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር እስኪርባቸው አልጠበቁም፡፡ እንቅልፍ የወሰደው፣ ያንጐላጀጀው ወይም የተዘናጋ ወገናቸውን እንዳዩ ለቀም አድርገው ይበሉታል፡፡ ሦስት ወይም አራቱ በአንዱ ላይ የሚያብሩባቸው ጊዜዎች አሉ፡፡ በመጨረሻ እነኚህ አጋሮች እርስ በእርስ ለመበላላት አመቺ ጊዜ ይጠብቃሉ፡፡
በመጨረሻ በያንዳንዱ የሽቦ ቤት ውስጥ አንድ፣ አንድ አይጥ ብቻ ተረፈ፡፡ ተራፊዎቹ ከሁሉም በላይ ትልቆቹ፣ ፈጣኖቹና ብልሆቹ ነበሩ፡፡
በየአንዳንዱ ሽቦ ቤት አንድ፣ አንድ አይጥ ብቻ እንደተረፈ ብቁው ሥራ አስኪያጅ ተራ በተራ እየከፈተ ወደ ጐተራው እንዲገቡ አደረጋቸው፡፡
እነሱን የሚመስሉ ፍጡራንን መብላት የለመዱት ሦስቱ በሚገባ የተቀለቡት፣ ግዙፎቹ ሆዳም አይጦች በሮች እንደተከፈቱላቸው እየተንደረደሩ ወደ ጐተራ ሄደው ያገኙትን አይጥ ሁሉ ይዘነጣጥሉ ጀመር፡፡ የቻሏቸውን በሉ፣ ሌሎቹን ደግሞ በህይወት ከቆዩ እነሱን እንዳያጠቋቸው በመፍራት ገደሏቸው፡፡
በዚህ ዘዴ በተባለው ቦታና ጊዜ የነበረው ጐተራ ለጊዜውም ቢሆን ከአይጦች ነፃ ሆነ፡፡
ታሪኩ እዛ ላይ ቢያልቅም የምጠይቃችሁ ጥያቄ አለ፡፡ ብቁው ሥራ አስኪያጅ ሳጥናኤል እንኳን ሊያስበው የማይችለው ዘዴ እንዴት መጣለት? አይጦቹ እርስ በእርስ እንደሚበላሉ እንዴት አወቀ?
መልሱን እኔ ልስጣችሁ፡፡ ይህ ብቁ ሥራ አስኪያጅ ራሱ ወገኖቹን አንድ በአንድ የጨረሰ፣ የራሱን ጓደኞች እየበላ በመጨረሻ የትልቁ ጐተራ ሥራ አስኪያጅ ለመሆን የበቃ ኃያል ተራፊ ነው። የራሱን ህይወት ስኬት በጐተራው አይጦች ላይ ተጠቀመበት፡፡
የታሪኩ ሞራል - አይጦች እርስ በእርስ ይበላላሉ።     

Read 3748 times