Saturday, 21 May 2016 14:44

የቀዳማዊ ኃ/ ስላሴ የወርቅ ሰዓት ዳግም ለጨረታ ሊቀርብ ይችላል

Written by 
Rate this item
(8 votes)

ንብረትነቱ የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የነበረውና ባለፈው ህዳር ወር ላይ በታዋቂው ዓለምአቀፍ አጫራች ኩባንያ ክርስቲ አማካይነት በጨረታ ሊሸጥ በዝግጅት ላይ ሳለ፣ የንጉሱ ቤተሰቦች ባሰሙት ተቃውሞ ሳቢያ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ታግዶ የቆየው 1 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የወርቅ ሰዓት በቅርቡ ዳግም ለጨረታ ሊቀርብ እንደሚችል ብሉምበርግ ዘገበ፡፡
ንጉሱ ከአንድ ጣሊያናዊ ባለሃብት በስጦታ እንዳገኙት የተነገረለትና ፓቴክ ፊሊፒ የሚል ስያሜ ያለው ይህ እጅግ ውድ የወርቅ ሰዓት፣ ጄኔቫ ውስጥ ለጨረታ ሊቀርብ ሲል የንጉሱ ቤተሰቦች “ሰዓቱ ከንጉሱ የተዘረፈ ነው፤ ሊመለስልን ይገባል” በማለት ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን ተከትሎ፣ የጄኔቫ ፍርድ ቤት ሽያጩ ለጊዜው እንዲሰረዝ በመወሰን ጉዳዩን ሲያጣራ ቆይቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ በመጨረሻም ሰዓቱ የንጉሱ ቤተሰቦች እንዳሉት ተዘርፎ የተወሰደ መሆኑን የሚያረጋግጥ ተጨባጭ ማስረጃ አለማግኘቱንና በመጪዎቹ ሶስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥም ሰዓቱን ለሽያጭ እንዳያቀርብ በአጫራቹ ድርጅት ላይ የጣለውን ጊዚያዊ እግድ ያነሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ የፍርድ ቤቱ ቃል አቀባይ ኦሊቨር ጆርኖት ተናግረዋል፡፡
ጊዚያዊ እግዱ የሚነሳ ከሆነ አጫራቹ ድርጅት ሰዓቱን ዳግም ለጨረታ ሊያቀርበው እንደሚችል የጠቆመው ዘገባው፣ ይህም በንጉሱ ቤተሰቦች፣ በአጫራቹ ድርጅትና ሰዓቱን ከንጉሱ በስጦታ ያገኘነው ስለሆነ ባለቤትነቱ የኛ ነው በሚሉት የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኢብራሂም አቡድ ቤተሰቦች መካከል ቀጣይ የባለቤትነት ውዝግብ ሊፈጥር እንደሚችል ገልጧል፡፡

Read 3966 times