Saturday, 21 May 2016 16:42

ገድሎ ማዳን!

Written by  ፍፁም ንጉሤ -
Rate this item
(9 votes)

     ስልኩ በተደጋጋሚ ቢጠራም የሚያነሳበት ጊዜ ሰስቶ ችላ ብሎታል፡፡ ደሞ ርብቃ አትሆንም፤ እሷ ኮሌጅ ትምህርቷ ላይ ናት፡፡ በበርካታ ባለመኪናዎችና ሾፌሮች ዘንድ በመታወቅ ላይ ያለ መካኒክ ነው፤ኤፍሬም፡፡ ከደንበኞቹ ሁሉ ይኸኛው ይበልጥበታል፡፡ ያገለገሉ መኪኖችን እየገዛ፣ እያስጠገነ፣ እያሳደሰ መልሶ ይሸጣል፡፡ ሲከፍለውም እፍስ አድርጐ ነው፡፡ አስር ሰዓት ገደማ ነበር መኪናዋን የጀመራት፤አሁን አስራ አንድ ሰዓት ሞልቷል፡፡ ኤፍሬም መናደድ ጀምሯል፡፡ ደንበኛው ደሞ ያለወትሮው ተጣድፎበታል፡፡
“ሃሎ ጌታዬ፤ በቃ ከ30 ደቂቃ በኋላ እንመጣለን” ሲል ሰማው፡፡
“ሰላሳ ደቂቃ!” አለ ኤፍሬም፡፡
“አታልቅም?” ደንበኛው ነው፡፡
በዚች አጋጣሚ ለነዝናዛው ደዋይ መመለስ ፈለገ፡፡ እጁን በጠቆረችው ስትራቾ ጠርጐ ስልኩን አነሳ፤ “ሃሎ? እ… ጌች…” ስልኩን በትከሻውና በጆሮ ግንዱ አጣብቆ ይዞ አቀረቀረ፡፡ አልቆየም፤ በድንጋጤ “ምን?” ብሎ ጮሆ፤ ቀና ሲል የመኪናዋ ኮፈን ክፉኛ መታው፡፡ አይኖቹ ነጭ ብቻ የሆኑ እስኪመስሉ ድረስ ፈጠጡ፡፡ ጌቾ የቅርብ ጓደኛው ነው፤ ያለውንም ሰምቶታል፡፡ ሆኖም እንደ መብረቅ ብልጭታ አስደንጋጭ ስለሆነበት “ምን እያልከኝ ነው?” ሲል መልሶ አስደነገጠው፡፡ “ነገርኩህ----ርብቃ ዱባይ ሆቴል ሰገነቱ ላይ ከዚያ ከበፊት ጓደኛዋ… አረብ ሀገር ከነበረው ጋር …”
“ምን? መጣ እንዴ?”
“አዎ ቀለበት ምናምን ሳያስብ አልቀረም… ሊወስዳት መሆን አለበት…”
ኤፍሬም ጆሮውን ማመን አቃተው፡፡
“አሁኑኑ ሄደህ እውነቱን ባይኖችህ አይተህ ቁርጥህን እወቅ፤ምናልባት ደግመህ ላታያት ትችላለህ”  ቀስ በቀስ ሁሉም ነገር እየዞረበት ነው፤ ኤፍሬም፡፡
ርብቃ ከሌለች የማይኖር እስኪመስለው ድረስ የገዛችው የተገዛላት፣ ፍቅሩም ብቻ ሳትሆን ጣኦቱም ጭምር ናት፡፡ ስለዚህ ይህ ወሬ ለሱ መርዶ ነው፤ የመርዶ መርዶ፡፡
ደንበኛው እየተንቆራጠጠ ነው፡፡ “ኤፍሪ ኧረ ጨርሳት”
“ይቅርታ ለረዳቴ ደውልለት” አለው ኤፍሬም፤መንገዱ የጠፋበት ይመስል እየተደነባበረ፡፡
“ለምን? ኤፍሪ… እንዴ… ወዴት ነው?”
“ይቅርታ ባስቸኳይ መሄድ አለብኝ --- ይቅርታ…”
ታክሲ ወደሚያገኝበት ይከንፍ ጀመር፡፡ የደንበኛው እሮሮ ከጀርባው ቢሰማውም አልቆመም፡፡ ይሄ ሰው የገንዘብ ቦርሳው ቢሆንም ርብቃ ደግሞ የነፍስ ናት፤ ልቡን ይዛ የምትዞር…
ተማሪና ሰራተኞች የሚወጡበት ሰዓት በመሆኑ መንገዱ ተጣቧል፡፡ ተዘጋግቷል፡፡ ቶሎ መድረሱን ተጠራጠረ፡፡ መኪና ሊያውሱት ወደሚችሉ ወዳጆች መደወል ጀመረ… “ኤፍዬ ሰላም ነው?” ሰላምታም ጊዜ ይፈልጋል፤ ወደ ጉዳዩ ገባ፡፡
 “ውይ ሶሪ … እኔ አሁን ከከተማ እየወ…” ዘግቶ ወደ ሌላው… አይኖቹ ግራና ቀኝ ታክሲ ያድናሉ፡፡ ልቦናው ካዛንችስ መሃል ወደሚገኘው “ዱባይ” ሆቴል ሰገነት ላይ ወጥቷል፡፡ ሌላኛው፤ “አጐቴ ይዟት ወጣ” አለው፡፡ ኤጭ አለ ኤፍሬም፤ በብስጭት፡፡ ወደ ሚኒባስ ታክሲ ሮጦ ገባ፡፡
የለበሰውን ያስታወሰው ሊቀመጥ ሲል ግራና ቀኝ በመጠጋት ሳይሆን በሽሽት አይነት ሲሸጋሸጉ ነበር፡፡ ዘይትና ግሪስ የጠገበ ቱታውን እንዳያወልቀው፣ ከውስጥ አሮጌ የተቀዳደደ ሱሪ ነው የለበሰው፡፡ ጊዜም አማራጭም የለውም፡፡ ታክሲው እየሄደ ቢሆንም የቆመ ያህል ሆነበት፤ “እባክህ ንዳው!”
“እና ምን እያደረገ ነው!?” ጣልቃ ገባ ረዳቱ፡፡
“ኤፍሪ አባቴ… ሰላም ነው?” ሹፌሩ ያውቀዋል፡፡
“ምን ሰላም አለ፤ በዚች ደቂቃ ካዛንችስ መገኘት ነበረብኝ”
“አብሽር እንሞክራለን፤ ረዳቴ ለተናገረው ይቅርታ” አለ ሾፌሩ በተጨናነቀው ጐዳና መሹለኪያ እየፈለገ፤ “ስላላወቀህ ነው”
“የማያውቀውንስ መዝለፍ አለበት?” አለ አንዱ ተሳፋሪ፤ ጣልቃ በመግባት፡፡
“ሳይሆን” ሊከላከልለት ፈለገ፤ኤፍሬም፡፡
“ነው እንጂ” ሌላኛዋ ለጠቀች፡፡ ድምጿ የነገረኛ ይመስላል፡፡ ይዋጋል፡፡ ሾፌሩ ረዳቱን “ዝም በል” በሚል ጠቀስ አደረገው፡፡ ኤፍሬምም ሃሳቡን ወደ ርብቃ አዞረ፡፡ ሾፌሩ አቋራጭ መንገዶችን እየፈለገ ሲጓዝ ተስፋው አንሰራራ፡፡ የታክሲ ሾፌሮች መንገዶችን ሁሉ ማወቃቸው ይገርመዋል፡፡ የአቆራራጭ መንገዶችን የፈጠሩም ይመስለዋል፡፡
ጓደኛው በስልክ “ለመጨረሻም ጊዜ ሊሆን ይችላል የምታያት…” ያለውን ሲያስብ ሆዱ ባዶ፤ ምንም የሌለበት ሆነበት፡፡ ፍርሃት ለቀቀበት፤ብርድ ብርድ አለው፡፡
“ለምን ርብቃ… ርብቅዬ … ለምን?”
የመጀመሪያው ቀን ትዝ አለው፡፡ የዛሬ ሶስት አመት፡፡ አሮጌ ቮልስ ሊጠግን ተደውሎለት መንደሯ፣ ደጃፏ ድረስ ሄዶ ከቤቷ ስትወጣ አያት… ሱቅ ደርሳ ስትመለስም አያት፡፡
“የናንተ ናት?” ሊቀልድ ነበር፡፡
“ፈረስ ነው ያለን ታክመዋለህ?” ብላ አስቃው ገባች፡፡ ጨርሶ ለሙከራ መኪናዋን ሲያስጮሃት ወጣች፡፡ ከጀርባዋ የሚታየው የደሃ መኖሪያ ያፈራት አትመስልም፤ ልዩ ናት፡፡ ገባች ወደ ሱቁ፡፡ በመጨረሻ ለባለሱቁ ሹክ ብሎት ብሮች ሰጥቶት ሄደ፡፡ ከቀናት በኋላ ተገናኙ፡፡ “ኤፍሬም” ሲላት፤“ርብቃ…” ስትል በመቅለስለስ ነፍሱን ፍስስ አደረገችው፡፡ “አመሰግናለሁ” ብላ አከለችበት፡፡
“ለምኑ?”
“ረሳኸው?”
በግብዣ አንበሸበሻት፤ አድራሻ ተለዋወጡ፤ በቃ ጓደኞች ሆኑ፡፡
ከታክሲ ቢወርድም ገና ግማሽ መንገድ ይቀረዋል፡፡ ወደ ጓደኛው ደወለ፤ “ጌች እዚያው ቆይ …”
ጓደኛው እየተማረረ፤ “ስንት ጉዳይ ጥዬ… ቶሎ …ና”
“እየመጣሁ ነው፤ ከሄዱ እንኳን ወዴት እንደሆነ እያቸው…”
“ፍጠን አልኩህ!”
“ምን እያደረጉ ነው?”
“ኖ ኤፍ… ልነግርህ አልችልም፤ ሼም ነው” ስልኩን ዘጋበት፡፡
ሆዱ ውስጥ እሳት ነደደ፡፡ የቅናት እሳት ሆድ እቃውን ሁሉ ለበለበበት፡፡ ሰገነት ላይ ሼም ነገር!? ወፈር ቀላ ያለው ባላንጣው፣ ርብቃን እጇን ይዞ አስነስቷት ድንገት ከፊቷ በርከክ ብሎ፣ አይን የሚያጭበረብር ቀለበት አውጥቶ፤“ርብቅዬ ታገቢኛለሽ?” ሲላት በሁለት እጇ እያነሳችው… ያ እንደ ህልም ምስል የሚያስለመልም ውበቷ ፈክቶ፤ “አዎ…” ስትለው… ታየው፡፡
…ኤፍሬም በበርካታ መንገደኞች መሃል… እየሮጠ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ተጋጭቷል… የተገጩት ዞረው ቱታውን ሲያዩ… ዘለፋና ስድብ ጀርባው ላይ ሲያወርዱበት፣ እሱ የርብቃ “አዎ” ውስጡን በጩኸት ሞልቶት ሩጫውን ቀጥሏል፡፡
ኮንትራት መያዝ ፈለገ፡፡ በቂ ብር የለውም፡፡ ኤቲኤም ካርድ ግን ይዟል፡፡ ማሽኑን ባይኑ ፈለገ፤ ማዶ ላይ ባለ ህንፃ ስር አየ፤ ወደዚያ ሮጠ፡፡
ብዙ ጥንዶች የተዋወቁ ሰሞን እብድ ሊሉ ይችላሉ፡፡ ሲከራርሙ ያረግቡታል፡፡ የኤፍሬም ይለያል፤ በየቀኑ እየጨመረ እያደገ፣ ቁመቱን በልጦታል፡፡ ፍቅሩ በዝቶ እሷን ሲያስመልከው ስስታም አደረገው፡፡ ስስቱ በፍርሃት እየሞላው ሲሄድ ጠርጣራ አደረገው፡፡ ጥርጣሬው ደሞ ስጋትን፣ ስጋቱ ቅናትን አውርሶት ጨቅጫቃ፣ ነጭናጫ አደረገው፡፡ ይሄ ነው ከርብቃ የሚያጋጨው እንጂ ኤፍሬም የርብቃን ፍላጐቶች ሞልቶ፣ ወላጆቿን ያሳረፈ ምርጥ ደግ ሰው ነው፡፡ ትምህርቱን እሷን አስመርቆ ሊቀጥል ተስማምተው፣ እየከፈለ ኮሌጅ እያስተማራት ያለው እሱ ነው…
ሁለት ወጣቶች ቀደሙት፡፡ ተማሪዎች ናቸው፡፡ ብር አውጥተው ስለሚደግሱት የምሽት ፓርቲ እያወሩ ነወ፡፡ በልጆቹ ተናዶ፤በወላጆቻቸው አበደ፡፡ መፀዳጃ ቤት እንደተያዘበት ሰው ተንቆራጠጠ…
በፍቅራቸው እልፍኝ ሆነው፣ መላ አለሙን ሁሉ ረስተው፤ “ዘንድሮ ነው የምመረቀው” ጆሮው ስር ልጥፍ ብላ በለሰለሰ ትንፋሿ ለስለስ እያደረገችው፤ “ምርቃቱና ሰርጋችን አንድ ላይ ቢሆን ደስ ይለኛል” ስትለው በደስታ አየር እስክታጣ ሲጨመጭማት፣ እንደ ምንም አላቃው ያጣችውን ያህል አየር ስባ፣ “ሶስት ወር ማለት ነው፤ እስከዚያ ገንዘብ ከመቆጠብ ባላነሰ ይሄን ቅናትህን አለቅልቀህ መድፋት አለብህ ስትለው… “አሁን ትቼ” የሚላትን አስታወሰ፡፡  
“በፊት የቮልስ ሞተር ነበርኩ”
“አትቀልድ፤ ስልኬን መጐርጐርስ መቼ ተውክ!”
“ብሎክ አረገዋለሁ ብለሽ አልነበር” ስልኩን የገዛላት እሱ ነው፤ሁሌም ይቆጨዋል፡፡
“ግን ቻት ታደርጉ ነበር”
“ምን አለበት?”
“ለምን?”
“እኔ ግን ያንተ ብቻ ነኝ” አይኖቿን አይኖቹ ውስጥ ልትከታቸው የፈለገች መስላ፤ “የመጀመሪያ ጓደኛ አይዘጋም አይረሳም…” ብድግ ብሎ …ሆዱን ሲይዝ… እሳቱን ሊያጠፋ ውሃ አብዝቶ ሲጠጣ…
ሁለተኛው ወጣት የኤቲኤም ማሽኑን ሲደበድብ፤ “አንተ ሌላ አለ እኮ” ብሎ በቁጣ ሊያንቀው ደርሶ ነበር …”ፒስ በቃ …ፒስ..ፍሬንድ” አለና ብሩን ይዞ ሮጠ፡፡ ኤፍሬም ብሮቹ የቀሩበት ያህል እጆቹን እያስገበገበ ደቅኖ ጠበቀ፡፡
“ያማራትን እየገዛሁ ሳይተርፈኝ ለሷ ተርፌ፣ ወላጆቼን ረስቼባት ሳልጦራቸው፣ የሷን ዛሬና ነገ ሳሳምር … እሷ…የድሮዋን በኔ ዛሬ ላይ ዝርፍጥ ብላ ስትጠብቅ…እናቴ ረግማኝ ነው… ጡቷን በውበት ለውጬባት” ኤፍሬም በቁጭት ተንገበገበ፡፡ …ብሮቹን ይዞ ላዳ ታክሲ በዓይኑም በእግሩም ፈለገ፡፡ ቀናውና አግኝቶ ተሳፈረ፡፡
በቅርብ ጊዜ አንድ ወር ገደማ ፎቶ አገኘባት፡፡ ከሱ ጋር ከኖረችው በላይ አብሯት የኖረ ፎቶ፡፡ እውነተኛው የድሮ ቮልስ ሞተር ሆነ፤ ነደደ፡፡ “ይሄን ያህል?” ብላ ፊቱ ብታቃጥልለትም የሱ እሳት አልጠፋም፡፡ ይኸው እውነቱ “እኔን ትዋሸኛለች? ሚስቴ ሳትሆን በባል ቦታ ብኖርላት…” ብሎ በገነ፡፡
“ከዚህ በላይ አትፈጥንም?”
በሁኔታው ፈርቶት የነበረው አሽከርካሪ፤ በቱታውና በጣቶቹ ጥቁረት የተረጋጋ መሰለ፡፡
“መቼም ስለ መኪናዋ ታውቃለህ?”
“አዎ ትፈጥናለች”
“ሰርቼ ለቅጣት ለጥገና መገበሩ መሮኛል!”
“በኔ ኃላፊነት እኔ ልንዳት”
ሹፌሩ በስጋት አየው፡፡ አይኖቹ ውስጥ አንዳች ሃቀኝነት ያየ መሰለው፤ መሪውን ለቀቀለት፡፡ ወዲያው ላዳዋ ሹልክ ሹልክ፣ ስንቅር ድንቅር ስትል፣ አካባቢው በጥሩምባ ተሞላ፡፡ ዝብርቅርቅ ያለ የሰርግ አጀብ መሰለ…
በቀደም ምሽት ከኮሌጅ ስትወጣ ሊቀበላት ሄዶ ካንዱ ጋር እየተሳሳቀች ደረሰና፤ “ምንድነው ሸክም እንደበዛበት ባሌስትራ እጥፍ እስክትይ ያንከተከተሽ” ሲል ጠየቃት፡፡  
“እንዴት የሚያዝናና ልጅ መሰለህ” መለሰችለት፡፡ ወዲያው ስልኳ ሲጠራ፣ ስልኳን ስታየው አይኖቿ ውስጥ ያየው ብልጭታ ካንዴላውን እሳት እያስረጨው፤ “ማነው?” ሲል አፈጠጠባት፡፡  
ካዛንቺስ ደረሰ፡፡ ከፊቱ ዱባይ ሆቴል ይታየዋል፡፡ ከዱባይ መጥቶ ዱባይ ሆቴል!…ሰገነቱን በዓይኑ እየፈለገ… ላዳዋን ክንፍ ያላት አስመሰላት፡፡ ወዲያው ሹፌሩ፤ “እያየህ” ብሎ ጮሆ ሳይጨርስ፣ ሌላ ጩኸት፣ ጋጋታ “ወይኔ!” አለ ባለ ላዳው ጭንቅላቱን ይዞ፡፡
 የትራፊክ ፖሊስ ፊሽካ፣ የብዙ መኪናዎች ጥሩምባ፣ተደበላለቀ…
“መጣሁ” አለ ኤፍሬም ለሹፌሩ፡፡
“ዕብድ ነህ?”
“እመነኝ” ወርዶ ሮጠ፡፡
ትንሷ አዲስ መኪና በላዳዋ ተጐድታለች…ሾፌሩ አብዷል፡፡ ኤፍሬም ሰገነቱን እያየ ሮጠ፡፡ ደወለ፤ “ጌች የት ነህ? የሉም?!”
“አ---ኤፍሪ…” ወዲያው ሳቅ…ጆሮውን ተጠራጠረ “ማነው የሚስቀው…?”
“ኤፍሪ በቃ ጌም ኦቨር…እቤት ና”
“ሰውዬ?”
“አፕሪል ዘ ፉል ነው እኮ” ሳቁን እየለቀቀው፡፡
 “ለፈን ነው…” ረዥም ሳቅ፡፡ ኤፍሬም ስልኩን እየዘጋ ወደ መሬቱ ዝቅ ዝቅ እያለ ተዘረፈጠ፡፡ ሦስት ሰዎች ቀረቡት፡፡
 ባለ ላዳው፣ የተገጨው መኪና ባለቤትና ግዙፍ ትራፊክ ፖሊስ፡፡  አንስተው ወሰዱት፡፡ ኤፍሬም … ትንፋሽ ያለው በድን ሆኗል፡፡ ከፊቱ የተከመረበትን የገንዘብ ዕዳ…ሲያስብ ሁሉ ነገሩ ጨላለመበት፡፡  

Read 3470 times