Tuesday, 24 May 2016 08:22

“የትዝታ ፈለግ”ን በወፍ በረር

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ይህ ጽሁፍ ሚያዝያ 21 ቀን 2008 ዓ.ም የአቶ አሰፋ ጫቦ ”የትዝታ ፈለግ” መጽሐፍ በጣይቱ የባሕልና ትምህርት ማዕከል አዳራሽ
በተመረቀበት ወቅት መጽሐፉን ለማስተዋወቅ ካደረግሁት ንግግር አጥሮና ተስተካክሎ (Edited) የቀረበ ነው፡፡

ዓለም ፀሐይ ወዳጆ
(Silver Spring, Maryland USA)

   የተወደዳችሁ እንግዶች፤ በቅድሚያ የዛሬው እንግዳችን አቶ አሰፋ ጫቦ ‹የትዝታ ፈለግ› በሚል ርዕስ ያሳተመውን መጽሐፍ ለምርቃት በማብቃቱ በጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከል ስም ‹እንኳን ደስ አለህ!› እላለሁ::
በዛሬው ምሽት የትዝታ ፈለግ  በሚል ርዕስ ለንባብ ያበቃውን መጽሐፉን ልንመርቅ ነው የተሰባሰብነው:: መጽሐፉን በማነብበት ወቅት ብዙ ወደ ማውቃቸው ጊዜያትና ግለሰቦች የወሰደኝ ሲሆን የአጻጻፍ ውበቱም እጅግ አስደንቆኛል፤ የባህሪይ አቀራረፅ ችሎታውና የአካባቢ ስዕላዊ መግለጫውም አርክቶኛል::
አቶ አሰፋ ጫቦ፤ ከተራራ አናት ላይ ከሚገኝ ሜዳማ ቦታ ላይ ጨንቻ ከተማ ነው የተወለደው:: ከጋሞ ሰንሰለት ተራራዎች አንዱ ጫፍ ላይ የሚገኝ ጠረጴዛ ነው ይላታል፤ጨንቻን ሲገልጣት፡፡  ከ 2ኛ- 6 ኛ ክፍል እዚያው ጨንቻ የተማረ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ አበባ ኮከበ ጽባህ እስከ ፲ኛ ክፍል ተምሮ አቋረጠ። ሆኖም በራሱ መንገድ ህግ ተምሮ መመረቅ ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ውድድሮችም ሁለቴ ተካፍሎ፣ከንጉሱ እጅም የወርቅ ኦሜጋ ሰአት ለመሸለም በቅቷል፡፡
በመጽሐፉ ውስጥ በወህኒ ቤት ሳሉ፣ በሙሉጌታ በቀለ አካሚነት (ገጽ15-18) ሰለሞን ደርቤን በእግሩ ማቆም መቻልን አልፎም ፈጣን ሆኖ የእስረኛ ምግብና ቡና አመላላሽ ተደርጎ መመደቡን አሳይቶ አስደምሞኛል:: የአገራችንን የአብያተ ክርስቲያኑንም ጭምር ድንቅ ውበት በማስቃኘት፣ ለቱሪዝም አዳዲስ አካባቢዎችን ለማስተዋወቅ ሞክሯል፡፡
በመጽሐፉ ላይ በጠቀሳቸው (ገጽ 25-34) በረዘነና በወይናይ ባለው ችግር መነሻነት በትግራይና በኤርትራ መካከል የነበረው ቅራኔ ምን እንደሚመስል እንድናይ ያደረገበት ዘዴ አስገርሞኛል:: የሕግ አዋቂነቱን ለአቀራረቡ ማነጻጸሪያ ተጠቅሞበታል፡፡ “ረዘነ ወልዱና ወይናይ ሁለት የተለያየ ባህርይ ያላቸው ሰዎች ናቸው። ረዘነ ተጫዋች፤ተግባቢ፣ደግ፤ገራገር፤ተናጋሪና በመጠኑም ቢሆን ችኩልም ነው። ፈጣን ነው ማለት ይቻላል። ሀብታም ነው ማለትም ይቻላል። ወይናይ ምስኪን ነው። ሁለመናው ምስኪን ነው። ከ3 አመት በላይ ሲኖር ከመንሾካሸክ ያለፈ ድምጽ ሲወጣው አልሰማሁም። -----” ይለናል።
በመጽሐፉ (ገጽ19-24) ጎንደሬውን፤ቀናና የዋሁን፤እንደወጣ የቀረውን ዶ/ር ካሳሁን መከተን ያነሳዋል፡- ‹‹ በቀን ቢያንስ አንዴ ሳያነሳቸው የማይውላቸው ሁለት ነገሮች አሉ። አንደኛው ስለደባርቅ/ዳባት ነው። የኢትዮጵያን ኋላ ቀርነት ማስረጃ ያደርጋቸዋል። እስከ ዛሬ ማብራት እንኳን አልገባላቸውም! ይላል። “ሶሻሊዝም፤ሶሻሊዝም!” ይላሉ ደባርቅ መብራት መች ገባ ?” ይላል። ይህችው ነች! አይለዋውጥም!”
ብዙ ባለታሪኮና ተረቶች መጽሐፉን አጣፍጦለታል፡፡  እናቱን አክብረው “እንዬ” እያሉ ባደጉት ጓደኞቹ በእነ ዶክተር ገዛኸኝ በላይና በፍስሀ ዘለቀ ታሪክ ውሰጥ አጥልቆ የመንፈስን ከመንፈስ ጋር መዋሃድ እንዲሁም የህዝብን ሥነልቦናዊ አመለካከትን እንድናይ ያደርገናል::
“ነፍጠኛ” ማለት አማራ ብቻ ነው ማለት እምነት እንጂ እውነት እንዳልሆነና “ነፍጠኛ” (117-151) በሚል የሚበጠብጠንን ጥያቄ ለመመለስ ናችሁ የተባልነውን ሳይሆን ውስጣችን ገብተን ሆነን ያለነውን እንድናስተውል ይጎተጉተናል፡፡ ጋሽ አሰፋ፤“አቅብጦኝ ከደርግ ጋር ገጠምኩ” ብሎ አያውቅም:: አምኖ እንጂ ምናምን ፍለጋ ወይም ሰው ገፍቶት እንዳልገባ በግልጽ አስቀምጦልናል:: እንዲያውም “በመሸ በጠባ ቁጥር በጥሼ የምቀጥለው ማተብ የለኝም !” ይለናል::
በትረካዎቹ ጸሃፊው በንባብ የዳበረና የበሰለ መሆኑን ከማሳየቱም ሌላ ወደ አሜሪካ ስለ መምጣትና መኖር ያካፈለው ምክርም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ስለ ስደቱ ዓለም ችግርና ውጥንቅጥ ሲጽፍም፤ ስደተኛው በሃብት ድህነትና በአእምሮ  ድህነት መካከል ያለው ልዩነት የጠፋበት መምሰሉን ፍንትው አድርጎ ያሳየናል፡፡ በአጠቃላይ ጆሮ ጠገብነት ማወቅን አለመተካቱን ይገልጽልናል፡፡   
ጀግና ፍለጋ ጦር ሜዳ መሪዎች አምባ፣ የፖለቲካ ሰዎች አምባ እንሄዳለን:: ጀግና ሲገኝ አገር ያውቀዋል፤ ፀሃይ ይሞቀዋል:: ያልታወቁ በየቤቱ የታጨቁ ተራ ሰው የሆኑ ጀግኖች አሉ በማለት፣ በዕለት ተዕለት ኑሮአችን ያልተሰጣቸውን በመፈጸም የበለጠ ጀግና ስላደረጋቸው የአማቾቹ የቤት ሠራተኛ ስለሆነችው ስለ ወሎየዋ ዘውዲቱ አስማረ “የኔይቱ ጀግና!” (63-67) በሚል ርዕስ ይተርክልናል፡፡  “ጋሞ” ይላል “ጋሞ ግብር ገበረ እንጂ ሥርዓቱን አልገበረም” በማለት ጥፋቱን ስህተቱን በማመን መቀበልና ባደባባይ ይቅርታ መጠየቅ የጋሞነት መገለጫና አብሮ የተወለደ የውስጥ ባህርይ መሆኑን በመተንተን፣ ለየት ስላለው የአገርና የህዝብ አስተዳደር ሥርዓት ሲያጫውተን፤ አንዳንዶቻችን በአገራችን ውስጥ ይህ መኖሩን ባለማወቃችን እንቆጫለን:: ወደ ዛሬያችን ለማምጣት በምኞት እንጋልባለን::
 ሌላው የጋሽ አሰፋ ትልቅነቱ፣ እንደ አንዳንዶቹ ፀሃፊዎች በራሱ አራት ነጥብ ዘግቶ እመኑልኝ ሳይለን፣ “ያየሁትና የኖርኩት እንጂ ያጠናሁት አይደለም” ማለቱ ነው:: በትዝታዎቹ ውስጥ እየሾለከ የሁላችንንም ትዝታ ይቆሰቁሰዋል፡፡ በተለይ በመጽሃፉ የጠቀሳትን፣ ይህንን ማዕከል ‹‹ጣይቱ›› ብዬ እንድሰይም ምክንያት የሆነችኝን Empress Taytu and Menilik the II of Ethiopia ደራሲ ክሪስ ፕራውቲን  (Chris Prouty 111-115)  እንደኔው አግኝቶ ስላደነቃትና ስላሞካሻት ይበልጥ ተደስቻለህ::
ዛሬ በአገራችን ስለተንሰራፋው ሥርዓትም በማዘን እየገለጸ ወደተሻለ እንድንጓዝ ይማፀነናል:: በእስራት ብዛት የህዝብ ነጻነት ታፍኖ የቀረበት ዘመንም አገርም አለመኖሩን በማስረገጥ፣ለ“የጋራ ቤታችን ” የሚፈለገውን መጠነኛ ጥገና በማካሄድ ፈንታ መናድ የመረጡትን ያወግዛቸዋል፡፡ አገራቸውን ባለማወቅ ወይም ለማወቅ ባለመፈለግ፣ ነቀዝ የበላው ቤት እንድትሆን ማድረጋቸውን በመውቀስም፣የምትፈለገዋን  ከስህተቷ ልምድ የቀሰመች አዲሲቷ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንድንገነባ ይጣራል:: የትዝታ ፈለግ ራስ ወዳዶች እራሳቸውን እንዲጠይቁና እንዲፀየፉም ይገፋፋል፡፡ በተለይም ገጽ 244 “አልዘቅጥም መባል ያለበት ወደ ታች ወደ ምድር ቤት ምን ያህል ሲዘቅጡ ይሆን?›› ሲል በመጠየቅ ‹‹ከዚህ በላይ አልወርድም በቃኝ አይባልም! በቃኝ አታውርደኝ ተብሎስ አይፀለይም …” በማለት እነዚህን ወገኖች ይሸነቁጣቸዋል:: ከቁጣ ይልቅም ወደ ዳኝነት፣ ወደ ማመዛዘን እንድናደላ  ይጋብዘናል::
 አብርሃም ሊንከን እንዳለውና ጋሽ አሰፋም በመጽሃፉ ላይ እንደጠቀሰው፤ ‹‹ማንንም ያለ ቂም እንድንመለከት፣ሁሉንም በልግስና እንድናቅፍ፣በሃቅ ላይ እንድንጸና፣አምላክም ይህንን ሐቅ እንድናይ እንዲረዳን እንማጸን”:: ኢትዮጵያውያንንም የማይመጣን ነገር ከመጠበቅ ረጅምና ዝነኛ ታሪካችን ይገላግለን !
ጋሽ አሰፋም፤ “እመለስበታለሁ “ እያለ ያለፋቸውን ጉዳዮች፡- ስለ እስረኛው ቡና ማፍያ፣ ስለ ሁለንተናዊ የኑሮ ዘርፍ ማሟያ፣ ስለ ቀኝ አዝማች ታዬና ስለ ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም፣ ስለ አሜሪካ አገር ድመትና ውሻ ዘውድ መጫን፣ ወዘተ አሰባስቦ ሁለተኛ መጽሐፉን ለአንባቢያን እንዲያደርስ ያብቃው::
  “በትዝታ ፈለግ” ምክንያት እኔም እንደ ጋሽ አሰፋ ግርጫ ቤት መስራት አማረኝ:: እኔም ጨንቻን ወደ ታች የዞዞን ተራራ ማዶ ለማዶ ማየት አማረኝ:: ጨንቻን ለመሞት ሳይሆን ለመኖር መረጥኳት!! እዚያ ሰው አይሞትምና…በዝግታ መራቅ…ባልተስተዋለ መልኩ ማለፍ…አማረኝ!
   በድጋሚ እንኳን ደስ አለህ !!!

Read 2514 times