Tuesday, 24 May 2016 08:36

የአገሬ ሰው መከራ ---- በሱዳን እስር ቤቶች

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(7 votes)

  (የመጨረሻ ክፍል)
                          
                (የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ በቦታው ተገኝቶ ያጠናቀረው ልዩ ዘገባ)
    “አሁን ከእስር እንድንፈታ አይደለም የምንጠይቀው!... የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት፣ ከሱዳን መንግስት ጋር ተነጋግሮ፣ አገራችን ገብተን ቀሪ የእስር ጊዜያችንን የምንጨርስበትን ጊዜ እንዲያመቻችልን ብቻ ነው የምንጠይቀው!...”

     እዚያው ነኝ...ኡምዱርማን ስጅን አል ሁዳ...
እሱ ያወራል፣ እኔ እሰማለሁ...ከብረት ፍርግርጉ በስተጀርባ የቆመው ኑርሁሴን፣ ብዙ መከራ፣ ብዙ ስቃይ፣ ብዙ ምሬት... ብዙ ነገር ይተርክልኛል...የኡምዱርማን ስጅን አል ሁዳን መከራ፣ ተርከውትም ሰምተውትም አይዘልቁትም፡፡
የወንዜ ልጆች በዚህ ግቢ ውስጥ የሚያዩት መከራ፣ በ15 ደቂቃ ይቅርና በዘለአለም ዕድሜ ተተርኮ አያልቅም፡፡ ከኑርሁሴን ተረክ በስተጀርባ፣ ጎላ ያለ ድምጽ ተሰማኝ፡፡ የፖሊሱ ድምጽ ነው - በቃችሁ እያለን ነው፡፡
ኑርሁሴን በጭላጯ ሰከንድ፣ የመጨረሻዋን መልዕክቱን ወረወረልኝ፡፡
“አሁን ከእስር እንድንፈታ አይደለም የምንጠይቀው!... የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት፣ ከሱዳን መንግስት ጋር ተነጋግሮ፣ አገራችን ገብተን ቀሪ የእስር ጊዜያችንን የምንጨርስበትን ጊዜ እንዲያመቻችልን ብቻ ነው የምንጠይቀው!... አገራችን ገብተን ብንታሰር፣ በነጻ እንደተለቀቅን ነው የምንቆጥረው!...” አለኝ በልመና ድምጽ፡፡
አገራችን ገብተን እንታሰር!...
ፖሊሱ በቁጣ በአረብኛ ጮህ ብሎ ተናገረና፣ ከተለጠፍኩበት የብረት ፍርግርግ ጎትቶ አላቀቀኝ፡፡ በድንጋጤ ክው እንዳልኩ፣ ዘወር ብዬ ወደ ፍርግርጉ አየሁ...  ኑርሁሴን፣ ፊቱን አዙሮ ወደ ውስጥ አዘገመ...
በገባሁበት በር፣ ተመልሼ እየወጣሁ... ዘወር ብዬ አየሁት... ያው ከበስተጀርባዬ፣ የወንዜ ልጆች የታጎሩበት የመከራ ግቢ - ኡምዱርማን ስጅን አል ሁዳ!...
እኔ ወጣሁ!... እነሱስ መቼ ይሆን የሚወጡት!?... እነ ኑርሁሴን፣ እነ አብዱላዚዝ፣ እነ አብርሃለይ፣ እነ መሃሪ... እነዚያ ብዙ የወንዜ ልጆችስ፣ መቼ ይሆን ከዚህ የስቃይ ግቢ የሚወጡት!?...
መቼ?... መቼ?... መቼ?...
“መቼ?...” እያልኩ ወደ ግቢው በር አዘገምኩ...ናስርንና ሱሌይማንን ተከትዬ፣ ተፈትሸን ወደገባንባት አነስተኛ ክፍል አመራን...ፈትሾ ያስገባን ፖሊስ፣ ለሁለቱ መታወቂያቸውንና ሞባይላቸውን መልሶላቸው፣ እንዲወጡ ፈቀደላቸው፡፡
እነሱ ወጡ...
እኔና ወፍራሙ ፈታሽ ጠባቧ ክፍል ውስጥ ቀረን...ፓስፖርቴን ከተቀመጠበት አንስቶ በመግለጥ፣ ፎቶግራፌን አየና፣ ከእኔ ገጽታ ጋር መመሳሰሉን ለማረጋገጥ ቀና ብሎ አየኝ...
“ሃበሽ?...” ሲል ጠየቀኝ፡፡
“የስ!...” አልኩት በትህትና፡፡
ኮስተር እንዳለ ፓስፖርቴን አቀብሎኝ ከጎኑ ያስቀመጠውን ሞባይሌን ብድግ አድርጎ፣ መልሶ አፈጠጠብኝ...የኔ ሞባይል ስለመሆኑ የተጠራጠረ መሰለኝና፣ ላረጋግጥለት ፈለግሁ...
“የስ... ኢት ኢዝ ማይን...” አልኩት ፈገግ ብዬ፡፡
እያየኝ ዝም አለ፡፡ አይኑ ውስጥ የሆነ ነገር አያለሁ...
“መኒ... ጋንዛፕ...” አለኝ በተሰባበረ እንግሊዝኛ፣ ከኪሱ የሱዳን ፓውንድ መዘዝ አድርጎ እያሳየኝ፡፡
ደነገጥኩ...
“ኖ መኒ... ፊኒሽድ!...” አልኩት እየተርበተበትኩ፡፡
ኮስተር ብሎ ተጠጋኝና፣ የለበስኩት የቱታ ሱሪ ኪስ ውስጥ እጁን ከተተ፡፡
ጉድ ፈላ አልኩ፡፡ የኪሴን ገበር ሲገለብጠው፣ የተጣጠፈች ባለ 20 የሱዳን ፓውንድ ብቅ አለች፡፡ ናስር በኪሴ ያለውን ገንዘብ ሁሉ መኪናው ውስጥ ትቼ እንድወርድ ያስጠነቀቀኝ ለምን እንደሆነ ተገለጠልኝ፡፡
“ቴክ ኢት...” አልኩት ለፈታሹ ፈገግ ብዬ፡፡
“ኖ!... ዚስ ሊትል!... አዘር መኒ...” አለኝ ሌላኛውን ኪስ እየፈተሸ፡፡
ቀሪ ገንዘብ እንደሌለኝ ሲረዳ፣ ሞባይሌን እያሳየኝ፣ ልውሰዳት ሲል ጠየቀኝ...
እየተርበተበትኩ ለመንኩት... ስንዳረቅ ቆይተን፣ እንደማልረታለት ሲያውቅ በአረብኛ የሆነ ነገር ተናግሮ ሞባይሌን ሰጥቶ አስወጣኝ... በአረብኛ ከተናገረውን ነገር ውስጥ፣ ሃበሽ የምትለዋን ብቻ ነው ለማወቅ የቻልኩት... ምን ብሎኝ ይሆን?!...
ፊቱ ላይ ያየሁት ንቀት ግን፣ “ድሮስ ከሃበሻ ምን ሊገኝ!?... ችጋራሞች!...” ሳይለኝ እንዳልቀረ አስጠርጥሮኛል፡፡ ይበለኝ ግድ የለም!... “እናንተ እምታውቁኝ ታጥቄ፤ እሷ የምታውቀኝ አውልቄ!...” አለ አሉ መይሳው ካሳ - (ምሽትዬይቱ ጌታችንን ናቀቺው ብለው በንዴት ለጦፉ አሽከሮቹ)፡፡
ጭው ባለ በረሃ ውስጥ...
ፊቷን ወደ ካርቱም አቅጣጫ አዙራ፣ በረሃውን እየሰነጠቀች የምትጓዝ አሮጌ መኪና... መኪናዋ ውስጥ እኛ - እኔ፣ ናስር እና ሱሌይማን...ዝም ብለን... በየራሳችን ሃሳብ ተውጠን... መኪናችን ውስጥ አድፍጠን...
“ደማ መካ...” ይላል ታደለ ገመቹ፣ አንጀት በሚበላ ቅላጼ፡፡ ወደ ካርቱም እየተመለስን ነው...
“ተጫወት እንጂ?...” አለኝ ናስር ከጋቢና ሆኖ ዘወር ብሎ እያየኝ፡፡
“እ... እሺ...” አልኩት ፈገግ ለማለት እየሞከርኩ፡፡
ስለ ፈታሹ ፖሊስ እያሰብኩ ነበር፡፡ ለእነ ናስር ከፈታሹ ጋር የነበረንን ውዝግብ አጫወትኳቸው፡፡
“ጅቦች እኮ ናቸው!... ገንዘብ ካዩ፣ አስወልቀው ነው የሚወስዱብህ!...” አለኝ ናስር፣ የተለመደ ተግባራቸው መሆኑን ለማስረዳት፡፡ ነገሩ ለእኔ እንጂ ለእነ ናስር አዲስ አይደለም፡፡ የሱዳን ፖሊስና ባለስልጣናት በሙስና የተጨማለቁ መሆናቸውንና በየሰበብ አስባቡ ከሃበሻ ስደተኞች ገንዝብ መዝረፍ እንደማይሰለቻቸው አጫወቱኝ፡፡
“እዚህ አገር ስትኖር፣ ብር ከሌለህ መከራህ ብዙ ነው፡፡ በየሰበቡ ትያዛለህ፡፡ ገንዘብ ካለህ ለፖሊሶች ሰጥተህ ነጻ ትወጣለህ፡፡ ከሌለህ ግን እስር ቤት ይወረውሩሃል፡፡ ታስረህም ገንዘብ ከሌለህ መከራህን ነው የምታየው፡፡ የታሰረብህ ዘመድ ወዳጅ ሲኖርህም፣ ገንዘብ ከሌለህ ችግር ነው!....” አለኝ ናስር በስሜት ተውጦ፡፡
ናስር እንደነገረኝ... ፖሊሶች ከእስረኛው ከራሱ፣ ሊጠይቀው ከሚመጣ ሰው ጋር እንዲገናኝ ገንዘብ ያስከፍላሉ፡፡ የታሰረ ጓደኛና ዘመዱን ለመጠየቅ የመጣን ሰው ደግሞ፣ ገንዘብ ካልሰጠህን አናስገባህም ይላሉ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ፣ አንተም የወንጀሉ ተባባሪ ነህ፤ የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀትህ ጊዜው አልፎበታል፣ ለኢሚግሬሽን አስረክበንህ ወደ አገርህ ትመለሳለህ ብለው ያስፈራሩታል፡፡ በዚህ ሳቢያ ወገኖቹን ለመጠየቅ እየፈለገ፣ ለራሱ በመስጋት ወደ እስር ቤት ድርሽ የማይለው ሃበሻ ብዙ ነው፡፡ ናስርም እንዲህ ያለ ብዙ መከራን አስተናግዷል - በስጅን አል ሁዳ እስር ቤት በሚገኘው ወንድሙ በአብዱላዚዝ ሰበብ፡፡
አብዱላዚዝ ያለ ወንጀሉ መከሰሱን የሚናገረው ናስር፣ ፍርድ ቤቱ በነጻ እንዲያሰናብተው ለማድረግ፣ ይከራከርልኛል ብሎ ከፍተኛ ገንዘብ የከፈለው አንድ ሱዳናዊ ጠበቃ ነበር፡፡ ጠበቃው ግን ገንዘቡን ከተቀበለ በኋላ፣ ድራሹን አጠፋ፡፡ አፈላልጎ ሊያገኘው ቢሞክርም፣ መሰል ክህደት የተፈጸመባቸው የአገሩ ልጆች ይህ ክስተት የተለመደ ነገር በመሆኑ ተስፋ እንዲቆርጥ ነገሩት፡፡ ተስፋ ቆርጦ ተወው!...
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ወንድሙን አብዱላዚዝን በገንዘብ ለማስፈታት ያላደረገው ጥረት የለም፡፡ በሱዳናውያን ጓደኞቹ አማካይነት ላገኘው አንድ የእስር ቤቱ ሃላፊ፣ ወንድሙን ለማስፈታት 40 ሺህ የሱዳን ፓውንድ ከፍሎ ነበር፡፡ የእስር ቤቱ ሃላፊ ገንዘቡን ሲቀበል፣ በሶስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ እንደሚያስፈታው ቃል ገብቶለት ነበር፡፡
ናስርም ሰውዬው ወንድሙን ከዛሬ ነገ ያስፈታልኛል ብሎ ቢጠብቅም፣ ያለምንም ውጤት ሳምንታትና ወራት አለፉ፡፡ ተስፋ እማይቆርጠው ናስር፣ ያንኑ ግለሰብ አፈላልጎ አገኘው፡፡ ያንን ጉዳይ ከምን አደረስክልኝ፤ ካልሆነ ገንዘቡን መልስልን ሲልም ጠየቀው፡፡ ከግለሰቡ ያገኘው ምላሽ ግን፣ ስለታሰረው ወንድሙ ትቶ ስለራሱ ደህንነት እንዲጨነቅ የሚያስገድደው ነበር፡፡
“የምን ገንዘብ ነው የምታወራው?... አሁኑኑ ከዚህ አካባቢ ድራሽህን ካላጠፋህ፣ እንደ ዘመዶችህ ደበክ ወስጄ ነው የምወረውርህ!...” ነበር ያለው ኮስተር ብሎ፡፡
ናስር በቅጽበት ተሰወረ - ምክንያቱም ሰውዬው የሚያወራው ስለ “ደበክ” ነው፡፡
ደበክ - የምድር ሲኦል!...ከአስከፊው ኡምዱርማን ስጅን አል ሁዳ እጅጉን የከፋው የሱዳን እስር ቤት - ደበክ!...
በደበክ እስር ቤት ታስሮ የነበረው ኢትዮጵያዊው ስደተኛ ዳንኤል፣ ስለዚህ አስከፊ እስር ቤት ሲናገር በከፋ ምሬት ነው፡፡ እሱ እንደሚለው፣ ከደበክ ጋር ሲነጻጸር፣ ስጅን አል ሁዳ ገነት ነው፡፡“ደበክ ከካርቱም የሁለት ሰአት መንገድ ነው፡፡ ሐበሻ ሞቱን የሚመርጥበት እስር ቤት ነው፡፡ እኔም እዚያ ግቢ እንደገባሁ ነበር፣ ፈጣሪን ግደለኝ ብዬ አልቅሼ የለመንኩት!... ልክ እንደገባህ ጸጉርህን ትላጫለህ፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ገንዘብ ካልያዝክ፣ ሰው በተላጨበት ምላጭ ነው የሚላጩህ!... የምትተኛው ማዳበሪያ የተነጠፈበት፣ ቀዝቃዛ የሲሚንቶ ወለል ላይ ነው፡፡ ከእስረኛው ብዛት የተነሳ፣ ተመቻችተህ መተኛት አትችልም፡፡ መፈናፈኛ ቦታ ስለሌለ፣ ሁሉም በአንድ ጎኑ ነው የሚተኛው፡፡ መገላበጥ አይታሰብም፡፡
 ከክፍሉ ጥግ ላይ የሚገኝ ጉድጓድ ላይ ነው የምንጸዳዳው፡፡ ከአጠገቤ የሚተኛ ደቡብ ሱዳናዊ እስረኛ፣ ወደ ጉድጓዱ መሄጃ ቦታ ስላጣና ሽንቱን መቆጣጠር ባለመቻሉ እላዬ ላይ ይጸዳዳ ነበር...” ብሎኛል ዳንኤል የደበክን እስር ቤት በምሬት እያስታወሰ፡፡
ዳንኤል እንደነገረኝ...ደበክ የሚገኘው ከአባይ ወንዝ ዳርቻ ላይ ነው፡፡
“ፖሊሶቹ ከንጋቱ 12 ሰአት ይቀሰቅሱህና ቆጠራ ያደርጋሉ፡፡ ቀኑን ሙሉ የምትመገበው 6 ዳቦና አንድ ሲኒ ፉል ይሰጥሃል፡፡ ተሰልፈህ ወደ አባይ ወንዝ ዳርቻ ትወሰዳለህ፡፡
 እስከ 45 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በሚደርስ ሙቀት እየተቃጠልክ፣ የቤት መስሪያ የሸክላ ጡብ ስትሰራ ትውላለህ፡፡ ቢደክምህ እንኳን ለደቂቃ ማረፍ አትችልም፡፡ ስራህን አቋርጠህ፣ አርፈህ ከተገኘህ ስጋ በሚቆርጥ ጉማሬ 25 ጊዜ ትገረፋለህ፡፡“ከቀኑ ስድስት ሰአት ሲል ፊሽካ ይነፋል፤ ጠዋት የተሰጠህን አንድ ሲኒ ፉል በሶስት ዳቦ ትበላና፣ የአባይን ውሃ ጠጥተህ 30 ደቂቃ ታርፋለህ፡፡ ስድስት ተኩል ሲል ስራ ትቀጥላለህ፡፡ እስከ 9 ሰአት ስትሰራ ትውልና፣ ወደ ግቢ በሰልፍ ትገባለህ፡፡ የእረፍት ሰአትህ ከአስር እስከ አስራ አንድ ሰአት ነው፡፡ በዕረፍትህ የምታደርገው ነገር ቢኖር ልብስህን አውልቀህ ቅማል መልቀም ነው፡፡ ያለማጋነን ነው የምነግርህ፣ ለቅመህ የማትጨርሰው እጅግ የሚዘገንን ቅማል ነው በልብስህ ላይ የምታገኘው፡፡ ምክንያቱም በዛ ክፍል ውስጥ 120 ሰው ነው የሚተኛው፡፡ በእረፍት ሰዓትህ ቅማሉን ካላራገፍክ ማታ በሰላም መተኛት አትችልም፡፡ የደበክን መከራ ዘርዝሬ አልጨርሰውም!... በዚያ ግቢ ውስጥ መከራቸውን የሚያዩ ኢትዮጵያውያን ብዙ ናቸው” ብሎኛል ዳንኤል፡፡.
ድካምና ሙቀት ያሰቃዩኛል...መሃል ካርቱም በሚገኘው የማረፊያ ክፍሌ አልጋ ላይ ተዘርሬያለሁ...በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ጎግልን እበረብራለሁ...
አብዛኞቹ መረጃዎችና ዘገባዎች የመከራው ጉዞ ከመተማ እንደሚጀምር ያመለክታሉ፡፡ ዘ ጋርዲያን ባለፈው ነሃሴ ባወጣው ዘገባ፣ ከሱዳን ድንበር አቅራቢያ የምትገኘዋ መተማ፣ ስደተኞችን በህገወጥ መንገድ በማሸጋገር ዳጎስ ያለ ገንዘብ የሚታፈስባት የደራች የስደት ገበያ መሆኗን ገልጧል፡፡ የህገወጥ የሰዎች ዝውውር ማዕከል በሆነቺው በዚህች ከተማ በኩል፣ ብዙዎች ድንበር አልፈው ወደ ሱዳን ገብተዋል፡፡ እስካለፈው አመት መጨረሻ ድረስ በቀን እስከ 250 ስደተኞች በመተማ በኩል ድንበር አቋርጠው ወደ ሱዳን ይገቡ ነበር፡፡
በሚያዝያ ወር 2007 ላይ በዚህች ከተማ በኩል ወደ ሊቢያ የተሻገሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በአሸባሪው ቡድን አይሲስ በጭካኔ መገደላቸውን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በህገ ወጥ ደላሎች ላይ ጠበቅ ያለ ቁጥጥር ማድረግ ጀምሯል፡፡ መንግስት በወሰደው እርምጃ፣ በሱዳን ድንበር አካባቢ የሚንቀሳቀሱ 200 ያህል ህገወጥ ደላሎችና አዘዋዋሪዎችን ያሰረ ሲሆን ግማሽ ያህሉም በመተማ ከተማ የተያዙ ናቸው፡፡ ይህን እርምጃ ተከትሎ፣ በየቀኑ ወደ ሱዳን የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር ወደ 150 ያህል እንደደረሰ የዘገበው ዘ ጋርዲያን፣ አዘዋዋሪዎች ከመተማ በተጨማሪ ሌሎች ድንበር አካባቢዎችን እየመረጡ እንደሚገኙና ስደተኞችን ጫካ ለጫካ አልያም በበረሃ በእግርና በመኪና ማሸጋገር መቀጠላቸውን ጠቁሟል፡፡አንድ ስደተኛ በሱዳን በኩል አድርጎ ሊቢያ ለመግባትና ወደ አውሮፓ ለመሻገር በአማካይ 5 ሺህ ዶላር መክፈል ይጠበቅበታል ያለው ዘገባው፣ ክፍያው ከክልል ከተሞች አንስቶ ጉዞው በሚደረግባቸው የተለያዩ አካባቢዎች እንደሚከናወንና የስደተኞች ቤተሰቦችም ክፍያውን በሃዋላ ለአዘዋዋሪዎች እንደሚፈጽሙ ያትታል፡፡
የቅዳም ስሁር ዕለት ማለዳ...
በካርቱም መድሃኒያለም ቤተ ክርስቲያን ግቢ ወደተዋወቅኩት ወደ ደረጄ አመራሁ፡፡ በሱዳን ከ7 አመታት በላይ የኖረው ደረጀ፣ እሱ ራሱ ያለፈበት ነውና የስደቱን መስመር ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡ ደሬ እንዳጫወተኝ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ሱዳን የተዘረጋ የደላሎችና የህገወጥ አዘዋዋሪዎች ኔትወርክ አለ፡፡ በዚህ ረጅም ርቀት የሚሸፍን የስደት ጉዞ ውስጥ የሚሳተፉትና ሸቃባ ተብለው የሚጠሩት ህገወጥ አዘዋዋሪዎችና ደላሎች ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያንና ሱዳናውያን እንደሆኑም ነግሮኛል፡፡
እሱ እንደሚለው፣ ለቃሚ ተብለው በሚታወቁት በየክልልና ዞን እንዲሁም ወረዳ ከተሞች የሚገኙ ደላሎች አማካይነት ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚሰባሰቡት ስደተኞች በጎንደር በኩል አድርገው ወደ ሱዳን ለመግባት ሁለት አማራጮችን ይጠቀማሉ - በመተማ ወይም በሁመራ፡፡ በህገወጥ ደላሎችና አዘዋዋሪዎች መሪነት በበረሃና በጫካ ለቀናት በእግር ከተጓዙ በኋላ፣ ገላባት በተባለቺው የሱዳን የድንበር ከተማ ላይ ተሰባስበው፣ በጭነት መኪና ተሳፍረው ወደ ገዳሪፍ ጉዟቸውን ይቀጥላሉ፡፡ በአንድ ጭነት መኪና እስከ 400 ሰው ሊሳፈር ይችላል፡፡ አካባቢው ሞቃታማ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ፣ ጉዞው እጅግ ፈታኝ ነው፡፡ ብዙዎች በርሃብና በውሃ ጥም መንገድ ላይ ይቀራሉ፡፡ በዚህ መልኩ የሚጓዙ ስደተኞች፣ በገዳሪፍ በሚገኙና ስደተኞቸን ለማሳረፍና ለማሰባሰብ በተዘጋጁት መግዘን የሚባል ስፍራ አንድ ሁለት ቀን አርፈው፣ በሁለት አቅጣጫ ጉዟቸውን ይቀጥላሉ፡፡
አንደኛው ከገዳሪፍ በመደኔ እና በሶባ አድርገው አስር ቀናትን ከሚፈጅ አስቸጋሪ የበረሃ ጉዞ በኋላ ቀጥታ ካርቱም የሚያደርስ ሲሆን ሁለተኛው በአውቶብስ ተሳፍረው እያቆራረጡ ካርቱም የሚገቡበት ነው፡፡ ካርቱም ከደረሱ በኋላም፣ ኡምዱርማን ውስጥ በሚገኙ መግዘኖች ተሰባስበው፣ በሳሃራ በረሃ ፈታኝ ጉዞ አድርገው ከሁለት ቀን በኋላ ኩፍራ የምትባለው የሱዳን የድንበር ከተማ ይደርሳሉ፡፡
ኩፍራ ከደረሱ በኋላ አዘዋዋሪዎቹ ስደተኞችን ወደ ሊቢያ ለሚወስዷቸው ሌሎች ደላላዎች ያስረክቧቸዋል፡፡ አንድ ስደተኛ ወደ ሊቢያ ለሚደረገው ጉዞ ለአዲሶቹ ደላሎች እስከ 50 ሺህ ብር የሚደርስ ክፍያ መፈጸም እንደሚጠበቅበት አልጀዚራ በአንድ ወቅት አህመድ ከተባለው ታዋቂ ደላላ ጋር ያደረገውን ቃለመጠይቅ ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
ይህ የስደት ጉዞ፣ ሲናገሩትና ሲጽፉት እንጂ ሲሄዱት ቀላል አይደለም፡፡ ብዙ ፈተና፣ ብዙ መከራ፣ ብዙ ስቃይ አለበት...ስደተኞቹ በየደረሱበት ገንዘብ መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡ የያዙት ገንዘብ ሲያልቅ፣ አገር ቤት ከሚገኙ ዘመዶቻቸው ገንዘብ እያስመጡ ለአዘዋዋሪዎች ይከፍላሉ፡፡ መግዘን ውስጥ ለቆዩበት፣ በረሃውን ለማቋረጥ ለሚመራቸው ሰው፣ በጀልባ ለሚያሳፍራቸው ደላላ ወዘተ ሁሉ ገንዘብ ይከፍላሉ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ በሙቀት ይንገላታሉ፡፡ ርሃብና ውሃ ጥም ያሰቃያቸዋል፡፡ ሴቶች በደላሎች ይደፈራሉ፡፡ ይደበደባሉ፡፡
ከዚህ ሁሉ መከራ አምልጠው ካርቱም የደረሱም፣ ሌላ መከራ ይጠብቃቸዋል....ሱዳን ቪዥን ዴይሊ ድረገጽ በቅርቡ ያወጣው ዘገባ፣ በአገሪቱ መዲና ካርቱም ብቻ 2 ሚሊዮን የሚደርሱ ህገወጥ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንደሚገኙ አንድ የሱዳን ከፍተኛ የፖሊስ ሃላፊ ማስታወቃቸውን አስነብቧል፡፡
ከፍተኛ የህይወት መስዋዕትነትና ገንዘብ ከፍለው በህገወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው ሱዳን የሚገቡት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፣ ሱዳን ከገቡ በኋላም ሊቋቋሙት የሚቸግር ፈተና ይገጥማቸዋል፡፡ በኡምዱርማን ስጅን አል ሁዳ እስር ቤት ያገኘሁት ኑርሁሴን እንደነገረኝ...የካርቱም ፖሊስና ኢትዮጵያዊ ስደተኛ አይጥና ድመት ናቸው፡፡ በሚጣቃ /ጊዜያዊ የነዋሪነት መታወቂያ/ ሰበብ ብቻ፣ በመላ ሱዳን በሚገኙ አካባቢዎች በየቀኑ እስከ 60 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ይውላሉ፡፡ ሚጣቃ ይዘው ያልተገኙ ስደተኞች፣ እስከ 5000 የሱዳን ፓውንድ እንዲከፍሉ ይደረጉና ወደ አገራቸው ይመለሳሉ፡፡ የመክፈል አቅም የሌላቸውም ከ4 እስከ 6 ወር የሚደርስ እስር ይፈረድባቸዋል፡፡
ደረጀ እንዳጫወተኝ፣ አንድ የሱዳን ፖሊስ ኢትዮጵያዊ ስደተኛን ለማሰር ምክንያት አያጣም፡፡
ስደተኛው ሚጣቃ ይዞ ቢያገኘው እንኳን፣ ገንዘብ ካልሰጠኸኝ ብሎ ሚጣቃውን ተቀብሎ ይሰብርበትና፣ ህጋዊ አይደለህም ብሎ ወደ እስር ቤት ይወስደዋል፡፡
 ጫትና ሃሺሽም በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ ወህኒ የሚያስወረውሩ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ደረጀ እንደነገረኝ ከሆነ፣ በካርቱም ጫት የተጠቀሙ ብቻ ሳይሆኑ ቤታቸው ውስጥ የተገኘባቸው በርካቶች እስከ አስር አመት የሚደርስ እስር ተፈርዶባቸው በእስር ቤት ይገኛሉ፡፡
ካርቱምን ልለያት ነው...ነገ ወደ አገሬ ልመለስ ነው...ዛሬ ከማለቋ በፊት አንድ ነገር ማድረግ ይጠበቅብኛል፡፡
 ካርቱም ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሄጄ፣ በእስር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ የሚለውን ነገር ማጣራት አለብኝ...
ባረፍኩበት ሆቴል ስልክ፣ ካርቱም ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ደወልኩ...
ከተደጋጋሚ ሙከራ በኋላ፣ አንድ ሰው ስልኩን አነሳው...
“በካርቱም በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በሚመለከት መረጃ ለማግኘት ፈልጌ ነበር?...” ስል ጠየቅኩት፡፡
ስልኩን ያነሳው ሰው፣ የኤምባሲው የጥበቃ ሠራተኛ መሆኑን በመግለጽ፣ ስለምለው ነገር መረጃ ሊሰጠኝ እንደማይችል ነገረኝ፡፡
የሚመለከተውን አካል አግኝቼ ለማነጋገር ስለምፈልግ፣ ኤምባሲው የት አካባቢ እንደሚገኝ እንዲጠቁመኝ ጠየቅሁት፡፡
“ዛሬ’ኮ ስራ የለም፤ አመት በዓል ነው!...” ሲል መለሰልኝ፡፡
የኔ ነገር!...ለካ ዕለቱ አመት በኣል ነበር!?...
እውነቱን ነው - ዛሬ በእኛ አገርና በኛ ኤምባሲ ትንሳኤ ነው!...
በኡምዱርማን ስጅን አል ሁዳ እና በደበክስ፣ ዛሬ ትንሳኤ ነው!?...
በእስር ለሚማቅቁት ለእነ ኑርሁሴንስ፣ የመከራ ቀንበር ተሰብሮ ትንሳኤ የሚሆንበት ቀን መቼ ይሆን ?...
የሱዳኑ ጓዴ ደረጀ፣ እኩለ ቀን ላይ ወዳረፍኩበት ሆቴል መጣ...
“እኔ እያለሁማ፣ ፋሲካን በካርቱም ፉል አትቀበለውም!...” በማለት ወደ ቤቱ ወሰደኝ...ባለቤቱ የናዝሬቷ ልጅ መሲ ያዘጋጀቺውን፣ ቤት ያፈራውን ቀይ ወጥና ቅቅል ጋበዘኝ...እየበላን...ከመተማ አንስቶ እስከ ሊቢያ ስለሚዘልቀው አስቸጋሪ የስደት ጉዞ ሲተርክልኝ ቆየ...
በስተመጨረሻም... እኔ ራሴ ወደ ሊቢያ ለመሻገር የምፈልግ ስደተኛ መስዬ፣ ከደላሎች ጋር በመገናኘት ሁኔታውን ማጣራት እንደምችል ነገረኝ... በካርቱም ከሚታወቁት ቀንደኛ ደላሎች አንዱን እንደሚግባባውና ሊያገናኘኝ እንደሚችል ቃል ገባልኝ...አሁኑኑ አድርገው አልኩት...
ሰኢድ የሚባለው ኢትዮጵያዊ ደላላ ወደሚገኝበት ሰፈር አቀናን...ከብዙ ፍለጋ በኋላ...ሰኢድ አንዲት አነስተኛ የሽቶ መሸጫ መደብር ውስጥ እንደሚገኝ መረጃ አገኘን...ሰው ላክንበት...ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ፣ ከመደብሯ በስተጀርባ አንድ ከሲታ ራሰ በራ ወጣት ብቅ አለ - ታዋቂው ደላላ ሰኢድ ነው!...
ከደረጄ ጋር ሰላምታ ተለዋወጡ... እኔንም በጥርጣሬ አይን እያየኝ፣ እንደዋዛ ሰላም አለኝ...ሁለቱ በአረብኛ ሲያወሩ፣ በጥሞና እከታተላቸው ያዝኩ...ሰኢድ ዘወር ብሎ ተመለከተኝ - አይኖቹ ላይ ጥርጣሬ ይነበባል...
ከደረጄ ጋር ማውራታቸውን ቀጠሉ... ስለእኔ እንደሚያወሩ ገብቶኛል፡፡ ከደረጄ ጋር በተነጋገርነው መሰረት፣ ወደ ሊቢያ ለመሻገር ሁኔታዎችን እንዲያመቻችልኝ እየጠየቀው ነው፡፡
በመካከሉ ሰኢድ ድንገት ወደኔ ዘወር አለና ያልጠበቅኩትን ጥያቄ ወረወረልኝ...
“ለምን እስከ ካርቱም ያመጡህ ሰዎች አያሻግሩህም?...” በማለት፡፡
የምለውን አጥቼ ተቁለጨለጭኩ፡፡
“ስለተበላ እኮ ነው ወዳንተ ያመጣሁት!... አዲስ አበባ የሰፈሬ ልጅ ነው... ትንሽ ገንዘብ ልርዳውና አንተ ታሻግርልኛለህ ብዬ ነው ያመጣሁት...” አለና ጣልቃ ገብቶ ሊያስቀይስልኝ ሞከረ - ደረጄ፡፡ ሰኢድ መልስ አልሰጠውም... ሰረቅ አድርጎ አየኝና ወደ ደረጄ ዞረ... በአረብኛ የሆነ ነገር ነግሮት፣ በቆምንበት ትቶን በፍጥነት ሄደ... “ምንድን ነው ያለው?...” ስል ጠየቅኩት በጉጉት ደረጄን፡፡
“በሌላ ደላላ አማካይነት ወደ ሊቢያ ሊሻገሩ የተዘጋጁ ሌሎች ስደተኞች ስላሉ፣ ከእነሱ ጋር ሊልክህ እንደሚችልና፣ አብሮት የሚሰራውን ሌላ ደላላ አነጋግሮት እንደሚመጣ ነው የነገረኝ...” አለኝ - ደረጄ በጥርጣሬ አሻግሮ እያየው፡፡
ሰኢድ አልተመለሰም!...
ባንኖብናል!...
እኔ እንደ እነሱ አይደለሁም!...
እኔ በስደት በረሃ አቋርጠው ሄደው፣ በኡምዱርማን ስጅን አል ሁዳ ተቀብረው እንደቀሩት፣ መመለሻው እንደጠፋቸው የወንዜ ልጆች አይደለሁም!...
ዘና በአውሮፕላን እንደሄድኩ፣ ዘና ብዬ በአውሮፕላን ተመለስኩ!...
የወንዜን ልጆች እዚያው የበረሃ ስቃይ ውስጥ ትቼ፣ የድረሱልን ጥሪያቸውን ይዤ፣ በሰላም አገሬ ገባሁ...
ለጥሪያቸው መልስ ፍለጋ፣ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደወልኩ...
ይጠራል...
ይጠራል...
ይጠራል...
አይነሳም!...
.
በነጋታውም አይነሳም!...
.
በሌላኛው ስልኩም ሞከርኩ...
እሱም፣ ይጠራል እንጂ አይነሳም!...
.
አይነሳም!...
.
ምን ማድረግ እንዳለብኝ እያሰብኩ ነው...
እያሰብኩ...
በቅርቡ ለንባብ የበቃውን አዲስ አድማስ ጋዜጣ ገለጥሁ...
ባለፈው ወር መጀመሪያ ላይ ለህትመት በበቃው በዚሁ ጋዜጣ ላይ፣ በሱዳን እስር ቤቶች የሚማቅቁትን እነዚህን ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በተመለከተ የተሰራ ዘገባ አለ፡፡
ዘገባው ስለስደተኞቹ ሰቆቃ ይተርካል፡፡
በስተመጨረሻም...
ስለ ስደተኞቹ የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ፣ የሰጡትን ምላሽ ያስከትላል...
እንዲህ ይላል የቃል አቀባዩ ምላሽ...
“ሱዳን ውስጥ ታስረዋል ስለምትሏቸው ዜጎች መረጃው የለንም!...”
ቃል አቀባዩ ቀጠሉ...
“...ሆኖም መንግስትና ኢምባሲው ዜጎችን ችላ አይሉም!...”
.
ዜጎችን ችላ አይሉም የተባሉት መንግስትና ኢምባሲው፣ ከማንም ቀድመው ሊያውቁት የሚገባውንና ስለታሰሩት ዜጎች ስቃይ የሚያትተውን መረጃ፣ ከአንድ የግል ጋዜጣ ከሰሙ በኋላስ?...
ምን አድርገው ይሆን?...
ይሄን ለማወቅ ነበር ደጋግሜ ወደ ሚኒስቴሩ መደወሌ...
ለነገሩ...
ሚኒስቴሩ መረጃው ከደረሰው በኋላም ምንም እንዳላደረገላቸው፣ ከእስረኞቹ ምላሽ ቀድሜ ተረድቼያለሁ...
ምናልባት...
ከጋዜጣው ያገኘው መረጃ በቂ ሆኖ አላገኘው ይሆን?...
ግዴለም!...
ይሄው ተጨማሪ መረጃ ሰጥቼዋለሁ!...
ነው ይሄም አይበቃም?...

Read 3215 times