Tuesday, 24 May 2016 08:45

ጊፍት ሪል እስቴት የገነባውን የመኖሪያ መንደር ዛሬ ያስመርቃል

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

ጊፍት ሪል እስቴት በሲኤምሲና አያት አካባቢ ከሚያካሂዳቸው ሶስት የመኖሪያ መንደር ግንባታዎች አንደኛውን ሙሉ በሙሉ አጠናቆ ዛሬ በሚያካሂደው የምረቃ ስነስርዓት ለነዋሪዎቹ ያስረክባል።
ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለምረቃ የበቃው ይህ መንደር በ 16ሺህ 300 ስኴር ሜትር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን በውስጡ ያካተታቸው የ22 ቪላ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ከመንገድ፣ውሃ እና ኤሌክትሪክ ሃይል ዝርጋታ ጋር ተዳምሮ ከ132 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል።
የነዚህ መኖሪያ ቤቶች መጠናቀቅና ለደንበኞች መተላለፍ ሪል እስቴቱ እስካሁን ድረስ አጠናቆ ያስረከባቸውን ቤቶች ቁጥር 202 እንደሚያደርሰው ከጊፍት ግሩፕ ኩባንያ ህዝብ ግንኙነት መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ጊፍት ሪል እስቴት በሲኤምሲ እና ሃያት አካባቢ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ በሚያካሂድባቸው ቀሪ ሁለት መንደሮች ውስጥ በ2009 ዓ.ም 250 ተጨማሪ ቪላና አፓርትመንት ቤቶችን አጠናቆ ለደንበኞች ለማስረከብ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል። ከህዝብ ግንኙነት መምሪያው ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ጊፍት ሪል እስቴት በሲኤምሲ እና አያት አካባቢ ለሚያካሂደው የሪልእስቴት ልማት 16.3 ሄክታር መሬት ከመንግስት በሊዝ ተረክቧል።
በነዚህ አካባቢዎች በሶስት መንደሮች የሚያካሂዳቸው የግንባታ ፕሮጀክቶችም 1 ሺህ 300 ቪላና አፓርትመንት መኖሪያ ቤቶችን እንዲሁም የንግድና አገልግሎት ሰጪ ህንጻዎችን ያካተቱ ናቸው። የዚህ ግንባታ አጠቃላይ ወጪ ከ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚደርስ ሲሆን እስካሁን ከ1500 በላይ ለሆኑ ዜጎችም የስራ ዕድል ፈጥሯል።
የህዝብ ግንኙነት መምሪያው የዛሬውን ርክክብ አስመልክቶ ለሪልእስቴቱ ደንበኞች ባስተላለፈው መልክዕት፤ “የሪል እስቴት ዘርፉ ያሉበትን ችግሮች በመገንዘብ ደንበኞቻችን ላሳዩን ትዕግስትና ለሚያደርጉልን ያልተቆጠበ ድጋፍ በሪልእስቴቱ ስም የላቀ ምስጋና እናቀርባለን” ብሏል። “ጊፍት ሪል እስቴት ከደንበኞች ጋር የገባውን ውል ለማክበርና ፍላጎታቸውን ለማርካት ቁርጠኛ አቋም ይዞ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል” ሲልም ገልጿል፤ መምሪያው።በዛሬው የጊፍት ሪል እስቴት መንደር ቁጥር አንድ ምረቃ ስነስርዓት ላይ የከተማና ቤቶች ልማት ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የግንባታና ሪልእስቴት ዘርፍ አንቀሳቃሾች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙም ተገልጿል።ጊፍት ሪል እስቴት የቤቶች ልማት ዘርፍ ለማከናወን በ1998 ዓ.ም የተመሰረተ፣የዘመናዊ ቪላ፣ አፓርትመንት እና አገልግሎት ልማት በማከናወን ላይ የሚገኝ ሃገር በቀል ኩባንያ ነው።

Read 4272 times