Tuesday, 24 May 2016 08:47

በ600 ሚ. ብር ወጪ የተገዙ መድኀኒቶች ከአገልግሎት ውጪ ሆነዋል

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

 ለሆስፒታሎች  የመጡ መሣሪያዎች አገልግሎት የሚሰጡ አይደሉም
                 ከ2 ዓመት በፊት የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ኬሚካሎች እየተሸጡ ነው
                                    
    በመድኀኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ተገዝተው ወደ አገር ውስጥ የገቡና 600 ሚሊዮን ብር ገደማ ወጪ የተደረገባቸው መድኀኒቶች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው በመሆኑ ከአገልግሎት ውጪ እንደሆኑ የፌደራል ዋና ኦዲተር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰሞኑን ባቀረበው ሪፖርት ይፋ አደረገ፡፡
በኤጀንሲው በከፍተኛ ገንዘብ ተገዝተው ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ መድኃኒቶች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ሳያልፍ ለተገዛላቸው የጤና ተቋማት በማሰራጨት ሥራ ለይ ማዋል ቢገባም ይህ ሳይሆን በመቅረቱ ከጥቅም ውጪ ሆነው በዋናው መስሪያ ቤትና በቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች መጋዘኖች ውስጥ ተከማችተው እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡ እነዚህ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኀኒቶችና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች እንዲሁም ኬሚካሎች አገልግሎት ከሚሰጡ መድኀኒቶች ጋር አብረው በመጋዘኑ እንዲቀመጡ መደረጉንም ሪፖርቱ ገልጿል፡፡
በኤጀንሲው እየተገዙ በአገሪቱ ለሚገኙ የጤና ተቋማት እንዲከፋፈሉ የሚደረጉት ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ መሳሪያዎች፣ የመለዋወጫና የኬሚካል እጥረትና ችግር ያለባቸው በመሆኑ መሳሪያዎቹ አገልግሎት የማይሰጡ መሆኑንና መድኀኒቶችም በበቂ መጠን እየተከፋፈለ አለመሆኑን እንዲሁም የመጠቀሚያ ጊዜያቸው የተቀረበ መድኀኒቶችን እንደሚያከፋፍሉ ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡
የፌደራል ዋና ኦዲተር በናሙና ካያቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶች መካከል በትምሀርት መሳሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት፤ የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈና ለብዙ ዓመታት የተቀመጠ ብዛቱ አምስት ባለ 200 ሊትር የሆነ ናይትሪክ አሲድና ሌሎች ኬሚካሎች መኖራቸው መታወቁ ተገልጿል፡፡ በግብርና ምርት ማሳደጊያዎች አቅራቢ ድርጅት፤ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈ ኬሚካከሎች ለአርሶ አደሩ እየተሸጡ መሆኑንና ከ2 ዓመታት በፊት የአገልግሎት ዘመናቸው ያበቃ ኬሚካሎች በድርጅቱ ሳሪሳ ዳማ መጋዘን ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ልማት ማዕድን አ.ማ በካኦሊን ምርት ፈርጅ እና በቀንጢቻ ክሊኒኮች ውስጥ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ብዛት ያላቸው የተለያዩ መድኀኒቶች ተከማችተው እንደሚገኙም ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡   

Read 1144 times