Tuesday, 24 May 2016 08:51

የአዲስ አበባ ባቡርን የማዘመን ስራ እየተሰራ ነው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

በቀን እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር ገቢ እያስገባ ነው
    የአዲስ አበባ ባቡርን የማዘመን ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ የገለጸው የባቡር ኮርፖሬሽን፤ በአሁኑ ወቅት በ41 ባቡሮች በቀን ከ120ሺ እስከ 160ሺ ሰዎችን በማጓጓዝ ግማሽ ሚሊዮን ብር ገቢ እያስገባ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ለአቅመ ደካሞችና ለአካል ጉዳተኞች መወጣጫ ታስበው ከፍታ ባላቸው የባቡር ጣቢያዎች የተገጠሙ ስካሌተሮችና ሊፍቶች የደህንነታቸው አስተማማኝነት ተፈትሾ በቅርቡ ስራ ይጀምራሉ ያሉት የቀላል ባቡር ስራ አሥኪያጅ አቶ ሄኖክ ይልማ፤የወረቀት ቲኬትን የሚያስቀረው የኤሌክትሮኒክስ ቲኬትም የሙከራ ፍተሻዎች ተጠናቀው ወደ ስራ ይገባል ብለዋል፡፡   የኤሌክትሮኒክስ ካርዱን ለማስጀመር ከገንዘብ ዝውውርና ዳታ ሲስተም ጋር የተገናኙ ፍተሻዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ያስረዱት አቶ ሄኖክ፤የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማዘመን የግዴታ ኢ-ቲኬቱ አገልግሎት ላይ መዋል ስላለበት በቅርቡ እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡  በትኬት ሽያጭ የባቡር ኮርፖሬሽኑ አትራፊ እንደማይሆን የገለጹት ሥራ አሥኪያጁ፤ ትርፍ አግኝቶ ብድሩን ለመመለስ የማስታወቂያ ቦታዎችንና የገበያ ማዕከሎችን ለመገንባት የተያዘው እቅድ በጨረታ ሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ማስታወቂያዎች የሚደረጉት በባቡር ጣቢያዎች ብቻ ሳይሆን በባቡሩ የውስጥ አካላትም ጭምር ሲሆን ወንበሮች፣ የወንበር መደገፊያዎችና ብረቶች ለማስታወቂያ አገልግሎት እንደሚውሉ ያስታወቁት አቶ ሄኖክ፤ በባቡሩ የውስጥ አካላት ላይ ማስታወቂያ ለማስነገር የሚፈልጉ ድርጅቶች በጨረታው እየተሳተፉ ነው ብለዋል፡፡
በትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡ ላይ አሁንም የኤሌክትሪክ መቆራረጥ እየገጠመ መስተጓጎል የሚፈጠር ሲሆን ችግሩን ለመቅረፍ ጀነሬተሮች በግዢ ሂደት ላይ ናቸው ተብሏል፡፡ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እየተሻሻለ ቢሆንም አማራጭ ኃይል ሰጪ ጀነሬተሮች የግድ ያስፈልጉናል ያሉት አቶ ሄኖክ፤ የጀነሬተር ግዢው የዘገየበትን ምክንያት ተጠይቀውም፤ “የምንገዛው ጀነሬተር አቅራቢ ከሆኑ አለማቀፍ ድርጅቶች በመሆኑና አማራጮች በሚገባ መፈተሽ ስላለባቸው ነው” ብለዋል፡፡
በቅርቡ በባቡር ሀዲዱ ላይ ጎርፍ በመተኛት የባቡር እንቅስቃሴውን እያስተጓጎለ መሆኑን  አስመልክቶ የተጠየቁት ኃላፊው፤ ሲኤምሲ አካባቢ እንዲህ ያለው ችግር ማጋጠሙን ጠቅሰው ችግሩ የተፈጠረው የመንገድ ላይ ፍሳሽ ማስተናገጃ ቱቦዎች በመደፈናቸው በመሆኑ ከአዲስ አበባ መንገድ ትራንስፖርት ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመፍታት እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡  የባቡር አገልግሎት ሲጀምር ባቡሮች በየጣቢያዎቹ በየ6 ደቂቃው ይደርሱ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ከ15-20 ደቂቃ ያስጠብቃሉ፡፡ ይህ ለምን ሆነ ያልናቸው አቶ ሄኖክ፤“ቀደም ሲል የተወሰኑ ባቡሮች ብቻ ነበር የተመደቡት፤ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ፍላጎቶች እየታዩ 41ዱም ባቡሮች አገልግሎት እየሰጡ ናቸው፤የሚደርሱበት ደቂቃ መሻሻል ያልቻለው ሰዎች አጥሮችን እየዘለሉ ወደ ሃዲድ በመግባት አደጋዎች እየተፈጠሩ በመሆኑ፣ የባቡሮቹን ፍጥነት ለመግታት ተገድደን ነው” ብለዋል፡፡ አጥር እየዘለሉ ወደ ሃዲዱ በሚገቡ ግለሰቦች ክፉኛ ተቸግረናል ያሉት አቶ ሄኖክ፤“ህብረተሰቡ ቅጣት እንዳለው ሊገነዘብ ይገባል፤ከምንም በላይ ደግሞ ለህይወቱ ዋጋ መስጠት አለበት” ሲሉ አሳስበዋል፡፡  

Read 1611 times