Tuesday, 24 May 2016 08:53

አለም አቀፍ የአዋላጅ ነርሶች ቀን

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

24ኛው አለምአቀፍ የአዋላጅ ነርሶች ቀን ሜይ 5/2016 በመላው አለም የተከበረ ሲሆን በኢትዮጵያ ደግሞ ባለፈው ሳምንት አርብ ተከብሮ ውሎአል። ይህ በአል በአዲስ አበባ ሃርመኒ ሆል ሲከበር ከየክልሉ የተወከሉ አዋላጅ ነርሶች በበአሉ ላይ ተገኝተው ነበር። አለም አቀፉ የአዋላጅ ነርሶች (Midwifery) ቀን ሲከበር የነበረው መሪ ቃልም ሴቶችና ጨቅላ ሕጻናት የአዋላጅ ነርሶች ከምንም በላይ የሚያስቡዋቸውና የሚጨነቁላቸው (Women and Newborns: The Heart of Midwifery) የሚል ነው። በእለቱ የተለያዩ ጥናታዊ ስራዎች ቀርበዋል። ለዚህ እትም ለንባብ ያልነው በሁለተኛው ቀን ማለትም በፈረንጆቹ አቆጣጠር ሜይ 14/2016 የኢትዮጵያ አዋላጅ ነርሶች ማህበር ሌሎች ተመሳሳይ ማህበራትን ጋብዞ በእናቶች እና ጨቅላ ሕጻናት ጉዳይ ላይ አብረን እንስራ የሚል የጋራ የውይይት መድረክ ፈጥረው ነበር።
ተጋባዦቹ ማህበራትም የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር እና የኢትዮጵያ የሕጻናት ሐኪሞች ማህበር ሲሆኑ ሶስተኛው ማለትም የኢትዮጵያ አዋላጅ ነርሶች ማህበር ነው። የኢትዮጵያ አዋላጅ ነርሶች ማህበር ስለማህበሩ አሰራር ገለጻ አድርገዋል። በዚህም ቀን የተለያዩ አጋር ድርጅቶች በውይይቱ ላይ የተገኙ ሲሆን እርሱም ከጄፓይጎ፣ ሴቭ ዘ ችልድረን እና ሌሎችም ነበሩ። በበአሉ ላይ የተገኙ አዋላጅ ነርሶች የየራሳቸውን አስተያየት ሰጥተዋል። ሃሳባቸው በጋራ የሚከተለውን ይመስላል።
በስብሰባው ላይ የተገኙት አዋላጅ ነርሶች ያነሱዋቸው ሀሳቦች የሚመሳሰሉባቸው ነጥቦች ሲኖሩ እነርሱም በአብዛኛው በስራ ላይ ተገፋፍቶ መተላለፍ እንደሚኖርና ለአዋላጅ ነርሶቹ የሚሰ ጣቸው ግምት ዝቅተኛ እንደሆነ ነው። እንዲያውም ብዙውን ጊዜ እንደአላዋቂ እንደሚቆጠሩና ምናልባትም ከነባሮቹ አዋላጅ ነርሶች ይልቅ ሙያውን በተለየ ለመሰልጠን ለሚገቡ ተማሪ ዶክ ተሮች ቅድሚያ እንደሚሰጥ ተናግረዋል። አንዳንድ ጊዜ አንዲት እናት በሐኪም የምትታይበት አጋጣሚ እንኩዋን ቢኖር ሐኪሞች በአዋላጅ ነርሶች ከሚነገራቸው ይልቅ በተማሪ ሐኪሞች እንዲነገራቸው የሚመርጡበት አጋጣሚ ሁሉ እንደሚስተዋል ገልጸዋል። በእርግጥ አንዳንድ ሐኪሞች አዋላጅ ነርሶቹ ይህንን ቢያውቁ እርዳታው መልሶ ለሐኪሙም ጭምር ነው በማለት በእያንዳንዱ ሁኔታ የሚያሰለጥኑም ስላሉ ሊመሰገኑ ይባቸዋል የሚል ምስክርነትም ሰጥተዋል። ስለዚህም ሁሉም የሚሰራው ለጋራ አላማ ማለትም እናቶችን እና ጨቅላዎቹን ለማዳን እስከሆነ ድረስ የኢትዮጵ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር፣ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር እና የአዋላጅ ነርሶች ማህበር በጋር የሚሰሩበትን መድረክ መፍጠራቸው ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አዋላጅ ነርሶች ማህበር ተጠባባቂ ኡግዚኪዩቲቭ ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ኃይሉ ስለማህበሩ የስራ እንቅስቃሴ ከተናገሩት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል። የኢትዮጵያ አዋላጅ ነርሶች ማህበር አራት የትኩረት አቅጣጫዎች አሉት። እነርሱም፡- Capacity building’ Partnership and networking ‘Advocacy and representation’ Research and publication ናቸው። እነዚህ የትኩረት አቅጣጫዎች አቅምን የመገንባት፣ በትብብርና በቅንጅት ከሌሎች ጋር መስራት እንዲሁም ለሌሎች እገዛ ማድረግ እና እንዲሁም አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ምርምርና ህትመትን ማድረግ የሚሉትን በአጠቃላይ የያዘ ነው። ወደስራ ሲተረጎም የመጀመሪያው አቅጣጫው የአባላቱን ሙያ ማጠናከር ሲሆን ሌላው ደግሞ በትምህርት ላይ መስራት ነው። ይኼውም ከዩኒቨርሲቲዎችና የጤና ኮሌጆች ጋር በቅርበት መስራትን የሚመለከት ሲሆን በዩኒቨርሲቲዎቹ መደበኛ ትምህርት የሚሰጡ መምህራንን እውቀት በማጎልበት ረገድ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ስልጠናን መስጠት የኢትዮጵያ አዋላጅ ነርሶች ማህበር በትኩረት ከሚሰራቸው መካከል ነው። ሌላው ማህበሩ በትኩረት የሚሰራው ከጤና ጥበቃ ሚኒስር ጋር እና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ከአዋላጅ ነርሶች ስነምግባር ጋር እንዲሁም የሚጠበ ቅባቸውን ትክክለኛ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችላቸውን መመሪያና ደንብ መቅረጽ ነው። የማህበሩ ራእይ አንዲት እናት እና ጨቅላ ሕጻናት እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው የሚያስፈልጋቸውን አገልግሎት ከአዋላጅ ነርሶች እንዲያገኙ ማድረግ ነው። ባጠቃላይም የኢትዮጵያ አዋላጅ ነርሶች ማህበር አቅምን በመገንባት ረገድ የአዋላጅ ነርሶችን ትምህርት ለማጠናከርና በጥራት እንዲሰጥ ለማድረግ እና የአዋላጅ ነርሶች ልምዳቸውን በማካፈል ረገድ የሚኖራቸውን ሚና እንዲሁም የለውጥ ወኪል እንዲሆኑ ማስቻል እንዲሁም የአዋላጅ ነርሶችን ሙያዊ ብቃት ማሳደግና የተሻሻለ የጤና አገልግሎት እንዲሰጡ ማብቃት የሚሉና ሌሎችንም የስራ ድርሻዎች ለመወጣት ማህበሩ በትጋት እየሰራ መሆኑን አቶ ዳዊት ኃይሉ የአዋላጅ ነርሶች ማህበር ተጠባባቂ ዳይሬክተር አብራርተዋል። እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ሜይ 14/2016/ ተደርጎ በነበረው ስብሰባ አንዱ ትኩረት የነበረው የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር እንዲሁም የሕጻናት ሐኪሞች ማህበር እና የአዋላጅ ነርሶች ማህበር የእናቶችንና ጨቅላ ሕጻናቱን ጤንነት በሚመለከት በጋር መስራት የሚገባቸው በመሆኑ ህብረት እንዲፈጥሩ ለማድረግ የታለመ በመሆኑ የማህበራቱ ተወካዮች የየበኩላቸወን ሀሳብ ሰንዝረዋል። የኢትጵያ ሕጻናት ሐኪሞች ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዕጸገነት የሚከተለውን ብለዋል። “ብዙ ጊዜ አንድ የምታዘበው ነገር አለ። የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች እንዲሁም የህጻናት ሐኪሞችና አዋላጅ ነርሶች አብረው የሚሰሩበት ሁኔታ እጅግ የጠበበ ነው። ነገር ግን እኔ ተማሪ በነበርኩበትና እንደአሁኑ ብዙ ሐኪሞች ባልነበሩበት ጊዜ የማህጸንን ብዙ ነገር የተማርኩት ከአዋላጅ ነርሶች በመሆኑ ከፍ ያለ አድናቆት አለኝ። ነገር ግን አሁን እንደሚታየው ከሆነ በመሀል ክፍተት አለ። ስለዚህ አንድን ነገር ለመስራት ምን ያስፈልጋል በሚባልበት ጊዜ አስቀድሞ ክፍተቱን መዝጋት ያስፈልጋል። የዚህ አስፈላጊነት ደግሞ እናትና ሕጻን ምንጊዜም የማይለያዩ መሆናቸው ነው። ሕጻኑ መጀመሪያ ሲወለድ የሚገባው ከሕጻን ሐኪም እጅ ጋ ሳይሆን ከአዋላጅ ነርስ እጅ ነው። አንዲት እናት በምትወልድበት ጊዜ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነገር ካልገጠመ በስተቀር የምትወልደው በአዋላጅ ነርስዋ እጅ ነው። ከዚያ በሁዋላ እገዛ የሚያስፈልጋቸው ነገሮች ላይ የማህጸን ሐኪሙም የሕጻን ሐኪሙም የወለደችውንና የተወለደውን ይመለከታሉ። ጤንነትንም ያረጋግጣሉ። ስለዚህ የአዋላጅ ነርሶች የስራ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ማንም ሊክድ አይችልም። ስለዚህም ሁላችንም በአንድ አይነት አስተሳሰብ በጋራ አብረን የምንሰራበት መንገድ ቢኖር እናትየውንም ሆነ ጨቅላ ሕጻኑን በሚገባ ልንታደገው እንችላለን። ካለበለዚያ ግን ይህ የእኔ ኃላፊነት ነው ...ይህ የእኔ ኃላፊነት አይደለም የሚል ነገር ከመጣ በመሀል ላይ ክፍተት ይፈጠራል። የኢትዮጵያ የህጻናት ሐኪሞች ማህበር የእናቶችንና የጨቅላ ሕጻናቱን ጤንነት ለመጠበቅና ሞትን ለመቀነስ የሚያስችለውን አሰራር ከአዋላጅ ነርሶች ማህበርና ከኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን መግለጽ እወዳለሁ። ” ብለዋል።
የኢትጵያ ጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ምክትል ፕርዝዳንት ዶ/ር ባልካቸው ንጋቱ በበኩላቸው በትምህርት ዘመናቸው ከአዋላጅ ነርሶች ያገኙትን የእውቀት ማዳበርና ልምድ ማካፈልን እንደሚያደንቁና ባለሙያዎቹንም እንደሚያከብሩ ገልጸው በጋራ ለመስራት የተነሳውን ሀሳብ ያመነጨውንም ባለሙያ አመስግነዋል። ምክንያቱም ሶስቱ እህት ማህበራት አብረው በአስፈላጊ ጉዳዮች ላይ ሁሉ መስራታቸው ይበልጥ የእናቶችንና ጨቅላ ሕጻናቱን ጤንነት ለመጠበቅ ያስችላልና ነው። ይህ ቀጣይነት ያለውን ሕይወት ማለትም እናት... ልጅ ...እያለ የማይቋረጥ ግንኙነትን በጋራ እንደየድርሻው በመመካከር መመልከት ቀጣይነት ሊኖረው የሚገባ በጋር መስራቱንም ጥያቄ ውስጥ የማይከት ነገር ነው። አንዱ ያላንዱ መኖር አይችልም። ስለሆነም ከመውለድ በፊት ጀምሮ እስከ ከወሊድ በሁዋላ ብዙ በጋራ የሚሰሩ ስራዎች እንደሚኖሩ ግልጽ ነው። ምናልባትም እስከአሁን ድረስ አብረን አለመስራታችን ያስከተለው ችግር እንኩዋን ቢኖር ወደፊት እንዳይደገም ማድረግ ከኛ ይጠበቃል። ይህንን ለመወጣት ደግሞ ቁጭ ብሎ አስቦ ጽፎ ድጋፍ ለሚያደርግ አካል ማቅረብ ይገባል። ስለዚህ ይህንን ካደረግን ልንሰራ የምንችልባቸው መድረኮች ብዙ ናቸው። “ ከጤና ጥበቃ ሚኒስር ተወክለው የመጡት ዶ/ር ያሬድ ታደሰ በኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስር የእናቶችና ሕጻናት እንዲሁም ስርአተ ምግብ ዳሬክቶሬት የሕጻናት ጤና ኬዝ ቲም አባል በስብሰባው ላይ የሚከተለውን ማጠቃለያ ሰጥተዋል።
“ማህበራቱ እስከአሁን ድረስ ለስራው ያደረጉት ጥረትና የሰሩት ስራ ከፍተኛ መሆኑ እሙን ነው። ነገር ግን ጥምረቱም ይበልጥ አስፈላጊ መሆኑ አይካድም። የጨቅላ ሕጻን ክብካቤ የሚጀምረው ከእርግዝናው ጊዜ ጀምሮ ነው። ጤናማ ሕጻን የሚገኘው ጤናማ እናት ስትኖር ነው። እንዲያውም ጥምረቱ አሁን እዚህ የተገኛችሁት ብቻ ሳትሆኑ ሌሎችም የህክምና ባለሙያዎች ማህበራት ተጨምረው የየራሳቸውን ድርሻ የሚወጡበት መንገድ ቢዘጋጅ ጥሩ ይሆናል። የመጀመሪያ ማህበራቱ በስራቸው ሰፊ የሆነ የጤና ሰራዊት እንዳላቸው ግልጽ ነው። ስለዚህም ማህበራቱ ይህንን ኃላፊነት ሲወስዱ ለሚወክሉዋቸው የጤና ሰራዊት አባላት ልምዳቸውን እንደሚያካፍሉ አይካድም። አንዱ ትልቁ አጀንዳ የጤና ሽፋኑን ጥራት ባለው ሁኔታ ማዳረስ ነው። ስለዚህም ጥራትን ለማሳካት እና የተሻለ ደረጃ ለማዳረስ የሙያ ማህበራቱ በቅንጅት መስራታቸው ጠቀሜታው የጎላ ነው። ስለሆነም ያለንን ኃይል አሰባስበን ለዚህ ለታመነለት ለጨቅላ ሕጻናትና ለእናቶች ጤንነት ፍትሀዊ የሆነች ኢትዮጵያ እንድትኖረን መልካም ስኬት ለሁላችንም እላለሁ። ”ብለዋል።

Read 1853 times