Saturday, 28 May 2016 09:18

ኢትዮጵያ በ31ኛው ኦሎምፒያድ ላይ…

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(6 votes)

በአትሌቲክስ እና ብስክሌት እስከ 34 ኦሎምፒያኖች ማሰለፍ ትችላለች፡፡
 60 እጩ ኦሎምፒያኖች በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡
 4 ወርቅ፣ 4 ብርና 4 ነሐስ በድምሩ 12 ሜዳሊያዎች በኦሎምፒክ ኮሚቴ ታቅዷል፡፡
 3 ወርቅ፤3 ብርና 2 ነሐስ በአጠቃላይ 8 የኦሎምፒክ ሜዳልያዎች ተተንብዮላታል፡፡
 የማራቶን ኦሎምፒያኖች ምርጫ ላይ ብዙ ቅሬታዎች ተፈጥረዋል፡፡
የብራዚሏ ዋና ከተማ ሪዮ ዲጄነሮ ለምታስተናግደው 31ኛው ኦሎምፒያድ 70 ቀናት የቀሩ ሲሆን
206 አገራትን የወከሉ ከ1500 በላይ አትሌቶች በ28 የስፖርት አይነቶች የሚሳተፉበት ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ የተሳትፎ ታሪኳ ለ13ኛ ጊዜ በምትካፈልበት 31ኛው ኦሎምፒያድ በሁለት
የስፖርት አይነቶች በአትሌቲክስ እና ብስክሌት ውድድሮች እስከ 34 ኦሎምፒያኖችን ማሰለፍ
ትችላለች፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከ2 ሳምንት በፊት በ31ኛው ኦሎምፒያድ  በአትሌቲክስ
ውድድሮች የሚሳተፉ ኦሎምፒያኖችን ለመምረጥ በዝግጅት እና በልምምድ የሚቆዩ እጩ
አትሌቶችን ዝርዝር በማስታወቅ  በሆቴል አስቀምጦ ክትትል ማድረጉን ቀጥሏል፡፡ ከዚህ በታች
የቀረበው  በየውድድር አይነቶቹ ዝግጅታቸውን የጀመሩ 60 እጩ አትሌቶች ዝርዝር ሲሆን  በሚቀጠሉት ሳምንታት ከሚከናወኑ ልምምዶችና ዝግጅቶች በኋላ  ወቅታዊ ብቃቶቻቸውን በመንተራስ እና በሌሎች መስፈርቶች  በሪዮ ኦሎምፒክ  ኢትዮጵያን  የሚወክሉት ኦሎምፒያኖች ተለይተው ይታወቃሉ፡፡  በወንዶች አትሌቲክስ በስድስት ውድድሮች ማለትም በ800 ሜ 1፤ በ1500 3፤ በ5ሺ ሜ 3 ፤ በ10ሺሜ 3፤ በ3ሺ መሰናክል 3 እንዲሁም በማራቶን 3 አትሌቶችን እንዲሁም በሴቶች አትሌቲክስ በ800 ሜ 1፤ በ1500 3፤ በ5ሺ ሜ 3 ፤ በ10ሺሜ 3፤ በ3ሺ መሰናክል 3፤ በ20 ኪ ሜ ርምጃ 1 እንዲሁም በማራቶን 3 አትሌቶችን በአጠቃላይ 33 ኦሎምፒያኖችን የምታሳትፈበት ኮታ አላት፡፡ በተያያዘ በሪዮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ   ከ1992 በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በወንድ ብስክሌተኛ የምትሳተፍ ሲሆን በኦሎምፒክ የብስክሌት ጎዳና ላይ ውድድር ኢትዮጵያን ለመወከል የሚበቃው የብስክሌት ኦሎምፒያን ፅጋቡ ግርማይ ነው፡፡ ብስክሌተኛው የኦሎምፒክ ተሳትፎውን ያገኘው በ2015 የአፍሪካ ሻምፒዮንሺፕ በሁለተኛ ደረጃ
ባስመዘገበው ሚኒማው ይሆናል፡፡ በወንዶች 10 ሺህ ሜትር- ቀነኒሳ በቀለ፤ ታሪኩ በቀለ ፤ ሙክታር እድሪስ፤  ኢማና መርጊያ፤  ሞሰነት ገረመው፤ አዱኛ ታከለ ፤ ፀበሉ ዘውዴ ፤ ታምራት ቶላ ፤ሙሴ ዋሲሁን ፤ይገረም ደመላሽ፤  ኢብራሒም ጀይላና  ፤ብርሃኑ ለገሰ
በሴቶች 10 ሺህ ሜትር- ጥሩነሽ ዲባባ ፤ ገለቴ ቡርቃ፤ በላይነሽ ኦልጅራ፤ ዓለሚቱ ሃሮዬ፤ ነፃነት
ጉደታና ጐይተቶም ገ/ስላሴበወንዶች 5ሺህ ሜትር-  ያሲን ሃጂ ፤ዮሚፍ ቀልጀልቻ፤ ሐጎስ ገብረሕይወት፤ ጌታነህ ሞላ፤ ደጀን
ገብረመስቀል፤ የኔው አላምረውና ልዑል ገብረ ሥላሴ
በሴቶች 5ሺ ሜትር- አልማዝ አያና ፤ሰንበሬ ተፈሪ ፤ገንዘቤ ዲባባ፤ መሠረት ደፋር፤ ዓለሚቱ ሐዊና
ሐብታምነሽ ተስፋዬበወንዶች 1500 ሜትር- አማን ወጤ ፤ዳዊት ወልዴ፤ አማን ቃዲ ፤በቀለ ጉተማና መኮንን ገብረመድህን በሴቶች1500 ሜትር -ዳዊት ስዩም ፤ጉደፋይ ፀጋዬ፤ ባሶ ጎዶና አክሱማዊት አምባዬ
በወንዶች 800 ሜትር- መሐመድ አማን፤ ጃና ኡመር ፤ማሞሻ ሌንጮና ዮብሷን ግርማ
በሴቶች 800 ሜትር -ትዕግስት አሰፋ፤ ሃብታም ዓለም፤ ጫልቱ ሹሜና  ሊዲያ መለስ
በወንዶች 3 ሺህ ሜትር መሰናክል   አምሳሉ በላይ ፤ኃይለ ማርያም፤ አማረ ታደሰ፤ ሰቦቃ ጫላ፤
ባዩ ጅግሳ፤ ቶሎሳ ጌትነት ….
በሴቶች 3 ሺህ ሜትር መሰናክል-   ትዕግሥት ታማኙ ማህሌት ፍቅሬየርምጃ ውድድር ተካፋይ ሴቶች- ዓናለም እሸቱ፤ አስካለ ቲክስ ፤የኃልዩ በለጠውና አያልነሽ በለጠውየሜዳልያ ትንበያዎች እየወጡ ናቸው፤ ለኢትዮጵያም ተገምቷልከ31ኛው ኦሎምፒያድ በፊት በ12 ኦሎምፒያዶች ለመሳተፍ የበቃችው ኢትዮጵያ  21 የወርቅ፤ 7 የብር እና 17 የነሐስ በአጠቃላይ 45 ሜዳልያዎችን ሰብስባለች፡፡ ኢትዮጵያ  4 የወርቅ፣ 4 የብርና 4 የነሐስ በድምሩ 12 ሜዳሊያዎች ለማምጣት እንደምታቅድ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያስታወቀው ከወር በፊት ነው፡፡
በሪዮ ኦሎምፒክ አገራት ስለሚያስመዘግቧቸው የሜዳልያ ብዛቶች የሚተነብዩ በርካታ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ፡፡  የሜዳልያ ትንበያዎቹ በተለያዩ የስፖርት፤ የኢኮኖሚ፤ የመገናኛ ብዙሃናት እና ሌሎች ምሁራን በሚሰሩ ስሌቶች እና ቀመሮች የሚዘጋጁ ናቸው፡፡  የአገራትን የኢኮኖሚ ደረጃ እና ሌሎች ሁኔታዎችን በማገናዘብ፤ ባለፉት የኦሎምፒክ ውጤቶች በመንተራስ፤ እስከ ኦሎምፒክ በሚካሄዱ ትትልልቅ ውድድሮች የተመዘገበ ስኬትን በማስላት የሚሰሩ ትንበያዎች እና የውጤት ማመላከቻዎች ናቸው፡፡  በብዙ የኦሎምፒክ ሜዳልያ ትንበያዎች በ31ኛው ኦሎምፒያድ የሜዳልያ ሰንጠረዡን በአንደኝነት እንደምትጨርስ የተገመተላት  አገር አሜሪካ ናት፡፡ የቅርብ ተፎካካሪ
የምትሆነውና እንደውም በአንዳንድ ትንበያዎች መሪነቱን ልትወስድ እንደምትችል ግምት
የምታገኘው አገር ደግሞ ቻይና ሆናለች፡፡ የሜዳልያ ትንበያቸውን ይፋ ካደረጉት ተቋማት መካከል
ኢንፎስትራዳ፤ ቤንች ማርክ አናሊስስ፤ ግሬስ ኖት እንዲሁም ኦሎምፒክ ፕሪዲክሽን የተባሉት
ይገኙበታል፡፡
ኢንፎስትራዳ የተባለው የስፖርት መረጃዎች አዘጋጅ ተቋም በሰራው ትንበያ አሜሪካ 42 የወርቅ
በአጠቃላይ  102 ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ አንደኛ ደረጃ እንደሚኖራት ተገምቷል፡፡  ቻይና 31
የወርቅ በአጠቃላይ   78 ሜዳልያዎችን እንዲሁም  ራሽያ 22 የወርቅ በአጠቃላይ  66
ሜዳልያዎችን በማግኘት በተከታታይ ደረጃ እንደሚጨርሱ ተገምቷል፡፡ ቤንች ማርክ አናሊስስ የተባለ ተቋም ይፋ ባደረገው የትንበያ ሪፖርት ደግሞ ቻይና 39 የወርቅ ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ አንደኛ ደረጃን እንደምትወስድ ሲተነበይ፤ አሜሪካ 35 እንዲሁም ራሽያ 24 የወርቅ ሜዳልያዎችን እንደሚያሳኩ ተገልጿል፡፡ ሉችያኖ ባራ የተባለ ጣሊያናዊ የቀድሞ የኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል በሚያንቀሳቅሰው የሜዳልያ ፕሮጀክት ቻይና በአጠቃላይ 94 የኦሎምፒክ ሜዳልያዎችን በመውሰድ 82 የኦሎምፒክ ሜዳልያ የምትወስደውን አሜሪካ በመብለጥ መሪነቱን ትወስዳለች፡፡ ራሽያ ፤ ጀርመን፤ ጃፓን  እንዲሁም አውስትራሊያ በሜዳልያ ተከታታይ ደረጃዎችን ሊያገኙ ይችላሉ፡፡በሌላ በኩል ኦሎምፒክ ፕሪዲክሽን የተባለ ድረገፅ በሰራው ትንበያ  አሜሪካ  39 የወርቅ፤ 19
የብርና 29 የነሐስ ሜዳልያዎች በአጠቃላይ 87 የኦሎምፒክ ሜዳልያዎችን በ31ኛው ኦሎምፒያድ  በመሰብሰብ  አንደኛ ደረጃ እንደምትወስድ ሲተነበይላት፤ ቻይና  27 የወርቅ፤ 31 የብርና 15 የነሐስ ሜዳልያዎች በአጠቃላይ 73 የኦሎምፒክ ሜዳልያዎች  እንዲሁም ታላቋ ብሪታንያ  22 የወርቅ፤ 20
የብርና 16 የነሐስ ሜዳልያዎች በአጠቃላይ 58 የኦሎምፒክ ሜዳልያዎች  በመሰብሰብ ሁለተኛ እና
ሶስተኛ ደረጃ እንደሚያገኙ ተገምቶላቸዋል፡፡ኦሎምፒክ ፕሪዲክሽን የሜዳልያ ትንበያውን የሰራው
በወቅታዊ ውጤቶች፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ ትልልቅ ውድድሮች የዓለም ኻምፒዮና እና
ሌሎችን በማገናዘብ እንደሆነ ገልጿል፡፡ በዚሁ የኦሎምፒክፕሪዲክሽን ድረገፅ ኢትዮጵያ 3 የወርቅ፤
3 የብርና 2 የነሐስ ሜዳልያዎች በአጠቃላይ 8 የኦሎምፒክ ሜዳልያዎች  እንደምትሰበሰብ  
የተገመተ ሲሆን ከዓለም 26ኛ ደረጃ አሰጥቷታል፡፡ በአንፃሩ  በሜዳልያ ስብስቧ ከዓለም 12ኛ ደረጃ
እንደሚኖራት የተተነበየላት የቅርብ ተቀናቃኝ የሆነችው ኬንያ  ስትሆን በኦሎምፒክፕሪድክሽን
መሰረት በ31ኛው ኦሎምፒያድ  ከኢትዮጵያ በእጥፍየላቀ ውጤት እንደሚኖራት ተመልክቷል፡፡
በኦሎምፒክ ፕሪዲክሽን መሰረት ኬንያ 7 የወርቅ፤ 6 የብርና 3 የነሐስ ሜዳልያዎች በአጠቃላይ 16
የኦሎምፒክ ሜዳልያዎች እንደምትሰበሰብ ተገምቷል፡፡
ያወዛገበው የማራቶን ኦሎምፒያኖች ምርጫ
በ31ኛው ኦሎምፒያድ ኢትዮጵያን በመወከል የሚሳተፉ ኦሎምፒያኖች ሙሉ ዝርዝር  ይፋ አልሆነም፡፡ ሰሞኑን በሪዮ ዲጄኔሮው 31ኛው ኦሎምፒያድ የኢትዮጵያ ተሳትፎ የመጀመርያው ቡድን  ጊዜያዊ ዝርዝር የተገለፀ  ሲሆን በማራቶን በሁለቱም ፆታዎች 6 ኦሎምፒያኖች እና ተጠባባቂ አትሌቶችን ያካተተ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በማራቶን ቡድኑ በምርጫ መስፈርቶቹ እና በአስፈላጊው ሚኒማ መሰረት  በሁለቱም ፆታዎች 11 ማራቶኒስቶች በኦሎምፒክ ማራቶን ቡድኑ  በማካተት ከሳምንት በፊት ስም ዝርዝራቸውን በማሳወቅ ለዝግጅት ጠርቷቸዋል፡፡  የማራቶን አትሌቶች ምርጫ ውጤት ጊዜያዊ ማጠቃለያ ዝርዝር በማለት አትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት በኦሎምፒክ ማራቶን ኢትዮጵያን እንዲወክሉ ጥሪ የተደረገላቸው ማራቶን ሯጮች  በወንዶች 6 በሴቶች 5 ማራቶኒስቶች ናቸው፡፡ በኦሎምፒክ ለአንድ አገር በሚሰጠው የተሳትፎ ኮታ መሰረት በሁለቱም ፆታዎች ሶስት አትሌቶች ብቻ ለማሳተፍ የሚቻል ሲሆን በፌደሬሽኑ ጊዜያዊ ዝርዝር መሰረት በወንዶች 3 በሴቶች ደግሞ 2 ማራቶኒስቶች በተጠባባቂነት ተይዘዋል፡፡በወንዶች ምድብ በጊዜያዊ ማጠቃለያ ምርጫው ከተያዙት ስድስት አትሌቶች መካከል ሶስቱ ዋና
ተሰላፊዎች በያዝነው የውድድር ዘመን የዓለማችንን ትልልቅ የማራቶን ውድድሮች ያሸነፉ ሲሆኑ፤ እነሱም የ2016 ዱባይ ማራቶን አሸናፊው ተስፋዬ አበራ፤ የ2016 የቦስተን ማራቶን አሸናፊው ለሚ ብርሃኑ  እንዲሁም የ2016 ቶኪዮ ማራቶን አሸናፊው ፈይሳ ሌሊሳ ናቸው፡፡  በተጠባባቂነት ከተያዙት አስደናቂው ተመራጭ በኦሎምፒክ በ10ሺ ሁለት እንዲሁም በ5ሺ 1 የወርቅ ሜዳልያዎችን
የሰበሰበው ቀነኒሳ በቀለ ሲሆን በ2016 የለንደን ማራቶን 3ኛ ደረጃ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡ በ2015
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የብር ሜዳልያ ያገኘው የማነ ፀጋዬ እና በ2013 የዓለም ሻምፒዮና
የብር ሜዳልያ የወሰደው ሌሊሳ ዴሲሳ ሌሎቹ ተጠባባቂዎች ናቸው፡፡
በሴቶች ምድብ በጊዜያዊ ማጠቃለያ ምርጫው ከተያዙት አምስት አትሌቶች መካከል ሶስቱ ዋና
ተሰላፊዎች መካከል በ2015 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያ ያገኘችው፤ በ2016
የሻይንሜን ማራቶንን ስታሸንፍ 2 ሰዓት ከ19 ደቂቃ ከ52 ሰኮንዶች የሆነ ምርጥ ሰዓቷን
ያስመዘገበችው ማሬ ዲባባ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናት፡፡ ለሁለት ጊዜያት የበርሊን ማራቶን
ያሸነፈችው አበሩ ከበደ እና በዱባይ ማራቶን ለሶስት ጊዜያት ያሸነፈችው አሰለፈች መርጊያ ሌሎቹ
ቋሚ ተሰላፊዎች ናቸው፡፡ በተጠባባቂነት የተያዙት ማራቶኒስቶች ደግሞ የ2016 ዱባይ ማራቶንንን
ያሸነፈችው ትርፌ ፀጋዬ እና በ2015 በለንደን ማራቶን ያሸነፈችውና ዘንድሮ ሁለተኛ ደረጃ ያስመዘገበችው ትግስት ቱፋ ናቸው፡፡የማራቶን አትሌቶች ምርጫ ውጤት ጊዜያዊ ማጠቃለያ ዝርዝር በማለት አትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ይፋ ካደረገው መረጃ በኋላ አወዛጋቢ አጀንዳዎች ተፈጥረዋል፡፡አትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ጊዜያዊ ማጠቃለያ ዝርዝር በማለት የማራቶን አትሌቶች ምርጫ ውጤት ይፋ ካደረገ  በኋላ በርካታ አወጋቢ አጀንዳዎች ተፈጥረዋል፡፡ በምርጫው በርካታ አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች፤ የአትሌቶች ማህበር፤ ማናጀሮች እና አሰልጣኞች ቅሬታ ተፈጥሮባቸዋል፡፡ ለአትሌቶች ማህበር እና ለአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ የቅሬታ ማመልከቻ በማስገባት የተሟገቱትም ጥቂት አይደሉም፡፡ በአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ የተካሄደው የማራቶን ኦሎምፒያኖች ምርጫ ወቅቱን ያልጠበቀ፤ በአጭር ጊዜ በተደረጉ የመስፈርት ለውጦች ለመወሰን የበቃ፤ ከአገር ጥቅም ይልቅ የግለሰቦች ፍላጎትን ያንፀባረቀ፤ ግልፅ ያልሆኑ እና የማያሳምኑ የምርጫ መስፈርቶች ተግባራዊ የሆኑበት ተብሎም በስፋት የተተቸ ሆኗል፡፡ በተለይ ምርጫውን ያከናወነው የቴክኒክ ኮሚቴ
አንድም የማራቶን አሰልጣኝ በአባልነት ያላቀፈ በመሆኑ፤ በ10ሺ እና በ5ሺ እንዲሁም በ3ሺ

መሰናክል አሰልጣኞች እንዲሁም ልምድ የሌላቸው የኮሚቴ አባላት የተከናወነም በመሆኑም  ብዙ ቅሬታዎችን እንደፈጠረ እየተገለፀ ነው፡፡ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ የቴክኒክ ኮሚቴ ያካሄደው ምርጫ በፌደሬሽኑ ስራ አሰፍፃሚ ተገምግሞ መስተካከል አለበት የሚሉት አትሌቶች ለውጦች እንደሚኖሩ ተስፋ በማድረግ በተለያዩ መንገዶች ሰሞኑን ሲከራከሩ ተስተውለዋል፡፡ የአትሌቶች ማህበር የኦሎምፒክ ቡድን ምርጫው በድጋሚ ሊታይ እንደሚገባው እየገለፀም ነበር፡፡ የማራቶን ኦሎምፒያኖች ምርጫው ልምድ ያላቸው አንጋፋ አትሌቶች፤ የአትሌቶች ማህበር፤ የማራቶን አሰልጣኞችን እንዲሁም ማናጀሮችን ባካተተ ምክክር ሊወሰን እንደሚገባውም ይገለፃል፡፡በአትሌቲክስ ዘገባዎቹ ከፍተኛ እውቅና ያለው ሌትስራን የተባለው የአትሌቲክስ ድረገፅ በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ማራቶን ቡድን ዙርያ ሰፊ ትንታኔ በማቅረብ የመጀመርያው ነበር፡፡ ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት የአትሌቶቹን የማራቶን ልምድ በመዳሰስ በድረገፁ በተሰራው
ልዩ ትንታኔ በወንዶች በተጠባባቂነት የተያዘው ቀነኒሳ በቀለ የኦሎምፒክ ተሳትፎው ጥያቄ ውስጥ
መግባቱ እና በተለይ ደግሞ በሴቶች በ2016 የ2016 ደረጃን የምትመራው ትርፊ ፀጋዬ በተጠባባቂነት መያዟ አበይት መነጋገርያ ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል፡፡እንደተገለፀው በርካታ ምርጥ ማራቶኒስቶች ያሏቸው ኢትዮጵያ እና ኬንያ ማጣርያ ሊደረግበት በማይቻለው ማራቶን የኦሎምፒክ ቡድን መምረጥ ፈታኝ ተግባር መሆኑን ያመለከተው የሌትስራን  
ትንተና ፤ መመረጥ እያለባቸው የሚቀሩ አትሌቶች መኖራቸው እና ቅሬታዎች መፈጠራቸው የማይቀር ሁኔታ እንደሆነም ገልጿል፡፡ የማራቶን ውድድሮች ልምድ፤ በከባድ እና ሞቃታማ ማራቶኖች የሚገኝ ስኬት፤ በውድድር ዘመኑ ወቅታዊ ብቃት እና ውጤት፤ በ2015 የነበረ ውጤታማነት ፤ የዓለማችን ትልልቅ ማራቶኖች የፉክክር እና የፈታኝነት ንፅፅር፤ ዘንድሮ ሁለት
ማራቶን የሮጡ አትሌቶች በኦሎምፒክ ማራቶን ለሶስተኛ ጊዜ መወዳደራቸውን ሌሎችንም
ሁኔታዎች ከግምት ያስገቡ  የምርጫ መስፈርቶች ቢኖሩም ሙሉለሙሉ አሳማኝ ቡድን ለማሳወቅ
የሚከብድ መሆኑንም አብራርቷል፡፡
በሌትስራን ትንታኔ በተሰጠው ድምዳሜ መሰረት በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ማራቶን ቡድን ዝርዝር በሴቶች የተከናወነው ምርጫ ትርጉም የለሽ የሆነው ተጠባባቂ ሊሆኑ የሚችሉት አትሌቶች  ከዋና ተሳላፊዎቹ የተሻለ ስኬት ከማስመዝገባቸው አንፃር ነው፡፡ ሌትስራንዋና ተሰላፊ መሆን ያለባቸው ሶስቱ አትሌቶች የዓለም ሻምፒዮኗ ማሬ ዲባባ እንዲሁም ሁለቱ ተጠባባቂዎች ትርፌ ፀጋዬ እና ትግስት ቱፋ ናቸው ብሏል፡፡ በሌላ በኩል በወንዶች የተከናወነው ምርጫ  በተለይ የተስፋዬ አበራ እና የለሚ ብርሃኑ ዋና ተሰላፊነት እንደማያከራክር ተጠቅሶ የፈይሳ ሌሊሳ መካተት ግን የሚያሳምን አይደለምም ተብሏል፡፡  በተጠባባቂነት ከተያዙት ሶስተኛው ዋና ተሰላፊነት ለሌሊሳ ዴሲሳ ይገባ እንደነበር የተነተነው ሌትስ ራን፤ ቀነኒሳ በቀለ ደግሞ በማራቶን ተጠባባቂነት መያዙ በሪዮ ኦሎምፒክ ከእነጭራሹ ላይሳተፍ እንደሚችል የሚያመለክት ነው በማለት ድምዳሜውን አሰራጭቷል፡፡በማራቶን የኢትዮጵያ ወንድ ኦሎምፒያኖች
በወንዶች ማራቶን ኢትዮጵያ ባለፉት 12 ኦሎምፒኮች በነበራት ተሳትፎ 4 የወርቅ እና 3 የነሐስ
ሜዳልያዎች በማስመዝገብ በምንጊዜም የውጤት ደረጃ ከዓለም አንደኛ ነች፡፡ በኦሎምፒክ ማራቶን
ለኢትዮጵያ 4 የወርቅ ሜዳልያዎችን ያገኙት  ኦሎምፒያኖች በ1960  እኤአ በሮም ኦሎምፒክ እና
በ1964 በቶኪዮ ኦሎምፒክ አከታትሎ ያሸነፈው አበበ ቢቂላ፤ በ1968 እኤአ በሜክሲኮ ኦሎምፒክ
ማሞ ወልዴ እንዲሁም በ2000 እኤአ በሲድኒ ኦሎምፒክ ገዛሐኝ አበራ ናቸው፡፡ 3 የነሐስ
ሜዳልያዎች ደግ በ1968 ሜክሲኮ ኦሎምፒክ ማሞ ወልዴ ፤በ2000 እኤአ ሲድኒ ኦሎምፒክ
ተስፋዬ ቶላ፤ በ2008 እኤአ ቤጂንግ ኦሎምፒክ ፀጋዬ ከበደ የተጎናፀፏቸው ናቸው፡፡በ31ኛው ኦሎምፒያድ በወንዶች  ማራቶን  ኢትዮጵያን  የሚወክሉት ስድስት ማራቶኒስቶች በአትሌቲክስ ፌደሬሽን ምርጫ ላይ የተሰጣቸው ደረጃ  እንዲሁም ሌትስራን በተባለው የአትሌቲክስ ድረገፅ ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት በነበራቸው የውጤት ታሪክ በተሰራው ልዩ ትንታኔ መሰረት ከዚህ በታች የቀረቡት ናቸው፡፡ ተስፋዬ አበራ - በፌደሬሽኑ በ1ኛ ደረጃ የተመረጠ ሲሆን 24 ዓመቱ ነው፡፡ በ2016 የዱባይ (2:04:24) እና ሃምቡርግ (2:06:58) ማራቶኖች አሸንፏል፡፡ በ2015 ደግሞ 3 ማራቶኖችን  በመወዳደር 1 አሸንፎ በሁለቱ 2ኛ ሲሆን ያስመዘገበው አማካይ ሰዓት 2:09-2:10  ነበር፡፡ለሚ ብርሃኑ  - በፌደሬሽኑ በ2ኛ ደረጃ የተመረጠ ሲሆን 21 ዓመቱ ነው፡፡ በ2016 በዱባይ ማራቶን (2:04:33) ሁለተኛ ደረጃ  ሲያገኝ እንዲሁም በቦስተን ማራቶን  (2:12:45) አሸንፏል፡፡  በ2015 በማራቶን ባስመዘገበው ሰዓት ከዓለም 5ኛ ደረጃ የነበረውን ሰዓት ያስመዘገበ ሲሆን የዱባይ ማራቶንን (2:05:28) እና የዋርሶው ማራቶንን (2:07:57) ከማሸነፉም በላይ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና (2:17:37) 15ኛ ደረጃ ነበረው፡፡ፈይሳ ሌሊሳ -  በፌደሬሽኑ በ3ኛ ደረጃ የተመረጠ ሲሆን 26 ዓመቱ ነው፡፡ በ2016 የቶኪዮ ማራቶንን (2:06:56) አሸንፏል፡፡ በ2015 ደግሞ በዱባይ ማራቶን 4ኛ (2:06:35)፤ በሮተርዳም ማራቶን 5ኛ (2:09:55) እንዲሁም በበርሊን ማራቶን (2:06:57) አስመዝግቧል፡፡ቀነኒሳ በቀለ  - በፌደሬሽኑ በ4ኛ ደረጃ የተመረጠ ሲሆን 33 ዓመቱ ነው፡፡ በ2016 በለንደን
ማራቶን 3ኛ ደረጃን  (2:06:36) አስመዝግቧል፡፡ በተቀረው የማራቶን ልምዱ በ2014 የፓሪስ
ማራቶንን (2:05:04) ያሸነፈ ሲሆን በቺካጎ ማራቶን ደግሞ (2:05:51) 4ኛ ደረጃን  
አስመዝግቧል፡፡
የማነ ፀጋዬ  - በፌደሬሽኑ በ5ኛ ደረጃ የተመረጠ ሲሆን 31 ዓመቱ ነው፡፡ በ2016 በቦስተን ማራቶን
3ኛ ደረጃ  (2:14:02) አስመዝግቧል፡፡ በ2015 ደግሞ በቦስተን ማራቶን 2ኛ ደረጃ (2:09:48) ፤
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ2ኛ ደረጃ የብር ሜዳልያ  (2:13:08) እንዲሁም በኒውዮርክ
ማራቶን 5ኛ ደረጃን (2:13:24) ያገኘ ነበር፡፡
ሌሊሳ ዲሳሳ -  በፌደሬሽኑ በ6ኛ ደረጃ የተመረጠ ሲሆን 26 ዓመቱ ነው፡፡ በ2016 በቦስተን
ማራቶን (2:13:32) 2ኛ ደረጃ ነበረው፡፡ በ2015 ደግሞ በዱባይ ማራቶን 2ኛ (2:05:52), በቦስተን
ማራቶን 1ኛ (2:09:17), በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 7ኛ  (2:14:54) እንዲሁም በኒውዮርክ

ማራቶን 3ኛ ደረጃ ያስመዘገበ ነበር፡፡
በማራቶን የኢትዮጵያ ሴት ኦሎምፒያኖች
በሴቶች ማራቶን ኢትዮጵያ ባለፉት 12 ኦሎምፒኮች በነበራት ተሳትፎ 2 የወርቅ ሜዳልያዎችን

በማስመዝገብ በምንግዜም የውጤት ደረጃ ከዓለም ሁለተኛ ነች፡፡  በኦሎምፒክ 2 የወርቅ

ሜዳልያዎችን በማራቶን ለኢትዮጵያ ያስገኙት በ1996 እኤአ በአትላንታ ኦሎምፒክ ፋጡማ ሮባ
እንዲሁም በ2012 እኤአ በለንደን ኦሎምፒክ ቲኪ ገላና ናቸው፡፡ በተያያዘ  በሴቶች የኦሎምፒክ
ማራቶን ሪከርድ ያስመዘገበችው የኢትዮጵያዋ ቲኪ ገላና ስትሆን በ2 ሰዓት ከ23 ደቂቃዎች ከ07
ሰከንዶች  በለንደን ኦሎምፒክ ነው፡፡
በ31ኛው ኦሎምፒያድ በወንዶች  ማራቶን  ኢትዮጵያን  የሚወክሉት አምስት ማራቶኒስቶች
በአትሌቲክስ ፌደሬሽን ምርጫ ላይ የተሰጣቸው ደረጃ  እንዲሁም ሌትስራን በተባለው የአትሌቲክስ
ድረገፅ ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት በነበራቸው የውጤት ታሪክ በተሰራው ልዩ ትንታኔ
መሰረት ከዚህ በታች የቀረቡት ናቸው፡፡
ማሬ ዲባባ  - በፌደሬሽኑ በ1ኛ ደረጃ የተመረጠች ሲሆን 26 ዓመቷ ነው፡፡ በ2016 በለንደን
ማራቶን (2:24:09) 6ኛ ደረጃ ነበራት፡፡ በ2015 ደግሞ በሻይናሜን ማራቶን 1ኛ (2:19:52),
በቦስተን ማራቶን 2ኛ (2:24:59) እንዲሁም በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1ኛ ደረጃ የወርቅ
ሜዳልያ (2:27:35) አስመዝግባለች፡፡
አሰለፈች መርጊያ -  በፌደሬሽኑ በ2ኛ ደረጃ የተመረጠች ሲሆን 31 ዓመቷ ነው፡፡ በ2016 በለንደን
ማራቶን 5ኛ ደረጃ (2:23:57) ነበራት፡፡ በ2015 በዱባይ ማራቶን 1ኛ (2:20:02), በለንደን
ማራቶን 4ኛ (2:23:53) እንዲሁም 2nd በኒውዮርክ ማራቶን 2ኛ (2:25:32) ነበረች፡፡
አበሩ ከበደ  - በፌደሬሽኑ በ3ኛ ደረጃ የተመረጠች ሲሆን 29 ዓመቷ ነው፡፡ በ2016 በቶኪዮ
ማራቶን  (2:23:01) አሸናፊ ነበረች፡፡ በ2015 ደግሞ . በዱባይ ማራቶን 5ኛ (2:21:17)፤ በቦስተን
ማራቶን 7ኛ (2:26:52) እንዲሁም በበርሊን ማራቶን 2ኛ (2:20:48) ነበረች፡፡
ትርፌ ፀጋዬ  - በፌደሬሽኑ በ4ኛ ደረጃ የተመረጠች ሲሆን 29 ዓመቷ ነው፡፡ በ2016 የዱባይ
ማራቶንን ስታሸንፍ የዓመቱን ፈጣን ሰዓት 2:19:41 አስመዝግባ ሲሆን በቦስተን ማራቶን 2ኛ (2:30:03) ነበረች፡፡ በ2015 በለንደን ማራቶን 3ኛ (2:23:41) እንዲሁም በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 8ኛ  (2:30:54) ነበረች፡፡
ትዕግስት ቱፋ  - በፌደሬሽኑ በ5ኛ ደረጃ የተመረጠች ሲሆን 29 ዓመቷ ነው፡፡ በ2016 በለንደን
ማራቶን 2ኛ (2:23:03) ነበራት፡፡ በ2015 በዱባይ ማራቶን አቋርጣለች፤ በለንደን ማራቶን 1ኛ
(2:23:22)፤ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 6ኛ (2:29:12)እንዲሁም በኒውዮርክ ማራቶን
3ኛ(2:25:50) ነበረች፡፡
ኬንያ እና አሜሪካስ…
በአትሌቲክስ የረጅም ርቀት እና የማራቶን ውድድሮች የኢትዮጵያ የቅርብ ተቀናቃኝ የሆነችው ኬንያ
በማራቶን ቡድን ምርጫዋ አምና በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና አቋርጠው የወጡ ሁለት የማራቶን
ሪከርድ ያስመዘገቡ አትሌቶች ዊልሰን ኪፕሳንግ እና ዴኒስ ኪሜቶን ከምርጫ ውጭ አድርጋለች፡፡
ይህም ለዓለም ሻምፒዮና ውጤት የተሰጠውን ግምት ያመለክታል፡፡የኬንያ ማራቶን ቡድን በሁለቱም ፆታዎች 8 ማራቶኒስቶች የተካተቱበት ሲሆን በ2008 ቤጂንግ ላይ በሳሙኤል ዋንጂሩ የተገኘውን የወርቅ ሜዳልያ ለመድገም ተጨማሪ አንድ ለሜዳልያ ለማግኘት እንዲሁም በሴቶች በ2012 ፕሪስካ ጄፔቶ ያገኘችውን የብር ሜዳልያ ወደ የወርቅ ሜዳልያ ለማሻሻል አቅደዋል፡፡ በወንዶች ኤሊውድ ኪፕቾጌ፤ ስታንሊ ቢዎት፤ ሲፕሪያን ኮቱትና ዌስሊ ኮሪር እንዲሁም በሴቶች
ጄምያ ሱምጎንግ ሄላህ ኪፕሮፕ፤ ፍሎረንስ ኪፕላጋትና  ቪዝሊን ጄፕኬሾ የተባሉት ማራቶኒስቶች ናቸው፡፡የኬንያ ማራቶን በኑድን ይፋ የሆነው ሜይ1 2016 ሲሆን ከኢትዮጵያ 2 ሳምንት ቀድሞ ነበር፡፡
በኢቴን እና ኤልዶሬት በካምፕ ሆነው ዝግጅታቸውን ጀረዋል፡፡
በሌላ በኩል አሜሪካ የማራቶን ቡድኗን በሎሳንጀለስ ማራቶን በተካሄደ ማጣርያ የመረጠች ሲሆን እነሱም የ10ሺ ሯጭ የነበረው ጋለን ሩፕ፤ መባ ክፍለእግዚ እና ጄርድ ዋርድ እንዲሁም በሴቶች አሚ ክራግግ ዴዘሪ ሊንደንና የ10ሺ ሯጭ የነበረችው ሻላኔ ፍላንጋን ናቸው፡፡ አሜሪካ የማራቶን ቡድኗን የመረጠችው ሚኒማውን ያሟሉ አትሌቶች በማራቶንን ማጣርያ በመለየት ከ1 እስከ 3 የወጡትን ነው፡፡ ኬንያ በዚህ መንገድ ምርጫውን ለማከናወን አቅዳ ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ የኦሎምፒክ ማጣርያውን ያቀደችው ኬንያ አመቺ ወቅት እና የውድድር ቦታ ባለመኖሩ እንዲሁም ከአትሌቶች፤ ከአሰልጣኞች፤ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገ
ምክክር ለመተው የተገደደች ሲሆን ቡድኑን የመረጠችው በ2015 እና በ2016 ማራቶኖች አትሌቶች
ያስመዘገቧቸውን ውጤቶች በማገናዘብ እንደሆነ ታውቋል፡፡
በተለይ የ2015 የቤጂንግ የዓለም ሻምፒዮና፤ በ2015 የተካሄዱት የኒውዮርክ፤ የቺካጎ እና የበርሊን
ማራቶኖች  እንዲሁም በ2015 እና በ2016 የተካሄዱት የቶኪዮ እና የለንደን ማራቶን ውጤቶችን
ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ በ2015 የተካሄዱ ሌሎች ትልልቅ ማራቶኖች እና በ2016
ከአፕሪል 30 መጨረሻ የተካሄዱ ማራቶን ውጤቶችም ከግምት ገብተዋል፡፡

Read 2566 times