Saturday, 28 May 2016 15:22

“የሰርጌ ቀን የበላሁት ኬክ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(14 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
አገሩ ሁሉ ሰርግ በሰርግ ሆነ አይደል፡፡ ለጎጆ ወጪዎች እንኳን ደስ አላቸው፡
ስሙኝማ…ዘንድሮ አልገጥም ያለን ነገር ምን መሰላችሁ… ‘እከሌና እከሊት ተጋቡ’ ከሚለው ዜና በሚቀራረብ መልኩ ‘እከሌና እከሊት ተፋቱ’ የሚለውን መስማት ‘የተለመደ’ ከምንለው በላይ እየሆነብን ነው፡፡ ምንድነው የመጣብን!  ለምንድነው ሰዉ ሁሉ ፍቺን እንዲህ ‘ቀላል’ ያደረገው! እናላችሁ…ሰማንያው የተጻፈበት ቀለም እንኳን ገና ሳይደርቅ መቀደድ መብዛቱ…አለ አይደል… አሪፍ አይደለም፡፡
የምር ግን…ዘንድሮ አማቶች እፎይ ሳይሉ አይቀሩም፡፡ ልክ ነዋ…በፈት እኮ ‘ከእያንዳንዱ ፈራሽ ትዳር ጀርባ አንዲት አፍራሽ አማት አለች’ የሚባል አይነት ነገር ነበር፡፡ ዘንድሮ… የሰበብ ችግር የለም፡፡ አንዳንድ ትዳሮች አማቶች ገና ሻንጣቸውን ሳያስገቡ በሁለትና በሦስት ወራቸው የሚፈርሱበት ዘመን ነው!
ይቺን እዩልኝማ…ሰውየው የምግብ ባለሙያ ነው፡፡ እናም… በርካታ ሰዎች ያሉበት ስብሰባ ላይ እየተናገረ ነው፡፡ “ሆዳችንን ውስጥ ያለው ነገር እዚህ ያለነውን ብዙዎቻችን ሊገድለን የሚችል ነው፡፡  ቀይ ስጋ ለጤንነት አደገኛ ነው፡፡ ለስላሳ መጠጥ የሆዳችሁን ግድግዳ ያሳሳዋል፡፡ የቻይና ምግብ ውስጥ የሌለ አስቀያሚ ነገር የለም፡፡  
አትክልት ለአንዳንዶቻችን አደገኛ ሊሆን ይችላል፡፡ የምንጠጣው ውሀ ውስጥ ያሉ ጀርሞች ስለሚያስከትሉት የረጅም ጊዜ ጉዳት ብዙዎቻችን አናውቅም፣” ካለ በኋላ  “ከመሀላቸው ከበላችሁት በኋላ ለዓመታት ያሰቃያችሁና የጸጸታችሁ ምግብ ምንድነው?” የሚል ጥያቄ ያቀርባል፡፡ የ75 ዕድሜ ያላቸው ሰው እጃቸውን አውጥተው ምን ቢሉ ጥሩ ነው….
“የሰርጌ ጊዜ የበላሁት ኬክ…” ብለው አረፉት፡፡
እናላችሁ…አንዳንዴ በተባራሪም ቢሆን በሚዲያ እንደምንሰማው ...በ‘እነሆ በረከት አለመጣጣም’ ከዋናዎቹ ችግሮች መሀል ነው ይባላል፡፡
እኔ የምለው… ሁሉም የአካል ክፍል እንደ ድሮው በቦታው፣ በቦታው አይደለም እንዴ! ‘አለመጣጣም’ የሚለው ይብራራልንማ!
የደከመው ካለ ማነው ለምን ደከመ? እንዴት ደከመ? ምን ሲል ደከመ? ከትዳር በፊት ካልደከመው ትዳር በያዘ በወር ተኩሉ ለምን ደከመው? ምናምን የሚሉ ጥያቄዎች ይጠየቁልን፡፡ እኔ የምለው እነ ደረቅ ጠጅ፣ እነ ፔርኖ፣ እነ ቮድካ በኦሬንጅ፣ እነ ‘ቪ’ ኪኒን… ለዚህ፣ ለዚህ በነፍስ ካልደረሱ ምን ያደርጉልናል! ቂ…ቂ…ቂ… “ቀላሉ መንገድ ቆንጆዋን አንጄሊና ጆሊን ማየት ነው ያልከን ወዳጃችን…እስቲ ታጫውተናለህ፡፡ አሀ…ሳንቀደም የዋና ፎቶዋን እንቸበችባለና!
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የቁንጅናን ነገር ካነሳን አይቀር ‘ወጥመድ’ (የስፓኒሽ ርዕሱ ‘ፉጂቲቮስ’) ላይ ኤስፔራንዛ ሆና የምትጫወተው ታሊያና ቫርጋስ ለካስ ዝም ብላ አልቆነጀችም! በእነሱ አቆጣጠር በ2007 ‘ሚስ ኮሎምቢያ’ ሆና የተመረጠች ሲሆን በ2008 ደግሞ በ‘ሚስ ዩኒቨርስ’ ውድድር ሁለተኛ ወጥታለች፡፡ ይገባታል፡፡
እናላችሁ…ሰማንያ ቀደዳ በዝቷል፡፡
(ሁኔታዎች የቀድሞ መልካቸውን እስኪይዙ ሰማንያ ወደ ሠላሳ አምስት ይቀነስልን!) ለነገሩማ እከሌና እከሊት መጋባታቸው ሳይሆን እሱዬው በምን መልክ “እንግባ… ብሎ የጠየቀበት መንገድ ዋናው ዜና ሲሆን የሆነ ግራ የሚያጋባ የሚመስል ነገር አለው፡፡
 አንዳንዴማ…ነገርዬው ሁሉ የሆነ ‘ሪያሊቲ ሾው’ ምናምን እየመሰለ ነው፡፡
እናማ… “የሰርጌ ቀን የበላሁት ኬክ…” አይነት ነገር በዝቷል፡፡  
ስሙኝማ… ፍቺ እንዲህ ከበዛ ‘የሚቀወጡ’ ቤቶች መአት ናቸው ማለት ነው፡፡
“ደግሞ ስሚ ትናንት የፌስቡክ ገጽሽን ሳይ ነበር…” “ጥሩ ነዋ… ፍሬንድ አደረግኸኝ!”  (ኮሚክ እኮ ነው፣ በአንድ ጣራ ስር እየኖሩ… ‘ይሄ ሜትር ከሀያ አንሶላ ወደ ሜትር ከሰማንያ ካልተለወጠ’ እየተባባሉ…ፌስቡክ ላይ ፍሬንድ ይደራረጋሉ — የመጨረሻዋ ቃል ባትመችም አማራጭ ስለጠፋ ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…”
“ፕሮፋይል ፒክቸርሽን አልወደድኩትም…”
“ምን ሆነ? እንደውም መአት ላይክ አግኝቼበታለሁ…”
“አንደኛ ነገር ክንድሽን ሁሉ ራቁትሽን አድርገሽ በቦዲ ብቻ የተነሳሽው ፎቶ ነው…”
“እንደውም ላንጋኖ ልክ ከዋናው ስወጣ የተነሳሁትን ልለጥፈው ነበር…”
“ሁለተኛ ነገር ያን ያህል መሳቅ ምንድነው…
“እና ብስቅስ ምናለበት!”
“አጅሪት እንዲህ እየሳቅሽ ነዋ ፍሬንዶችሽ ሦስት ሺህ ሰባት መቶ የሞሉት!” “ምን ታደርገዋለህ… የሰው መውደድ ይስጠኝ ማለት ነው…”
“ፕሮፋይል ፒክቸርሽን ካልለወጥሽ የእኔና አንቺ ነገር አበቃ…” በዚህም ሰማንያ ሊቀደድ ይችላል፡፡
እናማ… “የሰርጌ ቀን የበላሁት ኬክ…” አይነት ነገር በዝቷል፡፡  
እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኛማ… ባል ከጓደኛው ጋር እያወራ ነው፡፡
“ካገባሁ ጊዜ ጀምሮ ሚስቴ ልትለውጠኝ ብዙ ለፍታለች፡፡
 በየቀኑ የአካል እንቅስቃሴ እንድሠራ አድርጋኛለች፣ ሽክ እያልኩ እንድለብስ አድርጋኛለች፣ ጥሩ ምግብ እንድመገብ፣ ኪነ ጥበብ እንዳደንቅ፣ ሙዚቃ ቲያትር እንድወድ አድርጋኛለች፡፡ እንዲሁም እንዴት አድርጌ አክስዮን ገበያ ውስጥ እንደምሳተፍ አሳይታኛለች፡፡  አሁን ግን ፍቺ እፈልጋለሁ፡፡” ጓደኝየውም…
“ይሄን ያህል እንድትሻሻል አድርጋህ እንዴት ፍቺ ትፈልጋለህ…” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…
“በጣም ስላሻሻለችኝ፣ አሁን እሷ እኔን አትመጥነኝም…” ብሎ አረፈ፡፡
እናማ…ባሎቻችሁን የምትለውጡ ሴቶች፤ “እኔን አትመጥነኝም…” የሚያሰኘው መስመር አጠገብ እንዳትደርሱ ጠንቀቅ ነው፡፡
እናማ… “የሰርጌ ቀን የበላሁት ኬክ…” አይነት ነገር በዝቷል፡፡  
እናላችሁ… “ይትባረክ እንደ አብረሀም…” ብለን ሳንጨርስ… አለ አይደል… “ዓይንህ ለአፈር/ዓይንሽ ለአፈር” ተባባሉ ሲባል አሪፍ አይደለም፡፡
የሆኑ ሴቶች ከባሎች ጋር መኖር ስላለበት የፍቅር ግንኙነት ዙሪያ በሚያተኩር ‘ወርክሾፕ’ ላይ እየተካፈሉ ነበር፡፡
“ባሎቻችሁን የምትወዱ ስንቶቻችሁ ናችሁ?” የሚል ጥያቄ ይቀርብላቸዋል፡፡ ሁሉም እጆቻቸውን ያወጣሉ፡፡
ከዛም የስልጠናው መሪ… “ለመጨረሻ ጊዜ ባሎቻችሁን እወድሀለሁ ያላችሁት መቼ ነው?” ተብለው ይጠየቃሉ፡፡
አንዳንዶቹ “ዛሬ…”፣ አንዳንዶቹ “ትናንት…”፣ አንዳንዶቹ ጭርሱን ማስታወስ አልቻሉም፡፡ ከዛም ሁሉም የእጅ ስልኮቻቸውን እንዲያወጡ ተደረገ፡፡ አሰልጣኟ…
“ለባሎቻችሁ ‘የእኔ ማር እወድሀለሁ…’ የሚል ቴክስት ላኩላቸው…” ትላቸዋለች፡፡ ሁሉም ይልካሉ፡፡ ከዚያም ስልኮቻቸውን እየተለዋወጡ ባሎቻቸው የሰጧቸውን መልሶች እንዲያነቡ ተነገራቸው፡፡
ባሎቹ ከሰጧቸው ምላሾች መሀል አስሮቹ የሚከተሉት ናቸው…
አንቺን ማን ልበል?
አሀ፣ የልጆቼ እናት፣         አመመሽ እንዴ?
እኔም እወድሻለሁ፡፡
አሁን ደግሞ ምን ተፈጠረ?         መኪናውን እንደገና         አጋጨሽው እንዴ?
ያልሽው አልገባኝም፡
አሁን ደግሞ ምን ጥፋት         አጠፋሽ? አሁንስ ይቅር         አልልሽም፡፡
አትዘባርቂ፣ ምን             እንደምትፈልጊ ለምን         አትነግሪኝም!
በህልሜ ነው?
ይቺን መልእክት ለምን         እንደላክሽ ካልነገርሽኝ         ወዮልሽ!
አንቺ ሴትዮ… አልኮል መጠጥ መጠጣትሽን አቁሚ አላልኩም! ከእኔ ጋር መሆኑ ከሰለቸሽ መፋታት ነው፡፡
አንዳንዱ ባል ደግሞ ንግርት አለበት እንዴ!… ሰው ይደክመዋል ማለት ጥሩ ነዋ! አሀ… አፕታይዘሩን እዛ ሄዶ ይፈልጋ!  ቂ…ቂ…ቂ… እሷዬዋ ምን የምትል ይመስለኛል መሰላችሁ…
“ጧት ‘እንትን አምጪ’… ምሳ ሰዓት ‘እንትን አምጪ’… መክሰስ ሰዓት ‘እንትን አምጪ’….በእራት ሰዓት ‘እንትን አምጪ’… ምን መሰልኩህ…እኔ ከምግብ በፊት የምወሰድ የጨጓሯ ኪኒን ነኝ!…ወይ ምግብ መባረኪያ የጸሎት መጽሐፍ ነኝ…ወይስ ፕሌይስቴሽን ነኝ!” ቂ…ቂ…ቂ… የምር አሳዘነችኝ! እናላችሁ…ሰማንያ ቀደዳ በዝቷል፡፡
ሰወየው ሚስቱን ሊፈታ እንደሆነ ለጓደኞቹ ይነግራቸዋል፡፡
“ለምንድነው የምትፈታት?”
“በሀይማኖት አልተጣጣምንም…”
“በዚህ ዘመን በሀይማኖት አልተጣጣምንም ማለት ምን ማለት ነው?”፡
“እሷ ገንዘብ ታመልካለች፣ እኔ ደግሞ ምንም የለኝም…” ብሎ አረፈ፡፡
ማን ይሆን ማን እንጃ… ግን ምን አለ አሉ መሰላችሁ…
“ስኬታማ ወንድ ማለት ሚስቱ ልታጠፋው ከምትችለው በላይ ገንዘብ የሚያገኝ ነው፡፡ ስኬታማ ሴት ማለት የዚህ አይነት ወንድ የምታገኘዋ ሴት ነች፣” አለ አሉ፡፡
እናማ… “የሰርጌ ቀን የበላሁት ኬክ…” አይነት ነገር በዝቷል፡፡  
ሰውየው 98 ዓመታቸው ነው፡፡ ሴትዮዋ ደግሞ 95 ናቸው፡፡ ፍቺ ፍለጋ ጠበቃ ዘንድ ይሄዳሉ፡፡
“ለምን ያህል ጊዜ በትዳር ቆይታችኋል?” ሲል ጠበቃው ይጠይቃቸዋል፡፡ ሰውየው…
“75 ዓመታት…” ሲሉ ይመልሳሉ፡፡ ጠበቃውም…
“ታዲያ ለመፋታት ይህን ያህል ጊዜ ያቆያችሁ ምንድነው?” ብሎ ይጠይቃል፡፡ ሰውየው ምን ብለው ቢመልሱ ጥሩ ነው…
“ልጆቻችን እስኪያልቁ እየጠበቅን ነበር፡፡” ከዚህስ ይሰውረን፡፡
ሀሳብ አለን…ገና ለገና በይሆናል “ወይ ጉድ!” ከምንል፣ ሙያው ያላቸው ሰዎች ‘ውሀ የሚያነሱ’ ጥናቶች ይሥሩልንማ!
“የሰርጌ ቀን የበላሁት ኬክ…” አይነት ነገር በዝቷል፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 6084 times