Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 03 March 2012 14:19

ሙሰኝነት የሥርዓቱ አደጋ ሆኗል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“ቁርጠኛ ሌባ አለ፤ ቁርጠኛ ተዋጊ ግን የለም” - አቶ ስብሀት ነጋ

“ሥርዓቱ ቁርጠኛ ሌቦችን ነው የሾመው ማለት ነው?” - አቶ ሞሼ ሰሙ የኢዴፓ ሊቀመንበር

“እኔ ከ10 ዓመት በፊት የነገርኳቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ይነግሩናል” - ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ

“ቁርጠኛ ጠ/ሚኒስትር ቁርጠኛ ሌቦች መኖራቸውን ካወቀ ጠራርጐ ያስወጣል ወይም ራሱን ያስወጣል” -

አቶ ግርማ ሰይፉ በፓርላማ የመድረክ ተወካይ

ሙሰኝነት የሥርዓቱ አደጋ ሆኗል

 

በአገሪቱ የተንሰራፋውን የሙስና ወንጀል ለመዋጋት ፍላጐትና የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግና በተጨባጭ የሚታየው ግን ፍላጐት እንጂ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንዳልሆነ የኢትዮጵያ ሰላምና ልማት ዓለም አቀፍ ተቋም ዋና ዳይሬክተር አቶ ስብሀት ነጋ ገለፁ፡፡

በሥርዓቱ ውስጥ ቁርጠኛ ሌቦች ቢኖሩም ቁርጠኛ ተዋጊ ባለመኖሩ ሙስና ለሥርዓቱ አደጋ መሆኑንም አቶ ስብሀት ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሃይሉን አሰባስቦ እየሰራ አለመሆኑንና በሁሉም የሙስና አይነቶች ላይ በመዝመት ህዝቡንም ያሳተፈ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ ዘራፊ ስላለ ተዘራፊው ህብረተሰብ ንቃተ ህሊናውን አዳብሮ መጠበቅ ይኖርበታል ያሉት አቶ ስብሀት፤ ህብረተሰቡ በሙሰኞች ላይ ክንዱን ማንሳትና መዝመት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ ሙሰኞቹን በማጋለጡ ተግባር ላይ ህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግም አሳስበዋል፡፡

የአቶ ስብሀት ነጋን መግለጫ ተከትሎ አስተያየታቸውን የሰጡት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች መንግሥት ሥርዓቱ በሙስና የተጨማለቀ መሆኑን ማመኑ አንድ ነገር ሆኖ ይህንን ሁኔታ ለመቀየርና ከተጨማለቀበት የሙስና ሥርዓት ውስጥ ለመውጣት ሥር ነቀል ለውጥ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል፡፡

የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ፤ የአቶ ስብሀት ነጋን መግለጫ አስመልክተው ሲናገሩ “አቶ ስብሀት ከማንኛውም ተራ ሰው በተሻለ ለሥርዓቱ ቅርበት ያላቸው በመሆኑና ለረዥም ጊዜ ከሥርዓቱ ጋር አብረው የቆዩ ስለሆነ ስለጉዳዩ በጥልቀት ለማወቅ ይችላሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ክቡር ከንቲባውም በተለያዩ መድረኮች ሙስና በከፍተኛ ሁኔታ ለሥርዓቱ አደጋ ሆኖ መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡ ይህ አደጋ ደግሞ የሥርዓቱ ብቻ አይደለም የአገሪቱም ነው፡፡ እናም አቶ ስብሀት ሥርዓቱ በሙስና ዙሪያ ኃላፊነቱን በብቃት እንዳልተወጣ በማያሻማ ቋንቋ አስቀምጠውታል፡፡ ሥርዓቱ ቁርጠኛ ሌቦችን ነው የሾመው ማለታቸው ነው፡፡ እስከዚህ ድረስ በሥርዓቱ ውስጥ ያሉትን ሌቦች ያውቋቸዋል ማለት ነው፡፡ አሁን እኮ የቀራቸው ሥም መጥራት ብቻ ነው፡፡ ሥርዓቱ አውቆና ፈቅዶ ሙሰኞችን ቸል እንዳላቸው ነው የገለፁት፡፡ ሥርዓቱ በዚህ ደረጃ ሙስና አደጋ ሆኖብኛል እስከሚል ድረስና ተደጋጋሚ የሙስና ወንጀል የሚፈፅሙ ሰዎች እንዳሉ እየታወቀ እነዚህን ሰዎች ተከታትሎ ህጋዊ በሆነ መንገድ እንዲቀጡ ማድረግ የሚያስችል ሥራ ሲሰራ አይታይም” ብለዋል፡፡

“ቁርጠኝነት ማለት ሙስና የሚሰሩ ሰዎች እንዳሉ ማወቅና ማመን ብቻ አይደለም” ያሉት አቶ ሙሼ፤ ሙሰኞችን አግባብ ባለው ህጋዊ ሥርዓት ለፍትህ ሥርዓቱ አቅርቦ ቅጣት እንዲያገኙና ሌሎች እንዲማሩበት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ የሞራል ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ቃለመሃላም የፈፀሙበት ጉዳይ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣናቸውን ሲረከቡ ቃለመሃላ ከፈፀሙባቸው ጉዳዮች አንዱ የህዝብን ሃብት የመጠበቅ ሃላፊነት ነው፡፡ የተጠያቂነትም ጉዳይ አለበት፡፡ ሙስና ሰዎችን በመቅጣትና በማሰር ብቻ የሚፈታ ጉዳይም አይደለም፡፡ ሥርዓትን በመዘርጋት ነው፡፡ ለሙስና በር የሚከፍቱ ቀዳዳዎችን ሁሉ በመዝጋት፡፡ ሥርዓቱ ችግር ፈቺ ሆኖ ቢዘረጋ ሰዎች ወደ ሙስና እንዲሄዱ በር አይከፍትም፡፡ እናም “ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው” እንዲሉ አቶ ስብሀት ጉዳዩን በትክክለኛ ቋንቋ ያስቀመጡት ይመስለኛል ብለዋል፡፡

ሙስናን በማጥፋት ሂደት ውስጥ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ወሳኝነት አስመልክተው ሲናገሩም “በእርግጥ ህብረተሰቡ በዚህ ትግል ውስጥ የሚኖረው ተሳትፎ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፤ ሆኖም ሙስናን በመታገል ሂደት ዜጐች ምን ዋስትና አላቸው በሚባለው ደረጃ ሙስና ካለ ኔትዎርክ አለ ማለት ነው፡፡ ሙሰኞቹን አሳልፎ ለመንግስት ሲሰጥ ነገ በራሱና በቤተሰቦቹ ላይ ለሚደርስ አደጋ ምን ዋስትና አለው፡፡ ሙስናን መታገል እኮ የአርበኝነት ጉዳይ አይደለም፡፡ ስለዚህም ህብረተሰቡ ዋስትና የሚያገኝበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባዋል፡፡ ህጐች መመሪያዎች ደንቦች መውጣት አለባቸው፡፡ ሙሰኛ ባለስልጣናቱን በማሰር ማሳየት አለበት፡፡ አቶ ስብሀትም ቢሆኑ እንደ አንድ ዜጋ የሚያውቋትን ነገር ለኮሚሽኑ ማቅረብ ይገባቸዋል፡፡ ለዜጐች የሰጡትን ኃላፊነት እሳቸውም መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ አስተያየታቸው ፓርቲውን የማይወክልና የግላቸው መሆኑን ጠቁመው እሳቸው በስልጣን ላይ በነበሩበት ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ ሙሰኝነት በሥርዓቱ ውስጥ እየታየ መምጣቱን መስማታቸውን አስመልክተው ለጠቅላይ ሚኒስተሩ መግለፃቸውን ተናግረው በወቅቱ ምንም አይነት እርምጃ ሳይወስድ በመቅረቱ ሙስናው እየተስፋፋ መሄዱን ገልፀዋል፡፡ “አሁን እየተደረገ ያለው ኢህአዴግን ስልጣን ላይ ለማቆየት ራሳችንን የማጥራት ሥራ እየሰራን ነው ለማለት ያህል ነው፡፡ እስከ አሁን ድረስ በሆኑት ጉዳዮች ሁሉ ሊጠየቁበት ይገባል፤ ኢህአዴግ በቅቶታል በቃ አልቻለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግስት ሌቦች አሉ በማለት አሁን ገና ነው የነገሩን፤ ይህንን ሁኔታ ግን እኔ ከ10 ዓመት በፊት ነግሬአቸው ነበር፡፡ ለሙስናው መስፋፋት ዋንኛው ምክንያት ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድ አለመቻሉ ነው፡፡ በራሳቸው ሰዎች ላይ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ አለባቸው” ብለዋል፡፡ ሙስናን ለማስወገድ ዋንኛ መፍትሄውም ሲስተማቲክ ሥርዓትን መዘርጋት እንደሆነ ዶ/ር ነጋሶ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

የኢህአዴግ ባለስልጣናት እንደዚህ እውነት ሲናገሩ መስማት ጥሩ ነው ያሉት ብቸኛው የፓርላማ ተመራጭና የመድረክ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ በበኩላቸው፤ “ሙስናን ለማጥፋት አቶ ስብሀት እንዳሉት የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል፡፡ የፖለቲካ ቁርጠኝነቱ ቢኖር የመንግስት ሌቦችን ማስወገዱ እምብዛም አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ ቁርጠኛ የሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ቁርጠኛ ሌቦች መኖራቸውን ካወቀ ጠራርጐ ያስወጣል ወይም እራሱ ይወጣል” ብለዋል፡፡ ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል የሚለው የድሮው ተረት ተግባራዊ መሆን የጀመረው አሁን ይመስለኛል ያሉት አቶ ግርማ ሰይፉ፤ ሹመኞች ሥልጣን ላይ ባሉ ጊዜ ዘርፈው ለመውጣት ተዘጋጅተዋል ብለዋል፡፡ “በአግባቡና በሥርዓቱ ሥራቸውን ማከናወን የሚፈልጉ ባስልጣናት እንኳን ቢኖሩ እየፈሩ ስራቸውን አይሰሩም፡፡ ህዝቡ አገልግሎት ማግኘት አልቻለም፤ በሁለት በኩል ስለት ባለው መጋዝ እየተገዘገዘ ነው” ሲሉም ተናግረዋል - አቶ ግርማ፡፡

በ1997 እና 1998 የሙስና ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው ሰዎች ዛሬ እየተከሰሱ ነው ይህ ነገር እስከ አሁን ሳይታወቅ ቀርቶ አይደለም የሚሉት በፓርላማ የመድረክ ተወካዩ፤ ምክንያት እየተፈለገ ብቻ ያልፈለጉትን ለማስወገድ የሚሰራ ነገር መቅረት አለበት” ብለዋል፡፡ በሃይማኖት ተቋማትም ሙስና እንደነገሰ አቶ ስብሃት የተናገሩትን የጠቀሱት አቶ ግርማ፤ “እሱን ለምእመኑ ቢተውለት ጥሩ ነው፡፡ በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ ምእመኑ የራሱን እርምጃ በመውሰድ ሙስናን የሚታገልበት መንገድ አለው፡፡ ምእመኑ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ሙስና አለ ብሎ ካመነ እኮ በቃ ሙዳየ ምፅዋቱን መስጠት ማቆም ይችላል፡፡ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ሙስና ተንሰራፍቷል ብሎ ግን ግብር መክፈሉን ማቆም አይችልም” ሲሉ በማነፃፀር ገልፀዋል፡፡

በፀረ ሙስና ትግሉ ውስጥ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ወሳኝነት አስመልክተው ሲናገሩም፤ “በእርግጥ የሕዝቡ ተሳትፎ የመፍትሄው አካል ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ህብረተሰቡ ምን ዋስትና አለውና ነው በቁርጠኝነት ሙስናን ለመዋጋት የሚችለው፡፡ በግራንድ ኮራፕሽን (በትላልቅ ሙስናዎች) እኮ ሙሰኛው ማሰር ማሳሰር ሁሉ ይችላል፡፡ እስር ቤት፣ ስልጣን በእጁ ነው የፈለገውን ማድረግ ይችላል” ያሉት አቶ ግርማ፤ ህብረተሰቡ ለደህንነቱ ዋስትና ሊያገኝ በማይችልበት ሁኔታ በፀረ ሙስና ትግሉ ውስጥ ተሳትፎ ማድረግ ይገባዋል ማለቱ አግባብነት ያለው ነው የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልፀዋል፡፡

በፀረ ሙስና ትግሉ ውስጥ የፖለቲካ ቁረጠኝነት መኖሩ ዋንኛውና መሰረታዊው ጉዳይ መሆኑን የገለፁት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ፤ ለዚህ ደግሞ ከመንግስት ብዙ እንደሚጠበቅና ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለውን ሙሰኝነት ቆርጦ ሊዋጋ እንደሚገባው አስገንዘበዋል፡፡

 

 

 

Read 11457 times Last modified on Monday, 05 March 2012 15:36