Saturday, 28 May 2016 16:18

መንግስት ቢዝነስ ውስጥ ሲገባ፣ በወረፋ ይታጀባል (በአሜሪካም?)

Written by  ዮሃንስ . ሰ.
Rate this item
(9 votes)

የትራንስፖርት ደህንነት ኤጀንሲን ተመልከቱ - የአሜሪካ ኤርፖርቶችን በወረፋ አጨናንቆ
እያተራመሳቸው ነው።
   የአሜሪካ፣ የትራንስፖርት ደህንነት ኤጀንሲ ኤርፖርቶችን በወረፋ አጨናንቆ እያተራመሳቸው ነው።
በትልልቅ ኤርፖርቶች ላይ፣ ፍተሻና የፀጥታ ቁጥጥር የማካሄድ ስልጣን የተሰጠው የአሜሪካ
የትራንስፖርት ደህንነት ኤጀንሲ፤ ከሌሎች የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሁሉ የሚበልጥ ልዩ ስልጣን
አለው።
ያው፣ እንደሌሎቹ መስሪያ ቤቶች፣ የኤጀንሲው ስልጣኖችና ስራዎች፣ በአዋጅ ተዘርዝሯል። ነገር
ግን፣ ኤጀንሲው ሌላ ‘ልዩ ስልጣን’ ተጨምሮለታል - ይላል ታይም መፅሄት።
ምን የሚሉት ስልጣን ይሆን? ኤጀንሲው፣ “በዝርዝር የተገለፁትን ስራዎች የመፈፀም፣ እንዲሁም ንደአስፈላጊነቱ ሌሎች ስራዎችን የማከናወን ስልጣን አለው የሚል ሃሳብ የያዘ አንቀፅ በአዋጅ
እንደፀደቀ መፅሄቱ ገልጿል። በቃ፣ ይሄው ነው፡፡ ለኤጀንሲው ልዩ ስልጣን ተጨምሮለታል ሲባል፣
ሌላ ነገር አይደለም። ‘እንደ አስፈላጊነቱ’ የሚል ቃል ተጨመረለት ብለን ልናሳጥረው እንችላለን።
እና፣ ይሄው ነው ልዩ ስልጣን ማለት?
እንደአስፈላጊነቱ የሚል ቃል፣ እንዴት ብርቅ ይሆናል? ለአሜሪካ ብርቅ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ
ግን፣ “እንደአስፈላጊነቱ” የሚል ቃል ያልያዘ አዋጅ የለም ማለት ይቻላል። የስልጣኔ ልዩነት እዚህ
ላይ ነው።
‘እንደአስፈላጊነቱ’ በሚል ቃል የታጀበ ስልጣን፤ ልጓም የሌለው ወይም ገደቡ የማይታወቅ፣ መረን
የለቀቀ ስልጣን ነው። ይህን ስልጣን የያዘ ሰው፣ ያሻውን ነገር የማድረግ እድል ይኖረዋል። ምንም
ነገር ቢፈፅም፤ እንደ ስህተትና እንደጥፋት ሊቆጠርበት አይችልም። ከቁጥጥር ውጭ ነው።
ባለስልጣንን መቆጣጠር የሚቻለው፤ “በዝርዝር ከተሰጠህ ስራ እና ስልጣን እንዳትወጣ” በሚለው
መርህ ነው፡፡  “ከተፈቀደልህ ነገር ውጭ፣ ሁሉም ነገር ክልክል ነው” እንደማለት ነው። በዚዚያ
መንግስት፣ የህግ ተገዢ ይሆናል፡፡ አሳዛኙ ነገር፤ ይህንን መርህ በቀላሉ ማፍረስ ይቻላል፡፡ እንዴት?
“እንደአስፈላጊነቱ” የሚል የስልጣን ምርቃት፣ አዋጅ ውስጥ በመጨመር ነዋ። በቃ፤ መንግስት፣
“አስፈላጊ የመሰለህን ነገር መወሰንና ማድረግ ትችላለህ” ተብሎ መረን ይለቀቃል።
እንዲህ አይነት ልቅ ስልጣን በአሜሪካ አልተለመደም። እና፣ የትራንስፖርት ደህንነት ኤጀንሲ፣
እንዴት ልዩ ስልጣን ተሰጠው? እንዴት፣ “እንደ አስፈላጊነቱ” የሚል ቃል ተመረቀለት? ታይም
መፅሄት እንደሚለው፤ በኒውዮርክና በዋሺንግተን የደረሰው የአሸባሪዎች ጥቃት ነው ሰበቡ። በዚያ
ቀውጢ ጊዜ፣ በግርግር መሃል ነው፣ ለኤጀንሲው ልዩ ስልጣን የተሰጠው። ከዚያማ፤ ማን ይንካው?
ለተቆጣጣሪ ለኦዲተር አስቸገረ።
ሌሎች መስሪያ ቤቶች፣ እንደ ወጉ፣ በጀታቸውን ለምን ለምን እንዳዋሉት፣ በዝርዝር የማስረዳት ግዴታ አለባቸው። የትራንስፖርት ደህንነት ኤጅንሲ ግን፣ ይሄ አያስጨንቀውም። በዝርዝር ለማስረዳት አይገደድም። “እንደአስፈላጊነቱ” የምትለዋን አንቀፅ ይጠቅሳል። 4 ቢሊዮን ዶላር...
ለቁሳቁስ፣ ለደሞዝ፣ ለእንትን፣ ለምንትስ ወጪ አድርጌያለሁ፣ ብሎ ከዘረዘረ በኋላ፣ ሌላ 2 ቢሊዮን
ዶላር ደግሞ፣ በደፈናው ‘እንደአስፈላጊነቱ’ ተጠቅሜበታለሁ ይላል።ለነገሩ፣ በዝርዝር ኤጀንሲው ለኦዲተርየ ሚያቀርባቸው ስራዎችና ወጪዎችም፣ ጤና የላቸውም። የኤርፖርትን ፍተሻ ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አሸጋግራለሁ በማለት በዘመቻ የገዛቸው ቁሳቁሶች ውጤታማ እንዳልሆኑ ታይም መፅሄት በምሳሌነት አቅርቧል።ከአስር አመት በፊት፣ በ37 ኤርፖርቶች አዳዲስ በኤጀንሲው እንደተተከሉ የዘገበው ታይም
መፅሔት፣ ማሽኖቹ አየር ስበው በማስገባት የንጥረነገር ብናኞችን የሚመረምሩ እንደሆኑ ይገልፃል።
የፈንጂና የቦምብ ቁሳቁሶችን የነካካ ሰው፣ በማግስቱ አውሮፕላን ለመሳፈር ቢመጣ፣ ጉዱ ይፈላል።
ከመንገደኞች ልብስ ላይ ብናኞችን ስቦ እየወሰደ የሚመረምረው ማሽን፣ የቦምብ ወይም የፈንጂ
ጥቃቅን ብናኞችን ለይቶ ማወቅ ይችላል…ተባለ...።
ግን ብዙም አልቆየም፡፡ በኤጀንሲው የተተከሉት ማሽኖች በሙሉ ተበላሽተው ከአገልግሎት ውጭ
ሆነዋል። ማሽኖቹ ተገዝተው መምጣታቸውን ለማብሰርና ሪፖርት ለመፃፍ የሚቸኩል ባለስልጣን
እንጂ፣ በእርጥበትና በአቧራ እንዳይበላሹ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልጋቸው የሚያስታውስ ባለስልጣን
አልተገኘም፡፡ በቃ፣ ለማሽኖቹን ለመግዛት የወጣው? 30 ሚሊዮን ዶላር፣ በአንድ ሳምንት ሆይ
ሆይታ ቀልጦ ቀረ።
ግን በመቶ የሚቆጠሩ ሌሎች ‘አስተማማኝ መሳሪያዎች’ ተገዝተው መጡ። የፍተሻ ስራዎችን
በእጅጉ ያቃልላሉ የተባሉት እነዚህ አዲስ መሳሪያዎች በየኤርፖርቱ ተተከሉ። ምንድናቸው ሲባል፣
ለካ እርቃንን የሚያሳዩ መሳሪያዎች ናቸው። ባለስልጣናት ያማቸዋል? ጉድ ተባለ። እንደዚያ ‘ቁጣ
ይደርስብናል’ ብለው አላሰቡም - የኤጀንሲው ሃላፊዎች። ችግር የለውም፡፡ ከኪሳቸው የወጣ ገንዘብ
የለም፡፡ ‘እንደአስፈላጊነቱ’ በ40 ሚሊዮን ዶላር የተገዙት መሳሪያዎች፣ ተነቅለው ወደ ቆሻሻ መጣያ
ተወረወሩ።
ታዲያ በዚሁ ጊዜ፤ ኤጀንሲው ሃላፊዎች ጎን ለጎን ሌሎች አዳዲስ መሳሪያዎችን ለመትከል ዘመቻ
እያካሄዱ ነበር። ፍቱን መድሃኒት ተገኘ ሲሉም አበሰሩ። በቃ፣ ከእንግዲህ፤ “አሸባሪና ወንጀለኛ...
በኤርፖርት ውስጥ መፈናፈኛ አያገኙም” ተባለ። መሳሪያዎቹ፣ የተወራላቸው ያህል፣ ዋጋቸውም
ከፍተኛ ነው። እነዚህ አዳዲስ መሳሪያዎችን ለመትከል፣ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ
እንደተደረገ ታይም ገልጿል። ለመሆኑ ይሄ ተአምረኛ ቴክኖሎጂ፣ እንዴት ነው አሸባሪዎችን
መንጥሮ የሚያወጣው?
የሰውን የፊት መልክና ገፅታ፣ የአካል እንቅስቃሴና አኳሃን በካሜራዎች እየቃኘ፣ እዚያው በዚያው፣
ወዲያውኑ አሸባሪዎችን መንጥሮ የሚያወጣ የረቀቀ ቴክኖሎጂ ነው። ስለዚህ ...ጫማ እና ቀበቶ
እያስወለቁ መፈተሽ፣ ከእንግዲህ ተረት ሆኖ ይቀራል። እንደ ድሮ፣ የፍተሻ ሰራተኞችን በብዛት
እያሰለጠኑ መቅጠር አያስፈልግም። እንዲያውም፣ አሁን ያሉትንም ፈታሾች መቀነስ ይቻላል  
ተባለ፡፡ ምን ዋጋ አለው? የቢሊዮን ዶላር የወጣባቸው መሳሪያዎች፣ ውጤታማ አልሆኑም።  በርካታ
አሸባሪዎች ማንነታቸው ሳይታወቅ በተደጋጋሚ ለማለፍ ችለዋል። ይህም ብቻ አይደለም።
ቦምና ጦር መሳሪያ ደብቆ ለመግባት የሚፈልግ መንገደኛ ከመጣስ፣ በአዲሱ ቴክኖሎጂ ምክንያት
እንቅፋት ይገጥመዋል? ፍተሻውንስ ማለፍ ይችላል? ይሞከራ!
ሙከራው እንዲህ ነው። በሚስጥር የተመደቡ መርማሪዎች፣ እንደ መንገደኛ ሆነው ወደ ኤርፖርት
ይገባሉ። ባዶ እጃቸውን አይደለም። ቦምብ ወይም ጠመንጃ በድብቅ ለማሳለፍና ወደ አውሮፕላን
ለመሳፈር ነው የሚሞክሩት። አስገራሚው ነገር፣ ከ70 ሙከራዎች መካከል፣ 67ቱ ተሳክቶላቸዋል።
ሦስቱ ብቻ ናቸው በፍተሻ የተገኙት። በየኤርፖርቱ፣ ያ ሁሉ አዲስ መሳሪያ የተተከለውና ቢሊዮን
ዶላር የፈሰሰው፤ በከንቱ እንደሆነ ዋና ተቆጣጣሪው በግልፅ ተናግረዋል። ነገር ግን፣ ኤጀንሲው
ሃሳቡን አልቀየረም። እነዚያኑን መሳሪያዎችን የመትከል ዘመቻው አልተቋረጠም። ገንዘብም እየወጣ
ነው። ምን ይሄ ብቻ።
መሳሪያዎች በብዛት ስለተተከሉ፤ የፍተሻ ሰራተኞችን ማሟላት ያን ያህልም አስፈላጊ መስሎ
አልታያቸውም - ለኤጀንሲው ሃላፊዎች። ግን ደግሞ፣ መሳሪያዎቹ ውጤታማ ስላልሆኑ፣ ፍተሻው
ሊቀር አይችልም። የፍተሻ ሰራተኞች ደግሞ አልተሟሉም። እናማ፣ ይሄውና ሰሞኑን፣ የአሜሪካ
ኤርፖርቶች፣ በወረፋ ተጨናንቀው ሰንብተዋል። አየር መንገዶች፣ በወረፋ የዘገዩ ተሳፋሪዎችን
ለመጠበቅ የበረራ ሰዓታቸው እየተዛባ ተቸግረዋል። እንደዚያም ሆኖ፤ በአምስት ወራት ውስጥ 70ሺ
ተሳፋሪዎች፣ በረዥም የፍተሻ ወረፋ ሳቢያ፣ በረራ አምልጧቸዋል። ተፈትሾ ለመግባት የሁለት ሰዓት
የሦስት ሰዓት ወረፋ! የትም አገር ቢሆን፣ መንግስት ቢዝነስ ውስጥ ሲገባ፣ በሃብት ብክነትና
በወረፋ ይታጀባል።
የኤጀንሲው፣ ምላሽ ደግሞ ያዝናናል። ስለወረፋው ተጠይቀው የኤጀንሲው ሃላፊ በሰጡት መልስ፤
የመንገደኞች የጉዞ ባህርይ፣ ኤርፖርቶችን ያጨናንቃል ሲሉ ተጓዦችን ወቅሰዋል። የመፍትሄ
ሃሳብም አቅርበዋል።
አንደኛ ነገር፤ መንገደኞች፣ ከአንድ በላይ ቦርሳ ወይም ትልቅ ሻንጣ ከመያዝ ቢቆጠቡ፣ ወረፋው
ይቃለላል። ሁለተኛ ነገር፣ እኛ ወረፋ ለማሳጠር ብለን የኤርፖርትና የአውሮፕላን ደህንነትን ለአደጋ
አናጋልጥም፤ መንገደኞች ሦስት አራት ሰዓት ቀደም ብለው ኤርፖርት ቢደርሱ ችግሩ ይቃለላል
ብለዋል - የኤጀንሲው ሃላፊ።
እዚህ አገራችን ውስጥ፣ የታክሲ እጥረት ሲፈጠር፣ የመንግስት የሚሰጡትን አስተያየት አስቡት፡፡
ራሳቸው የፈጠሩትን ችግር፣ ህዝቡ ላይ በማላከክ እንዲህ ሲሉ ይታያችሁ፡፡ አንደኛ ነገር፣ ህዝቡ
በእግር የመጓዝ ልመድ ማዳበር አለበት። ሁለተኛ ነገር፣ በማለዳ 11 ሰዓት ገስግሶ ከቤት የሚወጣ
ከሆነ፣ የስራ መግቢያ ሰዓት ላይ የታክሲ ጭንቅንቅ ይቃለላል የሚል መፍትሄ እንደመስጠት ነው።
ለነገሩ፣ የአገራችን ባለስልጣናት፣ ከዚህም የባሰ አስተያየት ይሰጣሉ፡፡ እንዲህ አይነት አሳፋሪ ነገር
በአሜሪካም መታየቱ ግን ያስገርማል፡፡ “የራሱን ጥፋት፣ በዜጎች ላይ ማላከክ፣” ባለስልጣናትን
የሚያጠቃ በሽታ ነው ልበል?
መጥፎነቱ ደግሞ ምን መሰላችሁ? የአሜሪካ መንግስት፣ ቢዝነስ ውስጥ የሚገባው፣ በጥቂት ቦታዎች
ነው። በዚህ ምክንያት የሚፈጠረው ትርምስም ጥቂት ይሆናል፡፡ እኛ አገር ግን፣ መንግስት የማያቦካውና የማያማስለው የሕይወት መስክ የለም። በቃ፣ እዚህም እዚያም ውጤት የሌለው ፕሮጀክት፣ የቢሊዮን ዶላሮች ብክነት፣ ወረፋና እጥረት፣ ሙስናና የአየር በዓየር ጨዋታ በየመስኩ ይበራከታል። ለዚህ ሁሉ ጥፋት፣ ተጠያቂዎቹ ደግሞ፣ ያው ዜጎች ይሆናሉ።






Read 3526 times