Saturday, 04 June 2016 11:57

ደራሲዎችና ፖለቲካ

Written by  ተፈራ ወልደመድህን
Rate this item
(1 Vote)

በየትኛውም አገር ያለ ደራሲ ያገሩ ጉዳይ ያሳስበዋል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ደራሲ ስለሆነ ሳይሆን ሰው ስለሆነ ነው፡፡ የአገሩ ጉዳይ እምሽክ ድቅቅ የሚያደርገው ደግሞ ደራሲ ወይም አርቲስት ስለሆነ አይደለም፡፡ ደራሲ ግን ከግብዝነት በመነጨ ይሁን በፃፈው ድርሰት ሰበብ፣ ሃሳቡ ሰው ጋር ስለሚደርስለት እንደሆነ አላውቅም፣ ከሁሉም የበለጠ የአገር ተቆርቋሪ ለመምሰል ይጥራል፡፡ ግን ገበሬው ፣ ነጋዴው፣ ሃይማኖተኛው ሌላው ሁሉ አቅሙ በፈቀደ ልክ ለአገር ይቆረቆራል፡፡  ልዩነቱ ደራሲ በማይሞተው ብእሩ አሳቡን ይከትበዋል፡፡ አንዳንዱ የሚፅፈው ከራሱ አፍልቆ ሳይሆን ከህብረተሰቡ ወስዶ ነው፡፡ ቃላቱን አሳካክቶና የራሱን ጨምሮ ወይም መፅሐፍ ወይ መጣጥፍ ያደርገዋል፡፡ ስህተት ነው እያልኩኝ አይደለም፡፡
 ሀቀኛ ደራሲ የህዝብ አፈ ጉባኤ ነው ይሉ ነበር አብዬ መንግስቱ ለማ ፡አብዬ መንግስቱ የአባቴ ጓደኛ ነበሩ፡፡ የሩቅ ነው እንጂ ዝምድናም አለን፡፡ የአባቴ ጓደኛ በመሆናቸው ያወቅኋቸው ተሰምተው የማይታወቁ ገራሚ ትዝታዎች አሉኝ፡፡
 ከሚፈጥሯቸው ገፀ ባህርያት በላይ በአካል ሲያገኙዋቸው ይበልጥ ያስቃሉ የሚባልላቸው አብዬ መንግስቱ፤ “ደራሲና ፖለቲካ ግንኙነት ከፈጠረ ኮራፕት ይሆናል ባይ ነበሩ፡፡ አባቴ “አንተ መቼ ነው እንደፀጋዬ ገብረ መድህን በብእርህ የምትታገለው፤  ፊውዶ ቡርዣውን የምትቃወመው?” ሲላቸው፤ “ሰርቶ አደር ጋዜጣ ምን ሰርቶ ይደር” ብለውታል፡፡ ጋዜጣው የደረግ ልሳን ነበር፡፡ ደራሲ ከዚህ መዝለል እንዳለበት ለመግለፅ ይመስለኛል  እንደዚያ በአሽሙር ጎንተል ማድረጋቸው፡፡ “ያለፈው ስርዓት በህዝቡ ላይ ስላደረሰው በደል አትፅፍም ወይ?” ተብለው ሲጠየቁ፤ “የሞተ ሬሳ ስደበድብ አልውልም ” ብለዋልም ይባላል፡፡ እነ  ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህንና አያልነህ ሙላቱ፤ ለኢሰፓአኮ ምስረታ ግጥም ሲፅፉ፣ እሳቸው ሆዬ ዝም ብለው አብዮቱን ሸወዱት፡፡    አንድ ነገር ልብ በሉልኝማ! በደርግ ዘመን ሳንሱር ሲያደርግ የነበረው ጋሽ አያልነህ፤ አሁን የሚያሲዛቸው” ቁጥር አንድ ተበዳይ ሆኖ በየሚዲያው ሲደሰኩር አልታዘባችሁም? አባቴማ ገርሞት ገርሞት ገርሞት ሊሞት! “የመንግስቱ ለማ መሞት ስንቱን ጎዳ? እሱ ቢኖር አፋቸውን ነበር የሚያሲዛቸው” አለኝ፡፡ ወርቃማው ገጣሚ ደበበ ሰይፉ ይምጣብኝ፡፡ ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ፡፡  ደርግን ወደቀ ብሎ በብእሩ ሳይዘነጥነው ያለፈ፡፡ እኔም “ትውልድ ይዘምረው  ያንተን እንጉርጉሮ” ብያለሁ፡፡
 ከርዕሴ ወጣሁ እንዴ? አልወጣሁም ፡፡ ስለ ደራሲዎችና ፖለቲካ ልፅፍ ስነሳ፣ ከላይ የተጠቀሰው ሃሳብ ትዝ ብሎኝ ነው፡፡ አነሳሴ ግን ስለ እዚህ ዘመን ደራሲዎች ለመፃፍ ነው፡፡
 የድሮዎቹ ወላ ፀጋዬ ፣ ወላ አያልነህ ገብቷቸው ነው የሚፅፉት፡፡ የአሁን ዘመን ደራሲ ግን ብዙዎቹ ዝም ብለው ነው የሚዘባርቁት፡፡ ተስፋዬ ገብረአብ ይምጣብኝ አቦ፡፡ አለማየሁ ገላጋይ በአንድ ጋዜጣ ላይ አሪፍ አርጎ በብእሩ እንደገሸለጠው፤ “ተስፋዬ ከሚበጀው የሚፋጀው ይበዛል”  ልክ ነው፡፡ ግን ተስፋዬ አላማውን ያውቃል፤ አፈርሳለሁ ካለ ቢያንስ ይሞክራል፡፡
 ከነከሰ አይለቅም፡፡ አሁን በዚህ ዘመን ያሉት ብዙዎቹ ደራሲዎች ግን ፖለቲካቸው ቅድም እንዳልኩት ነው፡፡ ቀንድ እነክሳለሁ ብለው ጆሮ ይጠባሉ፡፡ ለህዝቡ ተቋርቋሪ ለመምሰል ይሁን የሚሰጣቸው ክፍያ አጓጉቷቸው የማውቀው ነገር ባይኖርም፡፡ የዚህ ዘመን ፀሐፊዎች ከጥቂቶች በስተቀር አይመቹኝም፡፡
  እኔ ወይ እንደ መንግስቱና ስብሀት አርፎ መቀመጥ ወይ ደግሞ እንደ ፀጋዬ የሚደግፉትን መደገፍ የሚቃወሙትን መቃወም ብዬ አስባለሁ፡፡ እውነት ከጋሽ አያልነህ ሙላቱና ከማሞ ውድነህ ይሄ ትውልድ መውረስ የሌለበት አድር ባይነትን ነው፡፡ ይህን ሁሉ የምዘበዝበው ብዙዎቹ የአገራችን ደራሲዎች፣ ፖለቲካን በተመለከተ “ዱካክ” ላይ ናቸው ለማለት ነው፡፡
መቃዥት አሁንም መቃዥት፤ የቃዡትን ይፅፋሉ፡፡ አንድ ደራሲ ስለተከፈለው፣ ለከፈለው አካል ሲል ይጮሀል፡፡ (ውሻ በበላበት ይጮሀል፡፡) ሌላ ሰው የተሻለ ሲከፍለው እንጀራዬ ነው ብሎ ይጮሀል፡፡
ምሳሌዬን እዩልኝማ፡፡ በአንድ ወቅት ደራሲና ኃያሲ አለማየሁ ገላጋይ - “ኢህአዴግን እከሳለሁ” አለ፡፡  ምን ብሎ ነው፤ የየትኛውን የህገ መንግስት አንቀጽ ጠቅሶ ነው የሚከሰው ብለን ተስገብግበን መፅሐፉን አኝከን በላነው፡፡ መቼም አማርኛን  ከዮሐንስ አድማሱ ቀጥሎ እንደሱ የሚጠቀምበት የለም አስብሎኛል፡፡ ጉድ ነው፤ ጉድ ነው ስንል የታሪክ ተመራማሪ ብርሃኑ ደበጭ መጣና፤ ቤተ ክርስቲያን የገባ ውሻ አደረገው፡፡ቀላል ተላጠበት፤ ጓደኞቹ አፏጩ፡፡ የእነሱም ጉድ እንዳይወጣባቸው ነው እንጂ አሁን ምን ያንጫጫቸዋል፡፡  እኔ እራሴ አለማየሁ ገላጋይ የኢህአዲግ አንደኛ ጋዜጣ በሆነው “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” ላይ ይፅፍ እንደነበረ ያወቅሁት ብርሃኑ ካጋለጠው በኋላ ነው፡፡ ጓደኞቹ ምን አለበት; ይሄ የድሮ ታሪክ ነው ገለመሌ አሉት፡፡
ጓደኛዬ፤ “ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም፤ ምድረ የባንዳ ዘር ብሎ መሳደቡን ሲያቆም እኛም ከእሱ አናት ላይ እንወርዳለን” ብሎ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” ጋዜጣ ላይ የፃፋቸውን ልማታዊ ድርሰቶች፤ ፎቶ ኮፒ አድርጎ አባዝቶ ሰጠኝ፡፡
ካነበብኳቸው በኋላ “ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት አይጠፋም አልኩት፡፡ እሱ ምን ያለኝ ይመስላችኋል የመፅሀፉ ርዕስ “ ኢህአዲግን እከሳለሁ” አይደል የሚለው? ለምን ርዕሱን “ኢህአዴግ አባቴን የክፉ ቀን ጓዴን እከሳለሁ አላለም?” አለኝ፡፡ በወቅቱ ጋዜጣው ላይ የሚፅፉ አንዳንድ ፀሐፊዎች፤ “ኢህአዲግ ዲሞክራሲ መኖሩን ለማረጋገጥ ፃፉ ፃፉ” እያላቸው ነው ተብሎ ይወራ ስለነበር፣ መጠራጠሬን አልክድም፡፡
ጠርጥር ከገንፎ አይጠፋም ስንጥር፡፡
 ደራሲና ኃያሲ አለማየሁ ገላጋይ ከ1990 እስከ ምርጫው ዋዜማ ድረስ ባሉት አመታት አብዮታዊ ዲሞክራሲ ጋዜጣን ሲያሾረው ደግሞ ከዚያ ወጣና ደግሞ መንግስት ባቋቋማቸው በግል ጋዜጦች ላይ ሲቀጠር፣ እሱ ሲዘጋ ደግሞ በሌላ በተቃዋሚ ፓርቲ ጋዜጦች ላይ ልማታዊ ያለውን መንግስት ሲከሸክሽ ኖረ፡፡
እኔ አብዮታዊ  ዲሞክራሲያዊ ጋዜጣ ላይ መፃፍ ነውር ነው እያልኩ አይደለም፡፡ ማንም ሰው መብቱ ነው፡፡ መንግስትም ሆነ ግለሰብ ታማኝ ጋዜጠኞቹን የት ማስቀመጥ እንዳለበት ያውቃል፡፡ ስለዚህ ጋዜጣው ላይ በመፃፉ ሳይሆን በተከታታይ ባደረጋቸው  ያመለካከት ለውጦች ላይ ግን ጥርጣሬ አለኝ፡፡     አንድ ጊዜ ኃያሲ አለማየሁ “የታሪክ ግርዶች የወደቀባቸው ዘፈኖች” የሚል ርዕስ በሰጠው ፅሁፉ ላይ (ሐምሌ 30 1995) “እደ እኔ አመለካከት ኪነ ጥበብ ማህበረሰቡን በታሪክ ድሪቶ የሚሸፍን ግርዶሽ ሳይሆን ተጨባጩን የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ያገናዘበ ለአገር ልማት ጠብታ አስተዋፅኦ የሚያበረክት መሆን አለበት” አለ፡፡
እሱ ነው ያለው እንግዲህ፡፡ ይሄ መብቱ ነው፡፡ በጥጥ የልጆች ልብስ ይሰራል ለመድፍ መስሪያነትም ያገለግላል፡፡ ዜና ኪነ ጥበብ ማንኛውም ነገር ልክ እንደዚሁ ነው፡፡ ግን ኪነት ላብዮቱ ካሉት ከነ ጋሽ አያልነህ ይሄ አመለካከት በምን ያንሳል፡፡ ኪነ ጥበብ ለልማት ይዋል ታሪክ ድሪቶ ይህ ታዋቂ ሀያሲ ተገለባብጦ “እንደ ስብሀት ገ/እግዚአብሔር ፃፉ ፣ እንደ ሰለሞን ደሬሳ ፃፉ ፣ እንደ አዳም ረታ ጥበብ ለጥበብነቱ ብላችሁ ተፈላሰፉ” ብሎ በዚህ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ስንቴ ነው የወተወተን? አቦ አታደናግሩን፡፡ ደግሞ እኮ ኪነ ጥበብ ለልማት ቢውል ምን ችግር አለው? ከሀዲስ አለማየሁ በላይ አሪፍ ደራሲ አለ? እንደሳቸው ለአገር ተቆርቋሪ ምርጥ ፖለቲከኛ አለ? የጋሽ ሀዲስ አለማየሁን ስም አነሳሁ እንዴ? ካነሳሁ ጥሩ ነው፡፡ እግረ መንገዴን ደራሲ ኃያሲ አለማየሁ፤ ዛሬ እንደዚህ “እሳቸው ከስብሀት አይበልጡም” እያለ ከማወዳደሩ በፊት እንዲህ ብሎ ያሞካሻቸው ነበር፡-
     “አገራችን ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር፣ የክቡር አዲስ አለማየሁ መንገድ ተስማሚ መድኃኒት ይመስለኛል፡፡ ስነ ፅሁፍም ከህዝባዊ ፋይዳ አንፃር ተመልክቶ ግልጋሎቱን ለአገር እድገት ማዋል ተገቢ ነው፡፡ ይህም ክቡር ሃዲስ የተቆናጠጡትን እርከን የሚያጋራ ይሆናልና ልብ ልንል ይገባል” (ምንጭ ታህሳስ 14/1966 አብዮታዊ ዲሞክራሲ ጋዜጣ) አሁን ይሄ የአቋም መግለጫ ነው? ምንድን ነው ? አንድ ምሳሌ ልጨምር፡፡ በ“አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ” ጋዜጣ ላይ የካቲት 3/1996  ደግሞ እንዲህ ብሎ መግለጫ አስተላለፈ፡- በእርግጥ ሳካብድ ነው እንጂ መግለጫ አይደለም፡፡“ዛሬ ህገ መንግስታዊ መብት የተጎናፀፈው የሴቶች እኩልነት ጥያቄ ፖለቲካዊ ምላሽ አግኝቶ መብቱ ስራ ላይ ቢውልም ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ የአለም አገሮች ውስጥ ነፃነቱ ወይም መብቱ ከወንዶች አለም ክበብ ወስጥ አልዘለቀም”፡፡ ይህንን ሁሉ ለማለት የፈለግሁት ኢትዮጵያ ውስጥ የአንዳንድ ደራሲዎች የፖለቲካ እውቀትና አቋም ተገለባባጭ ደካማ መሆኑን ለማሳየት እንዲሁም መላ ቅጡ የጠፋ ነው ለማለት ነው፡፡ ልጓም ካልተበጀለት  ችግር ይዞ እንደሚመጣ ለማጠየቅ ነው - በነቢብም በገቢርም አለማየሁን እንደ ምሳሌ አንስቼ ልፈታተነው የፈለግሁት ፡፡

Read 2416 times