Saturday, 04 June 2016 12:02

“የማናውቀው ዓለም” እየገባን ነው - ልብ እንበል

Written by  ዮሃንስ . ሰ.
Rate this item
(14 votes)

• መንግስት፣ ድሮ ድሮ፣ እንዳሻው ቢዝረከረክ መተማመኛ ነበረው - የሬዲዮና የቲቪ ፕሮፖጋንዳ፡፡ ዛሬ ግን፣ መተማመኛው አቅም እያጣ ነው፡፡ ተቀናቃኝ የፕሮፖጋንዳ ባለቤቶች በዝተዋል፡፡
• ጭፍን ተቃውሞ፣ ድሮ ድሮ፣ የቻለውን ያህል እያጋነነ ቢናገርና ቢቀሰቅስ መተማመኛ ነበረው - መዘዙ ቀርፋፋና ጥቂት ነው፡፡ ዛሬ ግን፣ በፍጥነት አገር ምድሩን ያደርሳል፡፡

     ሰሞኑን፣ በ12ኛ ክፍል ፈተና ላይ የተፈጠረው ቀውስ፤ አገርን ከድንዛዜ የሚያባንን ነጐድጓድ ነው፡፡ ልብ ብለን ብናስተውለው ይበጃል፡፡
በዚሁ አጋጣሚ፣ አይናችንን ገልጠን ዙሪያችንን ለመመልከት፣ እናም… “አዲስ የማናውቀው ዓለም” ውስጥ እየገባን መሆናችንን ለመገንዘብ ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡
በቀላል ዘዴ እንሞክረው፡፡
እንዲህ አይነቱ ቀውስ ከሃያ ዓመት በፊት ቢከሰት ብላችሁ አስቡ፡፡
ሃሳባችሁን በአጭሩ ላቋርጠው፡፡ እንዲህ አይነት ቀውስ፣ ያኔ ሊፈጠር አይችልም ነበር፡፡
አዎ፤ የ12ኛ ክፍል ፈተና ድሮም ቢሆን ሊሰረቅ ይችላል፡፡ ቢሆንም ግን፣ በዚያ ሰበብ፣ አገር ምድሩን የሚያዳርስና የብዙ ሚሊዮን ብሮች ኪሳራ የሚያስከትል ቀውስ ግን አይፈጠርም ነበር፡፡
የዛሬ ሃያ ዓመት፣ የሆነ ቦታ ላይ፣ የፈተና ወረቀት ቢሰረቅ እንኳ፣ መዘዙ፣ ያን ያህል “ጉድ” የሚያሰኝ አይሆንም፡፡ ቢበዛ ቢበዛ፣ ከአንድ ከተማ አልፎ የሚሻገር መዘዝ ሊያስከትል አይችልም - አገርን ሊያዳርስ ይቅርና፡፡ ለነገሩ፣ በአንድ ከተማም ውስጥ፤ የፈተና ወረቀት ብዙ ሰው እጅ ውስጥ ሊገባ አይችልም፡፡ “የፈተና ወረቀት አግኝቻለሁ” ብሎ፣ ለከተማው ተማሪዎች ለማሰራጨት እየነፋ፣ ጥሩምባ ነጋሪት እያስመታ የሚያወጅ ሰው አይኖርም፡፡ በአጭሩ፣ በያኔው “ዓለም”፤ ሁሉም ነገር ቀርፋፋ፣ ሁሉም ነገር የተራራቀ፣ ሁሉም ነገር በሹክሹክታ ነበር፡፡
ዛሬ ይሄ ሁሉ ተቀይሯል - በሞባይል ስልክ፣ በኢንተርኔት፣ በፌስቡክ፡፡
ከሃያ ዓመት በፊት፤ ዲጂታል ካሜራ፣ በአዲስ አበባ ሳይቀር፣ በጣም ብርቅ ነበር፡፡
የፈተና ወረቀቶችን በዲጂታል ካሜራ ፎቶ ማንሳት፣ ቀላል ስራ አልነበረም፡፡ ዛሬ፣ አብዛኛው ሰው የዲጄታል ካሜራ ባለቤት ነው - የሞባይል ስልክ ይዟልና፡፡ ፎቶ ማንሳት ብቻ አይደለም፡፡
በሴኮንዶች ውስጥ፤ ከዘገየም በደቂቃዎች ውስጥ፣ ፎቶዎቹን ከከተማ ከተማ፣ ከአገር ጫፍ እስከ ጫፍ፣ ከዚያም አልፎ ከአህጉር አህጉር መላክ ይችላል - በኢንተርኔት ተገናኝቷልና፡፡
የቦታ ርቀት፣ እንደድሮ “የማይዘለል ተራራ” አይደለም፡፡ ለምን?
ቦታዎችን የሚያቀራርብ “አዲስ ዓለም” ውስጥ እየገባ ነው፡፡ እንደ ድሮ መንቀራፈፍ የለም፡፡ ነገሮችን ከሚያፈጥን “አዲስ ዓለም” ጋር እየተቀላቀልን ነው፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ በሹክሹክታ፣ ከአንድ ከሁለት ሰው ጋር ከመነጋገር ውጭ ብዙም እድል ከማይገኝበት የድሮው ዓለም እየወጣን፣ ሁሉም ሰው ትልቅ “ስፒከር” ይዞ፣ ቀን ከሌት፣ በአገር በምድሩ ሁሉ ለማስተጋባት እድል ወደሚያገኝበት “አዲስ ዓለም” እየተጓዝን ነው፡፡
በዚህ የ21ኛው ክፍለዘመን “ልዩ ዓለም” ውስጥ፣ ቦታዎች ተቀራርበዋል፡፡ እንቅስቃሴዎች ፈጥነዋል፡፡ ድምፆች እስከ ጥግ ተከፍተዋል፡፡
በእያንዳንዱ ከእያንዳንዱ ንግግር፣ ከእያንዳንዱ ተግባርና ባህርይ የሚነጭ ውጤትና መዘዝም በዚያው ልክ… እንደ ብርሃን ፍጥነት ድንገት ደርሶ የሚያመጥቅ ወይም የሚያደባይ፣… አገር ምድሩን እያካለለ እልፍ ሰዎችን የሚያድን ወይም የሚጥል፣ በግዝፈቱ ጉድ እያሰኘ መዓት ሃብትን የሚፈጥር ወይም የሚያጠፋ ይሆናል፡፡
የሰሞኑ ቀውስም፣ የዚህ “አዲስ ዓለም” አንድ ገፅታ ነው፡፡
በእርግጥ በቴክኖሎጂ ግስጋሴ ምክንያት “ልዩ ባህርይ” የተላበሰው ይሄው አዲስ ዓለም፣ እንደማንኛውም ቴክኖሎጂ፣ ካሁን በፊት ያልነበሩ መልካም አማራጮችን በብዛት የሚያመነጭ ዓለም ነው፡፡
በአግባቡ ከተጠቀምንበት፣ በእውቀት፣ በኑሮ እና በስብዕና አስደናቂ ለውጥ የመቀዳጀት የሚያስችል እድል እናገኝበታለን፡፡ አንድ የሚነበብ መጽሐፍ በጣም ብርቅ በሆነበት፣ ቴሌቪዥን ይቅርና ሬዲዮ እንኳ የሩቅ ምኞት በነበረበት ቤተሰብ ውስጥ ላደገ ሰው፣ የዛሬው “ዓለም” በእርግጥም ልዩ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ልብወለድ ድርሰት ያነበብኩት፣ 7ኛ ክፍል በጥሩ ውጤት “አርአያ” የተሰኘው መጽሐፍ ከተሸለምኩ በኋላ እንደሆነ አስታውሳለሁ፡፡ ኢንሳይክሎፒዲያን በእጄ የነካሁት፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስገባ ነው - ሃምሳ ዓመት ያስቆጠረ የድሮ እትም ቢሆንም፡፡
ለነገሩ፣ የዩኒቨርስቲው የመማሪያና አጋዥ የሳይንስ መፃሕፍትም የጥንት ነበሩ፡፡ ዛሬ ይሄ ሁሉ ተቀይሯል፡፡ ዩኒቨርስቲው፣ እዚያው መቆም ይችላል፡፡ ዓለም ግን ተቀይሯል፡፡
በየጊዜው በአዳዲስ መረጃዎች የሚዳብር፣ የዛሬ የዘመኑ ኢንሳይክሎፒዲያ ብቻ ሳይሆን፣ እንደየዝንባሌያችን፣ ምርጥ የሳይንስና የትምህርት፣ የጥበብና የመዝናኛ አዳዲስ መፃሕፍትን በኢንተርኔት አማካኝነት ማግኘት እንችላለን - በትንሽ ጥረት፡፡
ኑሮንና ስብዕናን ለማበልፀግ የሚረዳ…እልፍ አይነት እውቀትንና መረጃን እንደልብ ከማግኘት በተጨማሪ፣ በእለት ተዕለት ሰራ፣ ለሙያችን የሚያግዙ አሰራሮችንና ዲዛይኖችን ማግኘት እንችላለን፡፡ መንፈሳችንን የሚያድሱ፣… በአርአያነት የሚያነሳሱ ጀግና ገፀባህርያትን አጉልተው በመቅረጽ የሚያበረክቱልን ብዙ የስነጥበብ ስራዎች (ልብወለዶች፣ ፊልሞች፣ የቲቪ ድራማዎች) እያማረጥን የማንበብና የማየት እድል ተፈጥሮልናል በዘመኑ ቴክኖሎጂዎች፡፡
ምናለፋችሁ! ቦታና ጊዜ የማይገድበው የተትረፈረፈ ፀጋ፣ በመዳፋችን ውስጥ ገብቷል ቢባል፣ ማጋነን አይሆንም፡፡
ይህንን እድል በአግባቡ ያልተጠቀምበት እንደሆነስ? ቦታና ጊዜ የማይገድበው የተትረፈረፈ መዘዝ ውስጥ እንገባለን፡፡
በፍጥነት መባነን የሚኖርብንም በዚህ ምክንያት ነው - በተትረፈረፈው ፀጋ በአግባቡ ለመጠቀም እንዲሁም ከመዘዝ ናዳ ለማምለጥ፡፡
ድሮ፣ እያንዳንዱ ንግግራችን፣ ተግባራችንና ባህሪያችን ምንም አይነት ውጤት ወይም መዘዝ አልነበረውም ማለት አይደለም፡፡ ነበረው፡፡ በትንሽ ከተማ የታጠረ፣ በጣም የተንቀራፈፈና በቁጥቁጥ የሚታይ ቢሆንም “ውጤትና መዘዝ” ድሮም ነበረ፡፡ የዓለማችን መሰረታዊው ተፈጥሮ አልተቀየረም፡፡
የዛሬ ዘመን ልዩ የሚሆነው፤ በቱርቦቻርጀር የፈጠነ፣ በአምፒሊፋየር የገነነ፣ በማባዣ የተትረፈረፈ ውጤት አልያም መዘዝ የምናገኝበት ዘመን በመሆኑ ነው፡፡
በድሮው “ዓለም” ውስጥ በድንዛዜ እየናወዝን፣ ደመነፍሳችንን በአዲሱ ዓለም ብንደናበር መጨረሻው አያምርም፡፡ መንግስት፣ እንደድሮው በአፈናና በፕሮፖጋንዳ ተማምኖ እንዳሻው መዝረክረክ የሚችል ከመሰለው፤ የስህተቶቹና የጥፋቶቹ መዘዝ እጅግ ሩቅ መስሎ የሚታየው ከሆነ ፣ ጉድ ይፈላል፡፡ የሰሞኑን ቀውስ ማየት ነው፡፡
ይህም ብቻ አይደም፡፡ ከሃያ ዓመት በፊት የመንግስት በጀት 10 ቢሊዮን ብር አይሞላም ነበር፡፡ ሩቡ እና ግማሹ ያህል ቢባክን ብላችሁ አስቡት፡፡ ዛሬ ግን በጀቱ ከ270 ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ሩብ ያህሉ ቢባክን፣ የቀውሱ መጠን ይታያችሁ፡፡
ዛሬ፣ እያንዳንዷ ስህተትና ጥፋት፣ ትልቅና ፈጣን መዘዝ ታስከትላላችሁ፡፡ ታዲያ ከድንዛዜ መባነን የሚገባው መንግስት ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎቻችንም በደመነፍስ ከመደናበር መላቀቅ አለብን፡፡
የምንሰራውን ነገር በጥንቃቄ መመርመር ይኖርብናል - መዘዙ ብዙ ነውና፡፡ ለእውነት ክብር ባመስጠት፣ “ለአሁኗ ቅጽበት ብቻ፣ ለአንዲት ቁንፅል ጉዳይ ብቻ ለእገሌ ወይም በእንትን ቡድን ላይ ብቻ…” በሚሉ ማመካኛዎች ራሳችንን እያታለልን፤ እንደመንግስት ሁላችንም በየፊናችን ፕሮፖጋንዳ የምናራግብ ከሆነ፣ እንደመንግስት የሰዎችን መብት የምንጥስ ከሆነና ጥላቻን ላይመንትን፣…አደጋውን አይተን በጊዜ ከዚህ የጥፋት ጉዞ ካልተቆጠብን፣ ጉድ ይፈላል፡፡
 ለምሳሌ፣ በጭፍን እምነት፣ በመንጋ ስሜት እና በዘረኝነት ጥላቻ፣ በየደቂቃው በፌስቡክ ሲሰራጭ የምናየውን ጥፋት፣ ካልገሰፅን፣ ወይም ደግሞ የምናስተጋባ ከሆነ፣ ማቆሚያ የሌለው መዘዝ ይጠብቀናል፡፡




Read 3968 times