Saturday, 04 June 2016 12:20

ኢህአዴግ የማይወዳቸው የግንቦት 20 ምሬቶች!!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(36 votes)

“የህይወቴ ቃና ለውጥ የጀመረው ኢህአዴግ ሥልጣን ሲይዝ ነው!”
· ቅሌትና ኪሳራ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ በዝተውብናል !

   የግንቦት 20 ሃያ አምስተኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል እንደተወራለት ባይሆንም ብዙዎቹን የመንግስት ባለሥልጣናትና መ/ቤቶች ሥራ አስፈትቶ በድምቀት ተከብሯል፡፡ (;ግንቦት 20 ውስጤ ነው!; በሚል!) በነገራችን ላይ ግንቦት 20ን ውስጤ ነው ለማለት የግድ ታጋይ ወይም የፓርቲ አባል መሆን አያስፈልግም፡፡ ኢህአዴግ ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ በሙስናም በሉት፣በዝምድና ---- ገንዘብ ቋጠር አድርጎ ፎቅ የገነባ ወይም ሌላ አትራፊ ቢዝነስ ውስጥ የገባ ሁሉ የግንቦት 20 ፍሬ በመሆኑ #ውስጤ ነው” ማለቱ አይቀርም፡፡ ዝም ብዬ ሳስበው፣ በእነዚህ 25 ዓመታት የተከሰቱ በጎም ሆነ ክፉ ፣ስኬትም ይሁን ውድቀት የግንቦት 20 ፍሬዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው፣በጥረታቸውና ትጋታቸው ሚሊየነር ለመሆን የበቁ ወጣቶች፣ የግንቦት 20 ፍሬዎች ናቸው፡፡ በሙስና፣በኔትዎርክ፣በኪራይ ሰብሳቢነት፣በመሬት ወረራ (ችብቸባ) ቢጠሯቸው የማይሰሙ ባለጠጋ የሆኑ ዋልጌ ዜጎችም የግንቦት 20 ፍሬዎች ናቸው፡፡
ሌላው ቀርቶ ምንም በሌለበት ፓርቲያቸውን ለ2 እና 3 ቡድን ከፋፍለው ዓመት ሙሉ “ህጋዊው አመራር እኔ ነኝ; እያሉ የሚወዛገቡ የተቃዋሚ አመራሮችም (መኢአድን ልብ ይሏል!) የግንቦት 20 ፍሬዎች ናቸው፡፡ መንግስት በአክራሪነት የፈረጃቸው ፓርቲዎች በሉ የግል ፕሬሶች፣በፓርላማ ሽብርተኛ ተብለው የተፈረጁ የፖለቲካ ድርጅቶች---ወዘተ የግንቦት 20 ፍሬዎች ናቸው፡፡ ለምን መሰላችሁ?-----ሁሉም በኢህአዴግ ሥርዓት ውስጥ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር፣ታላቁ የህዳሴ ግድብ፣በርከት ያሉ ኤፍኤሞችና የቴሌቪዥን ጣቢያዎችም የግንቦት 20 ፍሬዎች ናቸው፡፡  
በነገራችን ላይ የግንቦት 20ን አከባበር ሳልጨርስ ነው ወደ ግንቦት 20 ፍሬዎች የገባሁት፡፡ ስለዚህ ይቅርታ ይደረግልኝና የጀመርኩትን ልጨርስላችሁ፡፡ እናላችሁ---በበዓሉ አከባበር ዙሪያ አንዳንድ ቅሬታዎችና ተቃውሞዎች ተናፍሰው ነበር፡፡ ከፍተኛ ትችትና ነቀፋ የተሰነዘረው በምን ላይ መሰላችሁ? በአንዳንድ የመንግስት መ/ቤቶች (በሁሉም ሳይሆን አይቀርም!) ሰራተኛው በሙሉ (ካድሬውም ፕሮፌሽናሉም!)  በዓሉን በግዳጅ እንዲያከብር በመደረጉ ነው፡፡ (የደርግ ሥርዓት ቅርብ ነው እንዴ?) ቆይ ግን እንዴት ነው በዓል በቅጣትና በማስፈራሪያ የሚከበረው? እኔ የምለው --- ኢህአዴግ የዛሬ ስንት ዓመት 7 ሚሊዮን ደጋፊዎች አሉኝ እያለ ሲፎክር አልነበር እንዴ? አሁን የት ገቡ? ቢኖሩማ  ከመንግስት ሰራተኞች ጋር አይታገልም ነበር፡፡ ወይስ 7 ሚሊዮኑ የመንግስት ሰራተኞችን ጨምሮ ነው? (መሆናቸው አይቀርም በሚል!)
ወዳጆቼ-----ከዚህ በታች የምታነቡት ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል፣ባለፈው ሳምንት ለሠራተኞቹ የለጠፈው ማስታወቂያ (ማስጠንቀቂያ ቢባል ይሻላል! ሲሆን በማህበራዊ ድረገጽ ላይ ተሰራጭቶ ኢህአዴግ ክፉኛ ሲነቀፍ ነበር፡፡ (እሱም አበዛው እኮ!)
ለሆስፒታሉ ሠራተኞች በሙሉ
የግንቦት 20 በዓል 25ኛ ዓመት ክብረ በዓል ረቡዕ ግንቦት 17 በአክሱም ሆቴል ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ በደማቅ ሁኔታ ስለሚከበር ሁሉም ሠራተኛ በዓሉ ላይ እንዲገኝ እናስታውቃለን፡፡ ስለዚህ ቀኑ የሥራ ቀን በመሆኑ እንደ ሥራ ቀን ሁሉ ከጠዋቱ 2፡30 በአክሱም ሆቴል የሰዓት መቆጣጠሪያ ፊርማ ስለሚኖር ጠዋት በሰዓቱ ተገኝቶ ያልፈረመ ሠራተኛ እንደ ቀሪ ተቆጥሮ አስተዳደራዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ጭምር እናሳስባለን፡፡
ለጤናችን በጋራ እንስራ
አስገራሚ የግንቦት 20 ፍሬ ይሏችኋል ይሄ ነው፡፡ በድምቀት ለሚከበር በዓል የሰዓት መቆጣጠሪያ ፊርማ ለምን ያስፈልጋል? ከሁሉም ያስገረመኝ ደግሞ ከላይ በማስጠንቀቂያና በማስፈራሪያ ታጅቦ ሲያበቃ፣ወረድ ብሎ “ለጤናችን በጋራ እንስራ” የሚል ያለ ቦታው የገባ  ትሁት መፈክር መሸጎጡ ነው፡፡ በኋላ ላይ እንደሰማሁት ግን ሆስፒታሉ የትችት ናዳው ሲበዛበት፣ማስታወቂያውን አሻሽሎ በድጋሚ አውጥቶታል አሉ! (ካፈርኩ አይመልሰኝ አለማለቱ ያስመሰገነዋል!)
እኔ የምላችሁ ----ኢህአዴግ ነፍሴ ሲቪል ሰርቫንቱን ሁሉ የፓርቲ አባል አደረገው እንዴ? (ድከም ቢለው እኮ ነው!) ከዚህ በኋላ የህዝቡን ችግሮችና ጥያቄዎች ለመፍታት ካልተጋ በቀር የእስከዛሬው በሥልጣን ላይ የመቆያ ሥልቶች ብዙም አያዋጡም፡፡ ለዚህ ደግሞ የኦሮምያን ተቃውሞ መመልከት ይበቃል፡፡ መቼ 1ለ5 ከተቃውሞ አገደው? እንደውም ጥርነፋው ሳይጠቅመው አልቀረም፡፡ (በነገራችን ላይ የኦሮምያ ተቃውሞ የግንቦት 20 ፍሬ ነው!)
ወደ ቁም ነገሩ ስንመጣ - የ25 ዓመት የሥልጣን ዘመን ትርፍና ኪሳራ ስንተሳሰብ ማለቴ ነው፡፡ እቺን በበዓሉ አከባበር ላይ ያየናትን ህጸጽ፣ ከግንቦት 20 ኪሳራዎች እንመድባታለን፡፡ ምንም ትንሽ ብትመስል የመብት አፈና ናት፡፡ (#ምንም ብቀጥን ጠጅ ነኝ”! አሉ) በዚያ ላይ
በነገራችን ላይ የ“ቃና” ቲቪ ጋዜጠኞች፣ የግንቦት 20 ዕለት ካሜራቸውን ይዘው ሸገር ላይ ዞር ዞር ቢሉ ኖሮ፣ በርካታ ማስታወቂያዎችን በነጻ ሰርተው ወደ ጣቢያቸው ይመለሱ ነበር፡፡ ለምን መሰላችሁ? “የህይወቴ ቃና ለውጥ የጀመረው ግንቦት 20 ነው!”፣“የህይወቴ ቃና ለውጥ  የጀመረው ኢህአዴግ ሥልጣን ሲይዝ ነው!”፣“የህይወቴ ቃና ለውጥ የጀመረው ጀግናው የኢህአዴግ ሰራዊት አዲስ አበባ ሲገባ ነው!” ወዘተ --- ለማለት ያቆበቆቡ በርካታ የግንቦት 20 ፍሬዎችን ያገኙ ነበር፡፡ (ባለፉት 25 ዓመታት ኑሮ የተሳካላቸው ማለቴ ነው!)
በዘንድሮ የግንቦት 20 በዓል ምን ታዘብኩ መሰላችሁ? (ለኢህአዴግም ጭምር ነው የታዘብኩለት!) በገዢው ፓርቲ ላይ ያነጣጠሩ ከፍተኛ ምሬትና ተቃውሞዎች ናቸው!! (“አብዮታችን ሰላም አይደለም እንዴ?”)  ደግነቱ ግን በአካል ሳይሆን በማህበራዊ ሚዲያ ነው፡፡ (መንግስት የቴክኖሎጂ ጠላት ቢሆን ይፈረድበታል?) በነገራችን ላይ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር (መሬት ይቅለላቸውና!) “ግንቦት 20ን መቃወም፣የግንቦት 20 ፍሬ ነው!” ብለው ነበር ይባላል፡፡ (ግንቦት 20ን በግዳጅ ማክበር መጀመሩን ቢሰሙ እንዴት ያዝኑ?!) እስቲ በማህበራዊ ሚዲያ ከተሰራጩ  ተቃውሞዎቹ አንድ ሁለቱን እንቃኛቸው፡-
አንድ የፌስቡክ ጸሃፊ እንዲህ ሲል ተቃውሞውን ተንፍሷል፡- “ገጠሩን ከተማ እናደርገዋለን ብለን፣ ከተማውን ገጠር ያደረግንበት 25ኛ ዓመት!” (ማስረጃ ወይም መረጃ ግን አልጠቀሰም!) ሌላ በጣም የተቆጣ ፌስቡከር ደግሞ በፈረንጅ አፍ እንዲህ ብሏል፡- “The cost of freedom of speech in Ethiopia:- Death, Detention, Exile” (በኢትዮጵያ ሃሳብን በነፃነት መግለፅ የሚያስከፍለው ዋጋ፡- ሞት፣ እስር፣ ስደት!” አንዳንድ ንዴት የበረታባቸው የፌስቡክ ፀሐፊዎች ደግሞ ከኢሕአዴግ ደርግ ይሻል ነበር እስከ ማለት ደርሰዋል (የባሰ አታምጣ አሉ!) “በተለይ የህዝቡንና የአገር አንድነትን በመጠበቅ እንዲሁም ከፊውዳሎች ላይ ትርፍ ቤቶችን እየነጠቀ ለድሃው ቤት በመስጠት፣ ከባንክ ብድር አመቻችቶ መሬት እየሰጠ፣ግለሰቦች በረዥም ጊዜ ክፍያ መኖሪያ ቤት እንዲቀልሱ በማድረግ ለጭቁኑ ወገንተኝነቱን አሳይቷል፤ኢህአዴግ ግን ድሃውን ከመኖርያው እያፈናቀለ ሜዳ ላይ በመበተን መሬቱን ለሃብታም ይቸበችባል” በሚል ኢህአዴግ ክፉኛ የተነቀፈበትና ከተገረሰሰ 25 ዓመት ያስቆጠረው ደርግ በእጅጉ የተወደሰበት ጽሁፍ ፖስት ተደርጓል፡፡ “ከግንቦት 20 ፍሬዎች በከፊል” በሚል የቀረበው እንኳን ላለፉት 3 እና 4 ዓመታት ሲባል የከረመ ነው፡፡ አገር - መሪ የለም! መብራት - ኃይል የለም! ባንክ - ሲስተም የለም! ነጻ ፕሬስ - ነጻነት የለም! ሻይ - ስኳር የለም! ትምህርት - ጥራት የለም! ፍርድ ቤት - ዳኛ የለም! ኢንተርኔት - ኔትዎርክ የለም! (ልብ አድርጉ! ትችቶቹን ለማሳየት ያህል እንጂ አቋም አልያዝኩበትም!)
የዘንድሮ ግንቦት 20 ሞገስ ማጣቱን እንደኔ የታዘበና የተገነዘበ አንድ ፌስቡከር ምን አለ መሰላችሁ ? (አፍቃሪ ኢህአዴግ ይመስለኛል)  “ግንቦት 20 ተገቢውን ክብር ባያገኝ፣ተጠያቂዎቹ በሰማዕታት አደራ ላይ ያላገጡት ሹመኞች እንጂ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም”  (በዚህስ እኔም እስማማለሁ!) እስቲ ወደ ሌላ አጀንዳ ከማለፋችን በፊት፣ የእስካሁኑን የግንቦት 20 ትርፍና ኪሳራ እንተሳሰብ፡፡ እናላችሁ ------ አሁንም ኪሳራ እንጂ ትርፍ አልተመዘገበም፡፡ ኢህአዴግ በግንቦት 20 ሰሞን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተቃውሞ መዓት ማሰተናገዱ፣ በምንም ስሌት ስኬት ሊሆን አይችልም፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት ኢህአዴግ አገራዊ መግባባት ፈጥሮ ግንቦት 20ን ብሄራዊ በአል እንደሚያደርገው ብዙዎች ጠብቀው ነበር፡፡ (ጭራሽ ደርግ ይሻለኛል የሚል ትውልድ ፈጠረ!)
ወዳጆቼ፤ዘና ፈታ የምታደርግ፣ የግንቦት 20 ልዩ ጥያቄ እነሆላችሁ፡- (የህወሃት 40ኛ ዓመት በዓል ቢሆን ኖሮ፣ጥያቄው በትንሹ 11ሺ ብር ያሸልም ነበር!) ወደ ጥያቄው፡-
ከሚከተሉት ውስጥ የምታምኑት የመንግስት ተቋም የትኛው ነው? ሀ) ፖሊስ  ለ) ምርጫ ቦርድ  ሐ) ፍ/ቤት   መ) ኢቢሲ    ሠ) ት/ሚኒስቴር   ረ) ሁሉም   ሰ) መልሱ አልተሰጠም ታስታውሱ እንደሆነ ---- ከጥቂት ዓመት በፊት መንግስት ራሱ ይሄን የሚመስል ጥናት በውጭ ተቋም አሰርቶ ነበር፡፡
በነገራችሁ ላይ…በግንቦት 20 ሰሞን ለምንድን ነው ተቃውሞውና ምሬቱ የበዛው (መብት ቢሆንም!) ብሎ መጠየቅ ብልህነት ይመስለኛል፡፡ በተለይ ደግሞ “እቺን አገር ከድህነት አረንቋ መንቅዬ አውጥቼ፣ ባለ መካከለኛ ገቢ ሳላደርጋት ስልጣን አለቅም!) ብሎ ለተገዘተ አውራ ፓርቲ÷ዋና ሥራው ይሄ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ከየትኛውም አቅጣጫ ለሚሰነዘር ተቃውሞ ምላሽ ለመስጠት መትጋት እንጂ ፍረጃ ፋይዳ እንዴለው እንኳን ኢህአዴግ እኛም ተረድተነዋል፡፡ እኔ የምላችሁ-----“ዲሞክራሲ በአንድ ጀምበር የሚከሰት ሳይሆን ሂደት ነው” ሲባል አልነበር እንዴ? እሱ ነገር እምን ደረሰ? (እንደ ፈተናው እንዳይሰረቅ ብዬ እኮ ነው?) ለመሆኑ----“ሂደት” በዓመት ሲመነዘር ስንት ይሆናል? (ከ25 ዓመት በታች እንዳልሆነ ነቄ ብለናል!)
የዲሞክራሲ ነገር ሲነሳ ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ፤ የዛሬ 3 ወር ገደማ ከ3 የአውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባላት ጋር በተወያዩ ወቅት፣ በተለይ ጂያኒ ፒቴላ ለተባሉት የፓርላማ አባል ያጫወቷቸው ትዝ አለኝ፡፡ እኔ ያነበብኩት ሰውየው በወቅቱ ዘ አዲስ ስታንዳርድ ለተባለ የአገራችን የእንግሊዝኛ መጽሄት ከሰጡት ቃለ ምልልስ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ፒቴላ በዲሞክራሲ፣በሰብዓዊ መበት አያያዝና  በፕሬስ ነጻነት ---- ጉዳይ ላይ ቀልድ የሚያውቁ አይመስሉም፡፡ እሳቸውን በልማትና በኢኮኖሚ ዕድገት መሸወድ ከባድ ነው፡፡ (በአጭሩ ለልማታዊ መንግስት ውጋት ናቸው!)
“እንደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ሁሉ፣በኢትዮጵያም ልማት ከዲሞክራሲ ተነጥሎ ሊታይ አይችልም፡፡ የመንግስታችሁን ጋዜጠኞችን የማሰር ውሳኔም ሆነ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የመሰሉ አፈናዎች ጨርሶ በዝምታ አላልፍም፤በአደባባይ አወግዘዋለሁ፡፡ በጠ/ሚኒስትሩም ፊት እንዲሁ ተቃውሜአለሁ” ብለዋል - ፒቴላ፡፡
ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም፤ ስለ ዲሞክራሲ ያጫወቷቸውን ፒቴላ እንዲህ ይገልጹታል፡- “የዲሞክራሲ ጽንሰ ሃሳብ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዴት በሂደት እያደገ እንደመጣ አስረድቶኛል፡፡ እሱ አባቱ ያዘዙትን እየፈጸመ ቢያድግም፣ሴት ልጁ እሱ ያዘዛትን ዝም ብላ የማትቀበል መሆኗ እንደሚያስደስተው ነግሮኛል” ይላሉ - ፒቴላ፡፡
እንግዲህ የ25 ዓመት ትርፍና ኪሳራችንን ስንተሳሰብ፣የዲሞክራሲን ጉዳይ--የሰብዓዊ መብትን አያያዝ---የመቃወም መብትን----ወዘተ ማየታችን የግድ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ላለፉት ወራት  የተረጋጋ እየመሰለ ዳግም የሚያገረሸው የኦሮምያ ተቃውሞና ግጭት፣እስከ አሁን ድረስ ዘላቂ መፍትሄ አለማግኘቱ የአገራችን የሩብ ክፍለ ዘመን ታላቅ ኪሳራ ነው! ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ በኦሮምያ ለጠፋው የሰው ህይወትም ሆነ ሌሎች ውድመቶች በፓርላማ መንግስታቸውን በመከወል በይፋ ይቅርታ መጠየቃቸው ለብዙዎች ያልተጠበቀ ነበር፡፡ የሽግግር መንግስቱን ከኢህአዴግ ጋር ያቋቋሙትና የቀድሞው የኦነግ አመራር የነበሩት ሌንጮ ለታ “The Addis Standard” በተሰኘው ወርሃዊ የእንግሊዝኛ መፅሄት ላይ who is in control of Ethiopian በሚል ርዕስ ባቀረቡት ፅሁፍ፤ የጠ/ሚኒስትሩን ይቅርታ መጠየቅ ከልባቸው አድንቀዋል፡፡ ወዲያው ግን ቅሬታቸው ይከተላል፡፡ ይቅርታውን ተከትሎ ከመንግስት ከተጠበቁ በርካታ እርምጃዎች መካከል አንዱንም አልፈፀመም ሲሉ መንግስትን  ይተቻሉ - ታጋዩና ፖለቲከኛው ሌንጮ ለታ፡፡ ለመሆኑ ምን ነበር ከመንግስት የተጠበቀው? “ተቃውሞዎች ሲካሄዱባቸው ከነበሩ የኦሮምያ አካባቢዎች ልዩ የጸጥታ ሃይልን ማስወጣት፣በህገወጥ መንገድ የታሰሩ የተቃውሞው ተሳታፊዎችን መፍታት፣ በግጭቱ ቤተሰቦቻቸው ለተገደሉባቸው ወገኖች ካሳ መስጠት ----- ” ሲሉ ዘርዝረዋል ፤ሌንጮ ለታ፡፡
እናላችሁ ---- የግንቦት 20 ብቻ ሳይሆን የ25 ዓመቱ ታላቅ ቀውሳችን ወይም ኪሳራችን በኦሮሚያ ክልል ለወራት የቀጠለው አደገኛ ተቃውሞና ግጭት ነው፡፡ በነገራችን ላይ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ (በድሮ ስሙ ማትሪክ) ፈተና መሰረቁም ሌላው የሩብ ክፍለ ዘመን ቅሌታችን ነው!!! (ቅሌትና ኪሳራ በዝተውብናል!!)

Read 5828 times