Saturday, 04 June 2016 12:44

ከሽመና ሥራ ---- እስከ ሚሊየነርነት!

Written by  በማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(7 votes)

“ይቅርታ መጠየቅ ጀግንነት እንጂ ሽንፈት አይደለም”


የኮንሶው ተወላጅ አቶ ዱላ ኩሴ፤ቤሳቤስቲን አልነበራቸውም፡፡ ለብዙ ዓመታት በሽመና ስራ ላይ ቆይተዋል፡፡ በብዙ ልፋትና ትጋት፣ወጥተው ወርደው፣ ነው ለስኬት የበቁት፡፡ ዛሬ
በሚሊዮን ብሮች የሚንቀሳቀሱ የንግድ ድርጅቶች ባለቤት ሆነዋል፡፡ ባለጠጋ ናቸው፡፡ የ50 ዓመቱ ጎልማሳ አቶ ዱላ፤በልጆችም ተንበሽብሸዋል፡፡ የ17 ልጆች አባት ናቸው፡፡ በቅርቡ
በሚዲያ የሰጡት አንድ አስተያየት የአገሬውን ህዝብ ማስቆጣቱን የሚናገሩት ባለሃብቱ፤አሁን በሽማግሌ እርቅ ለመፍጠር እየተሞከረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ባለሃብቱ ከህዝቡ ጋር ቅራኔ
ውስጥ የከተታቸው ጉዳይ ምን ይሆን? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ማህሌት ኪዳነወልድ፤ ከአቶ ዱላ ኩሴ ጋር ይሄን ጨምሮ በስኬት ጉዟቸውና በንግድ ሥራቸው ዙሪያ አነጋግራቸዋለች፡፡

መቼ ነው የሽመና ሥራ የጀመሩት?
በ13 ወይም በ14 ዓመቴ ይመስለኛል፡፡ ለቤተሰቤ አራተኛ ልጅ ነኝ፡፡ ለ10 ዓመታት ያህል በሽመና ስራ ላይ ቆይቻለሁ፡፡ ስራዎቼንም የምሸጠው እዛው በአካባቢው ላሉ ሰዎች ነበር፡፡
ቀጣዩ ሥራዎስ ምን ነበር?
ወደ ጅንካ በመሄድ ለ4 ዓመታት ያህል ኦሞ ዞን ጂንካ ከተማ ላይ ሽያጩን ቀጠልኩ፡፡ በኋላም ወደ ወላይታ ተመልሼ፣ ማግና ሰዴቦራ /ብርድ ቦታ የሚለበስ የጋቢ አይነት/ መሸጥ ጀመርኩ፡፡ ለ3 ዓመታትም ቦዲቲ እየወሰድኩ ሸጫለሁ፡፡
እንግዲህ አቅም እየጠነከረ፣ ገንዘብ እየተሰበሰበ ሲመጣ፣ አነስተኛ ሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ ከፈትኩኝ፡፡ የቤት እቃና ልብስ መሸጥ ጀመርኩኝ፡፡ ብዙም ሳልቆይ ወደ ከተማ ወርጄ፣ ወደ ሆቴል ስራ ገባሁ፡፡
ተቀጥረው ነው ወይስ የራስዎን ሆቴል?
የራሴን ነው፡፡ ኮንሶ እድገት ሆቴል ይባላል፡፡ በ91 ዓመተ ምህረት ነበር ሆቴሉን አነስ አድርጌ የከፈትኩት፡፡ በኋላም የሸቀጣሸቀጥ ገበያው እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ፣ የሸቀጡን ሱቅ ዘጋሁትና የፅህፈት መሳሪያና የህንፃ መሳሪያ ከፈትኩ፡፡ እያልኩ እያልኩ እንግዲህ ----- አሁን ላይ ግምቱ 10 ሚ.ብር የሆነ 40 መኝታ ክፍሎች ያሉት ሆቴል፣ በ6 ሚ. ብር የተገነባ ባለ 3 ፎቅ ህንፃ እንዲሁም 4 የጭነት መኪኖች አሉኝ፡፡ በተጨማሪ በኮንሶ የቢጂአይ ወኪል አከፋፋይም ነኝ፡፡
መቼስ እዚህ ደረጃ ለመድረስ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ይሆናል ብዬ አልገምትም፡፡ እስኪ የገጠመዎትን ፈታናዎች ይንገሩኝ ----- ተስፋ የቆረጡበት ጊዜስ አልነበረም?
ኧረ በጭራሽ! አንድም ቀን ተስፋ ቆርጬ አላውቅም፡፡ በርግጥ ድካም አለው፡፡ ከአገር አገር ዞሬአለሁ፡፡  ብዙ ሰርቻለሁ፡፡ ባለትዳር ነኝ፤ ነገር ግን ተስፋ ለመቁረጥ አስቤ እንኳን አላውቅም፡፡
እንደዚያ ቢሆን ኖሮ እዚህ አልደርስም ነበር፡፡ አንድ ግዜ ግን በ1987 ዓ.ም አርባ ምንጭ ሸቀጣ ሸቀጥ ልገዛ ስሄድ በሽፍታ ተዘርፌአለሁ፡፡
በወቅቱ የነበረኝ 18ሺህ ብቻ ነበር፤ እሱንም ሌባ ወሰደብኝ፡፡
 ያ ጊዜ በርግጥ ከባድ ነበር፡፡ ያው ሰዎችም አልጨከኑም፤ አበደሩኝ፡፡ እንግዲህ፣ ጥሬ ግሬ፣ ብድሬንም መልሼ እዚህ አድርሻለሁ፡፡
እስኪ ስለ ትዳር ህይወትዎ ያጫውቱኝ?
ባለትዳር ነኝ፤ 17 ልጆችና 9 የልጅ ልጆች አሉኝ፡፡
ትልቁ ልጅዎ ስንት ዓመቱ ነው? ትንሹስ?
9 ወንድና 8 ሴት ነው የወለድኩት፡፡ ትልቋ ልጅ ሴት ናት፤ 30 አመቷ ነው፤ አግብታለች፡፡ ትንሷም ሴት ናት፤ አንድ አመቷ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ኮንትራክተር የሆነ ልጅም አለኝ፡፡
 በእርስዎና በኮንሶ ማህበረሰብ መካከል ቅራኔ መፈጠሩንና በዚህም የተነሳ ህዝቡ በእርሶ የንግድ ድርጅቶች ውስጥ መገልገል ማቆሙን ሰምቻለሁ፡፡ የቅራኔው መነሻ ምንድን ነው?
አዎ፤ አንድ እኔ የሰጠሁት አስተያት ነበረ፤ እሱ በሚዲያ ተላልፎ ህዝቡን አስቀይሟል፡፡
ህዝቡ በጣም ቅር ተሰኝቶብኛል፤ለዚህም ይቅርታ ጠይቄአለሁ፡፡ ሙሉ ኃላፊነቱ የኔ ነው፡፡
ምን ዓይነት አስተያየት ነበር የሰጡት?
ያልኩት ምንድን ነው…የሰዎችን ወሬ ሰምቼ፤ “ከኮልሜ ነው የመጣኸው ወደ ኮልሜ ትገባለህ፤ ልጅህም አዋሳ ይሂድ ተብያለሁ፣ማህበረሰቡም አካባቢውን ልቀቅ ብሎኛል” ነበር ያልኩት፡ ሆኖም ይህን አስተያየት ቸኩዬ መስጠቴ ስህተት ነበር፡፡ በኋላም ወሬው ሀሰት መሆኑን ደረስኩበት፡፡
አሁን ጉዳዩ ምን ደረሰ?
በመጀመሪያ በባህላችን መሰረት በሽማግሌዎች አደራዳሪነት፣ ከህዝቡ ጋር ተነጋግረን መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡ እኔም አስተያየቴ ስህተትና አግባብ የሌለው መሆኑን በማመን፣ ህዝብን ከልብ ይቅርታ ጠይቄአለሁ፡፡ በእኔ እምነት፤ ስህተትን አምኖ ይቅርታ መጠየቅ ጀግንነት እንጂ ሽንፈት አይደለም፡፡
የኮንሶ ህዝብ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር ጥያቄ ማቅረቡ ይታወቃል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
ጥያቄው በህገ መንግስቱ መሰረት የቀረበ ነው፡፡ ስለዚህ መንግስት ጉዳዩን እንደገና በረጋ መንፈስ አይቶት፣ ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ ቢሰጥ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
በአሁኑ ወቅትም ህብረተሰቡ ጥያቄውን በህጉ መሰረት አቅርቦ፣ የመንግስትን ምላሽ እየጠበቀ ነው፡፡
እርስዎ ከምንም ተነስተው፣ ለስኬት በቅተዋል፡፡ በህይወታቸው ስኬታማ የመሆን ህልም ላላቸው ወጣቶች  ምን ይመክራሉ?
ምንም!! የተለየ ምንም መስፈርት የለውም፡፡ ቁልፉ መስራት ነው፡፡ የሰራ ህይወቱን መቀየር ይችላል ባይ ነኝ፡፡


Read 2526 times